Google search engine

“ለኢትዮጵያ ይሰጥ የነበረው ዝቅተኛ ግምት አሁን ላይ ስለቀረ እኛም ወደ ዓለም ዋንጫው ለማለፍ ነው የምንጫወተው””የዓለም ዋንጫው የማጣሪያ ፉክክሩ ውስጥ ለመቆየት ዛሬ ደቡብ አፍሪካን ማሸነፍ ግድ ይለናል” አስቻለው ታመነ

2022 የኳታር ዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ

ኢትዮጵያ Vs ደቡብ አፍሪካ

ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 29/2014 /

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን /ዋልያዎቹ/ ኳታር ለምታዘጋጀው የ2022ቱ የዓለም ዋንጫ ከአፍሪካ ዞን ለማለፍ በምድብ 7 ከጋና፣ ከደቡብ አፍሪካና ከዝምቧቡዌ ተደልድላ የማጣሪያ ጨዋታዎቿን እያደረገች ሲሆን በእስካሁኑ ፍልሚያዋም አክራ ላይ በጋና 1-0 ስትሸነፍ በባህርዳር ስታድየም ባደረገችው የሜዳ ላይ ግጥሚያዋ ደግሞ ዝምቧቡዌን በአስቻለው ታመነ ብቸኛ ግብ 1-0 በማሸነፍ ቀጣይ የዛሬው ዕለት ጨዋታዋን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች፡፡

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመሩት ዋልያዎቹ ዛሬ የሚፋለሙት ከደቡብ አፍሪካ /ባፋና ባፋናዎቹ/ ጋር ሲሆን ይህ ግጥሚያም በሁለቱ ሀገራት ዘንድ ከፍተኛ ትኩረትም ተሰጥቶታል፤ ባፋና ባፋናዎች በዚህ የማጣሪያ ጨዋታ እስካሁን ከዝምቧቡዌ ጋር ተጫውተው 1-1 ሲለያዩ ጋናን /ብላክስታሮችን/ ደግሞ 1-0 በማሸነፍ ምድቡን እየመሩት ይገኛል፡፡ የእዚህ ምድብ ሌላኛው ጨዋታም በዛሬው ዕለት በጋናና በዝምቧቡዌ ብሔራዊ ቡድኖች መካከልም ይካሄዳል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዚሁ የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታው ላይ ዛሬ ደቡብ አፍሪካን ሲፋለም ቡድኑ ጥሩ ዝግጅት ማድረጉን የቡድኑ አባላቶች እየተናገሩ ሲሆን ከእነዛ ተጨዋቾች መካከልም በቅርቡ ጋብቻውን የፈፀመው የተከላካይ ስፍራ ተጨዋቹ አስቻለው ታመነም “አሁን ላይ ጥሩና ተስፋ ሰጪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ማሳየታችን እኛን እንደ ቀድሞ ዝቅተኛ ግምት እንዳይሰጠን አድርጎናል፤ የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታውን የምናደርገውም እንደከዚህ ቀደሙ ለተሳትፎ ብቻ ሳይሆን ለውድድሩ ለማለፍም ነው” ሲል አስተያየቱን ከሊግ ስፖርት ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ባደረገው ቆይታም ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተከላካይ ስፍራ ተጨዋቹን አስቻለው ታመነን ሊግ ስፖርት ከዓለም ዋንጫው የማጣሪያ ጨዋታው ጋር በተያያዘና በቅርቡ ስለፈፀመው ጋብቻ አናግራው የሰጣት ምላሽ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

ሊግ፡- ቅድሚያ ከጋብቻ ስነ-ስርዓትህ እንነሳና ምን መልክ ነበረው? ሚዜዎችህስ እነማን ናቸው?

አስቻለው፡- የጋብቻ ስነ-ስርዓቴ በቅርቡ ሲፈፀም በሚዜዎች ታጅቦ የተደረገ አልነበረም፤ በመስክ የፎቶ መነሳት መልኩ የተካሄደ የፕሮግራም ክንውንም ነበር፤ በዕለቱ ደስ ብሎኝ ነው ጋብቻዬን ያከናወንኩት፤ ወደፊት ደግሞ ዋናው የሰርግ ፕሮግራሜ ይኖራል ብዬም አስባለው፡፡

ሊግ፡- ጋብቻን የፈፀምክላት ባለቤትህ ማን ትባላለች? ትውውቃቻሁ ለምን ያህል ጊዜስ የዘለቀ ነው? እሷ እንዴትስ ትገለፃለች?

አስቻለው፡- ባለቤቴ እየሩሳሌም ዳርሰማ ነው የምትባለው፤ ትውውቃችንም ለሁለት ዓመት ከስድስት ወራት ያህል ጊዜ የዘለቀ ነው፤ እሷን ስገልፃት በጣም ጥሩና ትሁት እኔን ደግሞ በብዙ ነገር እየለወጠችኝ ያለች መልካም ባህሪህ ያላት ናት፤ እኔም የምወዳትን ልጅ በማግባቴ ደስ ብሎኛል፤ ለእዚህም ፈጣሪዬን አመሰግነዋለው፡፡

ሊግ፡- አሁን ወደ ትዳር ውስጥ ገብተካልና ጣዕሙን እንዴት አገኘከው?

አስቻለው፡- ወደዚህ ህይወት ውስጥ መግባት በጣም ነው ደስ የሚለው፤ ከአሁኑ ብዙ ነገሮችን እየተማርኩበትም ነው፤ በተለይም ደግሞ ስፖርተኛ ስትሆን ራስህን ከአጓጉል ነገሮች ለመሰብሰብና ከብዙ ነገሮችም እንድትቆጠብም ያደርግሃልና አሁን ደስ የሚለው ነገር ስፖርተኛው ሁሉ ወደ ትዳር ዓለሙ ውስጥ እየገቡ መሆናቸው ነውና ያላገባችሁ ካላችሁ እኔም ጣዕሙን እያየሁት ነውና አግቡም ነው የምለው፡፡

ሊግ፡- ባለቤትህን ግን የት አግኝተህ ነበር የጠበስካት? በቅድሚያስ ምኗን አይተህ ወደድክላት?

አስቻለው፡- የእኔዋን ልጅቷን አግኝቼ ፍቅረኛዬና ባለቤቴ ላደርጋት የቻልኩት ነዋሪነቷን ባደረገችበት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው፤ ምንም የሚጠላ ነገር ስለሌላትም ነው ሁሉን ነገሯን ወድጄም የግራ ጎኔ ላደርጋት የቻልኩት፤ በተለይ እሷ ለእኔ ያላት አመለካከት በጣም ጥሩ ስለሆነም ልትማርከኝም ችላለች፡፡

ሊግ፡- እግር ኳስን ትወዳለች?

አስቻለው፡- እሷ ስለ እኔ እግር ኳስ ተጨዋች መሆን እንጂ ስለ ኳስ ብዙም አታውቅም ነበር፤ ካለፈው ዓመት አንስቶ ግን ጨዋታዬን በዲ.ኤስ.ቲቪ እየተከታተለች ስለ ኳስ ጥሩ ግንዛቤን እያገኘች ነች፤ በርታም እያለችኝ ነው፡፡

ሊግ፡- አሁን ደግሞ ወደ ዋናው ጉዳያችን እናምራ ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታችሁን ጀምራችኋል፤ ዛሬም ደቡብ አፍሪካን በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም ትፋለማላችሁ፤ እያደረጋችሁት ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል? ከጨዋታውስ ምን ውጤትን እንጠብቅ?

አስቻለው፡- የደቡብ አፍሪካ አቻችንን ለምንፋለምበት የዓለም ዋንጫው የማጣሪያ ጨዋታ እኛ እያደረግን ያለነው ዝግጅት በጣም ጥሩ ነው፤ ተጋጣሚያችንም  ጠንካራ ከመሆኑ አኳያም ከእነሱ ወቅታዊ ብቃት ተነስተንም ነው እየተለማመድን የምንገኘው፤ በሜዳ ላይ ከምንሰራው ጠንካራ ልምምድ ባሻገር ያለን የቡድን መንፈስ በጣም ጥሩም ስለሆነ ዛሬ በሚኖረን የሜዳችን ላይ ጨዋታ ደቡብ አፍሪካን ለማሸነፍ ዝግጁ ነን፡፡

ሊግ፡- በዓለም ዋንጫው የማጣሪያ ጨዋታ ዛሬ ስለምትገጥሟት ደቡብ አፍሪካ ወቅታዊ አቋም ምን  ያወቃችሁት ነገር አለ?

አስቻለው፡- ባፋና ባፋናዎች አሁን ላይ ስላላቸው ወቅታዊ አቋም እኛ የቡድኑ ተጨዋቾች በደንብ ያወቅነው ነገር ባይኖርም አሰልጣኞቻችን ግን ስለእነሱ ካዩትና ከተመለከቱት ነገር ተነስተው ነው ጥሩ ልምምድን እየሰጡን ያሉት፤ ስለ እነሱ ጠንካራና ደካማ ጎን ተነግሮንም ነው እየተዘጋጀን የምንገኘው፤ የእነሱን ጨዋታ ደግሞ ዛሬ ወይንም ደግሞ ነገ እኛም ተጨዋቾች የምንመለከትበት ሁኔታም ስለሚኖር ለግጥሚያው በቂ ትኩረት በመስጠት ነው ወደ ሜዳ የምንገባው፡፡  /ቃለ-ምልልሱን ያደረግነው ሐሙስ ዕለት ነበር/፡፡

ሊግ፡- የዋልያዎቹን የአሁን ስብስብ በምን መልኩ ነው የምትገልፀው?

አስቻለው፡- ይሄ ቡድን ላለፉት አንድ ዓመታት አብሮ የቆየ ስለሆነ ጥሩ ነገርን በሜዳ ላይም ከሜዳ ውጪም እያስመለከተን ነው የሚገኘው፤ በእንቅስቃሴው በኩል መሻሻሎች እየታዩ ነው፤ የአሰልጣኙን ታክቲክ በመተግበሩ በኩልም መልካም ነገሮች አሉ፤ ሌላው ቡድኑ ሳይፈርስ አብሮ እንዲጓዝ የተደረገበት ሁኔታም በእያንዳንዱ ተጨዋች ዘንድ የቤተሰብ ያህል ግንኙነት እንዲመሰረትም ምክንያት ስለሆነው ይሄ ለቡድኑ ውጤታማነት እየጠቀመው ነው የሚገኘው፡፡

ሊግ፡- እኛ የተደለደልንበትን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ምድብን አሁን ላይ ስትመለከተው ምን ማለት ቻልክ?

አስቻለው፡- ምድባችን በጣም ጠንካራ እንደሆነ ነው የተመለከትኩት፤ ከዚህ ቀደም ለእኛ ኢትዮጵያኖች ዝቅተኛ ግምት ነበር የሚሰጠን፤ አሁን ላይ ግን ያ ሁኔታ ተቀይሯል፤ ሀገራቶች ለእኛ ከፍተኛ ግምት እየሰጡን መጥተዋል፤ ከጋና ጋር በነበረን ጨዋታ እኛ መሸነፍ አልነበረብንም፤ ጥሩ መጫወታችንም ነው ብዙዎቹ ለእኛ ጥሩ ግምቶች እንዲሰጡን ያደረገውና በቀጣይ ፍልሚያዎቻችንም በእዚህ መልኩ ተጉዘንና ጥሩም ተጫውተን ነው የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎቻችንን እንደከዚህ ቀደሙ ለተሳትፎ ብቻ ሳይሆን ወደ ኳታሩ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ጥሩ ውጤትን ለማስመዝገብ ጥረቶችን የምናደርገው፡፡

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ወደሚፈልገው ስኬታማነት እንዲያመራ በምን መልኩ መጫወት አለበት ትላለህ?

አስቻለው፡- ይሄ እኮ የታወቀ ነው፤ አሁን ላይ እኛን ውጤታማ እያደረገን የሚገኘው የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የአጨዋወት ታክቲክ /እንቅስቃሴ/ አለ፤ በዛ ደረጃም እየተጓዝን ነው፤ እሱ ለእኛ ሁሌም የሚጠቅመንን ነገር ነው እያሰራን የሚገኘው፤ ሀገራችን ከዚህ ቀደም ታደርግ በነበረው ብዙዎቹ የማጣሪያ ጨዋታዎቿ የአየር ላይና የረጅም ኳስ ላይ ብቻ በማተኮር በፊዚካል በሚበልጧት ሀገራቶች እየተሸነፈች ውጤት ያጣችባቸው ጊዜያቶች ነበሩ፤ ያ አጨዋወት እኛን ፈፅሞ አይጠቅመንም፤ ለእኛ የሚያዋጣን ኳስን መሰረት ባለው መልኩ ተቆጣጥረን በመጫወት በጋራ ወደፊት አጥቅተን ለመጓዝ ስንችል ነው፤ ይህን ነው በደንብ ማዳበር ያለብን በእዚህ መልኩ ስንጓዝም ነው የምንፈልገውን ውጤት ለማምጣት የምንችለው፡፡

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደ እነ ሱራፌል ዳኛቸው እና በዛብህ መላዮን የመሳሰሉ ተጨዋቾችን ዳግም ወደ ቡድኑ ጠርቶ ለመቀላቀል ችሏል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን አልክ?

አስቻለው፡- እኛን የተቀላቀሉን እነዚህ ተጨዋቾች በጣም አቅም ያላቸው ናቸው፤ ተጨማሪ ጥንካሬንም ለቡድናችን ይሰጡናልና ዳግም መምጣታቸው በጣም አስደስቶኛል፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ…?

አስቻለው፡- በዓለም ዋንጫው የማጣሪያ ጨዋታዎቻችን ላይ ለመቆየትና ወደ ዓለም ዋንጫውም ለማለፍ እድሎችን ለማመቻቸት ከደቡብ አፍሪካ ጋር የምናደርገውን የዛሬው የሜዳችን ላይ ጨዋታን የግድ ማሸነፍ ይኖርብናል፤ ምክንያቱም ይሄን ግጥሚያ ካደረግን በኋላ ማክሰኞ ከእነሱ ጋር ዳግም በሜዳቸው እንጫወታለን፤ እዚህ የድል ነጥብ ከያዝን ለእኛ በጣም ወሳኝ ውጤት ነው፤ ሁሌም የሜዳ ላይ አድቫንቴጅን መጠቀም ጥሩም ነውና ለማሸነፍም ነው የምንጫወተው፤ ለእዚህም ፈጣሪ ይርዳን፤ ህዝባችንም በፀሎቱ ያግዘን፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: