ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎው በአሁን ሰዓት ለፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን በመጫወት ጥሩ ብቃቱን በሜዳ ላይ እያሳየ ይገኛል፤ ተጨዋቹ ለአዳማ ከነማ ባለፈው ዓመት ሲጫወትም በሜዳ ላይ ለክለቡ ጥሩ እንቅስቃሴን በማስመልከቱም በስፖርት አፍቃሪው ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን እንዲያገኝም አድርጎታል፡፡
የፋሲል ከነማው የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ሱራፌል ዳኛቸው ይህንን ብቃቱን ተንተርሶም በቀጣይነት ቡድኑ በሚኖረው ጨዋታዎች ላይ ከዚህ በላይም ጥሩ ግልጋሎትን ለክለቡ ሰጥቶ ምርጥ የሚባል የውድድር ዓመትን እንደሚያሳልፍም ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብን በክረምቱ የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ከአዳማ ከነማ በመምጣት የተቀላቀለው ሱራፌል ዳኛቸው ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ ጋር በነበረው ቆይታ ክለባቸው በሊጉ የውድድር ተሳትፎ ስለሚያስመዘግበው ውጤትም አስተያየቱን ሰጥቶ አልፏል፤ “ፋሲል ከነማ ሊጉን እየተወዳደረ የሚገኘው ዋንጫውን ለማንሳት ነው” ይህን ድል የማሳካት አቅሙም አለን ካለ በኋላ በነገው ዕለትም ከሊጉ መሪ ቅ/ጊዮርጊስ ጋር ያላቸውን ጨዋታ አሸንፈው ከሜዳ እንደሚወጡም አስተያየቱን አክሎ ገልጿል፡፡
የፋሲል ከነማው የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ሱራፌል ዳኛቸውን በክለባቸው ዙሪያና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችን አንስተንለት የሰጠን ምላሽ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማን ወቅታዊ አቋም እንዴት ትገልፀዋለህ?
ሱራፌል፡- የፕሪምየር ሊጉ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ አሁን ያለን አቋም በሜዳችን ስንጫወት በጣም ጥሩ ነን፤ የሜዳችን ውጪም ጨዋታ የሚያበረታታ እንጂ ብዙም የሚያስከፋ ስላልሆነ በእዚሁ መልኩ ነው ውድድራችንን እያከናወንን የምንገኘው፡፡
የሊግ ግጥሚያዎቻችንን በሜዳችን ላይ ስናደርግ ብዙ ክለቦች ለመከላከል መጥተው ቢጫወቱም በእንቅስቃሴ ተበልጠው እና ብዙም የጎል ሙከራም ተደርጎባቸው ነው የሚመለሱት፤ ያ ጥሩነታችንን ያሳያል፤ ከዛ ውጪም የክለባችን በርካታ ተጨዋቾች እኔን ጨምሮ ጉዳት ላይ የነበረን ቢሆንም የአሁን ሰዓት ላይ ወደመልካም ጤንነት በመመለሳችን ያለንን ወቅታዊ አቋም የበለጠ ጥሩ የሚያደርግልን ይሆናል፡፡
ሊግ፡- የሊግ ተሳትፎአችሁ ላይ እንደክፍተት የተመለከትከው ነገር ምንድነው?
ሱራፌል፡- በፕሪምየር ሊጉ እያደረግን ባለው የውድድር ተሳትፎ ክለባችን ላይ እንደ ክፍተት የምጠቅሰው ነገር ቢኖር ወደ ተቃራኒ ቡድን የሜዳ ክልል መግባቱ እና አጥቅቶም በመጫወቱ በኩል ጥሩ ሆነን ሳለ ጎሎችን ማስቆጠሩ ላይ ድክመት አለብን፤ እንደምናገኛቸው የግብ እድሎች የአጨራረስ ችግር አለብንና ይሄን ክፍተት ለሻምፒዮናነት ከመጫወታችን አንፃር ከወዲሁ ልናርመው የሚገባን ነው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ክለባችሁ ለማንሳት የሚኖረው እድል የቱን ያህል ነው?
ሱራፌል፡- የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ የዘንድሮውን የሊግ ውድድር እያከናወነ የሚገኘው ዋንጫውን ለማንሳት ነው፤ ይሄን ድል ለማሳካት እንደምንችልም እኛ ተጨዋቾች ብቻ ሳንሆን የክለቡ አመራሮች እንደዚሁም ደግሞ ደጋፊዎቻችን ከፍተኛ እምነቱ ስላላቸው ለዚያ በሚገባ ተዘጋጅተናል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፉክክርን ከበርካታ ክለቦች የነጥብ መቀራረብ አኳያ እንዴት ተመለከትከው?
ሱራፌል፡- የዘንድሮ ፕሪምየር ሊግ ፉክክር ብዙ ክለቦች በነጥብ የተቀራረቡበት ስለሆነ በጣም ጥሩ ነው፤ የሊግ ዋንጫውንም ለማንሳት በርካታ ክለቦች እድሉም አላቸው፡፡ አሁን ላይ ግን ይሄ ቡድን ዋንጫውን ያነሳል የምትልበት ጊዜ ላይ አይደለንምና ስለ ሊጉ ጥሩ ፉክክር እየተደረገበት ስለመሆኑ ብቻ ነው መናገር የምፈልገው፤ ውድድሩ በዚሁ መልኩ እስከመጨረሻው ቢቀጥል ለሊግ ውድድሩ ድምቀት እና ለስፖርት ቤተሰቡም ጨዋታዎችን በብዛትና በስፋት ወደሜዳ መጥቶ ለመመልከት ያስችለዋልና ውድድሩን ይሄ እንዲያጋጥመው ነው የምፈልገው፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ የሊጉን መሪነት የጨበጠውን ቅዱስ ጊዮርጊስን ይፋለማል፤ ለእዚህ ጨዋታ ያደረጋችሁት ዝግጅት ምን ይመስላል… ምን ውጤትስ ከግጥሚያው ትጠብቃለህ?
ሱራፌል፡- ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ለሚኖረን የነገው ጨዋታ የተለየ የሚባል ዝግጅትን አልሰራንም፤ ያም ሆኖ ግን ተጋጣሚያችን ትልቅ እና ጠንካራም የሊጉ ክለብ ስለሆነ ከእነሱ ጋር የሚኖረንን ጨዋታ አሸንፈን ለመውጣት የሚቻለንን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን፤ ደግሞም እናሸንፋለን፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማን መለያ አጥልቀህ የቀድሞ ክለብህን አዳማ ከነማን በተቃራኒነት ተፋልመሃል፤ ጨዋታው ላይ መሳተፍ መቻልህ ምን ስሜት ፈጠረብህ… ግጥሚያውንስ እንዴት አገኘኸው?
ሱራፌል፡- የቀድሞ ክለቤን አዳማ ከነማን በተቃራኒነት የተፋለምኩበት ጨዋታ ለእኔ ኳስ ይዘን የተጫወትንበት እና በርካታ ጎል ሊሆኑ የሚችሉም አጋጣሚዎችን የፈጠርንባቸው ስለነበር በጨዋታው በጣም ተደስቻለው ክለባችን ግጥሚያውን አያሸንፍ እንጂ ጥሩ አቋም ላይ ሆኖ ነው ያገኘሁት፤ ጨዋታውንም ማሸነፍ ይገባን ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን የኳስ ነገር ሆነና እድለኛ ስላልነበርን ብቻ አሸናፊ ሳንሆን ቀረን፤ ከአዳማ ጋር በነበረን በዚህ ግጥሚያ የቀድሞ ቡድኔን ስፋለም ጥሩ ስሜት የተሰማኝ ቢሆንም የበለጠ ደግሞ ጨዋታው ላይ ጎል አስቆጥሬ ብወጣ ኖሮ ደስታዬን የመግለፁ ነገር ብዙ ባይኖርም ማንነቴን ማሳየት የምፈልግበት ግጥሚያ ይሆንልኝ ነበርና ደስታዬ የበለጠ ከፍ ይልም ነበር አሁንም ቢሆን ግን ጨዋታው ላይ ባየሁት ነገር ጥሩ ነገርን ለመመልከት ችያለውና ደስተኛ ነኝ፡፡
ሊግ፡- በፋሲል ከነማ ውስጥ በሚኖርህ ቆይታ የቀጣይ ጊዜ ጨዋታዎችስ ላይ ከአንተ ምን ይጠበቅ?
ሱራፌል፡- የዘንድሮው የውድድር ዘመን ላይ ከአዲሱ ክለቤ ጋር ያለኝ ጅማሬዬ በጣም ጥሩ ሆኖ ያገኘሁት ነው፡፡ የአዳማ ከነማ ክለብ ውስጥ ከነበርኩበት ጊዜም በተሻለ ጥሩ ብቃቴን በሜዳ ላይ እያሳየሁ ጅማሬዬን በማሳመር ላይም ነኝ፤ ለቡድኔ በምሰጠው አበረታች እና ተስፋ ሰጪ የሆነ እንቅስቃሴም ከወዲሁ በክለቡ አሰልጣኞች፣ ደጋፊዎች እና የቡድናችን አመራሮችም ዘንድ ጥሩ ተቀባይነትን እያገኘው ስለሆነ ይሄን ብቃቴን በቀጣይ ጊዜ የሊጉ ጨዋታዎች ላይም አጠናክሬ በማስቀጠል ክለቤን በሚገባ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች በአንተ እይታ እንዴት የሚገለፁ ናቸው?
ሱራፌል፡- ስለ ፋሲል ከነማ ደጋፊዎች የብዙ ክለብ ደጋፊዎችን ተመልክቻለሁ የሚሰጡት ድጋፍና ማበረታታት የተለየ ሆነው ነው ያገኘኋቸው፤ ቡድናቸውን ከልብ ይወዱታል፤ የማያቋርጥ ድጋፍንም ይስጡናል እና በእዚህ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የተለየ እንቅስቃሴን አሳይቷል ብለህ የምትጠቅሰው የክለባችሁ ተጨዋች አለ?
ሱራፌል፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ተሳትፎ ላይ እስካሁን ባደረግናቸው ጨዋታዎች ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያሳዩ የተመለከትኳቸው የክለባችን ተጨዋቾች በዋናነት መጂብ ቃሲም ነው፤ ከእሱ ውጪ ያሬድ ባየህ እና ሀብታሙ ጥሩ ሊጠቅስላቸው የሚችል አበረታች ብቃትን ለማሳየት ችለዋል