Google search engine

“ለቅዱስ ጊዮርጊስ በቋሚነት ተሰልፌ ለመጫወት ስጋት አያድርብኝም”አቤል እንዳለ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

በመሸሻ ወልዴ G.BOYS


ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደደቢት ያስፈረመው የአማካይ ስፍራው ተጨዋች አቤል እንዳለ በአዲሱ የውድድር ዘመን ለቡድኑ ጥሩ ብቃቱን በማሳየት አመቱን እንደሚጀምርና በክለባቸው የተሳካም የውድድር አመትን እንደሚያሳልፍ ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በዝውውር መስከቱ ያስመጣው ይኸው ወጣት ተጨዋች ወደ ቡድኑ በመግባቱም በጣም መደሰቱንና በቋሚ ተሰላፊነትም ለመጫወት የሚኖረውን ፉክክር በብቃት ለመወጣት መዘጋጀቱንም ይናገራል፡፡ ይህን ተጨዋች በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ አናግረነው ምላሹን ሰጥቶናል፡፡

ሊግ፡-እንኳን ለዘመን መለወጫ በአል በሰላም አደረሰህ?
አቤል፡- እናንተንም ፈጣሪ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፡፡
ሊግ፡- 2011 ዓ/ምን ረቡዕ እለት ልንሰናበት ችለናል፤ በአንተ በኩል አመቱ እንዴት አለፈ?
አቤል፡- እንደ ደደቢት እግር ኳስ ቡድን ተጨዋችነቴ የ2011 ዓ.ምን ያሳለፍኩት በጥሩ መልኩ ነው፡፡ በውድድር ደረጃ በሜዳ ላይ ክለባችን ምንም እንኳን ከሊጉ ቢወርድም በእንቅስቃሴ ደረጃ ጥሩ ስንጫወት የነበረበት አመት ነው፤ በተለይ ደግሞ ከፍተኛ የፋይናንስ ችግርና እጥረት ኖሮብን ለክለባችን ማሊያ አመቱን ሙሉ ለፍተን ስንጫወት የነበረበት ጊዜ ስለነበር በእኔም በኩል በአቋም ደረጃ ጥሩ ሆኜ በተለያዩ ትላልቅ ቡድኖች ደረጃ ተፈላጊ ተጨዋች የሆንኩበትና በስተመጨረሻም በአገራችን ትልቁ ክለብ ወደሆነውና የብዙም ዋንጫዎች ባለቤት ወደሆነው የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ እንድገባ የጥርጊያውን በር የከፈተልኝ አመት በመሆኑ በእዚህ አመቱን በጥሩ ሁኔታ ላሳልፈው ችያለሁ፡፡
ሊግ፡- አዲሱን አመት 2012 በምን መልኩ ልትቀበለው ዝግጁ ነህ?
አቤል፡- በብዙ ነገር፤ ምክንያትም በክረምቱ ወራት የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት አሁን ላይ የተቀላቀልኩት አዲሱ ቡድኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለው ስምና ዝና አንፃር ብዙ ደጋፊ ያለው ቡድን ስለሆነና ለእዚህም ታሪካዊ ቡድን ኳስን ስትጫወት ከፍተኛ ሃላፊነት ያለብህና በጫና ውስጥም ሆነህ የምትጫወትበት በመሆኑ ራስህን በከፍተኛ ብቃት ማዘጋጀት ስላለብህ በእዚህ መልኩ ነው ለክለቤ ውጤት ማማር ስል ከራሴ የሚጠበቅብኝን ጥሩ የሆነ የሜዳ ላይ ግልጋሎትን ልሰጥ ለአዲሱ አመት የተዘጋጀሁት፡፡
ሊግ፡- በእዚህ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስን እቀላቀላለሁ ብለህ ጠብቀህ ነበር?
አቤል፡- በፍፁም፤ ወደ ቡድኑ ልመጣ እንደምችል ጭምጭምታዎች የነበሩ ቢሆንም በእዚህ ጊዜ ውስጥ ግን ይሆናል ብዬ ግን አልጠበቅኩም ነበርና ሁሉም ነገር ድንገት ነው የሆነብኝ፡፡
ሊግ፡- ለቅ/ጊዮርጊስ ስትፈርምና ወደ ቡድኑ ስትገባ ምን አይነት ስሜት ነው ያደረብህ፤ ምንስ አይነት አቀባበል ተደረገልህ?
አቤል፡- የቅ/ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ እኔን ፈልጎኝና ምርጫውም አድርጎኝ የቡድኑ ተጨዋች ሲያደርገኝ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ የክለቡ ተጨዋች በመሆኔም ራሴን እንደ እድለኛ አድርጌም ነው የምቆጥረው፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስን ተቀላቅለሃል፤ ይሳካልሃል?
አቤል፡- አዎን፤ በእዛ ማንም ጥርጥር አይግባው፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ቡድን ነው፤ በዛ ላይ ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችንም ይዟል፤ ለእዚህ ቡድን ስትጫወትም ያለውን ጫና ስለማውቀው ራሴንም በደንብ ስለማዘጋጀው ጥሩ ለመጫወት አንዳችም ችግር አይኖርብኝምና ስኬታማ ጊዜን እንደማሳልፍ እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሊግ፡- ለቅዱስ ጊዮርጊስ በቋሚ ተሰላፊነት መጫወት አይከብድም?
አቤል፡- ይከብዳል እንጂ፤ ምክንያቱም ቡድኑ ትልቅ እና ጥሩ ችሎታ ያላቸውንም ተጨዋቾች በየጊዜው የሚይዝ በመሆኑ፤ ያም ሆኖ ግን አንተ ሁሌም ጠንክረህ እና በርትተህ የምትሰራ ከሆነ እና ጥሩ ብቃትህንም ማሳየት የምትችል ከሆነ መሰለፍ አይከብድም፤ እኔም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጣሁበት አንዱ ምክንያት ለቡድኑ ተሰልፎ ለመጫወት ያለውን ኮምፒቴሽን /ፉክክር/ ፈልጌው እና በእዚህም የራሴን ችሎታና አቅምም በደንብ ማወቅ ስለምፈልግም የክለቡን ጥያቄ ተቀብዬ ፊርማዬን አኑሪያለሁ፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት ሁለት አመታት የሊጉን ዋንጫ ሳያነሳ ቀርቷል፤ ከዚህ በኋላ በእናንተ ጊዜስ?
አቤል፡- በእኛ ጊዜ ይሄ ውጤት አልባ የሆነበት ዓመታት ፈፅሞ አይደገምም፤ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ ውጤት ማጣት ያልተለመደ ነበር፤ ውጤት ማጣቱም ቡድኑን የማይመጥነው እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲነገረን ስለሰማን እኛ ክለቡን በአዲስ መልክ የተቀላቀልነው ተጨዋቾችና ነባሮቹ በምደርገው የጋራ የስራ ጥረት የአዲሱ አመት ላይ ክለባችንን ለስኬት እንደምናበቃው እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሊግ፡- ደደቢት ለዛሬ እውቅናህና ማንነትህ የጥርጊያውን መንገድ የከፈተልህ ቡድን ነው፤ እንዴት ትገልፀዋለህ?
አቤል፡- የእውነት ነው፤ የኳስ ጅማሬዬ ተወልጄ ባደግኩበት ሃረር ጀጎል አካባቢ ቢሆንም ለሃረር ፖሊስ እና በኋላ ላይ ደግሞ ለአካዳሚ ቡድን ተጫውቼ ባሳልፍም በተስፋ ቡድን ደረጃ እና ዋናው ቡድን ደረጃ ላለፉት አራት አመታት በጥሩ ብቃቴ የተጫወትኩት እና የብዙዎችንም ክለቦች ትኩረት ስቤ ዛሬ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንድሄድ ያደረገኝ ደደቢት በመሆኑ ለክለቡ ታላቅ ምስጋና አለኝ፡፡ ከደደቢት በአጭር ጊዜ የሊጉ ቆይታዬም ነው ቅዱስ ጊዮርጊስን አሁን ላይ መቀላቀል የቻልኩትና የቀድሞ ቡድኔ ያለኝን አቅም አውጥቼ እንድጫወት ያደረገኝ ክለቤ ነው፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ወጣት ብሄራዊ ቡድን ተመርጠህ ተጫውተሃል፤ ስሜቱ ምን ይመስላል? ለብሄራዊ ቡድንስ ስለመመረጥ ምን ታስባለህ?
አቤል፡- ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተመርጦ መጫወት የሁሉም ተጨዋቾች ምኞትና ፍላጎት ነው፡፡ እኔም በወጣት ቡድን ደረጃ ይሄን እድል አግኝቼ ተጫውቻለሁ፤ የሃገር ማሊያ ለብሰህ እና መዝሙሩንም ዘምሮ መጫወት በጣም ነው ደስ የሚለውና ይሄን እድል በማግኘቴ ሁሌም እንድኮራ ያደርገኛል፡፡ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ስለመጫወት ደግሞ ቀጣዩ እና የአዲሱ አመት ዋናው ጉጉቴ ነው፤ ስለዚህም የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ተጨዋች ሆኜ ይሄን እድል ማግኘት እፈልጋለሁ፡፡
ሊግ፡- የኳስ ምኞትህ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ መጫወት እና ለብሄራዊ ቡድን ብቻ ነው?
አቤል፡- አይደለም፤ ለሁለት አመት ያህል ብቻ እዚህ ሃገር ከተጫወትኩ በኋላ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ወደ ውጪ ወጥቼ መጫወት፡፡ ይሄን ለማሳካትም ጭምር ነው ኳስን እየተጫወትኩ የምገኘው፡፡
ሊግ፡- ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባትዘዋወር ኖሮ በየት ቡድን እናገኝህ ነበር?
አቤል፡- በኢትዮጵያ ቡና ወይንም ደግሞ በአዳማ ከተማ ምክንያቱም ሁለቱም ቡድኖች ከቅዱስ ጊዮርጊስ በኋላ እኔን ለመውሰድ ጥያቄ ያቀረቡልኝ ቡድኖች ነበሩ፤ ያም ሆኖ ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅድሚያ ስላናገረኝ እና እኔም በክለቡ ውስጥ በቋሚ ተሰላፊነት ለመሰለፍ ያለውን ፉክክር በጣሙን ስለፈለግኩት እንደዚሁም ደግሞ የጠየቀኝ ቡድንም የሀገሪቱ ትልቅ ስለሆነም ወደ እነሱ ልጠቃለል በቅቻለሁ፡፡
ሊግ፡- በአሁን ሰአት ራስህን ምን አይነት ተጨዋች አድርገህ ትቆጥራለህ?
አቤል፡- እንደ አገራችን ኳስ ከሆነ በጥሩ ደረጃ ላይ ነው የምገኘው፤ ይህን ስልህ በቂ ነው እያልኩ አይደለም፤ ከዚህ በላይ አቅሜን ከፍተኛ ደረጃ ላይ አደርሼ የሃገሪቱ ጥሩና ምርጥ ተጨዋች መሆንም እፈልጋለሁ፤ በተለይ ደግሞ የአዲሱ ቡድኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በእኔ ላይ ሁሌም ሙሉ እምነት ሊያድርባቸው የሚችለውን ብቃቴን ለማሳየት ተዘጋጅቻለሁ፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…..?
አቤል፡- ለአዲሱ አመት መላውን የኢትዮጵያ ህዝብና የስፖርት አፍቃሪውን እንደዚሁም ደግሞ ቤተሰቦቼን፣ ከዛ ባሻገር የደደቢት ክለብ ውስጥ አብረውኝ የተጫወቱትን ጓደኞቼን በተለይ ደግሞ ለያብስራ እና ለዳዊት ወርቁ እንደዚሁም ደግሞ ለሌሎች ጓደኞቼ እንኳን አደረሳችሁ ማለትን እፈልጋለሁ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P