Google search engine

“ሁላችንም ተጨዋቾች ውጤቱን ቀልብሰን ወደተከታዩ ዙር ለማለፍ ተዘጋጅተናል” ምንይሉ ወንድሙ

መከላከያ /ኢትዮጵያ/ vs ሬንጀርስ /ናይጄሪያ/
የጨዋታ ቀን፡- ረቡዕ ህዳር 26/2011
የጨዋታ ሰዓት፡- 10፡00

የአፍሪካ ሀገሮች የተለያዩ ክለባትን የሚያሳትፈው የቶታል ኮንፌዴሬሽን ካፕ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ማክሰኞና ረቡዕ ዕለት የተካሄዱ ሲሆን ከእነዚህ ፍልሚያዎች መካከልም ሀገራችንን ወክሎ የተሳተፈው የመከላከያ ክለብ የናይጄሪያውን ክለብ ሬንጀርስ በመጀመሪያው ዙር ጨዋታው ተፋልሞ 2-0 ሊሸነፍ ችሏል፡፡
የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ወደናይጄሪያ ተጉዞ ከሬንጀርስ ጋር ባደረገው ጨዋታ 2-0 ሲሸነፍ ሁለቱም ግቦች የተቆጠሩበት በሁለተኛው አጋማሽ በፍፁም ቅጣት ምት ሲሆን ጨዋታውም ጠንካራ ፉክክር እንደተደረገበት እና አሸናፊው ሬንጀርስም ጥሩ ቡድን እንደሆነም እንቅስቃሴውን በመመልከት የመከላከያ ተጨዋቾችና የቡድኑ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ አስተያየታቸውን እየሰጡም ይገኛል፡፡
የመከላከያ ክለብ ከሬንጀርስ ጋር ስላደረገው ፍልሚያ የመልሱ ጨዋታ ላይ በምን መልኩ እንደሚቀርቡና ሌሎችንም ጥያቄዎች የቡድኑ ተጨዋቾች ከሆኑት ውስጥ አጥቂውን ምንይሉን ወንድሙም ጠይቀነው እንደሚከተለው ምላሹን ሰጥቶናል፡፡
በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ክለባቸው በናይጄሪያው ሬንጀርስ ሽንፈትን ስለማስተናገዱ
“የናይጄሪያውን ጠንካራ ክለብ ሬንጀርስ ከሜዳችን ወጥተን በተፋለምንበት ጨዋታ ምንም እንኳን ሽንፈትን ብናስተናግድም በጨዋታው እኛም እንደ እነሱ ሁሉ ጥሩ ነበርን፤ በአጠቃላይ የጨዋታው እንቅስቃሴ የግብ ዕድልም አግኝተን ሳንጠቀምበት ቀርተናል፤ የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታችን ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ስለተጫወትን ግብ ሳናስተናግድ የወጣንበት ነበር፤ በሁለተኛው አጋማሽ ግን ሁለት የፍፁም ቅጣት ምት ጎሎች ተቆጥሮብን ሽንፈትን ልናስተናግድ ችለናልና፤ አንዱ የፍፁም ቅጣት ምትም በዳኝነት ተፅህኖ የተገኘ እንጂ የሚያሰጥ አልነበረም፤ በእለቱ ከነበረው ጨዋታ አንፃር ሽንፈቱ እኛን የሚያስተምረንና ለቀጣዩ ጨዋታም ክፍተቶቻችንን እንድንመለከትበት ያስቻለን ጨዋታ ስለነበር የረቡዕን የመልስ ጨዋታችንን በተጋጣሚያችን ላይ የበላይነቱን ወስደን ውጤቱን ለመቀልበስ የሚቻለንን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን”፡፡
የናይጄሪያው ሬንጀርስ ክለብን አቋም በተመለከተ
“የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ተጋጣሚያችን የነበረውን የሬንጀርስን አቋም በተመለከተ ከእኛ ጋር ሲጫወቱም ሆነ ከዚህ በፊት ስለቡድኑ ከተመለከትነው የቪዲዮ ምስል በመነሳት ብዙ ነገሮችን አውቀናል፡፡ ሬንጀርስ ጠንካራና ጥሩ ቡድን ነው፤ ኳስን በመቆጣጠርና መስርተውም የሚጫወቱ ናቸው፤ ያ ስለሆነም ናይጄሪያ ላይ ከተሸነፍንበት እና ከገባብን ሁለት ግብ በመነሳት የመልሱ ጨዋታ ላይ እኛም ኳስን ተቆጣጥረን እና በሙሉ ኃይላችንም አጥቅተን በመጫወት ውጤቱን ለመቀየርና ወደቀጣዩ ዙርም የሚያሳልፈንን ውጤትም ለማስመዝገብ ዝግጁ ነን”፡፡
የመከላከያ እግር ኳስ ክለብን ወቅታዊ አቋም በተመለከተ
“የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ የአሁኑ ሰአት ላይ ያለው ወቅታዊ አቋም ጥሩ የሚባል ነው፤ የውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ላይም ጥሩ ኳስን በመጫወት የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ እና የአሸናፊዎች አሸናፊን ዋንጫ ሊያነሳ ችሏል፤ የኢንተርናሽናል ጨዋታው ላይም ቡድኑ በመጀመሪያው ግጥሚያ ይሸነፍ እንጂ ብዙም መጥፎ የሚባል ሆኖ አላገኘሁትም ያም ሆኖ ግን የግብ ዕድሎችን በምናገኝበት ሰዓት ያንን ልንጠቀምበት ይገባል”፡፡


የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የውድድር ተሳትፎአቸው ላይ ሊያመጡት ስላሰቡት ውጤት
“የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ከእዚህ ቀደም በእዚህ የውድድር ተሳትፎው በአብዛኛው ያመጣው ውጤት ጥሩ የሚባል አይደለም፡፡ ከአንድ ዙር በላይም ብዙ አያልፍም፤ ያ ሁሌም ይቆጨኛል፤ ስለሆነም የአሁኑ ተሳትፎአችን ላይ ግጥሚያችንን በሽንፈት ብንጀምርም በመልሱ ጨዋታ ላይ ከፈጣሪ ፈቃድ ጋር ውጤቱን ቀይረንና ረጅሙን የውድድር ጉዞም በማድረግ የከዚህ ቀደም ጥሩ ያልነበረውን ውጤታችንን በማሻሻል ለአገራችን እግር ኳስ ሪከርድ የሆነ ውጤት ለማስመዝገብ እና ያልተጠበቀ ውጤትና ታሪክም ለመስራት እንፈልጋለን”፡፡
የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ ስላለው ቆይታና በቀጣይነት ስለሚኖረው ግልጋሎት
“የመከላከያ እግር ኳስ ክለብን ከተቀላቀልኩበት ጊዜ አንስቶ ያለኝ ቆይታ ጥሩ የሚባል ነው፤ የእኔ ዋንኛው እቅዴና ህልሜም ቡድኑን ለጥሩ ውጤት ማብቃትና ራሴንም ለፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ማድረስ ስለሆነየአሁን ሰአት ላይ ያለኝን ብቃት በማሳደግ በቀጣዩ ጊዜም ለእዚያ ደረጃ የሚያደርሰኝንአቅም ለመያዝ በጥረት ላይ ነው የምገኘው”፡፡
ወደ ግብፅ ተጉዞ የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ሙከራን ሊያደርግ ስለመሆኑ
“የሰማችሁት መረጃና ጉዳዩ ይሳካልኝ እንጂ የእውነት ነው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጋና አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ ነው የእኔን እንቅስቃሴ በመመልከት ወደ ግብፅ ተጉቼ የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ሙከራን እንዳደርግ እድሉ በአዲሱ ወኪሌ አማካኝነት የተመቻቸልኝ፤ ሁኔታውንም ለቡድኔ አሳውቄያለው፤ የክለቤ ፍቃድ ከሆነም በእዚህ የ15 ቀን ጊዜ ውስጥ ወደስፍራው የማመራበት እድሉ ይኖረኛልና በሙከራውጊዜም የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት እልሜን እንደማሳካው እርግጠኛ ነኝ”፡፡
የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኑ ላይ ስለተደሰተበት እና ስለተቆጨበት አጋጣሚ
“የእግር ኳስን እየተጫወትኩ ባለሁበት የአሁን ሰአት ላይ በጣም ከተደሰትኩባቸው ጊዜያቶች መካከል የቅድሚያን ደረጃ ሰጥቼ የምጠቅሰው የቅርብ ጊዜያቶች ውስጥ ክለባችን ያገኛቸውን የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ድሎች ነው፤ በተለይ ደግሞ የአሸናፊዎች አሸናፊን ዋንጫ ባነሳንበት ወቅት በክለቡ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበ ድል ስለሆነ ያ የስኬት ድላችን የተለየ የደስታ ስሜትን ሊፈጥርብኝ ችሏል፡፡ በእግር ኳስ ዘመኔ ዋናው ቁጭቴ ብዬ የምጠቅሰው ደግሞ በአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታችንን በቅርቡ ከጋና ጋር አድርገን በደረሰብን ሽንፈት ምክንያት ከ31 አመት በኋላ ወደአፍሪከ ዋንጫው ያለፍንበትን የቅርብ ታሪክዳግም ለመስራት እቅድን ይዤ ዕድሉን በማጥበብ ልናሳከው ያልቻልንበትን ጨዋታ ነው”፡፡
በመጨረሻ…
“መከላከያ የአሁን ሰአት ላይ እንደቡድን ያለው አቅም ጥሩ የሚባል ነው፤ ክለባችን በሁሉም መልኩ እየረዳንና ጥሩም እንክብካቤ እያደረገልን ይገኛልና በእዚሁ አጋጣሚ የቡድናችንን አመራሮች፣ አጠቃላዩን የክለቡን አባላቶች እንደዚሁም ደግሞ ደጋፊዎቻችንን ማመስገን እፈልጋለሁ፤ ከእዚያ ውጪም ማስተላለፍ ከምፈልጋቸው መልዕክቶች መካከል የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽንካፕ የመልሱ ጨዋታ ላይ ውጤቱን ለመቀልበስ እና የተሻለም የአማረም ውጤት እንድናስመዘግብ የስፖርት ቤተሰቡ ከእኛ ጎን እንዲሆን ጥሪዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P