በመሸሻ_ወልዴ
የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብን ከደደቢት በመምጣት የእዚህ ዓመት ውድድር ከመጀመሩ በፊት በዝውውር መስኮቱ ሊቀላቀል ችሏል፤ ይሄ ተጨዋች ወደ ክለቡ ሲያመራም ዋንኛ እቅዱና ግቡ የነበረውም ባለፉት ሁለት ዓመታት ክለቡ ያጣውን የሊጉን ዋንጫ ዳግም በማግኘት የክለቡን የቀድሞ ዝና መመለስ እንደዚሁም ደግሞ የራሳቸውንም ተጨዋቾች ስም ማስጠራት ቢሆንም በኮቪድ 19 የሀገሪቱ የሊግ ውድድር በመሰረዙ ያ እልሙ ሳይሳካ ቀርቷል፤ ወጣቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች የአብስራ ተስፋዬ ግን በመጪው ዓመት ውድድሩ ሲካሄድ አስቀድመው አልመው የነበሩትን ዋንጫ እንደሚያገኙ በእርግጠኝነት ይናገራል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን የእዚህ ዓመት ላይ ለመቀላቀል የቻለው የአብስራ ተስፋዬ ወደ አዲሱ ቡድኑ መምጣቱን ተከትሎና በቡድኑ ውስጥም ስላሳለፋቸው ጊዜያቶች ተጠይቆ ምላሾቹን የሰጠ ሲሆን ከእነዛም መካከል የሚከተሉት ይገኝበታል፡፡
ባለፈው ዓመት የዝውውር መስኮት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጫወት ስለመምጣቱ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሹን ሲሰጥ “ለቅዱስ ጊዮርጊስ መጫወት መታደል ነው፤ ያም ሆኖ የመጨረሻ ግቤ ግን አይደለም” በማለት በኳስ ተጨዋችነት ዘመኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ውጪም ወደ ባህር ማዶም በመጓዝ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት የመጫወት እልሙ አለኝ ሲል ተናግሯል፡፡ ወጣቱ የአብስራ ከዛ በተጨማሪም በክለቡ ስለነበረው የእዚህ ዓመት ቆይታም ምላሹን እንዲሰጥ ተጠይቆ “እንደ መጀመሪያ ዓመት የክለቡ ተሳትፎዬ ጥሩ የውድድር ጊዜን አሳልፌያለው፤ በአንድ ወቅት የደረሰብኝ ጉዳት ደግሞ በወሳኝ ጨዋታዎች ላይ እንዳልጫወት ስላደረገኝ ለቡድኑ በሜዳ ላይ ልሰጥ ካሰብኩት ከፍተኛ ግልጋሎት አንፃር ያንን ላደርግ ባለመቻሌ ተከፍቻለው ብሎም ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ከቅዱስ ጊዮርጊሱ የአብስራ ተስፋዬ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታን ባደረግንበት ወቅት ተጨዋቹ የሰጠንን ምላሽ ከእዚህ በታች ባለ መልኩ አቅርበነዋል፤ ተከታተሉት፡፡
ኮቪድ 19 ለወራቶች ከእግር ኳስ በመራቁ በውስጡ ስለተፈጠረበት ስሜት
“እንደሚታወቀው ለእዚህን ያህል ጊዜ ከኳሱ ለመራቅ መቻል ለእኔ ብቻ አይደለም ለሁላችንም ተጨዋቾች ጭምር ነው ስሜቱ ከባድ ሊሆንብን የቻለው፤ ይሄ ያጋጠመን ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለሆነና ለሰፊ ወቅትም አርፈን የማናውቅ በመሆናችን አስቸጋሪ ጊዜያቶችንም ነው እያሳለፍን የምንገኘው፤ ይሄ ደግሞ ለእኛ ተጨዋቾች ብቻ ሳይሆን ለተመልካቾችም አሰልቺ ነገሮችን እየፈጠረባቸው ይገኛልና በፈጣሪ እገዛ ይህ ወረርሽኝ ጠፍቶልን ወደምንወደው እግር ኳሳችን እንደምንመለስ እርግጠኛ ነኝ”፡፡
በኮቪድ ከእግር ኳሱ በመራቅህ በአንተ እና በቤተሰብህ ዘንድስ የተፈጠረ የተለየ ነገር አለ?
“አዎን! ከዚህ በፊት ለብዙ ጊዜያት እነሱን አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር አላገኛቸውም ነበር፤ አሁን ግን የተፈጠረው አጋጣሚ ሁሉንም በሰፊው ጊዜ እንዳገኛቸው ስላደረገኝ በጋራ ጥሩ ጊዜን እያሳለፍን ነው የምንገኘው፤ በእዚህ መልኩም ከቤተሰቦቼ ጋርም በመሆኔ በጣሙን ደስተኛ እንድሆንም ነው ያደረገኝ”፡፡
ኮቪድ 19 ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ከስፖርት እንቅስቃሴዎች እና ከሌሎች ነገሮች ጋር በተያያዘ ወቅቱን በምን መልኩ እያሳለፈ እንደሆነ
“ብዙ የእረፍት ወቅቶችን እንደማግኘቴ መጠን የስፖርት እንቅስቃሴዎችን በፕሮግራም እሰራለው፤ ከዛ ውጪ ደግሞ ፊልም አያለው፤ የፕሌይስቴሽን ጌሞችን እጫወታለውና በዚህ መልኩ ነው ጊዜዎቹን እያጠፋው የምገኘው”፡፡
ያለ ኳስ ህይወት
“በጣም ከባድ ነገርን ነው እያሳለፍን የምንገኘው፤ ከላይም ልገልፀው ችያለው፤ የምትወደውን ነገር አይደለም ለአራት እና ለአምስት ወራቶች ለአንድ እና ለሁለት ሳምንት እንኳን ውድድሮች ተቋርጠው ኳሱን ስታጣው የሚሰማህ መጥፎ ስሜት አለና ያን መቋቋም መቻል አስቸጋሪ ሆኖ ነው ያገኘሁት፤ ስለዚህም ፈጣሪ ፈቅዶ ወደ ኳሳችን መመለስ የግድ ነው ያለብን”፡፡
አሁን ላይ ምን ናፈቀህ?
“ኳስ ነዋ! የፕሪምየር ሊግ ውድድራችን በፍጥነት እንዲመለስ ነው”፡፡
ቅ/ጊዮርጊስ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ካጣ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል፤ ዘንድሮም እናንተ በገባችሁበት ዓመት ላይ በኮቪድ 19 ምክንያት የሀገሪቱ የሊግ ውድድር በመሰረዙ ሶስተኛውን ዓመትም ይዟል፤ ይሄን ክለብ ለእንደዚህን ያህል ወቅቶች ያለ ዋንጫ ስታየው ምን አልክ?
“ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ክለቦች ትልቁ፣ ሀያሉና አንጋፋውም የሆነ ቡድን ነውና ይሄን ቡድን ያለ ዋንጫ ለሁለት ዓመት ማየት መቻል በጣም ያማልና ለተጨዋቹ፣ ለደጋፊው እና ለአመራሮቹ ከባድ የሆነ ነገር ነው የፈጠረባቸው፤ ዘንድሮም ቢሆን ክለቡን በአዲስ መልክ የተቀላቀልነውም ተጨዋቾች ከነባሮቹ ጋር በመሆን ይሄን ዋንጫ በማንሳት የክለቡን ስምና ዝና ዳግም እንመልሳለን ብለን ብንጓዝም፤ መጀመሪያ ላይ አጋጥሞን የነበረውን ጥሩ ያልነበረውን አቋማችንን እያስተካከልን ለመምጣት ብንችልም፤ የሊጉን ዋንጫ ለማግኘት ስንፎካከር ብንቆይም ውድድሩ በኮቪድ 19 በመቋረጡ ያንን እልም እንዳናሳካ አድርጎናልና በጣም ነው ያዘንነው፤ ያም ሆኖ ግን የቀጣይ ዓመት ላይ ታሪካዊውን የድል ውጤት ለመጎናፀፍ እንደምንችል የአሁን ሰዓት ላይም ከያዝናቸው ምርጥ የተጨዋቾች ስብስባችን አንፃርም እርግጠኛ ሆኜም ነው የምናገረው”፡፡
በኮቪድ 19 የእግር ኳሱ ውድድር ባይቋረጥ ኖሮ ቅ/ጊዮርጊስ የሊጉን ዋንጫ ዘንድሮ ያነሳ ነበር?
“እኔ በበኩሌ አፌን ሞልቼ መናገር እችላለው፤ ምክንያቱም ራሳችንን ከጨዋታ ወደ ጨዋታ በማሻሻል በጥሩ ደረጃ እና አቋምም ላይ እንገኝ ነበርና፤ ከዛ በተጨማሪም አጠቃላይ ተጨዋቾቻችንም በከፍተኛ የመጫወት ፍላጎት ላይም እያለን ነው ውድድሩ የተቋረጠውና ከነበረን የቡድን ስራ አንፃር የክለቡን ስምና የውጤት ዝናን ዳግም እንመልሰው ነበር”፡፡
ቅ/ጊዮርጊስ በዘንድሮው የሊጉ ተሳትፎ ውጤት ያጣባቸው ጊዜዎችም ነበሩ፤ እነዛ ችግሮቹ ምንድን ናቸው?
“እነዛ ውጤት ያጣንባቸው ጊዜያቶች በጣም የሚያናድዱ ናቸው፤ በተለይ ደግሞ በሜዳችን ላይ የምንጥላቸው ነጥቦችም ናቸው ሊጉን በሰፊ የነጥብ ልዩነት እንዳንመራና በጥቂት ነጥብ ልዩነቶችም የሌሎቹም ተከታዮች እንድንሆን ያደረገን፤ ከሜዳችን ውጪ ስንጫወት ጥሩ ውጤት ነው ያለን፤ ዋጋ ያስከፈለን የሜዳችን ላይ ጨዋታዎችም ናቸው፤ በተለይ ደግሞ ከአሰልጣኛችን ጋር ከተወሰኑ ጨዋታዎች በኋላ የነበሩት አንድአንድ አለመግባባቶችም ናቸው ሊጎዱን የቻሉት”፡፡
በቅ/ጊዮርጊስ ያሳለፍከው የእዚህ ዓመት ቆይታ ጥሩ የሚባል ነው?
“እንደ መጀመሪያው ዓመት የክለቡ ተሳትፎዬ በጣም ደስተኛ ነበርኩ፤ በሲቲ ካፑ የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ አልተሰለፍኩም ነበር፤ ያኔም ለምን አልገባውም ብዬም ራሴን ጠይቄ ነበር፤ በኋላ ግን ገብቼ መጫወት ስጀምርና ጥሩም ለመንቀሳቀስ ስችል በጣም ተደሰትኩ፤ በተለይ ደግሞ ወሳኝ ወሳኝ በሚባሉት የክለቡ ጨዋታዎች ላይ ማለትም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በግማሽ ፍፃሜው ላይ ስንጫወት ጎል ከማስቆጠሬ በተጨማሪ የግብ ኳስን ስላስቆጠርኩ በፍፃሜውም ጨዋታ ላይ ሻምፒዮና ስንሆን የጨዋታው ኮከብ ተብዬ የተሸለምኩበት አጋጣሚም ስላለ በክለቡ የእዚህ ዓመት ቆይታዬ ጉዳትን እስካስተናገድኩበት ጊዜ ድረስ በብዙ ጨዋታዎች ላይ የተሰለፍኩ ስለነበር እነዛ በጣም ደስተኛ አድርገውኛል፤ ደስተኛ ያላደረገኝ ደግሞ ጉዳት በደረሰብኝ ጊዜ ነበር”፡፡
እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለ ክለብ ውስጥ ተጫውቶ ጉዳትን ማስተናገድ መቻል ምን አይነት ስሜት ነው የሚፈጥረው?
“ለቅዱስ ጊዮርጊስ እየተጫወትክ መጎዳት እና ከሜዳ መራቅ ነገሮችን በጣም ነው ከባድ የሚያደርግብህ፤ ምክንያቱም ይሄ ቡድን ባልተለመደ ሁኔታ ከዋንጫ ከራቀ ሁለት ዓመታትን ስላስቆጠረና ክለቡም ሆነ ደጋፊውም ከአንተ የሚጠብቀው ብዙ ነገር ስላለ ነው፤ ያ ጉዳትም ወደ ቡድኑ በገባሁበት ዓመት ላይ ሲያጋጥመኝ ለእኔ ነገሮችን ሁሉ አስቸጋሪ አድርጎብኝ ቆይቶ ነበር። እነዛም ምንድናቸው ጉዳቴ በሁለት እና ሶስት በሆኑ ወሳኝ የሆኑ የቡድናችን ጨዋታዎች ላይ ማለትም ከመቐለ 70 እንደርታ፣ ከባህር ዳር ከተማ እና ከሰበታ ከተማም ጋር በነበሩት ጨዋታዎች ላይ እንዳልጫወት ስላደረገኝ ያ አስቆጭቶኛል”።
ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጫወት የመጣከው ምንን ሰንቀህ ነው?
“ወደ ክለቡ ገና ስገባም ይሄን ነገር ተናግሬዋለው፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጣሁት ባለፉት ሁለት ዓመታት ክለቡ ያጣውን ዋንጫ ከጓደኞቼ ጋር ሆነን ዳግም ወደ ቤቱ መመለስ አለብኝ እንደዚሁም ደግሞ የቡድኑን እና የእኛንም ስም በወርቃማ ቀለም ማስፃፍ አለብኝ የሚለውን እልም ሰንቄ ነበር የተጓዝኩት፤ ዘንድሮ ይህ እሳቤዬ በኮቪድ ምክንያት ውድድሩ በመቋረጡ ሳይሳካ ቀርቷል፤ በሚቀጥለው ዓመት ላይ ግን ጠንክረን በመስራት ያ እልማችንን እውን እንደምናደርገውይሰማኛል”።
የፕሪምየር ሊጉ የመጪው ዘመን ውድድር ያለ ተመልካች ይካሄድ ተብሎ ቢወሰን ስለሚኖረው ስሜት
“የአብዛኛው ሀገራት የሊግ ውድድሮች ያለ ተመልካች እና ያለ ደጋፊ ተከናውነው ፍፃሜያቸውን አድርገዋል። ያ መሆን መቻሉም በጣም ከባድ ነገር ነው። በተለይ እንደ ተጨዋቾች ሆነህ ስትመለከተውም ነገሮችን አስቸጋሪም ያደርግብሃል። ከዛ ውጪ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላሉ በርካታ ደጋፊዎች ላላቸው ቡድኖችም ኳሱን ያለ ደጋፊዎቻቸው ማከናወንም ተፅህኖን ይፈጥርባቸዋል ብዬም አስባለውና ከፈጣሪ ጋር የምንወደው የሊግ ውድድራችን ተጀምሮልን ዋንጫውን የምናነሳበትን ሁኔታ አሁን ላይ ሆኜ እያሰብኩ ነው ያለሁት”።
ከነዓን ማርክነህ እና አዲስ ግደይ ክለባችሁን ስለመቀላቀላቸው
“የሁለቱ ተጨዋቾች ወደ ቡድናችንለመምጣት መቻል ካሳለፉት ጥሩ የውድድር ዘመን አንፃርና በጣምም የሚጠቅሙን ስለሆኑ ለቡድኑ ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው፤ ምክንያቱም የእነሱ ወደእኛ መምጣት ባለን ላይ አዲስ ሀይል መቀላቀል ይሆናልም ብዬ ስለማስብ ነው። ሌላው ሊጠቅመን የሚችለው ነገር ሁሉም የቡድኑ ተጨዋች በርትቶ እንዲሰራ እና በአግባቡም ኳሱን እንዲጫወትና ስራውንም እንዲሰራየሚያደርግም በመሆኑ ነውና ከፈጣሪ ጋር ከእነሱ ጋር አብረን የምንጫወትበት እድል መምጣቱ ጥሩ ነው”፡፡
ከተጨዋቾቹ ወደ ክለቡ መምጣት ጋር ተያይዞ የክለቡ ቋሚ ተሰላፊ ለመሆን ስለሚኖረው ፉክክር
“ይሄ በኳስ ያለ ነው፤ እኛም ዓምና ወደ ቡድኑ ስንመጣ የተለያዩ ነበርና አዳዲስ ተጨዋቾች በክለቡ ይገኙ ነበርና ጠንክረን በመስራት ያን ፉክክር ተቀላቅለን አቅማችንን አውጥተን ለመጫወት ሞክረናል፤ አሁንም ሌላ ተጨዋች መምጣቱ ይበልጥ እንድንሰራ ያደርገናል፤ ከነበረን ነገር ላይም አቋማችንን ይጨምርልናልና ተፎካክሮ መጫወቱ ጥሩ ነው የሚሆነው”፡፡
በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተመለከትካቸው ነገሮች ያስገረመህ
“በቅዱስ ጊዮርጊስ የእዚህ ዓመት የተጨዋችነት ቆይታዬ ያስገረመኝ ብዙ ነገር ባይኖርም ቡድኑ ከኢትዮጵያ ካሉ ቡድኖች ብቻ ሳይሆን ውጪ ከሚገኙ ቡድኖች ጋርም በአደረጃጀቱ እና በአንድአንድ አካሄዶቹ የሚመደብ እና ሁሉንም ነገር ያሟላ ክለብ መሆኑ ያ የተለየ ያደርገዋል፤ ከዛ በተጨማሪ ተጨዋች ሲጎዳ ጊዜ የሚሰጥ ቡድን አይደለም ወዲያው ነው ሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ወደ ውጪ ወስዶም የሚያሳክመውና ያ ለእኔ በጣም አስገርሞኛል፤ ለተጨዋቾችም ልዩ ክብር ያለውም ፕሮፌሽናል አካሄድን የሚከተል ክለብም ነው”።
በእግር ኳስ ምርጡ ጥምረትህ ከማን ጋር ስትጫወት ነው?
ስለዛ ተጨዋች ብቃትስ ምን ትላለህ?
“ምርጡ ጥምረቴ ከአቤል እንዳለ ጋር ስጫወት ነው፤ ስለ እሱ ችሎታና ብቃትም ሁሌም እንደተናገርኩ ነው። አቤል በእግር ኳሱ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት የመሀል ሜዳ ተጨዋቾች የተለየ ተሰጥኦ ያለውና ብዙ ነገርንም ለመስራት አቅም ያለው ተጨዋች ስለሆነ ከእሱ ጋር እና ከጎኑ ሆኜ ስጫወት ሁሉም ነገር ይቀለኛል፤ አቤል ካለም ነው በጣም ጥሩ የሆነ እንቅስቃሴንም አድርጌ ከሜዳ የምወጣው”።
በተቃራኒነት መግጠም ስለሚያስደስተው ተጨዋች
“እስካሁን ይሄ ነው ያልኩት ተጨዋች ባይኖርም በደደቢት ክለብ ውስጥ አብረውኝ የተጫወቱትን ጓደኞቼንና ተጨዋቾች ብገጥማቸው እና ብፋለማቸው እንደዚሁም ደግሞ የሚጫወቱበትን ቡድን አሸንፈናቸው ብንወጣ ሁሌም ነው በጣም ደስ የሚለኝ።
በኳስ ዘመንህ በተቃራኒነት ከተፋለምካቸው ተጨዋቾች ለአንተ በጣም አስቸጋሪ የሆነብህ ተጨዋች
“የእግር ኳስን ስጫወት ሜዳ ላይ ብዙም ስለማልቆም ያጋጠመኝ አስቸጋሪ ተጨዋች ባይኖርም አንዴ ግን ለደደቢት ዋናው ቡድን ባደግኩበት ዘመን ላይ ከሐዋሳ ከተማ ጋር ስንጫወት ልምዱ የሌለኝ ተጨዋች ስለነበርኩና ቡድናችንም ከያዛቸው ወጣት ተጨዋቾች አንፃር ጫናም ስላለብን በእግር ኳስ ተጨዋችነት ጉዞው የተካበተ ልምድ ያለው ሙሉዓለም ረጋሳ በተወሰነ መልኩ ፈትኖኝ ነበርና ያን አልረሳውም”።
በደደቢት ክለብ ውስጥ የነበረህን ቆይታ በምን መልኩ ነው የምትገልፀው?
“በደደቢት የነበረኝ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ምንም እንኳን ክለቡ ከፋይናንስ ችግር ጋር በተያያዘ አሳዛኝ በሆነ መልኩ ወደ ከፍተኛው ሊግ ሊወርድ ቢችልም ጥሩ የሚባል ጊዜን ነው ከክለቡ ጋር ለማሳለፍ የቻልኩት፤ ይሄ ቡድን ብዙ ነገሮችን ያስገኘልኝና የተማርኩበት ነበር፤ ያም ሆኖ ግን የቡድኑ በዛ ደረጃ ላይ ተገኝቶ የቀድሞ ስሙና ዝናውን በፍጥነት ሊያጣው መቻሉ በጣም ነው እንዳዝን ያደረገኝ”፡፡
በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ የካምፕ ጓደኛ ማን ነው?
“በካምፕ አልኖርም፤ ነገር ግን ጨዋታ በሚኖረን ሰዓት እና ስንሰባሰብ አልያም ደግሞ ወደ ክፍለ ሀገር በምንወጣበት ሰዓት ከአቤል እንዳለ ጋር ነው የእኔ ጓደኝነት፤ ከእሱ ጋርም ነው በጣም የምንቀራረበውና አብረንም የምንውለው”፡፡
በእግር ኳስ ተጨዋችነትህ የአንተ ምርጡ ተጨዋች
“ከበፊቶቹ ምንያህል ተሾመ ከአሁኖቹ ደግሞ አቤል እንዳለ የእኔ ምርጥ ተጨዋቾች ናቸው”።
ከባህር ማዶ እግር ኳስ የማን ክለብ አድናቂ ነህ?
“የባርሴሎና እና የባርሴሎና ብቻ እነሱን ነው የማደንቀው፤ እነሱንም ነው የምደግፈው”።
ባርሴሎና ዘንድሮ የላሊጋውን ዋንጫ አጣ። ሪያል ማድሪድም የዋንጫው ባለቤት ሆነ ምን አልክ?
“የባርሳ ዋንጫ ማጣት በጣም ያሳዝናል፤ ከኮቪድ በፊት ጥሩ ጉዞን አድርገው ነበር። ያም ሆኖ ግን ሪያል ማድሪዶች ኳሱ ተቋርጦ እንደገና ሲጀመር ያለውን ክፍተት በመጠቀም ሻምፒዮና ሊሆኑ ችለዋል”።
ከባህር ማዶ ስለሚያደንቀው ተጨዋች
“አንድሬስ ኢኒዬስታን ነው የማደንቀው፤ ለእኔ ሁሌም ምርጡና ለየት የሚልብኝም ተጨዋች ነው”።
ከእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የምደግፈው
“የእነሱን ሊግ ማየት እንጂ የትኛውንም ክለብ አልደግፍም”።
ከሊጋቸው የምታደንቀውስ ተጨዋች
“የማንቸስተር ሲቲውን ኬቨን ደብረዩንን”።
ሊቨርፑል ከ30 ዓመት በኋላ የሊጋቸውን ዋንጫ አንስቷል። ይሄን ስትመለከት ምን አልክ?
“ዋንጫው በጣም ነው የሚገባቸው። አይደለም ዘንድሮ ዓምናም ጥሩ የሆነ የውድድር ዘመንን ስላሳለፉ እንደዚሁም ደግሞ አጠቃላይ ተጨዋቾቻቸውም ማለትም በቋሚነት የሚሰለፈውም ተቀይሮ የሚገባውም በአንድ አይነት አቋም ላይ ስለነበሩ እና ያላቸው ህብረትና አንድነትም አስገራሚም ስለነበር ድሉ ለእነሱ ነበር የሚገባው”።
በእግር ኳስ ተጨዋችነትህ ጉዞ አሁን ላይ የምትፈልገው ስፍራ እና ቦታ ላይ ደርሰሃል ማለት ይቻላል?
“በጭራሽ በእዚህ ዕድሜዬ አሁን ላይ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ መጫወት መቻሌ መታደል ቢሆንም ይሄ ብቻ ለእኔ በቂ አይደለም፤ ለቅዱስ ጊዮርጊስ መጫወትምእንደ አንድ አንድ ተጨዋቾች የመጨረሻ ግቤም አይደለም፤ ስለዚህም ከዚህ የተሻለ ነገር ሰርቼ ወደ ባህር ማዶ ሄጄ የምጫወትበትንም ነገር ነው እያሰብኩ ያለሁት ከዛ በፊት ግን በቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ውስጥ ብዙ ድሎችን ማሳካት እፈልጋለውኝ፤ ያን ማድረግ ስችልም ሌላውን ግቤን እመታለውኝ”፡፡
የጌታነህ ከበደ የአቤል ያለው እና የሄኖክ ውል ማራዘም
“የእነሱ ውል ማራዘም ለክለቡ ጥልቅ ጥቅም ነው የሚሰጠን፤ ምክንያቱም ካላቸው የተጨዋችነት ልምዱ አንፃር በብዙ ነገርም ይረዱናልና”፡፡
በመጨረሻ…..?
“የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በኳሱም ሆነ በህይወታችን እንድናድግ ከሚያደርግልን ድጋፍ አንፃር ይሄን ቡድን በውጤት የምንክስበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፤ ክለቡ ዝናብና ፀሐይ የማይሉ ምርጥ ደጋፊዎች አሉት፤ ስለዚህም ለእነዚህ ደጋፊዎች አሁንም ከጎናችን ሁኑ ብዬ በመጪው ዓመት የተሻለ ነገር ሰርተን በውጤት እንደምንክሳቸው እርግጠኛ ነኝ፤ ከዛ ውጪም በኳሱ ከእኔ ጎን ለሆኑት ፈጣሪዬ ቤተሰቦቼ፣ ጋደኞቼ፣ ላሰለጠኑኝ አሰልጣኞች እና ለደጋፊዎቻችን ምስጋና አለኝ”፡፡
https://t.me/Leaguesport