በ15ኛው የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫ ለክለቡ መከላከያ ጥሩ እንቅስቃሴን በማሳየት በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን እያተረፈ ይገኛል፤ በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኑ ካሳደገው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እግር ኳስ ቡድን አንስቶ ወደ ውጪ ሀገር በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ ስዊድን ሀገር ሄዶ የተጫወተውና አሁን ተመልሶ ከመጣ በኋላ ደግሞ ባሳለፍነው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ ለሲዳማ ቡና ክለብ ለመጫወት የቻለው ቢኒያም በላይ ዘንድሮ ያ የሚታወቅበትን ምርጡን ብቃት በማሳየት አዲሱ ክለቡን መከላከያ ለውጤት ለማብቃትና ዳግምም ቀድሞ ወደነበረበት የብሔራዊ ቡድን ተጨዋችነት ለመመረጥ ጠንክሮ እንደሚሰራም ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል፡፡
የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫ ላይ ከአዲስ አበባ ከተማና ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሁለቱን ግጥሚያዎች ሲያደርግ ቡድኑ ለድል የበቃባቸውን ግቦች ከማስቆጠር ባሻገር በልዩ ብቃት የጨዋታዎቹም ኮከብ ተብሎ ለሁለት ጊዜ የአዋርድ የዋንጫ ሽልማትና በእያንዳንዱም ጨዋታ ላይ የ12 ሺ ብር ሽልማትን ከአዘጋጆቹ ሊበረከትለት የቻለውን ይኸውን ተጨዋች ሊግ ስፖርት በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ አናግራው የሰጣት ምላሽ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ሊግ፡- በቅድሚያ ሁለተኛ ልጅ ከባለቤትህ ስለተበረከተልህ እንኳን ደስ አለህ?
ቢኒያም፡- በጣም አመሰግናለው፡፡
ሊግ፡- መቼ ነበር ሁለተኛ ልጅህን ባለቤትህ ያበረከተችልህ?
ቢኒያም፡- በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ የመክፈቻ ጨዋታ ቀን ላይ ነበር ወደ አበበ ቢቂላ ስታድየም እያመራን በነበርንበት ሰዓት በስልክ ተደውሎልኝ ልሰማ የቻልኩት፤ ያኔም በጣም ተደሰትኩ፤ በዕለቱም ግጥሚያ ነበረንና አዳማ ከተማ ላይ ሁለቱን የድል ግቦቼን ሳስቆጠር ደስታዬ የበለጠ እጥፍ ድርብም ሊሆንልኝ ቻለ፡፡
ሊግ፡- ከባለቤትህ ጋር ያለህ የትዳር ህይወት ቆይታ ምን ይመስላል? እሷን በአጭር ቃላትም ግለፃት? ለአዲሱ ልጃችሁስ የወጣው ስም ማን ይባላል?
ቢኒያም፡- ከባለቤቴ ቃልኪዳን ጋር ያለኝ የእስካሁን የትዳር ህይወት ቆይታ በጣም ጣፋጭና የወደድኩትም ነው፤ እዚህ በነበርኩበት ሰዓት ላይም ሆነ በስዊድን ሀገር የተጨዋችነት ቆይታዬ ላይ አብረን ብዙ ጊዜያቶችን አሳልፈናል፤ እሷ የምትገርም አይነት ሚስት ናት፤ ሁሌም ከጎኔ ሆናም የሚያስፈልገኝን ነገሮች ሁሉ ታሟልልኛለች፤ በጣም ጥሩ የሆነች ልጅ ናት፤ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃም ከኳሱ ህይወቴ ጀርባ የእሷ መኖር ትልቅ ጉልበት ሆኖኝና በጣም ጠቅሞኝ የመጣሁበት ሁኔታም ስላለ በእዚህ አጋጣሚ እሷን ልገልፃት በማልችለው ቃላት ሁሉ በፈጣሪ ስም ላመሰግናት እፈልጋለው፤ በጣምም እወዳታለው፡፡ በሲቲ ካፕ የመክፈቻ ቀን ጨዋታ ላይ ለተወለደው ልጃችን እኛ ያወጣንለት ስም ደግሞ ባስለሄል ቢኒያም ይባላል፡፡
ሊግ፡- የመጀመሪያ ልጃችሁስ ስም?
ቢኒያም፡- ኤዶኒያስ ቢኒያም፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳሱ ለተለያዩ ክለቦችና ወደ ስዊድን በማምራትም ለመጫወት ችለሃል፤ ባሳለፍከው የኳስ ህይወትህ ደስተኛ ነህ?
ቢኒያም፡- በአብዛኛው በጣም ደስተኛ ሆኜ ነው ጊዜያቶቹን ያሳለፍኩት፤ ኳስ ተጨዋች ስትሆን ጥሩም ጥሩ ያልሆነም ነገር ሊያጋጥምህ ይችላል፤ ከአንተ የሚጠበቀው ግን የሚመጡትን ነገሮች ሁሉ ጠንካራ ሆነህ በአግባቡ መቀበል ሲኖርብህ ነው፡፡ እኔ ለምሳሌ ወደ ሲዳማ ቡና ዓምና ሁለተኛው ዙር ላይ ስመጣ ምንም እንኳን ቡድኑን ከመውረድ እንዲተርፍ ብናስችለውም ለእኔ ግን እንደ አንድ ተጨዋች ጥሩ ጊዜን ያሳለፍኩበት አልነበረምና ልቆጭ ችያለው፤ ከዛ ቁጭት ተነስቼም ነው አሁን ላይ ለአዲሱ ክለቤ መከላከያ ጥሩ ግልጋሎቴን ለመስጠት እየተዘጋጀው የምገኘው፡፡
ሊግ፡- ወደ ውጪ /ስዊድን/ ወጥተህ ለክለብ ስከንደርቡ፣ ሲራንስካ መጫወትህን ነበር ብዙዎቹ የሚያውቁት፤ ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ግን ወደ ሀገርህ ተመልሰህ ለሲዳማ ቡና ዘንድሮ ደግሞ ለመከላከያ ክለብ እየተጫወትክ ነው የምትገኘው……ከስዊድን እንዴት ተመለስክ?
ቢኒያም፡- ከስዊድን የተመለስኩት ለህዝብ በማይገለፅ ብዙ ነገሮችና ከቤተሰብ ችግርም ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው፡፡
ሊግ፡- በሀገሪቷ የነበረህ የተጨዋችነት ቆይታ ግን ምንድን ነበር የሚመስለው?
ቢኒያም፡- የተጫወትኩበት ክለብ በሁለተኛ ዲቪዥን ደረጃ ያለ ነበር፤ በአብዛኛዎቹ የክለቡ ግጥሚያዎች ላይም በቋሚነት ተሰልፌ ልጫወት ችያለው፤ በተለይ ወደዚህ ሀገር በመጣሁበት ዓመት ላይም ከ30 ጨዋታዎች በ28ቱ ላይ ለመጫወት በመቻሌ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ጎል ማግባትም ችያለው፤ የግብ ኳሶችንም ሰጥቻለው፡፡
ሊግ፡- ከአንተ ተሞክሮ በመነሳት ወደ ውጪ ወጥቶ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ መጫወት ምን ይመስላል? ለወጣቶችና ይሄን እድል ወደፊት ለሚያገኙ እግር ኳስ ተጨዋቾቻችን የምታካፍላቸው ነገር ካለ?
ቢኒያም፡- በቅድሚያ ወደ ውጪ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ ወጥቶ መጫወትን በተመለከተ ነገሮች እንደዚህ ሀገር ቀላል አይደሉም፤ ብዙ ነገሮች አልጋ በአልጋም አይሆኑልህም፤ ሁኔታዎች ሁሉ ከባድም ናቸው፡፡ እዛ ስትሄድ ቤተሰብህን፣ ሀገርህን፣ ባህልህን ትተሀ ነው የምትጓዘው፤ በተለይም ደግሞ እኛ የምናከብራቸው የተለያዩ ዓመት በዓሎችና የእምነትም በዓሎች ስላሉ እነዛ ነገሮች ሁሉ ይናፍቁሃል፤ ከማታውቀው ማህበረሰብም ጋር ነው የምትገናኘውና እነዚህን ነገሮች ሁሉ ልትቋቋማቸው ይገባል፤ በስዊድን ቆይታዬ ለእኔ እነዚህ ነገሮች እንዳሉ ያወቅኩ ቢሆንም ብዙ ነገሮች ባለቤቴ ከአጠገቤ ስለነበረች ሊሸፈኑልኝ ችለዋልና ይሄን ነው የተመለከትኩት፡፡ ሌላው ወደ ውጪ ወጥተው የመጫወት እድልን ለሚያገኙ ተጨዋቾች ምን ትመክራለህ ለተባልኩት ማንኛውም እግር ኳስ ተጨዋች ከለፋና ጠንክሮ ከሰራ እንደዚሁም ደግሞ በአሰልጣኙ የሚሰጠውን ስልጠና በደንብ አውቆና በግሉም ተጨማሪ ነገሮችን እየሰራ ከሄደ ከሁሉም በላይ ደግሞ እነዚህን ነገሮች አሟልቶ ዲስፕሊን ከሆነ ይሄን እድል ማግኘት እንደሚችል መናገር እፈልጋለው፤ እነዚህ ሁኔታዎችም ናቸው ስኬታማ የሚያደርጉህ፤ ስለዚህም ስራዎቹ ላይ በደንብ አድርጋችሁ ልፉባቸው ነው የምላቸው፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዓምና በአጋማሹ ላይ ለሲዳማ ቡና ተጫወትክ፤ ዘንድሮ ደግሞ ለመከላከያ ልትጫወት ዝግጁ ነህ፤ በሲቲ ካፑም ላይ መጫወት ጀምረሃል፤ መከላከያን እንዴት የቅድሚያ ምርጫ አደረግክ?
ቢኒያም፡- ወደ መከላከያ ያመራሁት ይሄ ክለብ የሀገሪቷ ትልቅና ማንኛውም ተጨዋችም ደግሞ ሊጫወትበት የሚፈልግ ቡድን በመሆኑ ነው፤ ለዛም ነው ክለቡን ቀዳሚ ምርጫዬ ያደረግኩት፤ ከእዛ ውጪም የእዚሁ ቡድን አሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌም ከዚህ በፊት በነበረኝ የስልጠና ህይወቴም ለብሔራዊ ቡድን መርጦኝ ችሎታዬን እያሻሻልኩ እንድጓዝ በብዙ ነገሮች የረዳኝና በቡድኑም እንደምፈለግ በነገረኝ ሰዓት ላይ አይኔን ሳላሽ ነበር ለክለቡ ፊርማዬን ላኖር የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- መከላከያ ባደረጋቸው የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ያለፉት ሁለት ጨዋታዎች ጥሩ አጀማመርን አሳይተሃል? ሁለት ጊዜም የሲቲ ካፑ ኮከብ ተጨዋች ተብለሃል፤ በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?
ቢኒያም፡- አዎን እንግዲህ ጥሩ ጅማሬን እያሳየው ነው፤ ለሁለት ጊዜያትም ያህል ክለባችን ድል ባደረገባቸው ጨዋታዎች ላይ የጨዋታዎቹ ኮከብ ለመባልም ችያለው፤ ይሄ ጉዞዬም በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላይ በራሴ ላይ ብዙ ነገሮች እንዲጠበቁብኝ ነገሮችን እያከበደብኝ ነውና ለእዛ ከዚህ በኋላም ጠንክሬ እንድሰራና ለሌሎች የኮከብነት ሽልማቶችም እንድበቃም ትምህርቶችን እየሰጠኝ ነውና የአሁኑን ጉዞዬን ቡድኔን በውጤት ከመጥቀም ጋር አያይዞ ያዝልቅልኝም ነው የምለው፡፡
ሊግ፡- በመከላከያ ክለብ ውስጥ ዘንድሮ ጎልተህ የምትወጣ ይመስልሃል?
ቢኒያም፡- መከላከያ የሀገሪቱ ትልቅ ቡድን ከመሆኑ አኳያ በአሁን ሰዓት ሁላችንም የቡድኑ ተጨዋቾች ትልቅ ሀላፊነት ነው ያለብን፤ እንደ ግል ሳይሆን እንደ ቡድንም ነው ጎልተን ለመውጣት ጥረትን የምናደርገው አሁን ላይ በወጣቶች የተገነባ ጥሩ ቡድን አለን፤ እንደ ቡድን ጎልተህ ስትወጣም ነው የአንተም ጥሩነት የሚታየውና እኔም በዛ መልኩ ነው ለክለቤ ጠቃሚ ግልጋሎቴን ለመስጠት እየተዘጋጀው የምገኘው፡፡
ሊግ፡- የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ውድድርን እንዴት ተመለከትከው? የእዚህ ውድድር ዋንኛ ጉዞና ዓላማችሁስ እስከ ምን ድረስ ነው?
ቢኒያም፡- እስካሁን ይሄ ውድድር ለሁሉም ቡድኖች መልካም ሆኖ ራሳቸውን ለቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በደንብ እያዘጋጁበት ነው የሚገኘው፤ ሁሉም ቡድን ስህተቶቹን አርሞም በመምጣት የሊጉ ውድድር ላይ የተሻለ የሚባል ክለቡን ያሳያል ተብሎም ይጠበቃል፤ ከዛ ውጪም ወጣት ተጨዋቾችም በብዛት እየታዩበትም ነውና ይሄ ውድድር ሊዘጋጅ በመቻሉ አዘጋጆቹን ሳላመሰግን አላልፍም፡፡ በውድድሩ ላይ ስላለን ተሳትፎ ደግሞ ማለት የምፈልገው ይሄ በወጣቶች የተገነባው ቡድናችን ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ለውጦችን እያሳየ ነው፤ ሁለት ጨዋታዎችን አሸንፈንም የግማሽ ፍፃሜውንም ለመቀላቀል ችለናል፤ ከእዚህ በኋላም ያሉንን ጨዋታዎች በመርታት አቋማችንን በደንብ ከመፈተሸ ባሻገር የውድድሩ አሸናፊ ለመሆንም የምንበረታ ይሆናል፡፡
ሊግ፡- የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ቀድሞ ካሰለጠንክ አሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌና የእናንተም ክልል ተወላጅ ከሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ተጨዋችና የአሁኑ የክለባችሁ ረዳት አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ ጋር የተገናኘክበት አጋጣሚ አለና እነሱ ለአንተ እያደረጉልህ ስላለው እገዛ ምን የምትለው ነገር አለ?
ቢኒያም፡- ስለ አሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌ በተደጋጋሚ ጊዜ ብዙ ነገሮችን ብያለው፤ እሱ በወጣት ተጨዋቾች ላይ ካለው እምነት አኳያ እኔንም ከዚህ ቀደም ለብሔራዊ ቡድን መርጦኝ እንድጫወት ያደረገኝና ችሎታዬንም ከላይ እንደገለፅኩት ብዙ እንዳሻሽል ያደረገኝ ነው፤ ዮርዲን በተመለከተ ይህ የቀድሞ ተጨዋች ምንም እንኳን እኔ የተወለድኩበት ክልል ድሬዳዋ ልጅ ቢሆንም እሱ የእኛ ክልል ብቻ ሳይሆን የመላው የኢትዮጵያ ልጅም ነው፤ በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኑ ትልቅ አሻራውን አሳርፎ አልፏል፤ አሁን ደግሞ በአሰልጣኝነት ህይወት ሌላ ታሪክ ሊያስፅፍም ወደ ሙያው ብቅ ብሏልና እስካሁን ባለን የአሰልጣኝነትና የተጨዋችነት ግንኙነታችን እኔ በእግር ኳሱ በጣም ላድግ የምችልበትን ነገር ልክ እንደ አሰልጣኝ ዩሃንስ በሚገባ እየነገረኝና እያበረታታኝ ነው፤ ከእሱም ሆነ ከዩሃንስ ጋርም በመስራቴ እድለኛም ነኝ፤ እነሱ እንደ ወንድምም እንደ አሰልጣኝም ሆነው ነው እኔን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም በመቅረብ ልምምድን እየሰጡን ያሉትና በዚህ የጋራ ትብብር ስራ እየተመካከርን ክለባችንን መከላከያ ለታላቅ ውጤት ለማብቃት ተዘጋጅተናል፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዓምና ተሳትፎ እንደማድረግህ ውድድሩን እንዴት ተመለከትከው?
ቢኒያም፡- በጣም ጠንካራ ውድድር ነበር፤ ብዙ ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችን ልንመለከትበትም ችለናል፤ ይሄ ሊግ እያደገ እንደሚሄድም ያሳየን ፍልሚያም ነውና በጨዋታዎቹ የተደሰትኩበትም ዓመት ነው፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር የኮከብነት ሽልማቶችን ጠቅልሎ ወስዶ ታሪክ ሊሰራ ችሏል፤ በእዚህ ዙሪያስ ምን አልክ?
ቢኒያም፡- ለአቡኪ የውድድር ዓመቱ በጣም ልዩና ምርጥ ነበር፤ ስለ ችሎታው ለህዝቡና ለደጋፊውም በደንብ አድርጎም በሜዳ ላይ በማሳየት ሊያስመሰክርም ችሏል፤ ይሄ ተጨዋች ካሳየው ብቃት በመነሳትም የኢትዮጵያን እግር ኳስ አንድ እርምጃ ወደፊት ከፍ አድርጎ አሳይቷል፤ በቀጣይ ዓመትም ላይ ችሎታውን የበለጠ አሳድጎ ይመጣል የሚል ተስፋም አለኝ፡፡
ሊግ፡- ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ዳግም ስለመቀላቀል ከወዲሁ ምን እያሰብክ ነው?
ቢኒያም፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመመረጥ አሰልጣኞች የራሳቸው የሆነ እይታና አንተን ለመምረጥ የሚፈልጉበት ደግሞ የአጨዋወት መንገድ አላቸውና በቅድሚያ ይሄ ነገር ሊከበርላቸው ይገባል፤ እስካሁን ባለው ሂደት ለአገራችን ጥሩ ነገርን እየሰሩ ነው፤ ለአፍሪካ ዋንጫ እንድናልፍም አድርገዋል፤ መልካም ስራን እየሰሩ ነው፤ በእዚህ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ አሁን ላይ እኔ ኖርኩም አልኖርኩም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ እግር ኳስ ተጨዋች የቡድኑ ደጋፊ ነኝ፤ ሀገሬ ጥሩ ነገር እንዲገጥማትም እፈልጋለውኝ፤ ከዛ በዘለለ ደግሞ የእዚህ ቡድን አባል መሆንም ስለምፈልግ በቀጣይነት ከሚደረገው ምርጫ ጀምሮ ለዋልያዎቹ ለመመረጥ ጠንክሬ ነው የምሰራው፡፡
ሊግ፡- እናጠቃል?
ቢኒያም፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት እስካሁን ለመጣሁበት መንገድ ፈጣሪዬን በቅድሚያ አመሰግናለው፤ ሲቀጥል ቤተሰቦቼና ባለቤቴ አለች እነሱና የመከላከያ የኮቺንግ ስታፍ አባላትን እንደዚሁም ደግሞ የክለቡ አመራሮችንና የቡድን አጋር ጓደኞቼን ለማመስገን እፈልጋለው፡፡