Google search engine

“ሁለት ግብ ማስተናገዳችን ድክመታችንን ያሳያል” አብዱልከሪም መሐመድ /ፋሲል ከነማ/

 

ሊግ፡- በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ፋሲል ከነማ አል ሂላልን ገጥሞ 2-2 ተለያይቷል፤ ስለ ጨዋታው ምን ትላለህ?

አብዱልከሪም፡- እንደ መጀመሪያችን የእዚህ ውድድር ተሳትፎአችን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያችን ጥሩ የነበረ ቢሆንም ከሜዳ ላይ አድቫንቴጅ አኳያ ስናየው ደግሞ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ወይንም ደግሞ ጎል ሳናስተናግድ መውጣት ይኖርብን ነበር፤ ግን ኳስ ነውና ይሄ ውጤት ገጥሞናል፤ ስለዚህም አቻ መውጣታችን ለነገው የመልስ ጨዋታ ብዙና ትልቅ ነገር ከእኛ እንደሚጠበቅ ያሳየን ግጥሚያም ሆኖ አልፏል፡፡

ሊግ፡- ውጤቱ አስቆጭቷችኋል?

አብዱልከሪም፡- አዎን፤ የተቆጨነውም ጨዋታውን ካለማሸነፋችን በተጨማሪ ጎልም ስላስተናገድንበት ነው፤ ያም ሆኖ ግን የአቻ ውጤቱም አይከፋም፡፡

ሊግ፡- ለነገው የመልስ ጨዋታ ታዲያ በምን መልኩ እየተዘጋጃችሁ ነው?

አብዱልከሪም፡- ይሄን ጨዋታ በእነሱ ሜዳ ላይ ስለምናደርግ ከበድ ያለ ስራ ይጠብቀናል፤ ስለዚህም በጥሩ መልኩ ነው እየተዘጋጀን የሚገኘው፡፡

ሊግ፡- በባህርዳር ባደረጋችሁት የመጀመሪያው ጨዋታ ክፍተት ጎናችሁ ምን ነበር?

አብዱልከሪም፡- የእኛ ክፍተት ወይንም ደግሞ ጨዋታውን በአሸናፊነት እንዳንወጣ ያደረጉን ምክንያቶች ከእረፍት በመምጣታችንና ወደ ፕሪ-ሲዝን ልምምድ ከገባን በኋላም ተደጋጋሚ የአቋም መለኪያ ጨዋታን ልናደርግ ያለመቻላችን ነው፤ አንድ የወዳጅነት ጨዋታን ብቻ ነው ከኡጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር ያደረግነው፤ እነሱ ደግሞ ገና ሊጋቸው ስላልተጠናቀቀ ውድድር ላይ ነበሩ፤ ብዙ ነገሮችን እያረሙም ነበር የመጡት፤ ከዛም ውጪ ለብሔራዊ ቡድን ከእኛ ክለብ የተመረጡትም ተጨዋቾች ተሟልተው ልምምድን  ከእኛ ጋር ሲሰሩም አልነበረምና ያ በመቀናጀቱ ላይ መጠነኛ ክፍተትን ስለፈጠረብን ይሄም ጭምር ነው ውጤቱን እንድናጣ ያደረገን፡፡

ሊግ፡- ከመጀመሪያው ጨዋታ በጠንካራ ጎንነቱ የሚጠቀስላችሁ ነገር አለ?

አብዱልከሪም፡- በሜዳችን ጎል ተቆጥሮብን አቻ የወጣን ስለሆነ በዚህ ላይ ብዙ ነገርን ባልል እመርጣለው፤ ግን ቡድናችን ተደጋጋሚ ጎል ባያገባም ጎል ጋር መድረስ ይችላልና ይሄን እያሻሻልነው ልንጓዝ ይገባናል፡፡

ሊግ፡- የፋሲል ከነማ የመልስ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ ይደረጋልና ምን ውጤትን እንጠብቅ?

አብዱልከሪም፡- አሁን ላይ ለዚህ ጨዋታ በተሟላ መልኩ ነው ልምምዳችንን እየሰራን የምንገኘው፤ በመጀመሪያው ጨዋታ በሜዳችን ሁለት ግቦችን አስተናግደን አቻ ልንለያይ ችለናል፤ ከመመራት አንሰራርቶ ሁለት ግብ ማስቆጠርም ጥሩ ነው፤ ደግሞም አቻ ስለወጣን ጨዋታው አልቋል ማለት አይደለም፤ የአሁኑ የመልስ ጨዋታ ላይ ደግሞ እኛም እንደ እነሱ ከሜዳችን ውጪ በምናደርገው ጨዋታ ጎል የምናስቆጥርበት እድሉ ስላለን የተሻለ የሚባለውን ውጤት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረትን እናደርጋለን፡፡

ሊግ፡- የተሻለ ውጤት ማለት ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያሳልፋችሁን ነው?

አብዱልከሪም፡- ይህ እንግዲህ የሚታወቀው ከ90 ደቂቃ ልፋትና ጥረት በኋላ ነው፤ እኛ እንግዲህ ጨዋታውን ለማሸነፍ ነው ወደስፍራው የምናመራው፤ ከዛ የሚመጣውን ውጤት በፀጋ እንቀበላለን፡፡

ሊግ፡- በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ስለ እናንተ ተጋጣሚ አል ሂላል አቋም አንድ ነገር ብትል?

አብዱልከሪም፡- የሱዳኑ አል ሂላል ክለብ አፍሪካ ውስጥ አሉ ከሚባሉት ቡድኖች መካከል ስሙ በቀዳሚነት ሊጠቀስ የሚችል ነው፤ እስከ 7 እና 8 የሚደርሱ ተጨዋቾቹም ለብሄራዊ ቡድን የሚጫወቱ ናቸው፤ ጥሩ አቅምም አላቸው፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ……አንድ ነገር በልና እናጠቃል?

አብዱልከሪም፡- ፋሲል ከነማ እንደ ቡድን ጥሩ ነው፤ በክለቡ ያሉት ሁኔታዎች ሁሉም ደስ ይላል፤ ሁሉም ተጨዋቾች የሚግባቡበትም መልኩ ለየት ይላል፤ ወደዚህ ቡድን ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ባለው ነገርም ደስተኛም ነኝ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P