Google search engine

“ለመከላከያ የውጤት ማጣት አሰልጣኝ ብቻ ሳይሆን ተጨዋቾችም መቶ ፐርሰንት ተጠያቂዎች ነን” “ባለቤቴ ለእኔ ሁሉም ነገሬ ናት” አዲስ ተስፋዬ /መከላከያ/


የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ጠንካራው የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች አዲስ ተስፋዬ በዘንድሮው የፕሪምየር ሊግ
የውድድር ዘመን ተሳትፎአቸው ላይ ስላጋጠማቸው የውጤት ማጣት እና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከሊግ ስፖርት
ጋዜጣ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽን ሰጥቷል፤ እንደሚከተለውም ይቀርባል፡፡

ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመከላከያ የውጤት ማጣት ምስጢሩ ምንድነው?

አዲስ፡- የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ተሳትፎው ላይ ውጤት ሊያጣ የቻለባቸው ዋንኛው
ምክንያቶች የኮቺንግ ስታፉ ላይ በተለይ ደግሞ የዋናው አሰልጣኝ ስዩም የአመራርነት ብቃት ላይ ከተጨዋቾች የአሰላለፍ
ሁኔታዎች አንስቶ ሌሎች የተፈጠሩ ችግሮችና ምክንያቶች ናቸው፡፡
ሊግ፡- የአሰልጣኙ የአሰላለፍ ችግሮች እና ሌሎቹ ምክንያቶቹ ምን ነበሩ?
አዲስ፡- ከአሰላለፍ ስንነሳ ለቡድኑ ውጤታማነት የትኛው ጨዋታ ላይ የትኛውን ተጨዋች መጠቀም እንዳለብን
ያለማወቅ ችግር ነበር፤ ከዛ ውጪ ደግሞ የቡድኑን ተጨዋቾች ከልክ በላይ መቅረብ እና ፊት መስጠት እንደዚሁም
ደግሞ ውሳኔዎች ላይ አሰልጣኙ መዘግየትን ያሳይ ስለነበር እነዚህ ቡድኑን ሊጎዳው ችሏል፤ በቡድኑ ዙሪያም ይሄ
እንዲስተካከል ብዙ ጊዜ ልንነጋገር ብንችልም ያወራናቸው ነገሮች ሁሉ መፍትሔ ሊያመጡልን አልቻሉም፡፡
ሊግ፡- መከላከያ ላጣው ውጤት በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ላይ አድማ ማድረጋችሁ እና ከአቅም በታች መጫወታችሁም
እየተነገረ ይገኛል?
አዲስ፡- የመከላከያ ቡድን ላጣው ውጤት እኛ የቡድኑ ተጨዋቾች በፍፁም አድማ አላደረግንም፤ ያም ቢሆን ግን
ቡድኑ ውጤት እያጣ መሄድ ከጀመረ በኋላ ያሉት ሁኔታዎች ደስ የሚሉ ስላልነበሩ ሙሉ አቅማችንን አውጥተን
በመጫወቱ በኩል ያለው ሁኔታ ከአቅም በታች የመጫወት ያህል ነበር፡፡
ሊግ፡- ለመከላከያ የውጤት ማጣት ተጠያቂው አሰልጣኙ ወይንስ እናንተ ተጨዋቾች?
አዲስ፡- የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ዘንድሮ ላጣው ውጤት አሰልጣኙን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ አይደለም፤ እኛም
ጋር ከባድ ችግር ነበር፤ የቡድናችን ተጨዋቾችም 100 ፐርሰንት ተጠያቂዎች ነን፡፡
ሊግ፡- መከላከያ ከሊጉ ላለመውረድ መጫወቱ ምን ስሜት ፈጠረብህ?
አዲስ፡- መከላከያ የሀገሪቱ ትልቅ ቡድን ሆኖ አሁን ላይ ከሊጉ ላለመውረድ መጫወቱ እንደ ክለቡ ተጨዋችነቴ
የገጠመን የውጤት ማጣት በጣም ነው የሚያመው፤ ላለመውረድ መጫወታችንም የራስ መተማመንንም
አሳጥቶናል፤ ከዛ ውጪም ብዙ ጫና እንዲኖርብንም አድርጎናል፡፡
ሊግ፡- መከላከያ አሁን የሚገኝበትን ደረጃን ስትመለከት ምን አልክ? ውጤቱስ የሚመጥናችሁ ነው?
አዲስ፡- የፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ ክለባችን አሁን ላይ እያስመዘገበ ያለው ውጤትም ሆነ የሚገኝበት
ደረጃ ፈፅሞ አይመጥነውም፤ በእዚህ ደረጃ ላይ መገኘታችንም ከባድ ነውና የገጠሙን ሁኔታዎቹ ሁሉ በጣም
የሚያሳዝኑ ናቸው፡፡
ሊግ፡- መከላከያ ይሄ ውጤት ካልመጠነው ታድያ በምን ደረጃ ላይ ነው መገኘት የነበረበት?
አዲስ፡- የፕሪምየር ሊጉ የውድድር ተሳትፎ ላይ በዚህ ሰዓት እኛ መገኘት የነበረብን ከ1-2 ባለው ደረጃ ውስጥ ነበር፤
ይሄን ግን ማሳካት ሳንችል ቀረን፡፡
ሊግ፡- መከላከያ በዘንድሮው የሊጉ ተሳትፎ በሁሉም ዘንድ ስብስብ ብቻ ተብሏል?
አዲስ፡- ይሄን እንኳን አልቀበለውም፤ ቡድናችን የተጨዋቾች ስብስብ ብቻ አልነበረም ያለው፤ የተጨዋቾቻችን ስብስብ
ጥራትም አለው፤ ግን ምን ያደርጋል፤ የአሰላለፍ ችግራችን ቡድኑን የማይመጥነው ደረጃ ላይ አስቀምጦታል፡፡
ሊግ፡-መከላከያ ከሊጉ ይወርዳል? ወይንስ ሊጉ ላይ ይቆያል?
አዲስ፡- መውረዱን እንኳን ተወው፤ በቀሪዎቹ 5 ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ውጤት በማምጣት ቡድኑን ሊጉ ላይ
በእርግጠኝነት የምናቆየው ይሆናል፡፡
ሊግ፡-የኢትዮጰያ ፕሪምየር ሊግ ጠንካራው ተከላካይ ዘንድሮ ብዙም እየታየ አልነበረም፤ ምክንያቱ ምን ነበር?
አዲስ፡- የመከላከያ ክለብ ውስጥ በነበረኝ የእዚህ ዓመት ቆይታዬ እንደበፊቱ ብዙም በሜዳ ላይ ልታይ ያልቻልኩት
በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ አማካኝነት በተደጋጋሚ ጊዜ የመጫወትዕድል ሊሰጠኝ ስላልቻለ ነው፤ በእዚሁ ምክንያትም
ነው ከሜዳ ርቄ የነበረው እና ለቡድኔም የአቅሜን ያህል ግልጋሎት ሳልሰጠው የቀረሁት፡፡
ሊግ፡- የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ ያለህን የዘንድሮ አቋም በምን መልኩ ትገልፀዋለህ?
አዲስ፡- የፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ቆይታዬ ላይ ያሳየሁት የሜዳ ላይ ብቃት በተደጋጋሚ ጊዜ የመሰለፍ
እድልን የማላገኝ ስለነበር ወጣ ገባ ያለን አቋም ነው፤ አሁን ላይ ግን በጥሩ አቋም ላይ እገኛለው፡፡
ሊግ፡- የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ የውል ዘመንህ ዘንድሮ ይጠናቀቃል፤ የአዲስ ማረፊያ የት ይሆን?
አዲስ፡- የአሁን ሰዓት ላይ እኔ በዋናነት ትኩረት አድርጌ እየሰራው ያለሁት በቀጣዩ የሊጉ ጨዋታዎች ለክለቤ ውጤት
ማማር የሚቻለኝን ነገር በመስራት ቡድኑን ውጤታማ ለማድረግ ቢሆንም የውድድር ዘመኑን ሳጠናቅቅ ደግሞ አሁን ላይ
ብዙ ክለቦች እኔን ለመውሰድ ጥያቄዎችን እያቀረቡልኝ ስለሆነ ስለ እኔ ቀጣይ ማረፊያዬ ክለብ የውድድር ዘመኑ
መጨረሻ ላይ ምላሼን የምሰጣቸው ነው የሚሆነው፤ ወደ አንድ ትልቅ ደጋፊ ወዳለው ቡድን የማመራም ነው
የሚመስለኝ፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ስላለህ እለኸኝነት አንድ ነገር በለን? በቀጣይ ጊዜስ እንዴት እንጠብቅህ?
አዲስ፡- አዎን፤ ሜዳ ስገባ በተፈጥሮዬ ሽንፈት የሚባል ነገርን አልወድምና ሁሌም እልኸኛ ተጨዋች ነኝ፤ ለዛም
ይሆናል የእግር ኳሱ ላይ በመልካም ጤንነት ላይ ሆኜ ኳሱን እየተጫወትኩኝ የምገኘው፤ የቀጣይ ጊዜ የቡድናችን
ጨዋታዎችም ላይ ለቡድኔ መስጠት የምፈልገው ግልጋሎት ቡድናችን ካለበት የውጤት ችግር እንዲወጣ ጥሩ
ከመከላከል ባሻገር ጎሎችንም በማስቆጠር የበኩሌን ድርሻ ልወጣ አስቤያለውና ለዛ ጠንክሬ የምሰራ ነው የሚሆነው፡፡
ሊግ፡- የህይወት ዘመንህ አስደሳች እና አስከፊው ጊዜ የቱ ነው?
አዲስ፡- አስደሳቹ ጊዜ በጣም የምወዳትን የልጅነት ሚስቴን ሀዊ ያገባሁበት ቀን ሲሆን አስከፊው ደግሞ የእግር ኳስን
የ2009 ዓ/ም ላይ ይርጋለም ከተማ ላይ ስጫወት የተጎዳሁበትን እና ለ7 ወር ያህል ከሜዳ ያራቀኝን ቀን ነው፡፡
ሊግ፡- ባለትዳር እንደሆንክ እናውቃለን፤ ጋብቻህን መች ፈፀምክ? የትዳር ህይወቱስ እንዴት ይዞሃል?

አዲስ፡- ፈጣሪ ይመስገን የትዳር ህይወቴ በጣም ጥሩ ነው፤ ጋብቻዬን የመሰርትኩትም ከአንድ ወር በፊት የስምንት
ዓመታት የፍቅር ጓደኛዬ ከሆነችው ሀዊ ጋር ነው፤ ከእሷ ጋር በመሰርትነው ትዳርም ጥሩ እየተጓዝን ይገኛል፤ ልጅ
ለመውለድም በመንገድ ላይ ነው የምንገኘው፡፡
ሊግ፡- ባለቤትህን እንዴት ነው የምትገልፃት?
አዲስ፡- ባለቤቴ ሀዊ ለእኔ ብዙ ነገሬ ነች፤ በጣም ጥሩ የሆነች ልጅ ናት፤ በኳሱ አሁን ላይ ለደረስኩበት ደረጃ ትልቁን
አስተዋፅኦ አበርክታልኛለች፤ ስለዚህ እሷን ለመግለፅም ቃላቶች የሉኝም፤ በጣም እንደማከብራት እና እንደምወዳትም
በዚሁ አጋጣሚ መግለፅን እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…
አዲስ፡- መጪው ጊዜ ለፉትቦላችን እድገት ሲባል ከረብሻ የጠራ እና በነፃነትም እግር ኳስን የምንጫወትበት ጊዜ
እንዲሆንልን በመመኘት ለእዚህ ደግሞ ሁሉም የበኩሉን ቢወጣ በጣም ነው ደስ የሚለኝ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P