test
Google search engine

“ለሻምፒዮናነት ማንም ባይገምተንም እዛ ደረጃ ለመጓዝ ግን ተዘጋጅተናል”
አብዱልከሪም ወርቁ /ወልቂጤ ከተማ/


የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብን በከፍተኛው ሊግ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ቡድኑን በጥሩ ብቃቱ አገልግሏል፤ በሜዳ ላይ በሚያሳየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴውም በብዙዎች ዘንድ ከመደነቅ ባለፈ በአንድ አጋጣሚ ለሀገሩ የወጣት ብሔራዊ ቡድን እስከመመረጥ እና እስከመጫወት ደረጃ ላይም ደርሷል፡፡


በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ አምስተኛ ፖሊስ አካባቢ የተወለደው አብዱልከሪም ወርቁ የእግር ኳስን ከልጅነቱ ዕድሜ አንስቶ በማፍቀር በብሪሞ ሜዳ ላይ መጫወት የጀመረ ሲሆን ለኢትዮጵያ መድንና ተተኪ ቡድንም ተጫውቶ ነው ጥሩ ብቃቱን ካሳየ በኋላ ወልቂጤ ከተማን በመቀላቀል በኳስ ችሎታው ጥሩ ለውጦችን በማሳየት በስፖርት አፍቃሪው እይታ ውስጥ በፍጥነት እውቅናን እያገኘ የመጣው ከእዚህ ተጨዋች ጋር በክለቡ ጉዳዮች ዙሪያና በሌሎች የተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ያደረግነው ቆይታም ይሄንን ይመስላል፤ ተከታተሉት፡፡


በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ወልቂጤ ከተማ ባህር ዳር ከተማን ስለማሸነፉ እና ያለመሸነፍ ሪከርድ ጉዞውንም ስለማስቀጠሉ
“ከባህር ዳር ከተማ ጋር የነበረንን ጨዋታ ለማሸነፍ እና የያዝነውን ያለመሸነፍ ሪከርዳችንንም ወደፊት አስቀጥሎ ለማስጓዝም በወኔ ነበር ወደሜዳ የገባነውና ያን የምንፈልገውን የድል ውጤት በመጨረሻ ላይ ልናገኝ ችለናል፤ የጨዋታው አሸናፊ ስለሆንም በጣም ተደስተናል”፡፡
ባህር ዳር ከተማን ለማሸነፍ ስለቻሉበት መንገድ
“መጀመሪያ ከላይ እንደገለፅኩልህም ጨዋታው ላይ ከፍተኛ ወኔ ነበረን፤ ሌላው ግጥሚያውን እንደምናሸንፍም የእርግጠኝነት ስሜትም ነበረንና እንደ ህብረት በመጫወታችንም ጭምር ነው አሸናፊ ለመሆንም የበቃነው”፡፡
ስለ ተጋጣሚያቸው ባህር ዳር ከተማ
“ባህር ዳር ጠንካራና ከባድ ቡድን ነው፤ እንደዛ ቢሆኑም ግን ከእኛ ጋር ሲጫወቱ እኛ ከእነሱ ተሽለን ስለነበር አሸንፈናቸዋል”፡፡
ወልቂጤ ከተማ በሁለት ጨዋታዎች ላይ ነጥብ ጥሎ ነበር፤ ያ የቁጭት ስሜት ፈጥሮባችኋል?
“በጣም እንጂ፤ ለእዛ ቁጭት ምንም አይነት ጥያቄም አያስፈልገውም፤ ግቦችን ስተናል፤ በእዚህ ክፍተቶቻችን ላይ በአሁን ሰዓት ስራዎችን እየሰራንም ይገኛልና ወደፊት ጥሩ ቡድን ነው የምንሰራው”፡፡
የወልቂጤ ከተማ የእዚህ ዓመት ግቡና እልሙ፤ ቡድኑ የት ድረስስ ይጓዛል?
“ሰዎች እኛን ለሻምፒዮናነት ፉክክሩ ባይገምቱንም ሙሉ ለሙሉ ግን ሊጉን የምንጫወተው ዋንጫውን ለማንሳት ነው፤ እዛም ድረስ ለመጓዝ ተዘጋጅተናል”፡፡
ቡድናቸው ስለያዘው የተጨዋቾች ስብስብ
“ስብስባችን በወጣት የተገነባ እና ልምድ ባላቸው ተጨዋቾች የተዋቀረ ነው፤ ጥሩ የመጫወት አቅም ያለው ስብስብና አንድ ጥሩ ነገርን ለመስራት የሚችል ቡድንም ነው ያለን”፡፡
በወልቂጤ ከተማ ክለብ ውስጥ ስላለው የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው
“በቡድኑ ስቆይ አሁን ላይ ሶስተኛ ዓመቴን ይዣለው፤ በቆይታዬም በጣም ደስተኛ ነኝ”፡፡
እንደ ክለቡ ተጨዋችነትህ ወልቂጤ ከተማን አጠር ባለ መልኩ ስትገልፀው
“ይሄ ቡድን በእኔ አንደበት ሲገለፅ የእዛ አካባቢ ተወላጅ ባልሆንም መጀመሪያ “እንደ ቤቴ ነው የምቆጥረው፤ ብዙ ነገርን ያደረገልኝ ቡድንም ነውና የእዚህ ቡድን አንዱ አካል ተጨዋች በመሆን እያገለገልኩት በመሆኔ በጣም ነው ደስ ያለኝ”፡፡
ወልቂጤ ከተማን የቱ ነገር ለየት ያደርገዋል?
“እርስ በእርሳችን ከፍተኛ ፍቅር አለን፤ አብዛኞቹ ተጨዋቾችም ወጣቶች ናቸው፤ ይሄ ለየት ያደርገናል፤ ጉዞዋችንም የተሻለ እና ለትልቅ ደረጃም ላይ ያደርሰናል ብለን እየጠበቅን ነው”፡፡
ወልቂጤ ከተማ በቤትኪንግ የሊጉ ተሳትፎው ሁለት ጨዋታን አሸንፎ እና በሁለት ጨዋታም አቻ ተለያይቶ ጉዞውን ቀጥሏል፤ ከውጤት አንፃር ይሄን ስትገልፀው….?
“የእስካሁኑ ውጤት ጥሩ ነው፤ ስለለፋንበት ይገባናል ብዬም ነው የማስበው፤ ከእዚህ በኋላ ደግሞ በምናደርጋቸው ጨዋታዎች አሁን ላይ የያዝነውን ያለመሸነፍ ሪከርድም በማስቀጠል ለሻምፒዮናነቱ ፉክክር እንጫወታለን”፡፡
የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በዲ.ኤስ. ቲቪ ስለመተላለፉ እና ውድድሩ ያለተመልካች ስለመካሄዱ
“የእዚህ ጥቅም ለሁላችንም ተጨዋቾች ነው፤ ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች በኳስ ቴክኒኩ ላይ ጥሩ ችሎታው ስላለንና እነዚህ ጨዋታዎች ደግሞ በመላው ዓለም ላይ ስለሚተላለፉ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ወደ ውጪ ወጥቶ ለመጫወት እንድንችል ከፍተኛ ጥረት ልናደርግ እና አጋጣሚውን ለመጠቀም ጠንክረንም ልንሰራበት ይገባል”፡፡
በልጅነት ዕድሜው ወደ አዲስ አበባ ስታድየም ይገባ እንደነበርና ስለ ሚደግፈው ቡድንና ስለሚያደንቀው ተጨዋች
“በልጅነቴ ስታድየም እገባ እና ጨዋታዎችንም እከታተል ነበር፤ ማንንም ቡድን ሳልደግፍም ነበር ግጥሚያዎችን እከታተል የነበረው፤ ከተጨዋቾች ግን ለመስዑድ መሐመድ ከፍተኛ አድናቆት ነበረኝ፤ እሱንም ነው በኳሱ ተምሳሌቴ አድርጌም የተጓዝኩትና መስዑድ ለየት ያለ ተጨዋች ነው”፡፡
የእግር ኳስን መጫወት ሲጀምር ቤተሰብ አካባቢ ስለነበረው አመለካከት
“እነሱ በትምህርቴ ጠንክሬ እንድጓዝ ከመፈለግ ውጪ ኳስን አትጫወት በሚል የፈጠሩብኝ ነገር ምንም የለም፤ ሁለቱንም ነው በጥሩ ሁኔታ ሳስኬድም የነበረው፤ ከእዛ በኋላ ግን በኳሱ ለጥሩ ደረጃ መድረሴን ሲያውቁ ያበረታቱኝ ነበር፤ አሁንም ከጎኔ በሁሉም ነገርም አብረውኝ አሉ”፡፡
በመጨረሻ
“እንደ ታዳጊነት እልሜ ዛሬ ላይ በእግር ኳስ ተጨዋችነት እዚህ ደረጃ ላይ እደርሳለው በሚል መነሻነት ጠንክሬ በመስራት በቅድሚያ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ መጫወት መቻሌ በጣም ነው ደስተኛ ያደረገኝ፤ ይሄን እድል እንዳገኝም ያስቻለኝ ከፍተኛ ሊግ ላይ በነበርንበት ሰዓት እኔን በታዳጊነት እድሜዬ መልምሎኝ ወደ ቡድኑ ያስመጣኝ አሰልጣኝ ደረጄ በላይ ነውና ለእሱ ታላቅ ምስጋና አለኝ ሌላው ሳላመሰግናቸው የማላልፈው በታዳጊነት እድሜዬ እኔን አሰልጥኖኝ የቀረፀኝን አሰልጣኝ አለማየው መኩሪያን /አለምዬ/ እንደዚሁም ደግሞ ቤተሰቦቼን፣ ጓደኞቼን፣ የቡድን አጋሮቼን፤ ክለቤን ወልቂጤ ከተማንና ሁሌም ለቡድናችን ከፍተኛ ተቆርቋሪ ሆኖ በምንም ነገር የሚደግፈንን የክለባችንን ደጋፊና አመራር አቶ አበባውን ከልብ ለማመስገን እወዳለውኝ”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

P