በመሸሻ ወልዴ /GBOYS/
አለምአንተ ካሳ በቅፅል ስሙ ማሪዮ ይባላል፤ ለኢትዮጵያ ቡና በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ አማካኝነት ለሚከተለው የጨዋታ ፍልስፍናም ተመራጭ ተጨዋች ሆኖ ቡድኑን በጥሩ ሁኔታ እያገለገለ ይገኛል፤ ይሄ ተጨዋች ያለውን የሜዳ ላይ ብቃትም ብዙዎች ከወዲሁ እያደነቁለትም ይገኛል፤ ይህን የተጨዋቹን ብቃት አስመልክቶና ከክለቡ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ቡናው 6 ቁጥር ለባሽ እና የመሀል ሜዳ ተጨዋች ከጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጋር ቆይታ አድርጎ ነበርና ቃለ-ምልልሱ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው 5 ጨዋታዎች 6 ነጥብን ይዟል፤ የቡድናችሁን ጉዞ እንዴት ተመለከትከው? ውጤቱስ ይመጥናችኋል?
አለምአንተ፡- የኢትዮጵያ ቡና የሊግ ጉዞ ከጊዜ ወደ ጊዜ ብዙ መሻሽሎችን እያሳየ ሲሆን በእዚሁም ተሳትፎው ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ውስጥ ሁለቱን የሜዳ ውጪ ጨዋታዎቹን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ አንዱን ጨዋታ ደግሞ በሜዳው አሸንፏል፤ ከእዚሁ ጨዋታ በመነሳትም አሁን ላይ እያስመዘገብን ያለነው ውጤት ይመጥነናል ብለን ባናስብም ቡድናችን በአዲስ መልክ እየተገነባ እና አዲስ የጨዋታ ፍልፍስናንም ከመከተላችን አንፃር ውጤቱን ብዙ መጥፎ የምለው አይደለም፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን ሊጉ ላይ ከሌሎች ክለቦች ምን ይለየዋል?
አለምአንተ፡- ኢትዮጵያ ቡናን የሚለየው ይዞት የመጣው የጨዋታ ፍልስፍና ለሃገራችን ፉትቦል አዲስ መሆኑና እኛም የቡድኑ ተጨዋቾች በሌሎች አሰልጣኞች ሰልጥነን ከመምጣታችን አኳያ በእዚሁ ትልቅ እና በብዙዎች ዘንድም ከሚደገፍና በሚወደድ ቡድን ውስጥ ሆነን አዲሱን እና በሃገራችን ብዙም ያልተለመደውን የጨዋታ ታክቲክ በሜዳ ላይ ለመተግበር ከፍተኛ ጥረቶችን እያደረግን ያለንበት ሁኔታ መኖሩ ነው ቡድኑን ለየት እንዲል የሚያደርገው፡፡
ሊግ፡- ወደ ኢትዮጵያ ቡና መጥተህ የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን ልምምድ ስትሰራ ወይንም ደግሞ የጨዋታ ታክቲኩን ስትመለከት ከዚህ ቀደም አንተን ካሰለጠኑህ አሰልጣኞች የተለየብህ ነገር አለ?
አለምአንተ፡- አዎን፤ የኢትዮጵያ ቡናውን አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን በሚያሰራው ስራ ከሌሎች አሰልጣኞች ይለየዋል ብዬ የተመለከትኩት ነገር ቢኖር ብዙ ጊዜ ኳሶችን ከበረኛ አንስቶ በማንሸራሸር ነው ኳሱ እንዲጀመር የሚያደርገው፤ በእሱ የጨዋታ ታክቲክም በረኛ ተጨዋች ነው ተብሎ ነው የሚታመነው፡፡ በረኛ ለቡድኑ 11ኛም ተጨዋች ነው እንጂ በረኛ ነው ብቻ ተብሎም አይታመንም፡፡ በቡድናችን በረኛን እንደተከላካይም ነው የምንጠቀምበት፤ ይሄ ለክለባችንም ሆነ ለአገራችን እግር ኳስ እንደ አዲስ ነገር ነውና ይሄ እሱን ይለየዋል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ከእናንተ ጋር ያለው ግንኙነት ምን መልክ ያለው ነው?
አለምአንተ፡- እሱ ከእኛ ጋር ያለው ግንኙነት የወንድም ያህል ነው፡፡ ስናጠፋ የወንድምና የአባት ያህልም ጠርቶ ይመክረናል፤ ስራችንንም ወደነው እንድንሰራ ያደርገናል፡፡ ተቆጥቶን ወይንም ደግሞ ሰድቦን የሚያሰራን አሰልጣኝ አይነት አይደለምና እሱን በእዚህ በኩል ለየት ያደርገዋል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ አንድ ጨዋታን ብቻ ነው እስካሁን ያሸነፈው፤ ውጤት በምታጡ ሰአት አሰልጣኛችሁ ምንድነው የሚላችሁ?
አለምአንተ፡- ኢትዮጵያ ቡና የውጤት ማጣት በሚገጥመው ሰአት አሰልጣኙ ሁሌም የሚመክረን ጠንካራ ሆነን እሱ የሚፈልገውን ነገር እንድናደርግለት ብቻ ነው፤ በተለይ ደግሞ የሁልጊዜ ሃሳቡ በኳስ የሚከብደው ጎል ማስቆጠር ሳይሆን ጎል ጋር መድረስም ነው በሚል ይነገረናልና ይሄን ጎል ጋር የመድረስ ችግራችንን ቀርፈን ጎሎችን እስከማስቆጠር ደርሰናል፡፡ ይሄ ጎል ማስቆጠር የሚመጣውም በጊዜ ሂደት እንጂ በአንዴ ተቻኩለን እንዳልሆነም የነገረን ነገር ስላለ እሱ የሚፈልገውን እንጂ የማይፈልገውን ነገር እንዳናደርግም በቂ ትምህርት ሰጥቶናል፤ ከዛ ውጭም አሰልጣኙ ጫናንም አያሳድርብንም፤ እንደዚሁም ሃላፊነትንም ሙሉ ለሙሉ ወስዶልንም ነው እንድንጫወት እያደረገን የሚገኘውና በእዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን መጫወታችን እኛን እድለኛ ያደርገናል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና አሁን ላይ የያዘውን የጨዋታ እንቅስቃሴ የሚደገፍ አለ፤ በመንታ መንገድም ላይ ቆሞ የሚመጣውን ነገር የሚጠብቅ አለ፤ ከዛ ውጪ ደግሞ ጨዋታውን የማይደግፍም አለ፤ እንደ ቡድኑ ተጨዋችነትህ ከእዚህ በመነሳት ምን የምትለው ነገር ይኖርሃል? አሁን የያዛችሁት ይሄ የጨዋታ ታክቲክስ ለውጥ ይኖረዋል ብለህ ታስባለህ?
አለምአንተ፡- በፍፁም፤ ኢትዮጵያ ቡና አሁን ላይ የያዘው የጨዋታ ታክቲክ የአሰልጣኙ የራሱ ፍልስፍና እስከሆነ ድረስ ወደፊትም ቢሆን ይህን ታክቲክ በተጠናከረ መልኩ አስቀጥሎ እንደሚጓዝ በጣም እርግጠኛ ነኝ፤ የቡድናችንን አጨዋወት በተመለከተ ይህንን የጨዋታ ታክቲክ ይቃወሙ የነበሩ ደጋፊዎቻችን አሁን ላይ ወደ እኛ መጥተዋል፤ ምክንያቱም ቡድኑ ጎል አያገባም ነበር የሚሉትና አሁን ላይ ግን ጎል ማግባት ጀምረናል፡፡ የኳሱ እንቅስቃሴም ጥሩ ነው፤ ደጋፊዎቹ የሚፈልጉትም ኳስ የሚጫወተውን ቡናን እንጂ ኳስ የሚጠልዘውን ቡናን አልነበረምና ኳስን እየተጫወትን፣ ጎል ጋር እየደረስን፤ ጎል ማግባትም ስለጀመርን በጊዜ ሂደት ደግሞ የሚቃወሙን ደጋፊዎች ወደ እኛ ዘንድ ይመጣሉ ብለንም እያሰብን ነው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው የሰሞኑ ጨዋታዎች ሐዋሳ ከተማን በሰፊ ግብ ሲያሸንፍ ከድሬዳዋ ከተማ አቻ ተለይይቷል፤ እነዚህ ጨዋታዎች ምን መልክ ነበራቸው?
አለምአንተ፡- ሐዋሳ ከተማን በቅርቡ ድል ያደረግንበት ጨዋታ ሁላችንም በአሰልጣኙ የተሰጠንን ታክቲክ እሱ እንደሚፈልገው ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ባናደርግለትም በገባን መልኩ እና ልክ ግን ታክቲኩን ለመተግበር ሞክረን ጨዋታውን ለማሸነፍ ችለናል፤ ሐዋሳን ስናሸንፍ ሌላው የጠቀመን ነገር ቢኖር በሜዳ ላይ የነበረን ከፍተኛ የማሸነፍ ተነሳሽነት ነው፤ ያ በጣም ሊረዳን ችሏል፤ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር የነበረን ጨዋታ ደግሞ የኳስ ብልጫን እኛ በጣም ወስደንባቸዋል፤ እነሱ ተከላካይም አብዝተው ነበር ሲጫወቱ የነበረው፡፡ የአየር ንብረቱ ሞቃት በመሆኑ ለእኛ የተወሰነ ሰዓት ላይ ትንሽ ከብዶን ነበር፤ በጨዋታ እንቅስቃሴው በአጠቃላይ እኛ ከእነሱ የተሻልን ሆነን ብንጫወትም ያገኘናቸውን የጎል እድሎች ባለመጠቀማችን ግን 3 ነጥብ ማግኘት እያለብን ያንን ሳናሳካ ቀርተናልና ውጤቱ ፈፅሞ የማይገባን ሆኖ ነው ያገኘነው፡፡
ሊግ፡- ሀድያ ሆሳዕናን በሊጉ የምትፋለሙበትን የዛሬው ጨዋታ እንዴት እየጠበቃችሁት ነው?
አለምአንተ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊነታችን ከእዚህ በኋላ በአዲስ አበባ ስታድየም ላይ የሚደረጉ የቱንም ጨዋታዎች ፈፅሞ መሸነፍ እንደሌለብን ሁላችንም የቡድኑ ተጨዋቾች ቁርጠኛ እስከመሆን ደረጃ ላይ በመድረስ ከስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ በተለይ በዚህ ድንቅ ደጋፊ ፊት መሸነፍንም ፈፅሞ አንፈልግም፡፡ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር በሚኖረን ጨዋታ እነሱ ምንም እንኳን በደረጃው ሰንጠረዥ እታች ደረጃ ላይ ቢገኙም ሲጫወቱ ባንመለከታቸውም ከሰማናቸው ነገሮች በመነሳት ጠንካራ ቡድን እንደሆኑ በሚገባ ስላወቅን ይሄን ጨዋታ የምናደርገው ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ነው፤ ያ ስለሆነም በዛሬው ጨዋታ ሀድያን ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ታጅበን በማሸነፍ ደረጃችንን ወደ ላይ ከፍ እናደርጋለን፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና ውስጥ