Google search engine

“የመሰለፍ ዕድሉን ላግኝ እንጂ ቅ/ጊዮርጊስን ከዚህም በላይ እጠቅመዋለሁ” ሃብቶም ገ/እግዚአብሄር /ቅ/ጊዮርጊስ/

“የመሰለፍ ዕድሉን ላግኝ እንጂ ቅ/ጊዮርጊስን ከዚህም በላይ እጠቅመዋለሁ”

ሃብቶም ገ/እግዚአብሄር /ቅ/ጊዮርጊስ/

የ16ኛው የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ካስመለከቱን ምርጥ እና ተደናቂ ችሎታ ካላቸው ወጣት  ተጨዋቾች መካከል አንዱ ነው። ሃብቶም ገ/እግዚአብሄር ይባላል። በታዳጊው ቡድን ውስጥ በነበረው ቆይታ ጥሩ ጊዜን አሳልፏል። አሁን ላይ ደግሞ በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ውድድር ላይ ቅ/ጊዮርጊስ ተተኪ ተጨዋቾቹን ይዞበት በቀረበበትና በተወዳደረበት ጨዋታ ላይ አራት ግቦችን በማስቆጠር እና ለሶስት ጊዜያትም የየጨዋታዎቹ ኮከብ ተብሎ በመሸለም ውድድሩን ሊነግስበት በቅቷል።

ቅ/ጊዮርጊስ የመቻል አቻውን በሲቲ ካፑ አሸንፎ ሻምፒዮና ሲሆን ወሳኙንና ብቸኛዋን  የድል ግብ በማስቆጠር  በቡድኑ ደጋፊዎችና በሌሎችም የስፖርቱ አፍቃሪዎች ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈውን ሃብቶምን የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ በኳስ ህይወቱ ዙሪያ እና ቅ/ጊዮርጊስን ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮ ስላለው የኳስ ቆይታው አነጋግረነው ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል፤ ቃለ-ምልልሱም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል።

ሊግ፦ በቅድሚያ ለቃለ-ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆንክ ከልብ እናመሰግንሃለን?

ሃብቶም፦ እኔም የጋዜጣችሁ እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናችኋለሁ።

ሊግ፦ ውልደትህ እና እድገትህ የት ነው?

ሃብቶም፦ የተወለድኩት በወለጋ ጉትን በሚባል አካባቢ ሲሆን ዕድገቴ ደግሞ በመቀለ ከተማ ላይ ነው።

ሊግ፦ በቤተሰባችሁ ውስጥ ስንት ወንድም እና እህቶች አሉ?

ሃብቶም፦ ሶስት ወንድሞች እና ሁለት እህቶች ናቸው ያሉኝ፤ ከራሴ ጋር በአጠቃላይ ስድስት ልጆች ቤት ውስጥ እንገኛለን።

ሊግ፦ በቤተሰቡ ውስጥ ስፖርተኛው አንተ ብቻ ነህ?

ሃብቶም፦ አዎን፤ ሌሎቹ በየግል ስራ የተሰማሩ ናቸው።

ሊግ፦ የእግር ኳሱን ልጅ ሆነህ ስትጫወት የቤተሰብ ፍላጎት እና ፈቃድ ነበረህ? ወይንስ ትከለከል ነበር?

ሃብቶም፦ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያ ቤተሰብ ያኔ ኳሱን ስጫወት እነሱ ብዙም ደስተኞች አልነበሩም፤ በትምህርቱ ላይ እንዳዘነብል እና ጠንከር እንድልም ነበር የሚፈልጉት። ያም ሆኖ ግን የእኔ ኳስ የመጫወት ፍላጎቴ ከአቅም በላይ እና ከውስጤም ጋር የተያያዘ ሲሆን ጊዜ ቤተሰብንም ያለመስማት ነገር ተፈጠረ እና እነሱን ታግዬ ኳስ ተጨዋች ልሆን ቻልኩ።

ሊግ፦ የኳሱ መነሻህ ፕሮጀክት ነው?

ሃብቶም፦ አዎን፤ ሀይስ ስፖርት የሚባል ፕሮጀክት  ቡድን ነበረን፤ ካልተሳሳትኩኝ ትምህርት ቤቶች በሚያሰሩ በእንግሊዞች የሚረዳም የድርጅት ቡድን ነበር። በእነሱ ስር ታቅፈን ነበር ስንሰለጥን የነበረው።

ሊግ፦ ያኔ ስልጠናውን ስትወስዱ ከድርጅቱ ክፍያ ነበራችሁ?

ሃብቶም፦ ኸረ ምንም ክፍያ የለም። እንሰለጥናለን ከዛም በዓመት አንድ ወይንም ደግሞ ሁለት ማሊያ ይሰጠንና ትርፋችን እሱ ነበር።

ሊግ፦ ከመቀለ የቅ/ጊዮርጊስ የተተኪ ቡድን ምርጫን ለማድረግ በቀጥታ መምጣትህን ሰማን?

ሃብቶም፦ እውነት ነው፤ ይሄ የሆነውም በ2013 ዓ/ም ላይ ነበር። በወቅቱ የአሁኑ አሰልጣኛችን ሳምሶን ሙሉጌታ /ፍሌክስ/ ለቡድኑ ተተኪ የተጨዋቾች ምልመላን ቦሌ በሚገኘው የክለቡ ሜዳ ላይ ያደርግ ነበርና ያን እንደሰማሁ እዛ ምልመላ ላይ በቀጥታ ከመቀለ መጣሁ። ያኔ የኳስ ፍላጎቴ በጣም ከፍተኛም ነበርና ዕድሉ ሳያመልጠኝ ቀርቶ የክለቡን ምርጫ በማለፍ ልያዝ ቻልኩ።

ሊግ፦ ለቅ/ጊዮርጊስ የተተኪ ቡድን  ምርጫ ስትመጣ አዲስ አበባ ላይ ማን ጋር ተቀመጥክ?

ሃብቶም፦ እዚህ ወንድም ነበረኝ፤ ፀጋዬ ገ/እግዚአብሄር ይባላል። እሱም ጋር ነው  በመቀመጥ የኳስ ፍላጎቴን በሚገባ ያውቅ ስለነበር ምርጫ እንዳለ ነግሮኝ ለቅ/ጊዮርጊስ እንድሞክር  ያደረገኝና ለእኔ መንገዶችን ስለከፈተልኝ እና ትልቅ ቦታ ስላለሁም ለሚያደርግልኝ ነገሮች ሁሉ ከልብ ላመሰግነው እፈልጋለሁ።

ሊግ፦ ቤተሰቦችህ በመቀለ ነው የሚገኙት ሀገሪቷ  አሁን ላይ  ካለችበት ሁኔታ በመነሳት ስለ እነሱ ስላሉበት ሁኔታ የምታውቀው ነገር አለ?

ሃብቶም፦ አዎን፤ ወላጅ እናቴ፣ ወንድሜና እህቶቼ እዛ እንዳሉ ባውቅም ኳስን ስለ እነሱ እያሰብኩ መጫወቱ ትልቅ ተፅህኖ አለው። ምክንያቱም  እነሱን ካገኘዋቸው አሁን ሁለት ዓመት ሊሆነኝ ነው፤ ለአንድ ቀን ተለይቻቸው የማላውቀውን ቤተሰቦቼን ትንሽ ጊዜ ስትርቅ ራሱ ያለውን ስሜት ታውቀዋለውና ተፅህኖው ከባድ ነው።

ሊግ፦ ወላጅ አባትህስ?

ሃብቶም፦ እሱ ልጅ እያለሁ ነው ያረፈው። እናቴ ነች እንደ እናትም አባትም ሆና ያሳደገችኝ።

ሊግ፦ የቅ/ጊዮርጊስ የተተኪ ቡድኑን ምልመላ በአንዴ ማለፍ ቻልክ?

ሃብቶም፦ በአንዴ አይደለም ምርጫውን ያለፍኩት። ብዙ ሆነውም ነበር ምርጫውን ሲያደርጉ የነበሩት በኋላም ላይ አሰልጣኝ ሳምሶን በተደጋጋሚ ጊዜ ሰጥቶ ሲያየኝና አቅሜን አውጥቼም እንድጫወት ስላደረገኝ  ጥሩ ነገርን ተመለከተብኝና በስተመጨረሻም ለክለቡ አስፈረመኝ።

ሊግ፦ ከልጅነትህ  ዕድሜህ አንስቶ በአጥቂ ስፍራ  ነው መጫወት የጀመርከው ?

ሃብቶም፦ በአብዛኛው ጊዜ የመስመር ተጨዋች ነበርኩኝ። ወደእዚህ ከመጣሁ በኋላ ግን በአሰልጣኜ ሳሚ ፍሌክስ አማካኝነት አዲሱን ቦታዬን ልላመደው ቻልኩኝ።

ሊግ፦ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ የተተኪው ቡድን  ከገባ በኋላ ያለህ ቆይታ ምን ይመስላል?

ሃብቶም፦ በጣም አሪፍ ቆይታ ነበረኝ። በእዛም ቡድን ቆይታዬ የምትሰማቸው ነገሮችም ነበሩ።  ክለቡ ትልቅ ስለሆነ በታዳጊዎች ላይ እምነት የለውም የሚል ነገርም ነበር፤ ሆኖም ግን ቡድኑ ታዳጊዎች ላይ ጥሩ ስራን ሲሰራና ትኩረትም ሲሰጥ ተመልክቻለሁና አመለካከቴን ለመቀየር ችያለሁ።

ሊግ፦ ከሁለቱ ዓመታት የተተኪ ቡድኑ ቆይታህ ለአንተ ለየት ያለውና ስኬታማ ሆኜበታለሁ የምትለው የቱን ነው?

ሃብቶም፦ በዝዋይም በአሰላም በነበሩት የውድድር ተሳትፎአችን  ጥሩ ጊዜን ባሳልፍም ይበልጥ ግን 2014 ላይ የነበረኝ ቆይታ የላቀ ነበር። በእዛን ወቅት የሊጉ አጀማመራችን አሪፍ ነበር። መጨረሻ ላይ በሰራናቸው ጥቃቅን ስህተቶችም ነበር ዋንጫን እንዳናነሳ ያደረገን። በግሌ ግን በአምስት ጨዋታዎች ላይ በወለምታ ጉዳት ሳልሰለፍ  በመቅረት  በሌሎች ጨዋታዎች ላይ ስምንት ጎሎችን አስቆጥሬ ነበርና ይሄ የእኔን ስኬታማ ተጨዋችነት ያሳየኝ ነው።

ሊግ፦ የቅ/ጊዮርጊስን መለያ አጥልቆ መጫወት ስላለው ስሜት የምትለው ነገር ካለ?

ሃብቶም፦ የእውነት ያን ስሜት  ለመናገር  በጣም ከባድ እና ከምልህም በላይ ነው፤ ልዩ ስሜት ነው የሚሰማህ። ምክንያቱም ቅ/ጊዮርጊስ በጣም ትልቅ ቡድን ነው። ሚሊያውን ለብሰህ ለክለቡ ስትጫወት ሁሌም ውጤት የሚፈለግ በመሆኑ ጫና አለው። ማሊያውን ስትለብስ ምንጊዜም አሸናፊ መሆን አለብህና ያን ታላላቅ ተጨዋቾች አጥልቀው የተጫወቱበትንና የነገሱበትን ማሊያ እኔም ዕድሉን  አግኝቼ  ስለተጫወትኩበት የተለየ ስሜት እንዲሰማኝ እያደረገኝ ነው፤ ይህን ማሊያ አድርጌም ስለተጫወትኩበት ለእኔ ክብር ነው።

ሊግ፦ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ የዋናው ቡድን ከማደግህ ጋር ተያይዞ በቋሚነት ስለመሰለፍ ምን እያሰብክ ነው?

ሃብቶም፦ በቅድሚያ ለዋናው ቡድን ለማደግ በመቻሌ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤  ሲቀጥል ደግሞ ይሄ ቡድን የሀገሪቱን ትላልቅ አጥቂዎችን የያዘ በመሆኑ  ውሳኔው የአሰልጣኙ ቢሆንም የመጫወት ዕድሉን  ካገኘው አቅሙ እንዳለኝ ስለማውቅ የቋሚ ተሰላፊነቱን ቦታ ከእነሱ ጋር ተፎካክሬ እንደማገኘው በራሴ ላይ ከፍተኛ እምነቱ አለኝ።

ሊግ፦ በኳስ ተጨዋችነት የወደፊት ራዕይህ እና ግብህ ምንድን ነው?

ሃብቶም፦ ከህፃንነቴ ዕድሜ አንስቶ ለኳስ ጥልቅ ፍቅር ስላለኝ የእኔ የወደፊት ራዕዬ በትልቅ ደረጃ ላይ ማለትም በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላይ ተፅህኖ ፈጣሪ ተጨዋች መሆንና ብሎም ደግሞ በብሄራዊ ቡድን ደረጃና ወደ ውጪ በመውጣትም እስከ ፕሮፌሽናል  ተጨዋችነት ደረጃ ላይ ደርሼ መጫወትን እፈልጋለሁ።

ሊግ፦ የእግር ኳስን ልጅ ሆነህ ስትጫወት ተምሳሌትህ /ሞዴልህ/ ማን ነበር?

ሃብቶም፦ እንዳልኩህ እኔ መቀለ ነው ያደግኩት፤ ያኔ ኳስን ስጫወት ፕሪምየር ሊጉ ላይ ቡድን አልነበረውምና  ከምሰማቸው እና በቲቪም ከምመለከተው ነገር በመነሳት አደንቃቸው ከነበሩት ውስጥ የፊት መስመር ተጨዋችም ስለሆንኩ ጌታነህ ከበደን፣ ሳላህዲን ሰይድንና አዳነ ግርማን ነው ሳደንቃቸው የነበረው። እነሱ ተምሳሌቶቼም ነበሩ።

ሊግ፦ ከባህርማዶስ?

ሃብቶም፦ የሊዮኔል ሜሲ፣ የክርስቲያኖ ሮናልዶና የሀዛርድ አድናቂ ነኝ። በጣምም ነው የምወዳቸው።

ሊግ፦ ከባህርማዶ ቡድኖች የማን ደጋፊ ነህ?

ሃብቶም፦ የቼልሲ።

ሊግ፦  የእረፍት ጊዜህን በምን ታሳልፋለህ?

ሃብቶም፦ በእኛ ዕድሜ ብዙም የምናርፍበት ጊዜ ባይኖርም አብዛኛውን ቤተክርስቲያን በመሄድ ነው የማሳልፈው።

ሊግ፦ ቅ/ጊዮርጊስ መቻልን በማሸነፍ የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫን አንስቷል፤ አንተም በሶስት ጨዋታዎች ላይ ማን ኦፍ ዘማች ተብለህ ተሸልመሃል፤ ድሉ እና ስሜቶቹ እንዴት ይገለፃሉ?

ሃብቶም፦  ከመቻል ጋር የነበረን ጨዋታ በጣም ከባድ ነበር፤ ምክንያቱም ተጋጣሚያችን መቻል  ጠንካራ ቡድን ስለነበርና ለራሴም እያየዋቸው ያደግኳቸው እንደ እነ ምንይህሉ ወንድሙ የመሳሰሉትንና አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ተጨዋቾችም የነበሩበት ቡድንም ነበርና እኛ እነሱን አሸንፈን የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫን ከፍ አድርገን ስላነሳን ከምልህ በላይ በጣም ደስ ብሎኛል።

በውድድሩ ቆይታዬም ለሶስት ጊዜያት ያህል የየጨዋታዎቹ ኮከብ ተብዬ በመሸለሜ የተሰማኝ የደስታ ስሜት ከፍ ያለ ነው፤ ሽልማቱን ያገኘሁት የሀገሪቱ ትላልቅ ተጨዋቾች ባሉበትና ከትላልቅ ክለቦችም ጋር በተጫወትኩበት ሁኔታም ጋር በመሆኑ በራሴ ላይ እምነት እንዲኖረኝ አድርጓል። ይህንን የሽልማት ክብር ስጠብቀው የነበረም ነው፤ ፈጣሪ ዕድሉን ሰጥቶኝ  የኮከብነቱን ሽልማትን ስላገኘውም ደስ ብሎኛል፤ በራሴም ልኮራም ችያለሁ።

ሊግ፦የቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን አጠር ባለ ቃላት ስትገልፃቸው እና በዋንጫው ቀን ላይ ስለነበራቸው ድባብ ምን ትላለህ?

ሃብቶም፦ የእኛን ደጋፊ በቀላል ቃላት መግለፅ በጣም ይከብዳል። ወደ ቡድኑ ስመጣ እነዚህ ደጋፊዎች በልምምድ ሜዳ ያዩን ነበር። ጨዋታዎቻችንንም ይመለከቱ ነበር።  በሲቲ ካፑ የዋንጫው ዕለትም ሲደግፉን ያላቸው የድጋፍ ድባቡ በጣም የሚገርም ነበር። ለትልቅ ቡድን የሚመጥን ድጋፍንም ነበር ሲሰጡን የነበሩት። እነሱ ለእኛ የኋላ ደጀኖቻችን ነበሩ። ሞራልም ሲሆኑን ነበር። እነሱ ባሉበት ፊት በመጫወቴም ኩራት ይሰማኛል። ለሰጡን ድንቅ ድጋፍ ሁሉ ሊመሰገኑም ይገባል።

ሊግ፦ በሸገር  ደርቢ ከኢትዮጵያ ቡና ጋርም የመጫወትና ኮከብ ተጨዋች ተብለህም የመሸለም ዕድሉ ገጥሞሃል። ያን ሁኔታን እንዴት ነው የምትገልፀው?

ሃብቶም፦ የሸገር  ደርቢ  በኮቪድ እና በሌሎችም ምክንያቶች ከተቋረጠ ሶስት ዓመታት በኋላ አዲስ አበባ ላይ በነበረው በእዚህ ጨዋታ ላይ አይደለም ሜዳ ውስጥ ገብተህ  ተጫውተህ  እንዲሁ በቴሌቭዥን ስትመለከት ያለው ድባብና ድምቀቱ በጣም ደስ ከማለቱ በተጨማሪ ያስፈራል፤ እኔም በእዚህ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይ በታዳጊ ወጣትነት ዘመኔ ስለተጫወትኩኝም በጣም ዕድለኛ ነኝ። ደስም ብሎኛል። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የነበረን ጨዋታ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ነበር። ሁለታችንም ኳስን መስርተን ስንጫወትም ነበር። እነሱ በልምዱ የበለጡን ቢሆንም እኛ ደግሞ የአቅማችንን ያህል ተጫውተን፣ ለማሊያው  ያለንንም ፍቅር አሳይተንና ወደ ዋናው ቡድን ለማደግም በፍላጎት እንደ አንድ ሆነን ተጫውተን ግጥሚያውን በአሸናፊነት ያጠናቀቅንበት ሁኔታ አለና በጨዋታው ላይ የግጥሚያው ኮከብ ተጨዋች ስለተባልኩ በጣም ደስ ብሎኛል።

ሊግ፦ ለቅ/ጊዮርጊስ በሲቲ ካፑ በመጫወት የተለያዩ ሽልማቶችን ወስደሃል፤  በክብር የት አስቀመጥካቸው? የሽልማቶቹን ማስታወሻነትስ ለማን ሰጠ?

ሃብቶም፦ እነዚህ ሽልማቶች ለእኔ የመጀመሪያዎቼ ናቸው፤ ወደፊት ሌሎች ሽልማቶች ከፈጣሪ እርዳታና ድጋፍ ጋር ይኖረኛል ብዬም አስባለሁ። ሽልማቶችንም ጥሩ የማስቀመጫ ቦታ ፈላልጌና ቆንጆ ቦታም አሰርቼ በክብር አስቀምጣችኋለሁ። ያገኘሁትን ሽልማቶች በተመለከተ ማስታወሻነቱን የምሰጠው ለወላጅ እናቴ ነው። ምክንያቱም እሷ በአሁን ሰዓት በሀገራችን ውስጥ በተፈጠረው ሁኔታ ኗሪነቷ በመቀለ በመሆኑና ብዙ ነገሮችም በመዘጋታቸው የተነሳ  ካገኘዋትም ስለቆየው ይህን ክብር በቅርብ ሆና ብትመለከትልኝ ኖሮ ጥሩ ነበርና ፈጠሪ ብሎ ነገሮች ሲስተካከል ይህን ለእሷ ያበረከትኩትን የማስታወሻ ሽልማት ለእሷ እሰጣታለሁ። ይህንን ሽልማትም ከእሷ እንደዚሁም ደግሞ በመቀለ ከሚገኘው ወንድሜና እህቶቼ ጋርም በደስታ ማክበርም እፈልጋለሁ።

ሊግ፦ በመጨረሻ ማመስገን የምትፈልገው አካል ካለ ዕድሉን እንስጥህ?

ሃብቶም፦ በእግር ኳሱ ላይ ዛሬ ለምገኝበት ስፍራ ከእኔ ጎን ሆነው የመከሩኝን፣ የረዱኝንና ያበረታቱኝ ሰዎች በጣም ብዙ ናቸውና  ይሄ የመጀመሪያ ጊዜ ኢንተርቪዬ ስለሆነ የተወሰኑትን ስም ብቻ  በመጥቀስ ላመስግን። ሌሎቹን ደግሞ በሌላ ጊዜ እጠቅሳለሁ። በመጀመሪያ የድንግል ማሪያም ልጅን ፈጣሪን አመሰግናለሁ። ከእዛ በመቀጠል ቤተሰቦቼን በተለይም ደግሞ ወንድሜ በእኔ ላይ ከፍተኛ እምነት ስለነበረው እሱን ሲቀጥል ደግሞ አሰልጣኜን ሳምሶን ሙሉጌታን ከምልህ በላይ ክለቡን እንድወድ እና በራሴም እንድተማመንም ስላደረገኝ  እሱን፣ የቡድን አጋር ጓደኞቼ፣ የኮቺንግ ስታፉና ደጋፊዎቻችን ይመስገኑልኝ።

 

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P