Google search engine

ለቅ/ጊዮርጊስ ውጤታማና ጥሩ ብቃቴን ለማሳየት ተዘጋጅቻለሁ”ጋዲሳ መብራቴ /ቅ/ጊዮርጊስ/“

በመሸሻ ወልዴ G.BOYS


የቅ/ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ዘንድሮ ላለበት የፕሪምየር ሊግ ውድድር ዝግጅቱን ቢሾፍቱ ከተማ ላይ በሚገኘው የራሱ የልምምድ ስፍራ በመስራት ላይ ይገኛል፤ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ጊዜ በማንሳት የሚታወቀው ይኸው ክለብ ባለፉት ሁለት ዓመታቶች ዋንጫን ማጣቱ ካለው ስምና ዝና አንፃር በብዙዎች ዘንድ አግራሞትን የፈጠረ ሲሆን በደጋፊዎቹና በክለቡ አመራሮች እንደዚሁም ደግሞ በተጨዋቾቹና በኮቺንግ ስታፉ አካባቢም ከፍተኛ የሀዘንና የቁጭት ስሜትን ሊፈጥርባቸው እንደቻለም ታውቋል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የፕሪምየር ሊግ ዝግጅቱን እየሰራ በሚገኝበት የአሁን ሰዓት ላይ የፕሪ ሲዝን ልምምዳቸው ምን እንደሚመስል፣ ባለፉት ጊዜያቶች ስላጡት ዋንጫ እንደዚሁም ደግሞ ዘንድሮ ስለሚያስመዘግቡት ውጤትና ሌሎችንም ጥያቄዎች ጨምረን የክለቡን የተጨዋችነት ቆይታ ለሁለት ዓመታት ውሉን ላራዘመው የቡድኑ ተጨዋች ጋዲሳ መብራቴ ጠይቀነው ምላሹን ሰጥቶናል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊሱ ጋዲሳ መብራቴ በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑ በልደታው ኒያላ እና በሐዋሳ ከተማ ክለብ ቆይታው ጥሩ የሚባል የጨዋታ ጊዜን ያሳለፈ ቢሆንም እንዳለው የኳስ ብቃት ግን በቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ እነዛን መድገም አልቻለም፤ ከእዚህ ዓመት ጀምሮስ ጋዲሳን በምን መልኩ ቀርቦ እናገኘው ይሆን? ለሁሉም ምላሹን ሰጥቷል፤ ቃለ-ምልልሱም እንደሚከተለውም ይቀርባል፡፡
ሊግ፡- ለቅዱስ ጊዮርጊስ በድጋሚ ለመጫወት ውልን አራዝመሃል፤ ለቡድኑ ብዙ ካለመጫወትህ አንፃር ይሄን የውል ማራዘም ጠብቀህ ነበር?
ጋዲሳ፡- አዎን፤ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የመውጣት ሀሳቡ ስላልነበረኝ ውሌን እንደማራዝም እርግጠኛ ነበርኩ፤ ያለበለዚያማ ቡድኑን እለቃለው ብዬ የማስብ ከሆነማ ሰነፍ ተጨዋች ነኝ ማለት ነው፤ ስለዚህም በቡድኑ ውስጥ ያሉትን ቻሌንጆች ሁሉ መቋቋምን ስለፈለግኩ እና ለቅዱስ ጊዮርጊስም ጥሩ ነገርን መስራት ስለፈለግኩ ውሌን ላራዝም ቻልኩ፡፡
ሊግ፡- የቅ/ጊዮርጊስ የፕሪ-ሲዝን ዝግጅት ምን ይመስላል?
ጋዲሳ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ የፕሪ ሲዝን ዝግጅቱን መስራት ከጀመረ አሁን ላይ ሁለተኛ ወሩን ይዟል፤ ጥሩ ልምምድን እየሰራን ይገኛል፤ የመከላከልና የማጥቃት አጨዋወት ላይ በማተኮርም ቡድኑ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ስኬታማ ሊሆን የሚችልበትን ስራንም ነው በመስራት ላይ የምንገኘው፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ በእዚህ ዓመት ምን ውጤት ያመጣል?
ጋዲሳ፡- የፕሪ-ሲዝን ዝግጅታችንን መስራት ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ ሁላችንም ተጨዋቾች አሁን ላይ እያሰብን የምንገኘው በስኬታማነት የሚታወቀውን ቡድናችንን ለሻምፒዮናነት ለማብቃት ነው፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት ሁለት ዓመታቶች ባልተለመደ መልኩ ዋንጫን አጥቷል፤ ይሄ መሆኑ የሚያስቆጭ ነው፤ በእዚህ ዓመት የክለቡን አመራሮችም ሆነ ደጋፊዎቻችንን መካስ ይኖርብናል፤ ለእዚህ ደግሞ አሁን በሜዳ ላይ ከምናደርገው ልምምድ ባሻገር በአካል ብቃቱም በኩል ከሰርቢያ ባለሙያ አስመጥተንም ራሳችንን ጠንካራ ለማድረግ ተዘጋጅናልና፤ ዘንድሮ ሻምፒዮና ሆነን ወደምንታወቅበት የአፍሪካ ሻምፒዮና ውድድር የምንመለስ ይሆናል፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊግ ዋንጫን ባለፉት ሁለት ዓመታት ለማጣቱ የቱን ምክንያት ትጠቅሳለህ?
ጋዲሳ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊግ ዋንጫን ያጣበት ምክንያቶች የተለያዩ ናቸው፤ ከእነዛ መካከልም በሀገሪቱ ውስጥ ካለው የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት አኳያ ወደ ክልል ወጥቶ ማሸነፍ ከባድ የሆነበት ሁኔታ ስላለ ማሸነፍ የሚገባቸውንም የሜዳውም ሆነ የሜዳው ውጪ ጨዋታዎችንም ነጥብ ሊያጣ በመቻሉ ከዛ ውጪም ሁሉም ክለብ እኛ ላይ ጠንክሮ ስለሚመጣና የእኛም አቋም የወረደበት ሁኔታ ስለነበር እነዛ ሊጎዱን ችለዋል፤ በተለይ ደግሞ በአጥቂ ስፍራ ላይ የእነ ጌታነህና ሳላዲን መጎዳት ብዙ ጎል እንዳናስቆጥርም ስላደረገን ይሄ ጭምር ውጤት አሳጥቶናል፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስን በእዚህ ዓመት የተቀላቀሉት ተጨዋቾች ቡድኑን ይመጥናሉ?
ጋዲሳ፡- አዎን፤ ለዛም ነው ቡድናችን ያስመጣቸው፤ ተጨዋቾቹ በነበሩበት ክለብ ውስጥ ጥሩ ይንቀሳቀሱ የነበሩም ናቸው፤ ጊዮርጊስ ደግሞ ተጨዋች ሲያስመጣ በጥናት ላይ ተመርኩዞም ስለሆነ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ተጨዋቾች እኛን ተቀላቅለዋል፡፡
ሊግ፡- የኒያላውና የሐዋሳ ከተማው ምርጡ ተጨዋች ጋዲሳ በቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ ብዙም ጎልቶ አልታየም፤ ለምን? በቀጣይነትስ ጋዲሳን እንዴት እንጠብቀው?
ጋዲሳ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ እኔ መድረስ በምፈልግበት ደረጃ ለመጫወት ያልቻልኩት ለክለቡ አዲስ ተጨዋች ከመሆኔ ጋር ተያይዞና የራስ መተማመንንም አጥቼ ስለነበር በተለይ ደግሞ ሜዳ ላይ ኳስ ሲበላሽብኝ ጊዜ ከደጋፊው ጋር ያልተስማመሁበት ሁኔታም ስለነበር ነው፤ በኳስ እንዲህ ያሉ ነገሮች ያጋጥማሉ፤ ስለዚህም አሁን ላይ ከቡድኑ ጋር በደንብ ተላምጃለው፤ ክለቡ የሚፈልገውንም ነገር አውቄያለው፤ በዝግጅት ወቅቱም ጠንካራ ልምምድን እየሰራሁ በመሆኑ በኒያላና በሐዋሳ የነበረኝን ጥሩ የሆነ የተጨዋችነት ቆይታን በቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥም ጎልቼ በምታይበት መልኩ ስለተዘጋጀው ዘንድሮ ምርጥ ብቃትን አሳያለሁ ብዬ አስባለው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ጋዲሳ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብን የዘንድሮ የውድድር ዘመን ላይ ደጋፊው በጥሩ ቡድንነቱ እና በአሸናፊነቱም እንደሚመጣ ሁሉም ሊጠብቀው ይገባል፤ ከእኛ ጎን የሆኑት እነዚህ ምርጥ ደጋፊዎቻችን በእዚህ ዓመትም በልዩ ድጋፍ ስለሚመጡ እኛም በውጤት እናስደስታቸዋለን፡፡ ከዛ ውጪም እኔ ለክለቡ ውሌን ለሁለት ዓመት ከማራዘሜ አኳያም ክለቡን በደንብ መጥቀምና ለብሔራዊ ቡድንም መመረጥ እፈልጋለውና ለእዚያ ጠንክሬ እየሰራው ነው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P