በመሸሻ ወልዴ
ለቅ/ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫ ከዛም ቀጥሎ ደግሞ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጅማሬ ጨዋታዎች ላይ ለክለቡ በቋሚ ተሰላፊነት አገልግሎ ስኬታማና ጥሩ የሚባል የሜዳ ላይ ብቃቱን ከወዲሁ እያሳየ ይገኛል፤ ይኸው ወጣት ግብ ጠባቂ ባህሩ ነጋሽ ሲባል ተወልዶ ያደገው በአስኮ አካባቢ ነው፤ ከወላጅ አባቱ አቶ ነጋሽ ረጋሳ እና ከወላጅ እናቱ ወ/ሮ ሙሉነሽ ዓለሙ የተወለደው ይህ ግብ ጠባቂ አንድ ወንድም እና ሁለት እህቶች ያሉት ሲሆን ተጨዋቹ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የመሰለፍ ዕድልን እያገኘ ባለበት የአሁን ሰዓት ላይ ለቡድኑ ምርጥና ጥሩ ግብ ጠባቂ ሆኖለት በቀጣይነት ክለቡን ውጤታማ ለማድረግ መዘጋጀቱንም ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ መሸሻ ወልዴ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሹን ሰጥቷል፡፡
የቅ/ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብን ከታዳጊው ቡድን አንስቶ በማገልገል እና በእዚህ ዓመት ላይ ደግሞ ለዋናው ቡድን በቋሚ ተሰላፊነት መጫወት በመጀመር ተስፋ ሰጪን እንቅስቃሴ እያሳየ ያለውን ይኸውን ወጣት ግብ ጠባቂ ሊግ ስፖርት ጋዜጣ ስለኳስ ህይወት ጅማሬው፣ ስለቅ/ጊዮርጊስ ቆይታው፤ ለቡድኑ አሁን ላይ በቋሚ ተሰላፊነት ስለመጫወቱ እና በሌሎችም ጥያቄዎች ዙሪያ አናግረነው ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቶናል፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህሩ ነጋሽ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት ተገናኙ? በክለቡ ውስጥ ያለህ ቆይታስ ምን ይመስላል?
ባህሩ፡- ከቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘሁት በክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያ የታዳጊዎች ውድድር ላይ ለቡድኔ አስኮ ፕሮጀክት ስጫወት በሜዳ ላይ ባሳየሁት ጥሩ የግብ ጠባቂነቴ ብቃት ነው፤ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጊዜው ከማምራቴ በፊት ግን መጀመሪያ ላይ ከእዚሁ ውድድርና ከምጫወትበት የፕሮጀክት ቡድን በአሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ /ድሬ/ አማካኝነት ለኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን /u-17/ ተመርጬም ነበር፤ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከዛም ጭምር ነው በድጋሚም በደንብ አይተውኝ ወደ ታዳጊ ቡድናቸው ያስመጡኝ፤ ከእዚያን ጊዜ ጀምሮም እኔና ክለቤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይኸው ተሳስረን አሁን ላይ ጊዜው ደርሶ የዋናውን ቡድን በቋሚ ግብ ጠባቂነት እያገለገልኩት እገኛለውና በቡድኑ ውስጥ ባለኝ የእስካሁን ቆይታ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
ሊግ፡- ወደ ቅ/ጊዮርጊስ የዋናው ቡድን ከማደግህ በፊት በታዳጊው እና በተስፋው ቡድን ደረጃ የነበረህ የሜዳ ላይ ግልጋሎት ምን መልክ ነበረው?
ባህሩ፡- ቅ/ጊዮርጊስን በታዳጊውም ሆነ በተስፋው ቡድን ደረጃ ስቀላቀል ለቡድኑ የሰጠሁት ጥቅም በጣም ጥሩ እና በአበረታችነቱም የሚጠቀስ ነው፤ በእነዚህን ጊዜ ቆይታዎቼም የራሴን ችሎታ በግብ ጠባቂነቱ በጣም ከማደንቀው እና ለራሴም ተምሳሌቴ /ሮል ሞዴሌ/ ካደረግኩት የክለባችን የቀድሞው ኡጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ሮበርት አዶንካራ ብዙ ነገሮችን በመማርና በማወቅም ብቃቴን ከጊዜ ወደጊዜም አሻሽዬበታለውና ይሄ ለእኔ በጥሩነቱ የሚጠቀስ ነው፤ ከዛ ሌላም በተስፋ ቡድን ደረጃ ማለትም ለክለቡ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ስጫወትም አዳማ ላይ ፍፃሜ ባደረገው የ2007ቱ ዓ.ም ውድድር ላይም ቡድናችን ለዋንጫ እንዲቀርብም በማስቻል የውድድሩ ኮከብ ግብ ጠባቂም ተብዬ ሽልማቱን አግኝቻለውና በቅዱስ ጊዮርጊስ የተተኪው ቡድኖች ውስጥ ለቡድኔ የሰጠሁት ጥቅምና ግልጋሎት ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡
ሊግ፡- ግብ ጠባቂነትን ፈልገህ ነው የሆንከው?
ባህሩ፡- አይደለም፤ በአጋጣሚ ነው የሆንኩት፤ የእኔ ፍላጎት የነበረው ኳስ ተጨዋች መሆን ነበር፤ ያም ሆኖ ግን በታዳጊነት ዕድሜዬ ላይ እያለሁ የእኔ ጓደኛ እና ለኤሌክትሪክ የተተኪ ቡድን ይጫወት የነበረው ዘላለም በአስኮ ፕሮጀክት ልምምድ ይሰራ ነበርና የእኔን ቁመት አይቶና ሌላ አንድ ልጅንም ይዞን ወደዛ ሄደ፤ እዛ እንደደረስንም ልጁን ተጨዋች እኔን ደግሞ በረኛ ነው ብሎ አስመዘገበንና በፕሮጀክቱ መለማመድ ጀመርን፤ በበረኝነቱ ጥቂት ጊዜያት ከሠራው በኋላ በረኝነት በጣም የሚያለፋና ከዛ ውጪም የመጫወቻው ሜዳውም አቧራማ ስለነበር እዛ ላይ እየወደቅን ስንሠራ ይቀርብኝ ብዬ ተውኩት፤ ከ6 ወራት በኋላ ግን በሰፈር ደረጃ ላይ በተዘጋጀ ውድድር ለትላልቅ ልጆች በግብ ጠባቂነት ገብቼ ስጫወት ጥሩ መሆኔን ተከትሎ በረኝነቱን ወደድኩትና ከእዚህን ጊዜ ጀምሮ ነው በክብር አቶ ይድነቃቸው ተሠማ መታሰቢያ የታዳጊዎች ውድድር ላይ በመሳተፍ ጀምሬ በበረኝነቱ የቀጠልኩት፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ግብ ጠባቂ አለ እየተባለ በተደጋጋሚ ይነገራል፤ ይሄን እንደተጨዋችነትህ ስትሰማ በውስጥህ የሚፈጠርብህ ስሜት ምን ይመስላል?
ባህሩ፡- በእዚህ ንግግር ሁሌም ነው በጣም የማዘነው፤ ሃገራችን ውስጥ እኔ ግብ ጠባቂዎች አሉ ነው የምለው፤ ግብ ጠባቂ አለ ወይንም ደግሞ የለም ብለህ ለመናገር እኮ መጀመሪያ ግብ ጠባቂዎቹ በሜዳ ላይ በተደጋጋሚ የመሰለፍ እድልን ሊያገኙ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ብዙ ክለቦች ዜጋ ግብ ጠባቂ ስላላቸውና የመሰለፍንም እድል የሚያገኙት እነሱም ስለሆኑ የእኛን ልጆች ብቃት እንዳይታይ አድርጎታል፤ ታድያ ለኢትዮጵያዊ ተጨዋች የመሰለፍ እድሉ ሳይሰጠው እንዴት ነው ግብ ጠባቂ የለም ተብሎ ሊወራ የሚችለው፤ ግብ ጠባቂ እኮ የመሰለፍ እድልን ካላገኘ በችሎታውም ሆነ በአህምሮው ደረጃ እየወረደ ይመጣልና የኢትዮጵያ በረኞች የመሰለፍ እድልን በተደጋጋሚ ጊዜ ካገኙ አሁንም እደግመዋለው ጥሩ ብቃት ነው ያላቸው፡፡
ሊግ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስን የፕሪምየር ሊግ ጅማሬ በምን መልኩ ትገልፀዋለህ? በእዚህ ዓመትስ ምን ውጤትን ለማምጣት አልማችኋል?
ባህሩ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ የሊግ ጅማሬ ክለቡ ካለው ስምና ዝና አንፃር እንደዚሁም ደግሞ በተደጋጋሚም ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ከማንሳቱ አኳያ ስመለከተው ቡድናችን ያስመዘገበው ውጤት የሚገባው አይደለም፤ ቡድናችን በሶስቱም ጨዋታዎች አሸንፎ ሙሉ ዘጠኝ ነጥብ ማምጣትም ይገባው ነበርና ያን ልናሳካው አልቻልንም ስለዚህም አሁን ላይ በጣም ጠንክረን መስራት እንዳለብን በሚገባ ለመረዳት ችለናል፡፡
የእዚህ አመት ላይ በፕሪምየር ሊጉ ስለምናስመዘግበው ውጤት በተመለከተ ደግሞ ክለባችን ዛሬ ብቻ ሳይሆን ሁሌም የሚጫወተው የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ነው፤ ዘንድሮም ለእዚህ ድልም ነው የምንፋለመው፤ የእዚህ አመት ዋንጫ ደግሞ ለእኛ በጣም አስፈላጊያችንም ነውና ይሄን ዋንጫ ባለፉት ሁለት ዓመታቶች ከማጣታችን አኳያ የአሸናፊነት ክብሩ ወደ ቀድሞው ቡድኑ ይመለሳል፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ አቻ ከተለያየ በኋላ ዛሬ ስዑል ሽረን ይፋለማል፤ በእዚህ የዛሬ ጨዋታ ዙሪያ ምን የምትለው ነገር ካለ?
ባህሩ፡- ከስዑል ሽረ ጋር ያለን የዛሬው ጨዋታ በሜዳችን እና በደጋፊዎቻችን ፊት የምናደርገው ነው፤ ይሄን ፍልሚያም ማሸነፍ መቻል የግድ ነው የሚለንና ጨዋታውን በእርግጠኝነት አሸንፈን የደረጃ መሻሻልን እናሳያለን ቀድሞ ወደምንታወቅበትም የአሸናፊነት መንፈስ እንመለሳለን፡፡
ሊግ፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ የማደግ እድሉን ብታገኝም በቋሚ ተሰላፊነት ከዚህ በፊት ለመጫወት አልቻልክም፤ አሁን ግን ይሄን እድል አግኝተሃል፤ በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለ?
ባህሩ፡- ለቅ/ጊዮርጊስ የዋናው ቡድን ካደግኩበት ጊዜ ጀምሮ በቋሚ ተሰላፊነት ለመጫወት ያልቻልኩት በልምድም ሆነ በችሎታቸው ይበልጡኝ የነበሩ ግብ ጠባቂዎች ስለነበሩ ነው፤ መጀመሪያ ላይ ሮበርት አዶንካራ ነበር፤ እሱ ደግሞ ምርጥ እና ተደናቂ ግብ ጠባቂ ስለነበር ላስቀምጠው አልቻልኩም፤ ሮበርትን የሚያህል ግብ ጠባቂ በሃገራችን ውስጥ የለም፤ እሱን አድናቂው ከመሆኔ አኳያም እያየሁትም ነበር ያደግኩት፤ ከዛ ውጪም ሮበርትን መተካትም እንደምፈልግ በማለምም የእሱን ጨዋታዎችም በደንብ እከታተልም ነበርና ሜዳ ላይ ሲጫወት ሳየው እኔም እንደእሱ ተሰልፌ የምጫወተው መቼ ነው በሚል በማለምም ለችሎታው ትልቅ ክብር ሁሉ አለኝና በእዚህም የተነሳ ነው ለክለቤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቋሚነት ተሰልፌ ሳልጫወት የቀረሁት፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን አሁን ላይ ደግሞ በቋሚ ግብ ጠባቂነት እያገለገልኩ ያለሁት የቡድናችን በረኞች ውስጥ በተለይ ደግሞ በብቃቱም ሆነ ቡድኑን ሲመራ በሚያሳየው ብቃት በሀገራችን ውስጥ ከሚገኙት ግብ ጠባቂዎች መካከል በጣም የማደንቀው ለዓለም ብርሃኑ በጉዳት ከሜዳ የራቀበት ሁኔታ በመፈጠሩ በእዚያም የተነሳ ነው ለእኔ የመሰለፍ እድሉ ስለተሰጠኝ ክለቤን በጥሩ ሁኔታ እያገለገልኩ የምገኘው፡፡
ሊግ፡- ለቅዱስ ጊዮርጊስ በቋሚ ግብ ጠባቂነት በቀጣይነት ዘልቀህ የምትሰለፍ ይመስልሃል?
ባህሩ፡- ይሄ የሚወሰነው በአሰልጣኜ እንደዚሁም ደግሞ በራሴ ብቃትና ብቃት ብቻ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ አሁን ላይ የቡድናችን ግብ ጠባቂ ለአለም ብርሃኑ የብሄራዊ ቡድን ልምምድ ላይ ስለተጎዳ የእሱ አለመኖር የመሰለፍ እድሉን ሊፈጥርልኝ ችሎ ለክለቡ እየተሰለፍኩ ይገኛል፡፡ በረኛ ስትሆን የምታገኘው እድል አንድ ብቻ ስለሚሆንና እንደሌሎች የመጫወቻ ስፍራዎችም አማራጭ ስለማይኖርህ ሁሌም የተሰጠህን የመሰለፍ እድል በአግባቡ መጠቀም ይኖርብሃልና እኔም ይሄንን እድል በመጠቀም ለክለቤ በቋሚ ተሰላፊነት ለመጫወት እና ክለቤንም ለውጤት ለማብቃት ከፍተኛ ጥረት አደርጋለው፡፡
ሊግ፡- በአንተ የስፖርት ህይወት ውስጥ ቤተሰቦችህ ያላቸው አመለካከትና ድጋፍ ምን ይመስላል፤ ከዛም ውጪ የምታመሰግናቸው አካላቶች ካሉ?
ባህሩ፡- ቤተሰቦቼ የእግር ኳስ ጨዋታን ማዘውተር በጀመርኩበት ጊዜ ስለስፖርቱ ብዙም ግንዛቤው ስላልነበራቸው እንድማር እንጂ ኳስን እንድጫወት አይፈልጉም ነበር፡፡ ያኔ ኳሱን ስጫወትም ደስተኛ አልነበሩም፤ ያም ሆኖ ግን አትጫወት ብለው አይከለክሉኝም ነበርና ጠንክሬ እየሰራሁ በመሄዴ ነው አመለካከታቸውን አስቀይሬ ለእኔ ድጋፍን እያደረጉልኝ የሚገኘው፤ በተለይ እነሱ ከእኔ ጎን መሆን የጀመሩት ለኢትዮጵያ ሀ-17 ታዳጊ ብሄራዊ ቡድን ተመርጪ በነበረበት ጊዜም ነበርና በዚሁ አጋጣሚ እነሱን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ከቤተሰቦቼ ውጪ ሌላ የማመሰግናቸው በታዳጊ ቡድን ውስጥ ያሰለጠነኝን በላቸው ኪዳኔን እንደዚሁም ደግሞ የክለባችንን የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ኤሚን እኛ ስንጠራው ዳንዳ ነው የምንለው እሱን ከሚያሰራን በአውሮፓ ደረጃ ከሚሰጠን ስልጠና አኳያ በደንብ ያሰራን ነበርና በእዛ በጣም ነው የማመሰግነው፤ በግብ ጠባቂነቴ ዛሬ ላይ ለውጥ ለማምጣቴ ምክንያት የሆነኝ ምንም አይነት ጥያቄ አያስፈልገውም የኤሚ ስራ ነው ለእሱ ሁሌም የተለየ ክብርም ነው ያለኝና በድጋሚ ላመሰግነው እፈልጋለሁ፡፡ ሌላው የማመሰግነው የቡድናችንን ተጨዋችን ምንተስኖት አዳነን ነው፤ እሱ ጥሩ ተጨዋች እንድሆንም ህይወቴንም በምን መልኩ መምራት እንዳለብኝም በብዙ ነገሮች የሚመክረኝና የሚያበረታታኝም ስለሆነ አመሰግነዋለው፤ ሌሎቹም የቡድናችን ተጨዋቾችም ከጎኔ ስላሉም ለእነሱም ምስጋናው አለኝ፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ባህሩ፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነት ህይወቴን ትልቅ ደረጃ ላይ ማድረስ እፈልጋለሁ፤ ክለቤን ለውጤት ከማብቃት በተጨማሪም ለሀገሬ ብሔራዊ ቡድንም በመመረጥና በመሰለፍም ወደ ትላልቅ የውድድር መድረኮችም እንድታልፍ ማድረግን አልማለው፡፡