በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/
ለቅ/ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በዝውውር መስኮቱ ውላቸውን ካደሱት ተጨዋቾች መካከል አንዱ ሙሉዓለም መስፍን /ዴኮ/ ነው፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ቆይታው ለቡድኑ ጥሩ መጫወት የቻለው ይኸው ተጨዋች ዳግም ቡድኑን ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት እንዲያገለግል የተደረገ ሲሆን ተጨዋቹ በእዚህ ክለብ ቆይታው ዋንጫን ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የግድ ማምጣት እንዳለበት ይናገራል፤ “ለቅ/ጊዮርጊስ ተጫውተህ ስታሳልፍ ለአንተ ትልቁ ነገር ዋንጫ ማግኘት መቻል ነው፤ ያለበለዚያ ተጫውቼ አሳልፌያለሁ ብቻ ማለት ብዙ ዋጋ የለውም” ሲልም ሀሳቡን አስፍሯል፤ ከሙሉዓለም ጋር በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ቆይታ አድርገን የሰጠን ምላሽ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡
ሊግ፡- በቅ/ጊዮርጊስ ውስጥ የውል ዘመንህን በክረምቱ ወራት ስታጠናቅቅ ከክለቡ ጋር በድጋሚ እንደምትቀጥል ታውቅ ነበር?
ሙሉዓለም፡- አዎን፤ ምክንያቱም ከቅ/ጊዮርጊስ ውጪ ወደ ሌላ ክለብ የማመራበት ምንም አይነት ፍላጎቱ ያልነበረኝና ከክለቤም ጋር በጥብቅ እንፈላለግ ስለነበር ለሁለት ዓመት ውሌን አራዝሜ ዳግመኛ የቅ/ጊዮርጊስ ተጨዋች ልሆን ችያለሁ፤ ቅ/ጊዮርጊስ እኮ ማንኛውም ተጨዋች ሊጫወትበት የሚፈልግ ክለብ ነው፤ ሁሉም ተጨዋች የሚለፋውም ወደዚህ ቡድንም ለመምጣት ነውና የሁለታችን መጣጣም መቻል ንብረቱ እንድሆን አድርጎኛል፡፡
ሊግ፡- የቅ/ጊዮርጊስ ያለፉት ሁለት ዓመታት ቆይታህ ከዋንጫ ጋር የታጀበ አይደለም፤ ይሄ ለአንተ ምን ማለት ነው?
ሙሉዓለም፡- የእውነት ለመናገር ከክለቡ ጋር ዋንጫ አንስቼ ሻምፒዮና ለመሆን ብንችል በጣም ነበር ደስ የሚለኝ፤ ወደዚህ ቡድን የመጣሁትም በደስታ ይህንን ክብር አገኛለውም ብዬ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን በክለቡ በነበረኝ ቆይታ በውጤት ደረጃ ሊሳካልኝ አለመቻሉ በጣሙን እንዳዝን ነው ያደረገኝ፤ በተለይ ደግሞ የውጤት ማጣታችን ከእኔ በላይ አሳዛኝ የነበረው ለክለቡም ነበር፤ ምክንያቱም ይሄ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ደረጃ በተደጋጋሚ በመሳተፍ የሚታወቀው ታላቅ ክለብ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ዋንጫ ሲያጣ ለመጀመሪያው ጊዜም ነውና፤ እንደ ግልም ቅ/ጊዮርጊስ ውስጥ ስትጫወት ተጫውቼ አሳልፌያለሁ ብቻ ማለት ዋጋ የለውም የግድ የክብር ድሎችንም ልትጎናፀፍ ይገባልና ከክለቡ ጋር ዋንጫ አለማንሳቴ በድጋሚ ይቆጨኛል፡፡
ሊግ፡- በቅ/ጊዮርጊስ ውስጥ በነበረህ ቆይታህ በጣሙን ተፈላጊ ተጨዋች እንደሆንክ በዝውውር መስኮቱ ከተሰጠ የፊርማ ክፍያ ለማወቅ ተችሏል፤ ለዚህ ክፍያ በቀጣይነት የቱን ያህል አቻ ግልጋሎት ለመስጠት ተዘጋጅተሃል?
ሙሉዓለም፡- ቅ/ጊዮርጊሶች በዝውውር መስኮቱ ለእኔ የሰጡኝ የፊርማ ክፍያ ከፍተኛ ይሁን አይሁን ባላውቅም ውሌን በክለቡ እንዳራዝም ሲያናግሩኝ የሰጡኝ ብር ይገባዋል ብለው ነበርና እኔም አዎን ይገባኛል ብዬ ተቀብዬ ክለቤን ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት በስኬት ለማገልገል ተዘጋጅቻለሁ፤ አዎን፤ ባለፉት ጊዜያቶች ለቅ/ጊዮርጊስ ውጤት ማምጣትን አልቻልኩም ነበር፤ አሁን ግን ያን ከጓደኞቼ ጋር ማስተካከል በመቻል ክለቤ ላደረገልኝ ነገር ሁሉ ውለታውን መመለስ እፈልጋለሁ፡፡
ሊግ፡- ለቅ/ጊዮርጊስ ለመጫወት አዳዲስ ተጨዋቾች ፊርማቸውን አኑረዋል፤ የሚሳካላቸው ይመስልሃል?
ሙሉዓለም፡- ቅ/ጊዮርጊስ በዝውውር መስኮቱ ወደ ቡድናችን ያስመጣቸውን ተጨዋቾች በተመለከተ አሁን ላይ ሆኜ ይጠቅማሉ አይጠቅሙም ለማለት ጊዜው አይደለም፤ ምክንያቱም ስለ እነሱ ብዙ ነገር ማለት የምችለው ውድድሩ ሲጀመር ነውና ያም ሆኖ ግን ክለባችን ተጨዋቾቹን በነበሩበት ክለብ ውስጥ ጥሩ ችሎታን አሳይተው ስለቆዩ ይጠቅማሉ ብሎ አስመጥቷቸዋልና እነዚህ ተጨዋቾች እኛ ጋር በመምጣታቸው እንዲሳካላቸው እፈልጋለሁ፤ ወደ እኛ ስለመጡት ተጨዋቾች ከላይ የገለፅኩት ሀሳብ ለክለቡ መጫወት መቻል ቀላል ስላልሆነ፤ ቡድኑ ካለው ስምና ዝና አንፃርም ከፍተኛ ጫና ያለብህ ስለመሆኑና ኃላፊነትንም የምትሸከምበት ቡድን ስለሆነ ነው፡፡
ሊግ፡- ወደ ቅ/ጊዮርጊስ አንተ በምትጫወትበት ስፍራም ተጨዋች መጥቷል፤ ይሄ አያሰጋህም?
ሙሉዓለም፡- በፍፁም፤ ወደ ክለባችን ማንም ተጨዋች ይምጣ በእኔ ላይ አንዳችም የስጋት ስሜት አይፈጥርብኝም፤ ምክንያቱም የተጨዋቾች መምጣት እኔን የበለጠ ጠንክሬ እንድሰራ ያደርገኛልና፡፡
ሊግ፡- የቅ/ጊዮርጊስ የፕሪ-ሲዝን ዝግጅት ምን ይመስላል? አዲሱ አሰልጣኝንስ እንዴት አገኘኸው?
ሙሉዓለም፡- የፕሪ ሲዝን ዝግጅታችን በጣም ጥሩ ነው፤ ኳስ ላይ ባተኮረ መልኩ እንዴት እንደ ቡድን መጫወት እንዳለብን እና እንዴትም ጎል ማስቆጠር እንዳለብን የሚያሳይ ልምምድን እየሰራን ይገኛል፤ አሰልጣኙን በተመለከተ ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ብዙ ነገርን የሚያውቅ እና መረጃ ያለው ሰው ነው፤ ከዚህ በፊት የማናውቃቸውን ብዙ ነገሮች እያሳወቀን ይገኛልና በጣም ጥሩ አሰልጣኝ እንደሆነ ለመናገር እፈልጋለሁ፡፡
ሊግ፡- ካለፈው ዓመት አንስቶ በጉዳት ላይ የነበሩት ሳህላዲን ሰይድና ጌታነህ ከበደ ከቡድናችሁ ጋር ልምምድ ጀምረዋል፤ የእነሱ ወደ ሜዳ መመለስን በምን መልኩ ነው የምትመለከተው?
ሙሉዓለም፡- ሁለቱም አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ ከጉዳታቸው አገግመው ነው ወደ ልምምድ የተመለሱት፤ የእነሱ በመልካም ጤንነት ላይ ሆነው መገኘትና መለማመድ መቻልም ለቅ/ጊዮርጊስ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ይጠቅማልና ይሄ መሆን መቻሉ በጣም አስደስቶኛል፤ ምክንያቱም ሀገራችን እነዚህን ተጨዋቾች በቅርቡ ካጣች በኋላ የተፈጠረውን ነገር አይተናልና፤ ሁለቱም ጥሩ ችሎታ ያላቸው ተጨዋቾች ናቸው፤ ልምዳቸውንም ለብዙዎቹ የሚያካፍሉ ስለዚህ በቀጣይነት ለክለባችን ጥሩ ነገር ይሰራሉ ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ፡፡
ሊግ፡- የመጨረሻ ጥያቄ ከብሔራዊ ቡድን ውጪ ከሆንክ በርካታ ቀናቶችን እያስቆጠርክ ይገኛል፤ በምን ምክንያት?
ሙሉዓለም፡- የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን ጋር በነበረው የቻን አፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በእነሱ ሀገር ላይ ተሰልፌ ተጫውቼ እዚህ በነበረው የመልስ ጨዋታ ላይ ደግሞ ሳልሰለፍ ከቀረው በኋላ ከዓለም ዋንጫው የማጣሪያ ጨዋታ ጀምሮ ከብሔራዊ ቡድን ውጪ የሆንኩበትን ምክንያት ፈፅሞ አላውቀውም፤ ባውቀው ግን ደስ ይለኝ ነበር፤ ከብሔራዊ ቡድን ውጪ መሆኔ እኔን ብዙ አላስጨነቀኝም፤ ምክንያቱም ያለኝን ችሎታ ጠብቄ በማቆየትና ሌላም የተሻለ ነገርን በመስራት ነገም ለሀገሬ ተመልሼ እንደምጠራ ስለማውቅ ነው፡፡