“ለቅ/ጊዮርጊስ ክብር አለኝ፤ ይቅርታ ጠይቄ የነበረው ከፀፀቴ ለመዳን ብዬ እንጂ እንዲመልሱኝ ብዬ አልነበረም”
“ለፋሲል ከነማ ፊርማዬን በቅድሚያ ያኖርኩት ቡድኑ በቻምፒዮንስ ሊጉስለሚሳተፍና ስለሚመጥነኝ ነው”
አስቻለው ታመነ /ፋሲል ከነማ/
ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዘንድሮ ያሸነፈው ፋሲል ከነማ የክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ሲከፈት ቡድኑን ለመጪው ዓመት ይበልጥ ለማጠናከር የተለያዩ ተጨዋቾችን እያስፈረመ ሲሆን ከእነዛም መካከል የቅ/ጊዮርጊሱና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች አስቻለው ታመነ ይገኝበታል፡፡
ፋሲል ከነማ አስቻለውን ለሁለት ዓመት የውል ጊዜ ያስፈረመው ሲሆን ይህን የቀድሞ የደደቢትና የቅ/ጊዮርጊስ የተከላካይ ስፍራ ተጨዋችን ወደ ቡድኑ ስላደረገው ዝውውር፣ ከአዲሱ ቡድኑ ጋር ስለሚኖረው ቆይታና የቅ/ጊዮርጊስ ተጨዋች እያለ ስለነበረው ቆይታና ክለቡ ከዲሲፕሊን ጥሰት ጋር አያይዞ ጥሎበት ስለነበረው ቅጣት የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጥያቄዎችን አቅርቦለት ተጨዋቹ ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- ለቅ/ጊዮርጊስ ለስድስት ዓመታት ተጫውተህ የክለቡ የቦርድ ሀላፊዎች ባስተላለፉብህ የዲሲፕሊን የቅጣት ውሳኔና የውል ጊዜህንም በመጨረስህ ምክንያት ከክለቡ ጋር ተለያይተሃል፤ ይህ ይሆናል ብለህ ጠብቀህ ነበር?
አስቻለው፡- በፍፁም፤ ምክንያቱም የቅ/ጊዮርጊስና የእኔ የቡድኑ ቆይታዬ ትስስር በአብዛኛው በስኬታማነት የታጀበ እና በዚህ የውድድር ዘመን ላይምባጠፋሁት ጥፋት ተፀፅቼም ይቅርታ ጠይቄም ስለነበር ነው፤ያም ሆኖ ግን የክለባችን ቦርድ ባስተላለፈው የቅጣት ውሳኔ ሊፀና በመቻሉ ትልቁን ክለብ ቅ/ጊዮርጊስን ትቼ ወደ ሌላው ትልቅ ክለብ ፋሲል ከነማ በመግባት ፊርማዬን ላኖር ችያለው፡፡
ሊግ፡- ከቅ/ጊዮርጊስ በመለያየትህ የተከፋህ ይመስላል?
አስቻለው፡- የሚሰማህ ነገርማ ይኖራል፤ ምክንያቱም በዚህ ቡድን ቆይታዬ ብዙ ነገሮችን ከማግኘቴ ባሻገር በብዙ ነገሮች በህይወቴ የተለወጥኩበትም ቤት ስለሆነ ጭምር ነው፤ በህይወትህ ስትኖር አይደለም ለስድስት ዓመታት ከተጫወትክበት ቅ/ጊዮርጊስን ከሚያክል ትልቅ ቡድን መለየት ይቅርና ቤት ተከራይተህ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ስትለቅ እንኳን የሚሰማህ ስሜት አለና የእኔና የቅ/ጊዮርጊስ መለያየት በዚህ መልኩ ይሆናል ብዬ ፈፅሞ አልጠበቅኩም ነበር፡፡
ሊግ፡- የቅ/ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የቦርድ ሀላፊዎች ባስተላለፉብህ የዲሲፕሊን ቅጣት ውሳኔ በመፀፀት ክለቡን ይቅርታ ጠይቀህ ነበር፤ ያን ይቅርታ የጠየቅከው ዳግም ወደ ቡድኑ ይመልሱኛል ብለህ ነበር?
አስቻለው፡- እንደዛ እንኳን ፈፅሞ አላሰብኩም፤የቅ/ጊዮርጊስ ክለብን በወቅቱ ይቅርታ የጠየቅኩት ለቡድኑ ካለኝ ትልቅ ክብር አንፃር ላጠፋሁት ጥፋት ተፀጥቼ እንጂ እነሱ ዳግም ወደ ቡድኑ እንዲመልሱኝ ብዬ አይደለም፡፡
ሊግ፡- በቅ/ጊዮርጊስ ለስድስት ዓመታት ቆየህ፤ እነዛን ጊዜያቶች እንዴት ነው የምትመለከታቸው?
አስቻለው፡- በጣም ጥሩ ጊዜን ነው በአብዛኛው ያሳለፍኩት፤ ብዙ የስኬት ድሎችንም ከክለቡ ጋር ተጎናፅፌያለው፤ በግሌም የሀገሪቱ የኮከብ ተጨዋችነት ሽልማትን ላገኝ ችያለው፤ ከዛ ውጪም በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ደረጃም እስከ 16 ቡድኖች ወደሚገኙበት ስፍራ ላይም ልንደርስ ችለናልና እነዚህ ጊዜያቶች ጣፋጮች ነበሩ፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማን በዝውውር መስኮቱ ተቀላቅለሃል፤ ቡድኑ እንዴት የቅድሚያ ምርጫህ ሆነህ? ወደዚህ ቡድን በማምራትህስ ደስተኛ ነህ?
አስቻለው፡- ፋሲል ከነማን በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ሌሎች የቅድሚያ ጥያቄን ካቀረቡልኝ ቡድኖች በማስቀደም ፊርማዬን ላኖርለት የቻልኩት ቡድኑ እንደ ቅ/ጊዮርጊስ ሁሉ ትልቅ ክለብና የዘመኑም ሻምፒዮና በመሆኑ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ ስለሚወዳደር እኔም በዛ ውድድር ላይ መጫወቱን በጣሙን ስለፈለግኩትና ቡድኑም በኳስ ዘመኔ እያሳለፍኩ ከመጣሁበት ስኬታማ አቋም አንፃር እኔን ይመጥነኛል ብዬም ስላሰብኩ ነው፤ ከዛ ውጪም በዚህ ቡድን ውስጥ የሚገኙት ተጨዋቾችም ብዙዎቹን ስለማውቃቸውና በብሔራዊ ቡድን ውስጥም አብረን የተጫወትን ስለሆነም ቡድኑን የመጀመሪያ ምርጫዬ አድርጌዋለው፡፡ ወደ ፋሲል ከነማ በማምራቴ በጣም ደስተኛ ሆኛለው፤ እናንተን እንዳገለግላችሁ ስለመረጣችሁኝም ኩራት ተሰምቶኛልና ለሰጣችሁኝ ሀላፊነት በጥሩ ብቃት ላገለግላችሁም ዝግጁ ነኝ፡፡
ሊግ፡- በፋሲል ከነማ በሚኖርህ ቆይታ የተሳካ ጊዜያትን የምታሳልፍ ይመስልሃል?
አስቻለው፡- ከፈጣሪ እርዳታ ጋር እርግጠኛ ሆኜ ነው የምነግርህ፤ ጥሩና የተሳካ የውድድር ጊዜን የማሳልፍ ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉና በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎአችሁ ላይ ምን ውጤትን በአዲሱ የውድድር ዘመን የምታስመዘግቡስ ይመስልሃል?
አስቻለው፡- ፋሲል ከነማን ከጥንካሬው እንደተመለከትኩት በአንድ የሊግ ዋንጫ ብቻ መቆም አለበት ብዬ አላስብም፤ አሁን ላይ እኔን ጨምሮ ቡድኑን ይበልጥ የሚያጠናክሩለት ልጆች በዝውውር መስኮቱ ሊፈርሙለት ችለዋል፤ በስብስቡ ቀድመው የሚገኙት ተጨዋቾችም በየሚጫወቱበት ቦታ ላይ ጥሩ ብቃት ያላቸው ስለሆኑም ይሄ ቡድን በአዲሱ የውድድር ዘመን ላይ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ዳግም ያነሳል ብዬም ነው የማስበው፡፡ ሌላው የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎአችንን በተመለከተ ክለቡ ከዚህ ቀደም ብሎ ሁለት ጊዜ በኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ በመሳተፍ ልምድን ያገኘ ስለሆነ አሁን ላይ ከድክመቱ እና ከጥቃቅን ስህተቶቹ ተምሯል፤ ቀጣዩን የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎውን ከዛ በመነሳት የሚያደርገው ስለሆነ ስኬታማ ውጤትን በማምጣት ጥሩና ተከታታይ የውድድር ጉዞን ያደርጋል ብዬ አስባለው፡፡
ሊግ፡- ባሳለፍከው የእግር ኳስ ዘመንህ ደስተኛ ነህ፤ ወደፊትስ ደስተኛ የምትሆን ይመስልሃል?
አስቻለው፡- አዎን፤ የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ቆይታዬ ላይ ብዙ ደስታዎችንና ጥቂት ሀዘኖችን ብቻ ነው ያየሁት፤ ደስታዎቼ እንደ ቡድንም እንደ ግልም በርካታ ናቸው፤ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን አግኝቻለው፤ ኮከብ ተጨዋች ተብዬ ተሸልሜያለው፤ ከዚሁ ቡድን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተመረጡት የዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ አንዱ ሆኜም በመጫወት ሀገሬን ለአፍሪካ ዋንጫ እንድታልፍ አድርጌያለው፤ የተከፋሁበትን ጊዜ ብዬ የማስታውሰው በኢንተርናሽናል ውድድር መድረክ ተሳትፎአችን በደቡብ አፍሪካው ሰንዳውንስ ክለብ አዲስ አበባ ላይ ተሸንፈን ወደ ሩብ ፍፃሜ ሳናልፍ የቀረንበትንና ባልተለመደ መልኩም ክለባችን በተከታታይ ዓመታት ዋንጫን በማጣቱ ነው፡፡ በኳስ ህይወቴ ወደፊትም ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ደስተኛ መሆኔ አይቀርም፤ ለዛ ደግሞ ራሴን ከመቼውም ጊዜ በላይ አዘጋጀዋለው፡፡
ሊግ፡- የአውሮፓ ዋንጫን ለመከታተል ቻልክ?
አስቻለው፡- አዎን፤ የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን ደጋፊ ነበርኩ፤ ጣሊያን ስላሸነፈችም በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ….?
አስቻለው፡- በቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ቆይታዬ በጣም ጣፋጭና ምርጥ የሚባል የስኬታማነት ጊዜን ለማሳለፍ ችያለው፤ ከዚህ ቡድን አሁን ላይ ብለይም በነበረኝ ቆይታ ከጎኔ አብራችሁኝ ለነበራችሁት ደጋፊዎቻችን እንደዚሁም ደግሞ አመራሮቻችን ከፍተኛ ምስጋናን አቀርባለው፤ ከዚህ በኋላ ደግሞ በአዲሱ ቡድኔ ፋሲል ከነማ ውጤታማ ጊዜ ስለሚጠበቅብኝ ያን በተግባር ሜዳ ላይ ለማሳየትና ክለቡንም ውጤታማ ለማድረግ ከፈጣሪ እርዳታ ጋር የሚቻለኝን ሁሉ አደርጋለው፡፡
“ለቅ/ጊዮርጊስ ክብር አለኝ፤ ይቅርታ ጠይቄ የነበረው ከፀፀቴ ለመዳን ብዬ እንጂ እንዲመልሱኝ ብዬ አልነበረም”“ለፋሲል ከነማ ፊርማዬን በቅድሚያ ያኖርኩት ቡድኑ በቻምፒዮንስ ሊጉስለሚሳተፍና ስለሚመጥነኝ ነው” አስቻለው ታመነ /ፋሲል ከነማ/
ተመሳሳይ ጽሁፎች