Google search engine

“ለኢትዮጵያ ቡና የተለየ ተጨዋች አይደለውም፤ ለክለቡ አቅሜን ሳልሰስት ሁሉን ነገሬን እሰጠዋለውኝ” አቤል ከበደ /ኢትዮጵያ ቡና/

በመሸሻ ወልዴ

የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ ጥሩ እንቅስቃሴ ከሚያሳዩ ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነው አቤል ከበደ በሊጉ ውድድር ባህርዳር ላይ በተደረገው ጨዋታ በቀይ ካርድ መውጣቱን ተከትሎ የአራት ጨዋታ እገዳ ተጥሎበት እንደነበር ይታወቃል፤ ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ስታድየም በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ለቡድኑ ጥሩ ሲጫወት የተመለከትነው ይኸው ተጨዋች በአሁን ሰዓት ከቅጣት የተመለሰ በመሆኑ እና ባለፉት ጥቂት የማይባሉ ጨዋታዎች ላይ ለቡድኑ የሚጠበቅበትን ግልጋሎት ያልሰጠ በመሆኑ በቅጣቱ ዙሪያ እና ስለቡድናቸው ወቅታዊ አቋም እንደዚሁም ስለ ቀጣይ ጊዜ ጉዞአቸው አውርተነው ምላሹን ሰጥቶናል፤ ተጨዋቹ ከጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጋር ያደረገው ቆይታም የሚከተለውን ይመስላል፤ ተከታተሉት፡፡


ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ጥሩ እንቅስቃሴን እያሳየህ በነበርክበት ሰዓት ቀይ ካርድ ተመልክተህ ለአራት ጨዋታዎች ያህል ለመሰለፍ አልቻልክም ነበር፤ በዚህ የተፈጠረብህ ስሜት ምንድን ነበር?
አቤል፡- ለኢትዮጵያ ቡና ስጫወት በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቼ ክለቤን ለአራት ጨዋታዎች ያህል ለማገልገል አለመቻሌ ከፍተኛ የሆነ የቁጭት ስሜት ነው የተሰማኝ፤ በተለይ ደግሞ በሸገር ደርቢው ጨዋታ መጫወትን ፈልጌ ስላልተሳካልኝም በጣሙን ቆጭቶኛል፤ ያም ሆኖ ግን ከዚህ ቅጣት እያስቆጨኝም ቢሆን ሁለት የተማርኳቸው ጥሩ ጥሩ ነገሮች አሉ፤ የመጀመሪያው የቡድኔን ጨዋታዎች ከውጪ ሆኜ ስመለከት የራሴ ብቃት በምን ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው የሚለውን እና ከሌሎች ተጨዋቾች ጋርስ ስነፃፀር እንዴት ነኝ የሚለውን አውቄበታለው፤ ሌላው ደግሞ ምነው በዚህ ጨዋታ ላይ ኖሬ ቢሆንና ቡድኔን በጠቀምኩም በማለት ያሰብኩበትም ሁኔታ ስላለ እንደአጠቃላይ ግን ከዚህ በኋላ በቀይ ካርድ ከሜዳ በፍፁም መውጣት እንደሌለብኝ ነው ልረዳ የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- አንተ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከወጣህ በኋላ ኢትዮጵያ ቡና ባደረጋቸው አራት ያህል ጨዋታዎች አጥጋቢ የሚባል ውጤትን ለማምጣት አልቻለም፤ በዚህ ላይስ ምን ስሜት አለህ?
አቤል፡- በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣት መቻል ቡድንህን በምትፈልገው መልኩ እንዳታገለግለው እና እንዳትጠቅመው ስለሚያደርግህ ሁሌም ቢሆን በጣም ያማል፤ ለኢትዮጵያ ቡና እኔ ባህርዳር ላይ በተደረገው ጨዋታ በቀይ ካርድ ወጥቼ ቅጣትን ካስተናገድኩበት ጊዜ ጀምሮም ሆነ አቡበከር ናስር ደግሞ ጎንደር ላይ ከፋሲል ከነማ ጋር ስንጫወት ግጥሚያው እንደተጀመረ በጉዳት መውጣቱ ቡድናችንን በውጤት ደረጃ የጎዳው ነገር በመኖሩ ያ እኔን በጣም አስቆጭቶኛል፤ በፊት አጥቂነት ከመጫወታችን አንፃር የሁለታችን አለመኖር ክለቡን ጎድቶታል፤ ያን ስል ግን እኛን በተለየ መልኩ ለማስቀመጥ እንዳልሆነ ሁሉም ሊረዳኝ ይገባል፤ ምክንያቱም ቡና ውስጥ ሲጀመር የተለየ የሚባል ተጨዋች የለምና፤ እኛ ጋር በንፅፅር አሰልጣኙ ያመነበትን ተጨዋች ስለሚያሰለፍ እንጂ ሁሉም ተጨዋች እኩል ነው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ውጤትን እያጣ ነው፤ የወደፊት ጉዞው አስፈሪ ነው ማለት ይቻላል?
አቤል፡- በፍፁም፤ ምንም አስፈሪ ነገር የለም፤ ቡድናችንን ተመልክተከው እንደሆነ ከአንድ ቡድን ጋር ስንጫወት ያ ቡድን ባለው እና ጥሩ በሚለው ብቃቱ አይደለም እኛን እያሸነፈን የሚገኘው፤ በአብዛኛዎቹ ጨዋታዎች እኛ የተሻልን ሆነን በምንሰራቸው ጥቃቅን ስህተቶች ነው ውጤትን የምናጣውና የቡና ቀጣይ ጉዞው አይደለም ሊያስፈራ አሁን ከያዝነው የተሻለ ነገርን ነው በዚህ ዓመት የምጠብቀው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ለአንድ ቡድን ከሜዳ ወጥቶ ማሸነፍ ከባድ ሆኗል እየተባለ ነው፤ ይሄ አባባል ያስማማሃል?
አቤል፡- እኛም ሆንን አሰልጣኛችን ይሄን በፍፁም አናምንበትም፤ አሰልጣኛችንም በተደጋጋሚ የሚነግርንም ክልል ሄዶ ማሸነፍ ይቻላል በሚል ነው፤ ምክንያቱም ወደ ክልል ሄደን የምናደርጋቸውን አብዛኛዎቹን ጨዋታዎች እንደተመለከትናቸው ጥሩ ተንቀሳቀስንበት እና ጥሩም ጎል የማስቆጠር እድሎችን እያገኘን ነው፤ ያም ሆኖ ግን ተጋጣሚዎቻችን አንድ ጎል ካገቡ በኋላ የሰው ቁጥር አብዝተው ስለሚከላከሉ እና በራሳችን ጥቃቅን ችግርም ነው ውጤትን እያጣን ያለውና ይሄን አስተካክለን ውጤታማውን ቡና በቀጣዮቹ ጊዜያት ማሳየት ነው የምንፈልገው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በአዳማ ከተማ ማንም ባልገመተው እና ባልጠበቀው መልኩ 3-0 ተሸንፏል፤ ስለዚያ ጨዋታ ምን ማለት ይቻላል?
አቤል፡- በናዝሬቱ የአበበ ቢቂላ ስታድየም በአዳማ ከተማ የደረሰብን የ3-0 ሽንፈትን እኔ የምገልፀው ክለባችን ከወልዋሎ አዲግራቱ ጨዋታ ጀምሮና የሸገር ደርቢውን ጨዋታ አካቶ ተደጋጋሚ ግጥሚያን በቀናቶች ልዩነት በማድረጉ እና ከጉዞውም አኳያ በእያንዳንዱ ተጨዋች ላይ የመዳከም ሁኔታ ሊፈጠር በመቻሉ ነው፤ በሳምንት ሶስቴ ያለበቂ እረፍት መጫወት ከባድና ጫና ያለውም ስለሆነ ቡና በእዚህ መልኩ በአዳማ ሊሸነፍ ችሏል፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ተሰልፈህ ስትጫወት ጥሩ የተንቀሳቀስክበት የአዲስ አበባ ስታድየም የሚደረገው ቀጣይ ጨዋታ ላይ ወደ ሜዳ የምትመለስበት ሁኔታ ይፈጠርልሃል ተብሎ ይጠበቃል፤ ሜዳው ናፍቆሃል?
አቤል፡- አዎን፤ በጣም ነው የናፈቀኝ፤ ምክንያቱም ቡድናችን አሁን ላይ ውጤት እያጣ ነውና ይሄን ክለብ ከቡድን አጋር ጓደኞቼ ጋር ያለኝን ብቃት አሻሽዬ በመቅረብ በውጤት ቡድኑን ልታደገውም ይገባል፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና አንተ የተለየ ተጨዋች ነህ?
አቤል፡- በእዚህን ሰዓት እና ወቅት እኔ እንዲህ አይነት ተጨዋች ነኝ ብዬ አላስብምም፤ አላወራምም፤ ቡና ውስጥ እንደተመለከትከው በእኔም ቦታ የሚጫወተው ሀብታሙ ጥሩ አቅምና ብቃት ያለው ተጨዋች ነው፤ አንድአንድ ጊዜ ኳስ ችሎታ ብቻ ሳይሆን እድልም ስለሆነ እኔ፣ አቡኪ እንደዚሁም ደግሞ ማናችንም ተጨዋቾች ወደሜዳ ብንገባ ሽንፈት ሊመጣም ይችላልና ያን ነገር ነው ማየት፤ ስለዚህም አሁንም ደግሜ መናገር የምፈልገው እኔ ራሴን የተለየ ተጨዋች አድርጌ የማልቆጥር ተጨዋች እንደሆንኩ ነው፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና በምታደርጋቸው የቀጣይ ጊዜ በርካታ ጨዋታዎች ችሎታህን ያለስስት ትሰጣለህ?
አቤል፡- ለኢትዮጵያ ቡና በምጫወትባቸው ጨዋታዎች ሁሌም ነው አቅሜን ሳልሰስት መጫወትን የምፈልገው፤ በሜዳም ሆነ ከሜዳችን ውጪ በምናደርጋቸው ጨዋታዎችም ሁሉ ክለቤን ውጤታማ ማድረግ ቀዳሚው ግቤና ዓላማዬም ነው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና ውጤት በሚያጣ ሰዓት በመልበሻ ክፍል ውስጥም ሆነ ደጋፊውን ስትመለከቱ ምን አይነት ስሜት ነው የሚሰማችሁ?
አቤል፡- ቡድናችን ውጤት በሚያጣ ሰዓት የእኛ እና የደጋፊው ስሜት አንድ አይደለም፤ እኛ ኳሱ እንጀራችን እስከሆነ ድረስ በጣም እንናደዳለን፤ ደጋፊውም ውጤትን ይፈልጋልና እነሱን ለማስደሰት ነው የምንፈልገው፤ ያኔ እኛ አዲስ ይዘን በመጣነው አጨዋወታችን ውጤት ለማምጣት ምንድን ነው ድክመታችን ብለን ነው ራሳችንን የምናርመው እና እንደተጨዋችነታችን የሚሰማን የራሳችን ስሜት አለ፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና እያደረጋቸው ባሉት የሊጉ ጨዋታዎች እንደድክመት እና ክፍተት የምትጠቅሰው እና ማሻሻልስ የምትፈልጉት ነገር ምንድን ነው?
አቤል፡- ማሻሻል አለብን ብዬ የማስበው ኳስን ከበረኛ አስጀምረንና መስርተን ለመጫወት ካስብን በኋላ አወጣጥ ላይ የምንቸገርበት ነገር አለ፤ ከዛ ውጪ መሀሉ ላይ በጣም ጥሩ ብንሆንም አልፎ አልፎ ኳስን በማዘጋጀት ላይና ፊት ላይም ያለነው ኳስ እንዲደርስ የመጠየቅ እና የማስገደድ ስራ ላይ ተግተን ልንሰራ ይገባል፡፡

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና ከወልቂጤ ከተማ እና ቀጣዩንም ጨዋታ በሜዳው ያደርጋል፤ ምን ውጤትን ከቡድናችሁ ትጠብቃለህ?
አቤል፡- ከወልቂጤ ከተማ ጋር የምናደርገው ጨዋታ እነሱ ወደ አሸናፊነት መንፈሱ ተመልሰው የመጡና እየተሻሻሉ ያሉ ስለሆኑ እኛም በሜዳችን እና በደጋፊዎቻችን የምናደርገው በመሆኑ ጥሩ ጨዋታ ይታያል፤ ያም ሆኖ ግን እስካሁን ቡድናችን በሜዳው ላይ ጨዋታ በጣም የተሻለ ሆኖ የቀረበት አጋጣሚ ስላለ ጨዋታውን ድል ያደርጋል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P