Google search engine

ሀድያ ሆሳህና ይወርዳል ብላችሁ አታስቡ፤ ከዛ ስጋት ነፃ ነን‘” ይሁን እንዳሻው /ሀድያ ሀሳዕና/


በመሸሻ ወልዴ


ሀድያ ሆሳህና የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ዘንድሮ ነው የተቀላቀለው፤ በሊጉ ካደረጋቸው ጨዋታዎች ውስጥም በኢትዮጵያ ቡና የደረሰበት የ5ለ1 ሽንፈት እና በሌሎች ቡድኖችም የደረሰበት ሽንፈት በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ አስቀምጦት ስለነበር ቡዙዎች ሀድያ ወደመጣበት መመለሱ አይቀሬ ነው ሲሉም ተሰምተዋል፤ ይህን አስመልክቶና በክለባቸው የሊጉ ተሳትፎ ዙሪያ ከቡድኑ ስኬታማ ተጨዋች ይሁን እንዳሻው ጋር ቆይታ ያደረግን ሲሆን ይህም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡
ስለ ሀድያ ሆሳዕና፣ ስለፕሪምየር ሊጉ የውድድር ጅማሬና አሁን ላይ ስላለው አቋም
“የፕሪምየር ሊጉን ዘንድሮ የተቀላቀለው ሀድያ ሆሳዕና ሙሉ ቡድኑ ማለት ይቻላል ዘንድሮ አዲስ ነው፤ ተጨዋቾቹም ከተለያዩ ቡድኖች የመጡ ናቸው፤ ውል ያራዘሙትም በጣም ጥቂት እና አምስት የሚደርሱም ተጨዋቾች ናቸው፤ ቡድናችን ይህን የሊግ ውድድር ማድረግ የጀመረውም በአዲስ መልክ ተዋቅሮ ባለበት ሁኔታ ነው፤ በውድድሩ ጅማሬ ለቡድናችን ወደ ሜዳ ቤስት ኢለቨን /11/ የሚገባው አንዱ ከአንዱ ጋር ተጫውቶ እና ተላምዶም በማይተዋወቅበት ሁኔታ ነው፡፡ ሁሉም ከተለያየ ቡድን ስለመጣም ቡድናችን ጊዜ ይፈልጋል ብዬም አስቀድሜ ተናግሬ ነበርና የሊጉ ጅማሬ ጨዋታዎች ላይ ነጥቦችን የጣልነው ቡድኑ አዲስ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ እና ቡድናችን ጥሩ ሆኖም በጥቃቅን ስህተቶች ጎል ስለሚገባበት እና እኛ ደግሞ የምናገኘውን የግብ አጋጣሚም ስለማንጠቀምበት ነው ያ ጎድቶናል፤ አሁን ላይ ግን በክለባችን በኩል የተወሰነ መዋሀድ እና መናበብ፤ እንደዚሁም ደግሞ አንዱ ከአንዱም ጋር የመቀናጀት ነገርን እያሳየን ስለሆነ ውጤት ማምጣት ጀምረናልና ይሄንንም ማስቀጠል ይገባናል”፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእዚህ አመት ተሳትፏችሁን በተመለከተ ውጤት ካለማምጣት ጋር እንደዚሁም ከመውረድ አንፃር የስጋት ስሜት ይፈጠርባችኋል
“ሀድያ ሆሳዕና በእዚህ በኩል ከምንም አይነት ነገር ነፃ ነው፤ ፈፅሞ አንሰጋም፤ ምክንያቱም በሜዳ ላይ የምታየው ነገር ቡድኑን ለዛ ስጋት የሚዳርገው አይደለምና ቡድናችን ላይ አሁን ጥሩ ነገር አለ፤ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ስንጓዝም ደግሞ ከዚህ በላይ እንደምንሻሻል እናውቃለንና ቡድናችን በተሻለ ውጤት ሊጉን ይጨርሳል ብለን እያሰብን ነው”፡፡
በኢትዮጵያ ቡና በርካታ ግቦች ተቆጥሮባችሁ ተሸነፋችሁ፤ ስለዛ ሽንፈት ምክንያት
“ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረን ጨዋታ ለቡድናችን ሽንፈት እንደምክንያት የምጠቅሰው እነሱ ከእኛ የተሻሉ ስለሆኑ ሳይሆን በደቂቃዎች ልዩነት የተከላካይ ክፍላችን ላይ በተፈጠሩ ክፍተቶች ጎሎች ስለተቆጠሩብንና ተጨዋቾቻችንም በስነ-ልቦናው ደረጃ መውረድ ስለቻሉና ስለተረበሹ ነው፤ በጨዋታው እስከ 30ኛው ደቂቃ ድረስ ቡድናችን ጥሩ ነበር፤ ሜዳውም የእኛ ይመስል ነበር፤ ተጭነናቸውም እንጫወት ነበር፤ ጎል ሲገባብን ግን ቡድናችን እየተሸነፈም የመጣ ስለነበር በሳይኮሎጂ ወረደ፤ አጥቂዎቻችን ደግሞ ጎል አያገቡም ነበርና ያ ጎድቶናል፤ በዚህ ላይ ጨዋታውን የምታደርገው ከቡና ጋር ነው፤ እነሱ በደጋፊዎቻቸውም ፊት ነው የሚጫወቱት፤ ጎል ማግባታቸው ለእነሱም ብዙ አይነት መነሳሳትም ፈጥሮላቸዋልና ቡና ጎሎችን ካገባ በኋላ ነው ራሱን አረጋግቶ በመጫወቱ እኛን ሊያሸንፈን የቻለው”፡፡
ሀድያ ሆሳህናን በቀጣይነት እንዴት እንጠብቀው፤ አንተንስ
“በዘንድሮ ውድድር ሀድያ ሆሳህናን ጥሩ ደረጃ ላይ ጠብቁት፤ ይሄን የምለው በሜዳ ላይ የሚያሳየው እንቅስቃሴ ጥሩ እና ስህተቱንም በፍጥነት ሊቀርፈው ስለሚችል ነው፤ ያን ስህተት መቀነስ ከቻልንና የተወሰኑ ተጨዋቾችን በሊጉ አጋማሽ ላይ ማካተት ከቻልን ጥሩ ተፎካካሪ እንሆናለን፤ በቶፕ አራት ውስጥም ሆነን እንጨርሳለን፤ እኔን በተመለከተ እንደ ግሌ ብዙ ሀላፊነት አለብኝና ለክለቤ ጥሩ ነገርን ለመስራት ዝግጁ ነኝ፤ ሌሎችም ሃላፊነት የሚጣልባቸውም ልጆች አሉና ቡድኑን ጥሩ ደረጃ ላይ እናደርሰዋለን”፡፡
በመጨረሻ..
“ለሁሉም የክርስትና እምነት ተከታዮች፤ እንደዚሁም ደግሞ ለቡድናችን ደጋፊዎች፣ ተጨዋቾች አሰልጣኞችና ለቤተሰቦቼ መልካም የጥምቀት በዓል እንዲሆንላቸው እመኛለው”፡፡

? Hossan sport

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P