Google search engine

“ለባህርዳር ከተማ ካለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት ልናስመዘግብለት ተዘጋጅተናል”ሳምሶን ጥላሁን /ባህርዳር ከተማ/

‘‘እዚህ ሀገር ላይ አንድ ሰው አንድ ቦታ ላይ ስትዝናና ካየህ ዓመቱን ሁሉ ሊያወራብህ ይችላል”
የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብን ጨምሮ ቀደም ሲል በነበረው የእግር ኳስ ህይወቱ ለቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ለደደቢት እና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫውቶ አሳልፏል፤ ይሄ ተጨዋች ሳምሶን ጥላሁን ሲሆን ባሳለፍነው የክረምቱ ወራት ደግሞ በተከፈተው የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት አዲሱን ክለቡን ባህር ዳር ከተማን በመቀላቀል የአሁን ሰአት ላይ ለእዚሁ ቡድን በአማካይ ስፍራ ላይ እየተጫወተ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ባለፈው ዓመት የተቀላቀለው የባህርዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ በአዲሱ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በመመራት ሊጉን በጀመረበት በእዚህ ሰዓትም ለቡድኑ ጥሩ ግልጋሎትን መስጠትምጀምሯል፡፡
የባህርዳር ከተማው አዲስ ፈራሚ በተለያዩ ክለቦች የእግር ኳስን ሲጫወት በአብዛኛው የጨዋታ ጊዜያቶቹ ጥሩ እንቅስቃሴን በማሳየት ያሳለፈ ሲሆን ይኸውን የአማካይ ስፍራ ተጨዋች በኳሱ ላይ ቀደም ሲል ስለነበረው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ፣ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በክረምቱ ወራት ስለመለያየቱ፣ ስለአዲሱ ቡድኑ ባህርዳር ከተማ፣ ስለዘንድሮው የፕሪምየር ሊግ ውድድር ተሳትፎአቸው እና ስለቀጣይ ጊዜ የኳስ ህይወቱ የተለያዩ ጥያቄዎችን ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ለተጨዋቹ አቅርቦለት በሚከተለው መልኩ ምላሹን ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ተለያይተህ ወደ ባህርዳር ከተማ ክለብ አምርተሃል፤ክለቡን የለቀቅክበት ዋንኛ ምክንያት ምን ነበር?
ሳምሶን፡- የኢትዮጵያ ቡና ቡድንን በመልቀቅ ወደ ባህርዳር ከተማ ያመራሁበትን ዋንኛ ምክንያት በአጭሩ ልንገርህ እነሱ ከእኔ እኔም ከእነሱ ጋር ስላልተፈላለግን እንደዚሁም ደግሞ የውል ዘመኔም ስለተጠናቀቀ በክረምቱ ወራት የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት የባህር ዳር ከተማ ቡድንን ልቀላቀል ችያለሁ፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናዎች አንተን ከቡድኑ ጋር እንዳትቀጥል ያልፈለጉበት ምክንያት ምን ነበር?
ሳምሶን፡- የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ውስጥ በነበረኝ የተጨዋችነት ቆይታ የውል ዘመኔን ልክ እንዳጠናቀቅኩ ከቡድኑ ጋር እንዳልቀጥል በመፈለግ ወደ ባህርዳር ከተማ ክለብ ያመራሁበትን ምክንያት እንዲህ እንዲህ ነው ብዬ ባልነግርህም የውል ጊዜዬን ጨርሼ ነበርና ከቡድኑ ጋር እንድቀጥል የቀረበልኝ ምንም ነገር ስለሌለ በሰላም ነው ከቡና ጋር ለመለያየት የቻልነው፡፡
ሊግ፡- ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረህ ያለፉት ሁለት አመታት ቆይታህ ቡድኑን በሚገባ አገልግያለሁ ብለህ ታስባለህ?
ሳምሶን፡- ኢትዮጵያ ቡናን አዎን! ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም በቆይታዬ ክለቡን በጥሩ ሁኔታ አገልግያለሁ፤ ምንአልባት ክለቡን በምችለው አቅም አላገለገልኩትም ብዬ የማስበው ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ የእግር ላይ ጉዳትን ባስተናገድኩበት ጊዜ ብቻ ነው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን በሚገባ አላገለገለም የሚሉህም አሉህ፤ ይሄስ ያስማማሃል?
ሳምሶን፡- በፍፁም፤ ከላይ የገለፅኩት ነገር አለ፤ እኔ ቡናን አላገለገልኩትም ብዬ የማስበው ባለፈው ዓመት አጋማሽ አካባቢ ከደቡብ ፖሊስ ጋር በነበረን ጨዋታ ጉዳትን አስተናግጄ ነበር፤ ያ ጉዳትም ጠንከር ያለ ነበርና ከፋሲል ከነማ ጋር የነበረን ጨዋታ ላይ በደንብ ሳይሻለኝ ወደ ሜዳ ገባውና ለክለቤ ስጫወት ጉዳቱ ተባባሰብኝና ከሜዳ ወጣሁ፤ ከእዚህን ጊዜ ጉዳት ጀምሮም ነው ቡናን በምፈልገው መልኩ ያለገለገልኩት እንጂ ላለፉት አንድ ዓመታት ከግማሽ ወራቶች ክለቤን በጥሩ ሁኔታ አገልግዬዋለሁ፤ በተለይ ደግሞ የመጀመሪያ ዓመቴ ላይ ክለቡን ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ለዋንጫው ፉክክር እስኪጫወት ድረስም ልጠቅመው ችያለው፤ እንዲህ በሆነበት ሁኔታ ግን ሁሉንም የቡና ደጋፊዎች የሚወክል ባይሆንም ዓምና ከፋሲል ከነማ ጋር በነበረው ጨዋታ ተጎድቼ ስወጣ በአንድአንድ ደጋፊዎችና በክለቡ አካባቢ ከሜዳ የወጣው ቡድኑ ውጤት ስለሌለው ሳይጎዳ አውቆ ነው የሚሉ ነገሮችም ይናፈሱ ነበርና በዚህ ቅሬታም ነበረኝ፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውስጥ ባለህ የተጨዋችነት ቆይታህ ከብቃትህ አንፃር የምትፈልገው ደረጃ ላይ ተቀምጠሃል?
ሳምሶን፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውስጥ ኳስን ስጫወት ዓላማዬ ብዙና ለትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ቢሆንም፤ በታላላቅ ቡድኖች ውስጥ ተጫውቼ ባሳልፍም የአሁን ሰአት ላይ የምፈልግበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ አልልም፤ የእኔ የኳስ ህልምና ምኞት ወደ ውጪ አገር ሄጄ እስከፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ ላይ ደርሶ መጫወት ነበር፤ ያን ማሳካት ግን አልሆነልኝም፤ በተወሰነ ደረጃ ላይ ግን በኳሱ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ መቻሌ በራሱ በአበረታችነቱ መጥቀስ የምፈልገው፡፡
ሊግ፡- ከኢትዮጵያ ቡና ከተለያየህ በኋላ የባህርዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ እንዴት የቅድሚያ ምርጫህ ሊሆን ቻለ?
ሳምሶን፡- የኢትዮጵያ ቡናን የውል ጊዜዬ እንዳጠናቀቅኩ ወደ ባህርዳር ከተማ ያመራሁት የክለቡ አዲሱ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በመሆኑና እሱ ደግሞ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በብሄራዊ ቡድን ውስጥ በነበረኝ የተጨዋችነት ቆይታዬ እኔን እና የእኔን ችሎታ በሚገባ የሚያውቅ እና በሁሉም ነገርም ችሎታዬን የሚረዳኝ በመሆኑም ነው፤ የእሱ ጥሪ ከባህርዳር ሲመጣልኝ ስራዬን ለመስራትም ብዙ ስለማይከብደኝና ከልጅነቴ አንስቶም ስለሚያውቀኝ እንደዚሁም ደግሞ የባህርዳር ከተማ የመጫወቻ ሜዳም ጥሩ እግር ኳስን ለመጫወት በጣሙን አመቺም ስለሆነ ቡድኑን እና አሰልጣኙን የቅድሚያ ምርጫዬ በማድረግ የክለቡ ተጨዋች ልሆን በቅቻለሁ፡፡
ሊግ፡- ባህርዳር ከተማ በሊጉ ከጅማ አባጅፋር ጋር ከሜዳው ውጪ አቻ ተለያይቶ በሜዳው ደግሞ የአምናውን ሻምፒዮና መቐሌ 70 እንደርታን በማሸነፍ ጨዋታዎቹን ጀምሯል፤ ከአሁኑ ያሳካው ውጤት እና የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ያማረ ነው ማለት ይቻላል?
ሳምሶን፡- አዎን በጣም እንጂ! ያም ሆኖ ግን ገና ብዙ መስተካከል ያለበት ነገር አለ፤ ያ ሲስተካከል ደግሞ ከዚህ የበለጠ ጥሩ ቡድንና ከአምናው የተሻለ ውጤትም የምናስመዘግብ ይሆናል፡፡
ሊግ፡- ባህርዳር ከተማ በሊጉ ጅማሬው ማስተካከል አለበት ብለህ የምታስበው ነገር ምንድነው?
ሳምሶን፡- በፕሪምየር ሊጉ ላይ እየተሳተፈ ያለው ክለባችን አዲስ ቡድን እየገነባ እና እያዋቀረ ከመሆኑ የተነሳ አሁን ላይ ማስተካከል ያለበት የቡድን ስራ ላይ ነው፤ በእያንዳንዱ ግጥሚያዎቻችን ላይ ኳስን በሚገባ ተዋህደን ልንጫወት ይገባናል፡፡ ያንንም በአሰልጣኛችን አማካይነት አሁን ላይ ጠንክረን እየሰራንበት ይገኛልና ከዚህ በመነሳት ጥሩ ቡድንነታችንን በቀጣዮቹ ጨዋታዎች የምንመለከተው ይሆናል፡፡
ሊግ፡- ባህርዳር ከተማ በሊጉ ተሳትፎው ምን አይነት ቅርፅ ያለው ቡድን ይዞ ይቀርባል… በውጤት ደረጃስ የአመቱ ውድድር ሲጠናቀቅ ምን ውጤትን ይዞ ለመፈፀም ተዘጋጅቷል?
ሳምሶን፡- ባህርዳር ከተማ ባለፈው አመት በነበረው የውድድር ተሳትፎው ለዋንጫ የሚፎካከር ቡድንን ሰርቶ ማለፉ ይታወሳል፤ ዘንድሮ ደግሞ በተጨዋቾች ስብስቡ ከአምናው የተሻለ ልጆችን የያዘበት ሁኔታዎች ስለተፈጠሩለት በደረጃው ሰንጠረዥ ካለፈው አመት የተሻለ እና ጥሩ የሚባል ውጤትን ይዞ ለመፈፀም ተዘጋጅቷል፤ የቡድናችንን ቅርፅ በሚመለከት አሰልጣኛችን ጥሩ ችሎታ ያለውና የተካበተ ልምድም ያለው ጥሩ አሰልጣኝ ስለሆነ ኳስን የሚጫወት ቡድንን ነው እየሰራ የሚገኘውና ይህንን ከልምምዳችን አንስቶም እየተመለከትነው ይገኛል፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጅማሬ ጨዋታዎች ቡድናችሁ ላይ የተመለከታችሁት ጠንካራ እና ደካማ ጎን ምንድነው?
ሳምሶን፡- የባህርዳር ከተማ ክለብ በሊጉ ጅማሬ ያለው ጠንካራ ጎን የአምናውን ውጤት የመያዝና የማሸነፍ መንፈሱንም ማስቀጠል መቻሉ ነው፤ ክፍተት ጎኑ ደግሞ ከአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ተሳትፎ ጀምሮ አይተነዋልና ጥቃቅን ችግሮች አሉብን እነዚያንም እናርማቸዋለን፡፡
ሊግ፡- ባህርዳር ከተማ የዓምና ሻምፒዮናውን መቐለ 70 እንደርታን በሜዳውና በደጋፊው ፊት 3ለ2 አሸንፏል፤ ጨዋታው ምን መልክ ነበረው…የድል ውጤቱስ ለእናንተ ይገባ ነበር..?
ሳምሶን፡- የባህርዳር ከተማና የመቐለ 70 እንደርታ የቅዳሜ ዕለት ጨዋታ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ነበር፤ ከዛ ውጪ በመጀመሪያው አጋማሽም ሆነ በሁለተኛው አጋማሽ አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች እኛ የተሻልንም ነበርን፤ እነሱ በሁለተኛው አጋማሽ ላይ የተወሰነውን ደቂቃ ብቻ ጥሩ ሊጫወቱ ሞክረዋልና ግጥሚያውን በአጠቃላይ በድል አድራጊነት ልናጠናቅቅ የቻልው ከእነሱ የተሻለ ቡድንን ይዘን ስለቀረብንና ተደጋጋሚም የጎል እድሎችን ስለፈጠርን ነውና የአሸናፊነቱ ውጤቱ ይገባናል፡፡
ሊግ፡- ሳምሶን ጥላሁን መዝናናት በጣም ያበዛል፤ መዝናናት ማብዛቱም በእግር ኳስ ተጨዋችነቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዳይደርስ በጣም ጎድቶታል የሚሉ አካላቶች አሉና በዚህ ዙሪያ የምትለው ነገር ካለ..?
ሳምሶን፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በምትጫወትበት ሰአት በመዝናኛ ስፍራ ብዙ ሰው የሚያውቅህ ከሆነ አንተ ምንም ነገርን አድርግም አታድርግም ነገሮች ሁሉ ሁሌም ለአንተ አስቸጋሪ ነው የሚሆኑብህ፤ ለምሳሌ አንተ የሰው ልጅ ነህና መዝናናት ያምርሃል፤ እዝናናለሁ ብለህም ወደ መዝናኛ ስፍራ የምታመራበት ጊዜም ይኖርሃል፤ ያኔ ታድያ እዛ መዝናኛ ቦታ ላይ ስትዝናና አንድ ሰው ካየህ ያ ሰው አመቱን ሙሉ ሊያወራብህ ይችላልና ይህን በሚገባ አውቃለው፤ እዚህ ላይ ወደ ራሴ ስመጣልህ እኔ የሰው ልጅ ከመሆኔ የተነሳ አልዝናናም ወይንም ደግሞ አልደሰትም የምልህና የምዋሽህ አይነት ተጨዋች አይደለሁም፤ ሁሉንም ነገር በግልፅ ልንገርህ እኔ መዝናናት ባለብኝ ሰአትና ጊዜ እንደዚሁም ደግሞ እኔን ፈፅሞ በማይጎዳኝ መልኩ እዝናናለሁ፤ ከዛ ውጭ መዝናናት በማብዛቱ በእግር ኳሱ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ለመገኘት አልቻለም የሚለው ነገር በእኔ በኩል ብዙ ተቀባይነት የለውም፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ውጪ እስከአሁን አላገኘክም፤ ይሄን ዋንጫ በድጋሚ ማንሳት አልናፈቀህም..?
ሳምሶን፡- ይናፍቀኛል እንጂ! አዎን፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ እያለሁ ብቻ ነው ይሄን ዋንጫ ያገኘሁት ከደደቢት ጋር እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታዬ ሁሉ የጥሎ ማለፉን ዋንጫ አግኝቼ ነበር፤ የጥሎ ማለፉን ዋንጫ ግን ከሌላ ማንም ቡድን ጋር ያላነሳው ስለሆንኩ አሁን ላይ ይሄን ዋንጫ ከምጫወትበት ክለብ ጋር ማግኘትን በጣሙን አልማለሁ፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ሳምሶን፡- የባህርዳር ከተማ ደጋፊዎች ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ስንጫወት ለቡድናችን የሰጡት ድጋፍ በጣም የአማረ እና በጣምም ደስ የሚል ነው፤ እነሱን ስመለከታቸው ልክ የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች በነበርኩበት ሰዓት ይሰጠን የነበረውን ምርጥ የሆነ ድጋፍን ነው እንዳስታውስም ያደረገኝና በእዚህ መልኩ በቀጣዮቹም ጊዜያቶች ላይ የእነሱ ከእኛ ጎን መሆን መቻል ለምናመጣው ጥሩ ውጤት ይጠቅመናልና ይሄን ሊቀጥሉበት ይገባል፤ በሊጉ ጅማሬ ለሰጡን ጥሩ ድጋፍም ከልብ እናመሰግናቸዋለን፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P