Google search engine

“ሻምፒዮና ባንሆን እንኳን ሁለተኛ ሆነን ለኮንፌዴሬሽን ካፑ እናልፋለን” “አርጀንቲና የዓለም ዋንጫው አሸናፊ ትሆናለች” ሀብታሙ ታደሰ /ባህርዳር ከተማ/

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ12ኛው ሳምንት ጨዋታ ባህርዳር ከተማ ከሲዳማ ቡና ጋር ባከናወነው ግጥሚያ 1-1 ተለያይቷል፤ ለባህርዳር ከተማ  ዱሬሳ ሹቤሳ መሪ የሆኑበትን ግብ ሲያስቆጥር። ለሲዳማ ቡና ደግሞ አበባየሁ ዩሃንስ በመጨረሻው ደቂቃ ላይ የአቻነቷን ግብ ከመረብ ሊዶላት ችሏል።

ይኸው የሊግ ውድድር በትናንትናው ዕለትም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን  በዕለቱ በነበሩት ጨዋታዎችም ኢትዮጵያ መድን ከፋሲል ከነማ ጋር ጨዋታውን ያለ ግብ ሲያጠናቅቅ አርባምንጭ ከተማም ከለገጣፎ ለገዳዲ ጋር ግጥሚያውን በአቻ ውጤት አጠናቋል።

በእስካሁኑ የሊግ ጨዋታ ውድድሩን ኢትዮጵያ መድን ሲመራ አንድ ተስተካካይ ግጥሚያ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚቀረው ቅ/ጊዮርጊስ በአንድ ነጥብ ተበልጦ በሁለተኝነት ደረጃ ይከተላል።

የባህርዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብም  በእስካሁኑ የሊግ ጨዋታው በ ደረጃ ላይ ይገኛል። የባህርዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ በሊጉ እያደረገ ባለው ጨዋታ ዙሪያ በሜዳ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን እያሳዩ ከሚገኙት ተጨዋቾች መካከል ሀብታሙ ታደሰን የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ አነጋግሮት የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቶታል፤ ተከታተሉት።

ሊግ፦ በኢትዮጵያ ፕሪምየር  ሊግ  ቀደም ሲል በባህርዳር ከተማ አሁን ደግሞ  በድሬዳዋ ከተማ ላይ የውድድር ተሳትፎን እያደረጋችሁ ይገኛል፤ በጨዋታዎቹ ዙሪያ ምን አልክ?

ሀብታሙ፦ የባህርዳር ቆይታችን እንደ መጀመሪያ ጨዋታዎቻችንና እንደ አዲስ የቡድን ስብስባችን በመቀናጀቱ በኩል በቶሎ መግባባት ስላልቻልን ጉዞአችን በውጤት የታጀበ አልነበረም፤  አሁን ላይ ግን ወደ ድሬዳዋ ካመራን በኋላ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ መግባባቱ ስለመጣን ውጤቱን ለመቀየር ችለናል።

ሊግ፦ ባህርዳር ላይ ላጣችሁት ውጤት ምክንያቱ ያለመቀናጀት ችግር ብቻ ነበር?

ሀብታሙ፦ በዋናነትማ ችግሩ እሱ ነበር፤ ከእዛ ውጪ ደግሞ ወደ ሜዳ ስንገባ እያንዳንዱን ጨዋታ አንድ እና አንድ ለማሸነፍ ብለን ብንጫወትም የተቃራኒ ቡድን በቀላሉ ያገኘንና ነጥብ ይወስድብን ስለነበርና  ያ ሳይሳካልንም ሲቀር ደግሞ  የደጋፊ ጫናም ስላለ በፈለግነው መልኩ ለመጓዝ አልቻልንም።

ሊግ፦ ወደ ድሬዳዋ ካመራችሁ በኋላ በዋናነት ያሳያችሁት መሻሻል ምንድን ነው? የድሬ ቆይታችሁስ ጥሩ ነው ማለት ይቻላል?

ሀብታሙ፦ አዎን፤ የእስካሁኑ ቆይታችንማ ጥሩ ነው። መሻሻላችን ደግሞ ህብረታችንና አንድነታችን ጥሩ መሆኑ ነው። በተለይም ደግሞ ሜዳ ስንገባ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ሁሉ ነገራችንን ለክለባችን ስለምንሰጥና ቡድናችንን ደግሞ ከምንም በላይ ስለምናስቀድምና ጨዋታዎችን በቀላሉ እያሸነፍንም በመጓጓዛችን ያ ነው የመሻሻላችን ምክንያቶች።

ሊግ፦ በእስካሁን የሊግ ጨዋታዎቻችሁ  ያላችሁ ጠንካራ ጎንና በክፍተቶቻችሁ ዙሪያ ደግሞ ማረም ያለባችሁ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ሀብታሙ፦ ወደ ጠንካራው  ጎናችን ሳመራ በዋናነት አንድነታችንና ህብረታችንን ነው የምጠቅሰው፤ እንደ ወንድማማችና እንደ ቤተሰብም ነው የምንተያየው። መግባባታችንም ሌላው ተጠቃሹ ጎን ነው። እያንዳንዱን ጨዋታም  በከፍተኛ ፍላጎትም ነው የምንጫወተው። ማን ምን ማድረግ እንደሚገባው በሚገባም  ነው  የሚያውቀውና ያ ሊጠቅመን ችሏል።  ማሻሻል ያለብን ደግሞ ጎል ካስቆጠርንና መሪ ከሆንን በኋላ ወደ ኋላ የምናፈገፍግበት ሁኔታ አለ። ያ አጨዋወት ደግሞ ምንም እንኳን ኳሱን ይዘን ለመጫወት ብንሞክርም በተጋጣሚ ቡድን ጫና ሲፈጠርብን ይታያልና ያን ልናሻሻል ይገባል።

ሊግ፦ የውድድር ዘመኑ ሲጀመር ቡድኖች ሊጉ ላይ ለመቆየት፣ መሀል ሰፋሪ ለመሆን፣ የደረጃ ተፎካካሪ ለመሆንና ሻምፒዮና ለመሆን ብለው ይጫወታሉ፤ የእናንተ ክለብ ከየትኛው ጎራ ነው?

ሀብታሙ፦ እኛ አንድ እና አንድ ሻምፒዮና ለመሆን ብለን ነው የምንጫወተው፤ ያ ካልተሳካ ደግሞ በሊጉ ላይ ሁለተኛ ወጥተን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ መሳተፍን ነው እልማችን ያደረግነው። ይሄን ስታይ ደግሞ የቡድናችንን ትልቅ መሆንንም ያስመለከተን ነው።

ሊግ፦ የክለባችሁን አመራሮች እና ደጋፊዎቻችሁን በተመለከተ ምን ትላለህ?

ሀብታሙ፦ አመራሮቻችንን እና ደጋፊዎቻችንን በተመለከተ ሁሌም ከጎናችን ናቸው፤ ጨዋታዎችን እንድናሸንፍ ይፈልጋሉ። ውጤት ሲኖርም ስናጣም ያበረታቱናል። የጎደለንን ነገርም ያሟሉልናል። ለማሊያው ክብርም እንድንጫወት ያደርጉናልና  በእዚህ በኩል ሊመሰገኑም ይገባል።

ሊግ፦ የባህርዳር ስብስብ ምርጥ ነው ማለት ይቻላል?

ሀብታሙ፦ አዎን፤ ስብስቡ ጥሩ ስለሆነም  እኮ ነው ውጤትን እያስመዘገብንና  የደረጃ ፉክክሩ ውስጥም ገብተን የምንገኘው። በተለይም ደግሞ ከያዝናቸው ተጨዋቾች ውስጥ ወጣቶች ስለሚበዙና ከእዚህ ቀደምም ዋንጫ የማንሳት ልምድ የሌላቸው ተጨዋቾቾችንም በመያዛችን የበለጠ እንድንነሳሳ ስለሚያደርገን ከቡድናችን  ዘንድሮ ጥሩ ነገርን እንጠብቃለን።

ሊግ፦ የሊጉን ፉክክር በምን መልኩ አየኸው?

ሀብታሙ፦ የእዚህ ዓመትን ጨዋታዎች እስካሁን እንዳየሁት ጠንካራ ነው። ሊጉን ጠንካራ ያደረገውም ያልተጠበቁ ቡድኖች ጭምር በደረጃው ሰንጠረዥ ከላይ የተቀመጡበት ሁኔታም ስላለ ነው። የሁለተኛው ዙር ሲጀመርና ጊዜው ሲነጉድ ደግሞ ነገሮች ሊቀየሩ  የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር ቢችልም የተፎካካሪ ክለቦች እየጨመሩ ስላሉ ጠንካራው ውድድር አሁንም ይኖራል።

ሊግ፦ የሊግ ፉክክሩ እንደ አምናው እስከ መጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ድረስ ይቀጥላል?

ሀብታሙ፦ ይመስለኛል። ያም ሆኖ ግን አንድአንዴ ስፖርተኛውና ክለባቶች  አርፈው ሲመጡ በቀድሞ አቋማቸው ላይ የማይገኙበትና ነገሮችም ሊቀየሩ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር ቢችልም ቡድኖች ከያዙት ተቀራራቢ ነጥብ አኳያ ፉክክሩ  እስከመጨረሻው ድረስ መጓዙ አይቀርም።

ሊግ፦ በዓለም ዋንጫው ምክንያት ሊጉ የዲ ኤስ ቲቪ ሽፋንን አጥቷል፤  ምን አልክ?

ሀብታሙ፦ በእዚህ ዙሪያ ማለት የምፈልገው ጨዋታዎችን በተመለከተ ግጥሚያዎቹ ሊተላለፉ ባለመቻሉ ስለምታሳየው እንቅስቃሴ አስተያየት የሚሰጥህ አካል የለም። ባለፈው ግጥሚያ  ላይም  ከሲዳማ ቡና ጋር ስንጫወት ጨዋታውን ህዝቡ ተመልክቶ ቢሆን ኖሮ የራሱን ፍርድ የሚፈርድበት ሁኔታና በእዛም ጨዋታ ላይ በሊጉ የመሪነት ስፍራ ላይ የምንቀመጥበት ሁኔታም  ሊፈጠር  ይችል የነበረ ቢሆንም የጨዋታው አለመተላለፍ እኛን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ቡድኖች ሊጎዳቸው ይችላል።

ሊግ፦ ለባህርዳር ከተማ ሙሉ አቅሜንና ግልጋሎቴን እየሰጠው ነው ትላለህ?

ሀብታሙ፦ አሁን ላይ ሙሉ አቅሜን  እየሰጠው አይደለም። ምክንያቱም ከእዚህ በፊት ጎሎችን የኢትዮጵያ ቡና  ቡድን ተጨዋች በነበርኩበት ሰዓት አስቆጥር ነበርና ያን እያሳካሁት ስላልሆነ በጊዜ ራሴን እየጠየቅኩኝ ነው ያለሁት። ያም ሆኖ ግን በጠበቅኩት ልክ ባይሆንም ወደ ሜዳ በገባው ሰዓት የሚቻለኝን ነገር ለክለቤ እያበረከትኩኝ ነው።

ሊግ፦ በእስካሁኑ ጨዋታዎቻችሁ ያስቆጨህ ግጥሚያ የቱ ነው? ያስደሰተህስ?

ሀብታሙ፦ የውድድር ጊዜው ገና ስለሆነ አሁን ላይ ብዙ ማለት ባልወድም ተናገር ካልከኝ በጣም ያስደሰተኝ ግጥሚያ ኢትዮ- ኤሌክትሪክን ከመመራት ተነስተን ያሸነፍንበትን ጨዋታ ነው። የሚያስቆጨኝ ጨዋታ ደግሞ ከሲዳማ ቡና ጋር  በነበረን ጨዋታ በሊጉ የመሪነት ስፍራ ላይ መቀመጥ የምንችል ቢሆንም ጨዋታውን በአቻ ውጤት ስላጠናቀቅን ያ ሳይሳካልን ቀርቷል።

ሊግ፦ ባሳለፍከው የኳስ ህይወት ደስተኛ ነህ? አላሳካሁትም ብለህ የምታስበውና የምትቆጭበትስ?

ሀብታሙ፦ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሊጉን ዋንጫ አለማንሳቴ በጣም ይቆጨኛል። ያ ያልተሳካልኝ የሊጉ ቆይታዬ  ነው። ሌላው ደግሞ ለዋልያዎቹ ዳግም አለመጠራቴ የሚያስቆጨኝ ቢሆንም ይህ ሁኔታ በስራና በጊዜ የሚፈታ ስለሆነ ራሴን እየጠበቅኩ በመጓዝ ለብሄራዊ ቡድን እንደምጠራ አውቃለሁ።

ሊግ፦ ከእግር ኳሱ መጫወት በኋላ ጊዜህን በምን መልኩ ታሳልፋለህ?

ሀብታሙ፦ አብዛኛውን ጊዜ የማሳልፈው ፊልም በማየት፣ ሙዚቃ በመስማትና  በእረፍት ነው። እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎቻችንም ተጨዋቾች ራሳችንን ስለጠበቅንም ነው ዘንድሮ ጥሩ ውጤትን እያገኘንም ያለነው።

ሊግ፦ የዘንድሮ ስብስባችሁ በአብዛኛው አዲስ እንደሆነ ሁሉ አሰልጣኛችሁ ደግአረገም አዲሱ የቡድኑ ባለሙያ ነው፤ ስለ እሱ ምን አልክ ?

ሀብታሙ፦ ደገአረገን በተመለከተ ከሚሰጠን ስልጠና በመነሳት በታክቲክ በኩል ጥሩ እንድንሆን እያደረገን ነው። ከእዛ ውጪ እያንዳንዱን ጨዋታ በወኔ እንድንጫወትና የማሸነፍ መንፈስንም ይዘን ወደ ሜዳ እንድንገባና ደፋር እንድንሆንም እያደረገን ነው። በጣም ያበረታታናልም።

ሊግ፦ ወደ ኳታሩ የዓለም ዋንጫ እናምራ፤  ውድድሩን እንዴት ተመለከትከው? የማንስ ደጋፊ ነህ?

ሀብታሙ፦ የአሁኑ የዓለም ዋንጫ ብዙ ነገሮችን አሳይቶን እየተካሄደ ነው። ዓለምን ወደ አንድ ቦታ ሊሰበስባትም ችሏል። እግር ኳስን በደንብ አድርገን እንድናውቅም አድርጓል። ውጤት የምታመጣው ባለህ ስምና ዝና ሳይሆን በ90 ደቂቃ አቅምህ መሆኑም ታይቷል። ያልተጠበቁ ሀገራትም በወኔና በፍላጎት በመጫወታቸው ጥሩ ውጤትን ሊያስመዘግቡም ችሏል። እኛም በእግር ኳሳችን ዙሪያ ራሳችንን እንድናይና ማንም ወደ ሜዳ ከገባና በወኔና በጥበብ ከተጫወተ ግጥሚያን ማሸነፍ እንደሚችልም ተረድተንበታል። ወደ ድጋፍ ካመራው ቀድሞ ቤተሰቦቼ ስለ እነ አልሀጂ ዲዩፍ የነገሩኝ ነገር ስለነበርና ኮታችን እንዲጨምር ስለምፈልግና  አፍሪካዊ ቡድን ስለሆነም የሴኔጋል ደጋፊ  ነበርኩ። ከእነሱ ውጪ ደግሞ የአርጀንቲና ደጋፊ ነኝ።

ሊግ፦ ማን ዋንጫውን ያነሳል? አርጀንቲና ወይንስ ፈረንሳይ?

ሀብታሙ፦ እንደ ደጋፊነቴ አርጀንቲና ዋንጫውን ታነሳለች። 1-0 ታሸንፋለች። ያም ሆኖ ግን ጨዋታው ከባድ ፉክክርን ያስተናግዳል።

ሊግ፦ ሞሮኮ ግማሽ ፍፃሜ በመግባት የአፍሪካን ሪከርድ አሻሽላለች፤ ስለ እነሱ ምን አልክ?

ሀብታሙ፦ ይህቺ ሀገር አፍሪካ ብትሆንም ተጨዋቾቿ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ሊግ ላይ የሚጫወቱ ናቸው። ጥሩ ቡድን አላት ሰው የመጣክበትን መንገድ እንጂ አቅምህን አያይምና ምርጥ የሆነችው የእግር ኳስ ሀገር የሚገባትን ውጤት ልታመጣ ችላለች። ካሜሮናዊው ሳሙሄል ኢቶም ሞሮኮ ብዙ ትጓዛለች ብሏልና ያም ተሳክቶለታል።

ሊግ፦ በውድድሩ ምርጡና ቀልብህን የሳበው ተጨዋች?

ሀብታሙ፦ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ምርጡ ተጨዋች ሜሲ ነው። ለእሱ ሲባልም አርጀንቲና ዋንጫ እንድታነሳ እፈልጋለሁ።

ሊግ፦ ከኳታሩ የዓለም ዋንጫ ምን እንማር?

ሀብታሙ፦ለውድድሩ ለማለፍ ከእዚህ ቀደም ከጫፍ ደርሰን ነበር። ከእዛ እንደዚሁም ከእዚህ የዓለም ዋንጫም ሞሮኮን በመመልከት ለውድድሩ ለማለፍ ጠንክረን ልንሰራ ነው የሚገባን።

ሊግ፦ እናጠቃል?

ሀብታሙ፦ ከባህርዳር ጋር ሻምፒዮና የመሆን እልም አለኝ። ይሄ የሁሉም ተጨዋቾች እልምና ፍላጎትም ነው። ይሄን ካልኩ በኋላ  ፈጣሪ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልንም ነው የምለው።

 

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P