Google search engine

“ሀዲያ ገፅታውን ቀይሮ ስለመጣ የማይታመን ውጤት ያመጣል”ተስፋዬ በቀለ /ጃምቦ/ /ሀዲያ ሆሳዕና/ሀዲያ ሆሳዕና የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ውስጥ አራቱን በማሸነፍ እና በአንዱ ጨዋታ ላይ ደግሞ አቻ በመለያየት በ13 ነጥብ እየመራ ይገኛል፤ ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡናም አንድ ትርፍ ጨዋታን ተጫውተው በ13 ነጥብ እና በግብ ክፍያ ተበልጠው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ሀዲያ ሆሳዕና በእዚሁ የሊጉ ሻምፒዮና እስካሁን ድረስ ያልተሸነፈው ብቸኛው ቡድን ሲሆን ይህን ያለ መሸነፍ ሪከርድም በቀጣዮቹ ጨዋታዎች ላይ አስቀጥሎም ለማስጓዝ በጣሙን እየተዘጋጁ እንደሆኑ የቡድኑ ተጨዋቾች እየተናገሩ ይገኛል፡፡
ሀዲያ ሆሳዕና በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ነገ 4፡00 ሰዓት ላይ በጅማ ከተማ በሚገኘው የጅማ ዩንቨርስቲ ሜዳ ላይ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በሁለተኛ ስፍራ ላይ የሚገኘውን ፋሲል ከነማን የሚፋለም ሲሆን ይህም ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እያስመዘገቡት ካለው ስኬታማ ውጤት አኳያ ከወዲሁ በጣሙን እየተጠበቀም ይገኛል፡፡
የሀዲያ ሆሳዕናን የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጉዞ እና ስለ ቡድናቸው አቋም እንደዚሁም ደግሞ ዘንድሮ ሊያስመዘግቡት ስላሰቡት ውጤት እና ከራሱ የተጨዋችነት ተሳትፎው ጋር በተያያዘ ክለቡን ከመቐለ 70 እንደርታ ቡድን በመምጣት ከተቀላቀለው ስኬታማው የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች ተስፋዬ በቀለ /ጃምቦ/ ጋር ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ቆይታን ያደረገ ሲሆን ተጨዋቹ ምላሾቹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፡፡
ሊግ፡- ከእዚህ ጥያቄ እንነሳ… ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ከማምራትህ በፊት በመቐለ 70 እንደርታ ክለብ ውስጥ ነበርክ፤ በእዛ ቡድን ውስጥ ምን አይነት ጊዜን አሳለፍክ?
ተስፋዬ፡- በመቐለ 70 እንደርታ ውስጥ የነበረኝ ቆይታ ባሳለፍነው ዓመት በነበረው የሁለተኛው ዙር የዝውውር መስኮት ክለቡን ገና የተቀላቀልኩበት እና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያትም ብዙ ጨዋታዎችን ካለማድረጌ አኳያ እንዲህ ነበር ብዬ ለመናገር ፈፅሞ አልፈልግም፤ ቢሆንም ግን በቡድኑ ውስጥ ጥሩ ጊዜን ለማሳለፍ እና ክለቡን በሚገባ ለማገልገል መጥቼ ነበር፤ ኮቪድ ግን የሊጉን አጠቃላይ ውድድር ስላቋረጠው ሁሉም ነገር በእዛው ሊቀር ችሏል፡፡
ሊግ፡- ሀዲያ ሆሳዕናን ስትቀላቀል ዘግይተህ ነበር፤ ይሄ ሊሆን የቻለው በምን ምክንያት ነው? በኋላ ላይ ክለቡስ እንዴት ምርጫህ ሆነ?
ተስፋዬ፡- ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ዘግይቼም ቢሆን ለመምጣት እና ወደ ቡድኑ ውስጥም ለመግባት የቻልኩት እኔን ጨምሮ 6 እና 7 የምንደርስ ተጨዋቾች በመቐለ ከተማ ላይ በነበረው የሀገሪቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት በእዛ ከተማ ላይ ቆይታን ስላደረግንና ብዙ ቡድኖችም ተጨዋቾችን በማስፈረሙ በኩል ሞልተው እና የዝግጅት ጊዜያቸውንም ስለጀመሩ እኛ ነገሮች ከረፈዱ በኋላ በመምጣታችን ነው፤ ያም ሆኖ ግን መጨረሻ ላይ ተጨማሪ ተጨዋቾችን ማስፈረም የሚፈልገው የሀዲያ ሆሳዕና ክለብ በአሰልጣኙ አሸናፊ በቀለ አማካኝነት እኔን ለቡድኑ ስኳድ ይፈልገኝ ስለነበርና ከዚህ ቀደምም በአዳማ ቡድን ውስጥ ስላሰለጠነኝ፤ በክለቡ ውስጥ ካሉት አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች ጋርም ለሶስት ዓመታት ያህል ከእዚህ ቀደም በአዳማ ከተማ ክለብ ውስጥ በነበረኝ ቆይታዬ አብሬያቸው የተጫወትኩኝ ስለሆነ በእዛም ነው ምንም አይነት ነገርን ሳላንገራግር ለቡድኑ የመጫወት ፍላጎቴ ከፍተኛ ሆኖ ክለቡን የተቀላቀልኩት፡፡
ሊግ፡- በመቐለ የፖለቲካው አለመረጋጋት በተፈጠረበት ወቅት ከመቐለ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የመጣህበትን ሁኔታ ሳትነግረን?
ተስፋዬ፡- መጀመሪያ ላይ ስላልጠየቅከኝ እንጂ አመጣጤማ ይሄንን ነው የሚመስለው፤ በቅድሚያ የእኛን የመቐለ 70 እንደርታን አራት ተጨዋቾች ጨምሮ ሌሎች ሁለት የወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ተጨዋቾች ነበሩ፤ ከእኛ ጋር አንድ ዶክተርም አብሮን ነበር፤ ያን ጊዜም በከተማው ውስጥ ነዳጅ ስለሌለና ምንም አይነት እንቅስቃሴም ስላልነበር በእግራችን ከመቐለ ከተማ አንስቶ የትግራይ ድንበር ወደ ሆነችው አባይታ ዳርፉር ወደምትባለው 57 ኪ. ሜትር ወደ ሚፈጀው ቦታ ለመጓዝ መጀመሪያ ላይ የ30 ኪ.ሜትር የእግር ጉዞን አደረግን፤ ከዛም ቀሪውን ስፍራ ደግሞ ለእያንዳንዳችን 1ሺ 700 ብር በመክፈል በትራንስፖርት ተጓዝንና በመጨረሻም ወደ አዲስ አበባ ከተማ ልንመጣ ቻልን፡፡
ሊግ፡- ወደ ሀዲያ ሆሳዕና በመምጣትህ ለክለቡ ባዳ አይደለህም ማለት ነው?
ተስፋዬ፡- የእውነት ነው፤ ከላይ እንደገለፅኩትም አሰልጣኙ ከዚህ ቀደም ስላሰለጠነኝ እና ከብዙዎቹም ጋር አብሬያቸው ስለተጫወትኩኝ እንደዚሁም ደግሞ በደንብም ስለምንተዋወቅ የነባር ያህልም የተጨዋችነት ስሜትም ነው እየተሰማኝ ያለው፤ ቡድኑ ከሶስት እና አራት ነባር ተጨዋቾቹ በስተቀር በአብዛኛው አዳዲስ ልጆችንም ነው የያዘው፤ እነዛ በርካታ ተጨዋቾች ደግሞ እኛ ከዚህ ቀደም አብረን የተጫወትንና የተላመድንም ስለሆንን ከእዚህ ቡድን ጋር ጥሩ ነገርን እንሰራለን ብዬ አምናለው፡፡
ሊግ፡- ሀዲያ ሆሳዕናን ስትቀላቀል ስለ ቡድኑ ምን አውቀህ ነው? ዘንድሮስ ምን ነገሮችን እየተመለከትክ ነው?
ተስፋዬ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ይሄ ቡድን በፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው ላለመውረድ ይጫወት እንደነበር እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም የስፖርት ቤተሰብና ደጋፊው ጭምር በጣም ነው የሚያውቀው፤ ከዛ ውጪ ስለ ቡድኑ አጠቃላይ ሁኔታም ለመረዳት ለማንም የአደባባይ ሚስጥርም አይደለም፤ ይሄን ሁሉ አውቄ እና ቡድኑም በሁሉም መልኩ በተስተካከለ ሁኔታም ላይ ስለተገኘ ነው ወደ ክለቡ ገብቼ ልጫወት የቻልኩት፡፡
ሀዲያ ሆሳዕናና ከተቀላቀልኩ በኋላ በቡድኑ ውስጥ የተመለከትኳቸው ነገሮች በጣም ጥሩ ናቸው፤ ይሄ ቡድን ከአምናው በሜዳ ላይ እንቅስቃሴውም ሆነ ቢሮ አካባቢ ባለው የአመራሮቹ ስራ በብዙ መልኩ ተቀይሮ ነው የመጣው፤ ሀዲያ ባለፈው ዓመት ላለመውረድ ነበር የሚጫወተው፤ አሁን ግን ቡድኑ ስኬታማ ውጤትን በማምጣት የክለቡን ታሪክ እና ገፅታን እየቀየረ መጥቷልና በእዚህ ደረጃ ላይ መገኘቱ የቡድኑን ደጋፊዎችም አመራሮችንም እያስደሰተ ይገኛል፡፡
ሊግ፡- ባለፈው ዓመት ላለመውረድ ይጫወት የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና ዘንድሮ በጣም ተለውጧል፤ የፕሪምየር ሊጉን ውድድርም በአሁን ሰዓት ላይ እየመራ ይገኛል፤ የእዚህ ለውጥ ሚስጥር ምን ይመስልሃል?
ተስፋዬ፡- ለቡድኑ የለውጥ ሚስጥር መጀመሪያ ሊጠቀስ የሚችለው ነገር ቢኖር ቡድኑ ከአመራሩ አንስቶ ባለፈው ዓመት የሰራውን ስህተት ላለመድገም ብዙ ነገሮችን ተምሮ በመምጣቱ እና በቡድኑም ላይ ጥሩ ስራን በመስራቱም ይመስለኛል፤ ለምሳሌ ሀዲያ አምና በተጨዋቾች አሰባሰቡ በኩል በቂ የሆነ ስራን የሰራ አይመስለኝም፤ በእዚህ ዓመት ላይ ግን ልምድ ያላቸውንና ቡድኑንም በጣም መጥቀም የሚችሉ ልጆችንም ያመጣበት አጋጣሚ በመኖሩ ከዛ ውጪ ደግሞ የክለቡ አመራሮች ከእኛ ጎን በማንኛውም አጋጣሚዎች ሳይጠፉ እና የምንፈልጋቸውንም ነገሮች ኢንሴንቲቭን ጨምሮም ስለሚሰጡንና ስለሚያበረታቱን እነዚህ ነገሮችም ናቸው እኛን እያነቃቃን በውጤታማነታችን እንድንጓዝ እያስደረጉንም ያሉት፡፡
ሊግ፡- ሀዲያ ሆሳዕና ሊጉን የሚመራው ያለመሸነፍ ሪከርዱን እያስቀጠለ ባለበት ሰዓት ላይ ነው፤ ይሄ ያልሸነፍ ባይነት ጉዞው ይቀጥላል?
ተስፋዬ፡- እኛ እንግዲህ በእዛ መልኩ ነው ውጤቱን አስቀጥለን ለማስጓዝ እየተጫወትን የምንገኘው፤ ለእዛ እንዲረዳንም በቡድኑ ውስጥ የምንገኘው አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች ከዚህ ቀደም በአንድ ቡድን ውስጥ እንተዋወቅ እና እንግባባም ስለነበር ያ ይጠቅመናል፤ ሌላው አሰልጣኛችንም ሆነ የቡድኑ አመራሮች ይሄን ውጤታማነት እንደ እኛው ሁሉ የሚፈልጉት ስለሆነም የእነሱ እገዛ እና ምክሮችም ለጥሩ ነገር ያበቃናል ብዬም እያሰብኩ ነው፡፡
ሊግ፡- ሀዲያ ሆሳዕና በቤት ኪንግ የፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎ ዋንጫውን ያነሳል ወይንስ አያነሳም?
ተስፋዬ፡- ለሁሉም ነገር ፈጣሪ ነው የሚያውቀው፤ ቡድናችን በአሁን ሰዓት ላይ ከጅማሬው እየሰራ ያለው ስራ የከዚህ በፊቱን ጥሩ ያልነበረውን የክለቡን ኢሜጅ ወደ ጥሩ እና ፖዘቲቭ ወደ ሆነ መልኩ በመቀየር ላይ ስለሆነ ያ ከወዲሁ እየተሳካለት ይገኛል፤ ቡድናችን ዓምና እኔ ባልኖርበትም ላለመውረድ የሚጫወት ቡድን ነበር፤ አሁን ደግሞ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ የሊጉ መሪ ሆኗል፤ ይሄን ስኬትም ለማስቀጠል ተዘጋጅቷልና ቡድኑ ገፅታውን እየቀየረ ስለመጣ ዘንድሮ የማይታመን ውጤት ያመጣል፡፡
ሊግ፡- በቤት ኪንግ ተሳትፎአችሁ ጠንካራው እና ክፍተት ጎናችሁ የትኞቹ ናቸው?
ተስፋዬ፡- በውድድሩ ተሳትፎ እስካሁን ላስመዘገብነው ውጤት በጠንካራ ጎንነት የማነሳው ዋንኛው ጎን ከብዙዎቹ ተጨዋቾች ጋር ከዚህ በፊት ጭምር በሜዳ ላይ እንተዋወቅ እና በእንቅስቃሴም በኩል እንግባባ እና የአሰልጣኙንም ታክቲክ እንተገብርለት ስለነበር ነው፤ ሌላው የቡድኑ አመራሮች ከቡድኑ ጎን መሆናቸው ከሁሉም በላይ ጠቅሞናል፡፡ ወደ ክፍተት ጎን ሳመራ ደግሞ ይሄ ሊከሰት የሚችለው አሁን ሳይሆን ተደራራቢ ግጥሚያዎችን በ17 ቀናት ልዩነት ውስጥ 5 ጨዋታዎችን በጅማ ከተማ ላይ በቀጣይነት ስናደርግ ነው፤ ያኔም ነው የእኛ ቡድን ብቻ ሳይሆን የሁሉም ቡድን ክፍተት ጎኑ ብቻ ሳይሆን ሙሉ አቅሙም ሊታወቅ የሚችለው፡፡
ሊግ፡- በቤት ኪንኩ ለሀዲያ ሆሳህና ከባድ የነበረበት ጨዋታ የቱ ነበር?
ተስፋዬ፡- ከአምስቱ ጨዋታዎቻችን ውስጥ የመጀመሪያውን ገና ለቡድኑ መፈረሜን ተከትሎና ልምምድ ባለመስራቴም ባልጫወትበትም ለእኛ ከባድ ሳይሆን ፈታኝ የነበረብን ግጥሚያ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያደረግነው ነበር፤ ይሄ ጨዋታ የታክቲክ ጦርነት የነበረው ፍልሚያና ግጥሚያውን አሸንፎ ለመውጣትም ብዙ ጥረትን ያደረግንበት ስለነበርም የድል ጎሉን ለማስቆጠር እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ መሄድም አስፈልጎናል፡፡ ሌላው ከባህር ዳር ጋር እንደነበረን ግጥሚያ ባይሆንም ከወልቂጤ ከተማ ጋርም በነበረንና አቻ በተለያየንበት ጨዋታ እዛም ላይ ለተመሳሳይ በሚቃረብ መልኩ የተፈተንበት ሁኔታ ቢኖርም በተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ውስጥ ያገኘናቸውን የጎል እድሎች በእለቱ ከነበረብን የአጨራረስ ችግራችን አኳያ ነው ነጥብንም ለመጋራት የቻልነው፡፡
ሊግ፡- በቤት ኪንጉ ፕሪምየር ሊግ ለየት ያለ እና ወጣ ያለን ተጨዋች ተመልክተሃል?
ተስፋዬ፡- እኔ ከማውቀው እና እስካሁን ለቡድኔ ከተጫወትኩባቸው ጨዋታዎች አንፃር በእዛ ደረጃ ላይ የተመለከትኩትን ተጨዋች እስካሁን አላየሁም፤ ቢሆንም ግን ከቡድኑ አጨዋወት ጋር በመዋሀድ እና ለአሰልጣኙም የጨዋታ ታክቲክ ተገዥ በመሆን እንደዚሁም ደግሞ በእሱ አቅምና የዕድሜው ደረጃ ለቡድኑ የድል ጎሎችን እያስቆጠረ የሚገኘውን አቡበከር ናስርን በጥሩ ተጨዋችነት ተመልክቼዋለሁኝና ላደንቀው እፈልጋለሁ፤ አቡበከር በአሁን ሰዓት ለቡና ጎል በማስቆጠር፣ ፔናሊቲ በማስገኘት፣ ለቡድኑ ተጨዋቾች የግብ ኳስ በመስጠት ጥሩም እየተጫወተ ስለሆነም ነው ለቡና በፊት መስመሩ ላይ እሱ ባይኖር ከሚል ግምትም ተነስቼ ነው ለእሱ አድናቆቴን የሰጠሁት፡፡
ሊግ፡- ሀዲያ ሆሳዕና ሊጉን በ13 ነጥብ ይመራል፤ ፋሲል ከነማ ደግሞ በተመሳሳይ 13 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ይከተላል፤ ሁለቱ ቡድኖች ደግሞ በጅማ ዩንቨርስቲ ሜዳ ላይ ነገ ሊፋለሙ ቀጠሮን ይዘዋል፤ ይሄ ጨዋታ እንዴት ይጠበቅ…ማንስ የጨዋታው አሸናፊ ይሆናል?
ተስፋዬ፡- ከፋሲል ከነማ ጋር የሚኖረን የነገው ጨዋታ የሁለታችንም ቡድኖች በአሁን ሰዓት ላይ ከምንገኝበት የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ አኳያ እንደዚሁም ደግሞ ጠንካራ ቡድንንም ገንብተን ከመምጣታችን አንፃር ሲታይ ግጥሚያው በብዙዎች ዘንድ በጣም ተጠባቂ ሆኗልና ጥሩ ፉክክርን እንደምናደርግበት አምናለው፤ የነገው ተጋጣሚያችን ፋሲል ከነማ ጥሩ ቡድን እንደሆነ እናውቃለን፤ ኳስን በጥሩ መልኩም የሚጫወቱ ናቸው፤ ከዛ በተጨማሪም አሁን ላይ ወደ ማሸነፉም ስለመጡ ለእዚህ ጨዋታ በጥሩ ሁኔታ ስለተዘጋጀን በ90 ደቂቃው የጨዋታ ፍልሚያው ሜዳውም ይኸው ፈረሱም ይኸው በሚል ግጥሚያውን እየጠበቅን እነሱን ልናሸንፍ እና መሪነታችንንም ልናጠናክር ዝግጁ ነን፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተለያዩ ክለቦች ውስጥ እግር ኳስን ተጫውተህ አሳለፍክ፤ እነዛም ቡድኖችህ ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ፣ አዳማ ከተማ እና አምና ብዙ ቆይታ ባይኖርህም መቐለ 70 እንደርታ ነበሩ፤ ደስተኛ ሆነህ ነው ኳስን እየተጫወትክ ያለኸው?
ተስፋዬ፡- አዎን፤ እንዴትስ ደስተኛ አልሆን፤ በእግር ኳስ ታሪኬ እኮ ከመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ላይ ለደቡብ ምርጥ ቡድን ስጫወትና ለኢትዮጵያ ቡናዎችም ታጭቼ ለክለቡ እንድጫወት ስደረግ ጀምሮ በሀገሪቱ ውስጥ የተዘጋጁትን ዋንጫዎች ሁሉ ማንሳት ችያለሁ፤ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በ2000 ዓ/ም ላይ የክለቦች ህብረት ዋንጫን /የሚሊኒየሙን/ በ2003 ደግሞ የፕሪምየር ሊጉን እና የአሸናፊዎች አሸናፊን እንደዚሁም ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማን ዋንጫን ከመከላከያ ጋር ደግሞ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ስላነሳው እና በሌሎቹ ቡድኖች ውስጥ ደግሞ በጥሩ ሁኔታ የምወደውን ኳስ ስለተጫወትኩ እና አሁንም እየተጫወትኩ ስለሆነ ከእዚህ በላይ ምን ደስታ አለ፡፡
ሊግ፡- ቤት ኪንጉ በዲ.ኤስ.ቲቪ መተላለፉን አስመልክተህ ምን አልክ?
ተስፋዬ፡- በፕሪምየር ሊግ ደረጃ የእግር ኳስን ለ12 ዓመታት ስጫወት እንዲህ ያለውን እድሎች አግኝተን አናውቅም ነበርና የሀገራችን ኳስ በዲ.ኤስ.ቲቪ መተላለፉን ሳይ በመጀመሪያ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ የእዚህ ጨዋታ መተላለፍ መቻል ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት በጣም ጥሩ የሆነ ነገርም ነው፤ ተጨዋቾቻችን ወደ ውጪ ሀገር በመውጣት በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት የሚጫወቱበትን እድል ያገኛሉ፤ ከዛ ውጪ ታዳጊ ተጨዋቾችም ከእዚህ በፊት በዲ.ኤስ.ቲቪ ይመለከቱት እንደነበሩት የባህር ማዶ እግር ኳስ ሁሉ አሁን ደግሞ የሀገራቸው ተጨዋቾች ሲጫወቱ በየቤታቸው ሆነው የሚመለከቱበትም እድሉ ስለተፈጠረላቸው እና እነሱንም ለመሆን ስለሚጥሩ እና ተጨዋቾቹንም ስለሚያበረታቱ የእውነት ነው የምለው ይሄን እድል ወደ ሀገራችን እንዲመጣ ላደረገው የሊግ ካምፓኒው ኮሚቴና ለዲ.ኤስ.ቲቪ ከፍተኛ ምስጋናዬን ማቅረብ ነው የምፈልገው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ተስፋዬ፡- ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይባርክ፤ ሀገራችንንም ሰላም ያድርጋት፤ ከእዛ ውጪ መናገር የምፈልገው አሁን ላይ ለምጫወትበት ሀዲያ ሆሳዕና ክለብ አቅሜ በሚችለው መጠን ሁሉ ይህን ክለብ በሚገባ ለማገልገል እና ወደ ውጤታማነት ማማ እንዲጓዝም ጥረትን አደርጋለው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P