Google search engine

“ለእግር ኳሳችን አለማደግ አሁን ላይ እኛን አሰልጣኞች ጨምሮ ሁሉም ተጠያቂ ነው፤ ማንም ከደሙ ንፁህ የለም” አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው /ወልቂጤ ከተማ/

በመሸሻ ወልዴ G.BOYS

የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብን በአሰልጣኝነት የተረከበው ደግአረገ ይግዛው /ደጉ/ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ክለቡን በእቅድ ደረጃ አበረታች የሚባል ውጤት እንዲያስመዘግብና ጥሩ ቡድንም ለመስራት መዘጋጀቱን ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ በተጨዋችነት ዘመኑ ለተለያዩ ክለቦች ተጫውቶ ካሳለፈ በኋላ ወደ አሰልጣኝነት የተሰማራ ሲሆን ይህን ሙያው ወደ ተሻለ ደረጃ ላይ ለማሳደግም በዝግጅት ላይ ይገኛል፤ አሰልጣኝ ደግአረግ ከባለቤቱ ናርዶስ ፅጌ ሀረገወይን ጋር ትዳር መስርቶ የ18 ዓመቷን ሀብሳላትና የአንድ ዓመቷን ታሪክን ያፈራ ሲሆን ከእዚሁ አሰልጣኝ ጋር በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ቆይታን አድርገን ምላሹን ሰጥቶናል፡፡

ሊግ፡- ወደ አሰልጣኝነት ህይወት ከመግባትህ በፊት የእግር ኳስን ለማን ለማን ቡድኖች ተጫውተህ አሳለፍክ?
አሰልጣኝ ደግአረገ፡- ከልጅነት ዕድሜዬ አንስቶ የእግር ኳስን የተጫወትኩባቸው ክለቦች መጀመሪያ ላይ ለባህር ዳር ጨርቃጨርቅ ክለብ ሲሆን ከዛ በመቀጠል ለባህር ኃይል፣ለጉምሩክ፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪና ከአዲስ አበባም ወደ ትውልድ ክልሌ ተመልሼ ከሄድኩ በኋላም ለተለያዩ ቡድኖች ተጫውቼ አሳልፌያለሁ፤ ከእነዚህ ክለቦች ውጪ ሌላ ደግሞ በምርጥ ክልሎች ደረጃም ለባህር ዳር ከተማ የታዳጊ ፕሮጀክት ቡድንና ለጎጃም ምርጥ ቡድኖችም ለመጫወት ችያለሁ፡፡
ሊግ፡- በእዚያን ወቅት የእግር ኳሱን ስትጫወት ምን ምንን ውጤቶችን ከተጫወትክባቸው ቡድኖች ጋር አስመዘገብክ?
አሰልጣኝ ደግአረግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ ላይ በውጤት ደረጃ ትልቅ የሚባል ስኬትን ያስመዘገብኩት ለጎጃም ምርጥ ቡድን በተጫወትኩበት ጊዜ ከተለያዩ ክልሎች ጋር ተፋልመን ዋንጫን ያገኘንበትን ጊዜ ነው፤ ያኔ የጎጃም ምርጥ ቡድን ጠንካራ ስለነበርም ነው ሻምፒዮና ሊሆን የቻለው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን መጫወት ያቆምከውና ወደ አሰልጣኝነቱ ሙያ የገባኸው በምን ምክንያት ነው?
አሰልጣኝ ደግአረገ፡- የእግር ኳስን መጫወት ያቆምኩት ለሁለት ጊዜያት ነው የመጀመሪያው ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ ክለብ ለመግባት በተሰጠኝ የሙከራ እድል በእግሬ አካባቢ ጉዳት አጋጥሞኝ ሲሆን ሁለተኛውም ከጉዳት ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው፤ ያኔ መጫወት እንደማልችል ካረጋገጥኩ በኋላም ወደ አሰልጣኝነቱ ሙያ ለማምራት ችያለሁ፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን ተጫውተህ ባሳለፍክበት ዘመንህ ላይ ለአንተ ምርጥ የነበሩት አሰልጣኞች እነማን ነበሩ?
አሰልጣኝ ደግአረገ፡- በዋናነት አስቀድሜ ስሙን የምጠራው ነፍሱን ፈጣሪ ይማረውና ኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁን ነዋ! እሱ ትልቅ፣ የተለየ እና በማሰልጠን ችሎታውም የሀገር ሀብት የሆነ አሰልጣኝ ነው፤ መንግስቱ የተጨዋችነት ዘመኔ ላይ እኔን ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ከማምጣት ባሻገር በሚያሰራቸው የዝግጅት ጊዜም ሆነ የጨዋታ ላይ ልምምዶቹ ብዙ ነገሮችን እንዳውቅ ያደረገኝ አሰልጣኝ በመሆኑም በጣሙን አደንቀዋለሁ፤ ከእሱ ውጪም በሌሎቹም አሰልጣኞች ሰልጥኔ ከማለፌ ባሻገር ከእነሱ ብዙ ነገርንም የተማርኩበት ሁኔታ ስላለ ችንም ለኢንስትራክተሮቹ ካሳሁን ተካ እና ሰውነት ቢሻው እንደዚሁም ደግሞ ለአሰልጣኝ አስራት ኃይሌም አድናቆት አለኝ፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ ላይ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመምጣት ብትችልም መጫወት አልቻልክም፤ ያ ይቆጭሃል?
አሰልጣኝ ደግአረገ፡- በጣም እንጂ! እንዴትስ አይቆጨኝ፤ ያኔ ክለቡን የተቀላቀልኩት ወንጂ ላይ ተካሂዶ በነበረው የመኢሰማ ውድድር ላይ ጎጃምን ወክሎ ለመጣው ቡድን ስጫወት በአሰልጣኝ መርሻ ሚደቅሳ ከሚሰለጥነው እና እነ ፍላጎትንና ጳውሎስ ጌታቸው ማንጎን ከያዘው ከኢካፍኮ ቡድን ጋር ስንጫወት ነበር ኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ ተመልክቶኝ እኔን ወደ ቡድኑ የጠራኝ፤ በጊዜውም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ውጪ 5 እና 6 የሚሆኑ ክለቦችም ፈልገውኝ ነበር ያም ሆኖ ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ቡድን ከመሆኑ አኳያ ወደዛ አመራሁኝና በወቅቱ ወደ ቡድኑ ብገባም በወቅቱ የነበሩት ተጨዋቾች በልምድም ሆነ በእውቅና እኔን ይበልጡኝ ስለነበር ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሳልጫወት ቀርቻለሁ፡፡
ሊግ፡- ለቅዱስ ጊዮርጊስ በአንድ የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ተጫውተሃል ልበል?
አሰልጣኝ ደግአረገ፡- አዎን፤ ያን ግጥሚያ ያደረግኩትም የቀድሞ የቡድኑና የብሄራዊ ቡድናችን ዝነኛ አጥቂ እንደዚሁም ደግሞ ከቅርብ አመታት በፊት የክለቡ ስራ አስኪያጅ የነበሩት ፍስሃ ወ/አማኑኤል ከአሜሪካን ሀገር መጥተው ነበርና ለእሳቸው ክብር ሲባል ነው በሊሴ ገ/ማሪያም ት/ቤት ሜዳ ላይ የቀድሞ ተጨዋቾችና የአሁኑ ተጨዋቾች በሚል ውድድር ተዘጋጅቶ ነበርና እዛ ላይ ተጫውቻለሁኝ፤ ያኔ እንደውም ቅ/ጊዮርጊስ የዓመቱን ካለንደር ያወጣ የነበረበት ጊዜም ነበርና እኔም ከቡድኑ ተጨዋቾች ጋር አብሬ ፍቶ መነሳቴንን በካላንደሩ ላይ መውጣቴን አስታውሳለሁ፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ ሲያበቃ ወደ አሰልጣኝነቱ ሙያ ገባህ፤ ያኔ አሰልጣኝ የመሆን ፍላጎትህ ነበር? የስራ አጀማመርህስ ምን ይመስላል?
አሰልጣኝ ደግአረገ፡- ወደአሰልጣኝነት ሙያው ለመምጣት የቻልኩት የእግር ኳስን ተጫውቼ ካበቃው በኋላ ነው፤ ያኔ አሰልጣኝ መሆንም እፈልግ ነበር፤ በሙያው ላይ ለመሰማራት ከነበረኝ ፍላጎት አኳያም በመጀመሪያ የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርትን ለመማር ወደ ዩንቨርስቲ ገባው፤ እየተማርኩም የታዳጊ ወጣቶችን አሰለጥን ነበርና በዚሁ ነው የማሰልጠን ሙያውን የጀመርኩት፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ልታሰለጥን መጥተሃል፤ ወደ ወልቂጤ ከተማ ክለብ እንዴት ለማምራት ቻልክ? ከዛ በፊት የነበረህስ የታችኛው ሊግ የአሰልጣኝነት ሙያው ቆይታህስ ምን ይመስላል?
አሰልጣኝ ደግአረገ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ዘንድሮ ወደተቀላቀለው የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ለመምጣት የቻልኩት በቡድኑ አመራሮችና በወጣቱ የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ አበባው በሙያው ቆይታዬ ላይ ያለኝ ስራ ታይቶና ተገምግሞ ከፍተኛ እምነት ሊጣልብኝ በመቻሉ ነው፤ ወልቂጤዎች ወደ ቡድኑ ሲያመጡኝ እኔ ትልቅ ስም ያለኝ አሰልጣኝ ሆኜ አይደለሁም፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሁን ያለበት ሁኔታ ይታወቃል፤ እነሱ ያመጡኝ ለሙያዬ ከፍተኛ ክብርም ሰጥተው ነበርና በእዚህ አጋጣሚ አመራሮቹን በአጠቃላይ አመሰግናቸዋለሁኝ፤ በታችኛው ሊግ ስለነበረኝ የአሰልጣኝነት ሙያ ቆይታ ደግሞ ማለት የምፈልገው እኔ የመጣሁበት መንገድ ቅደም ተከተልን ፕሮሲጀሩን በጠበቀ መልኩ ነው፤ በስራ ቆይታዬ ደብረ ማርቆስ ዩንቨርስቲን አውስኮድን በማሰልጠን መልካምና አበረታች የሚባል ውጤቶችን አስመዝግቤያለው፤ በስራ ቆይታዬም ደስተኛ ሆኜ ነው ያሳለፍኩት፤ ከዛ ውጪም የተለያዩ ተጨዋቾችን ለታዳጊ ለኦሎምፒክና ለዋናው ብሔራዊ ቡድን የደረሱ እነ ታዲዎስ ተሰማን /የጎዳና ተዳዳሪ የነበረ/ እንደዚሁም ደግሞ እነ ሳሙኤልን እና ያሬድ ባየህን የመሳሰሉ ተጨዋቾች ለጥሩ ስፍራ እንዲደርሱም መሰረቱን ጥዬላቸው አልፌያለውና ያ ሁሌ ያስደስተኛል፡፡
ሊግ፡- ወልቂጤ ከተማ በእዚህ ዓመት ምን ውጤት ያመጣል? ምን አይነት ቡድንንስ በውድድሩ ላይ እንጠብቅ?
አሰልጣኝ ደግአረገ፡- ወልቂጤ ከተማ ለሊጉ አዲስ ቡድን ቢሆንም የእዚህ ዓመት ላይ ወደ ውድድር የሚገባው የራሱ የሆነ ጥሩ አጨዋወት ኖሮት አበረታች ውጤት እንዲያመጣ ነው፤ ወልቂጤ አሁን ላይ በወጣቶች ተገንብቶ ነው ልምምዱን እየሰራ የሚገኘው፤ ከዛ ውጪም አዳነ ግርማንም ያለውን የተጨዋችነት ልምድ ለወጣቶች እንዲያካፍልም አምጥተነዋልና ጥሩ ቡድን ይኖረናል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፕሮጀክት ስልጠና ከ1990ዎቹ አንስቶ ለዓመታት ሲሰጥ ነበር፤ ያ ስልጠና ግቡን መቷል?
አሰልጣኝ ደግአረገ፡- በፍፁም፤ ያ ፕሮጀክት ዓላማው ትልቅ የነበረ ቢሆንም የታለመለትን ግብ አልመታም፤ ከእሱ ይልቅ በንፅጽር 2001 አካባቢ ተጀምሮ የነበረው የፕሮጀክት ስልጠና የተሻለ ነበር፡፡ ከዛ በፊት የነበረው ስልጠና ለሪፖርት ማሟያ የነበረ ነው፤ ፕሮጀክቱን በአግባቡ ይሰጥ ስላልነበር የአገራችን ኳስ ሊጎዳ ችሏል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ላለማደጉ እና ወደ ታች እያሽቆለቆለ ለመሄዱ እነማን ተጠያቂ መሆን ይገባቸዋል?
አሰልጣኝ ደግአረገ፡- ሁላችንም ነና! አሁን ላይ በአሰልጣኝነት ማንም የሚተርፍም ሆነ ከደሙ ንፁህ ነኝ የሚል አካል ፈፅሞ የለም፤ ምክንያቱም መስራት ባለብን ልክ እግር ኳሱ ላይ አልሰራንም፤ ራሳችንን ለተሻለ ሙያ ለማብቃት ጥረትን አናደርግም፤ ከዛ ውጪ ኳሱ ከህይወት እና ከኑሮ ጋር እየተያያዘ በመሆኑና ምቹ የሆነም የስራ አትሞስፈር ባለመኖሩ እንደዚሁም ደግሞ የእግር ኳስ አደረጃጀቱን የምንመራበት መንገድ መርሀ አልባ ስለሆነም እነዚህ ለስፖርታችን አለማድረግ ትልቅ ችግር ሆነው አልፈዋል፡፡
ወደ ተጨዋቾች ጋር ስትመጣም የኮሚትመንት ችግር አለ፤ የስራ ባህል አለመኖሩ የትኩረት ማጣት ተጨዋቹ ፕሮፌሽኑን አለማወቁና አለመረዳቱ፤ የእግር ኳስ ተመልካቹ የኳስ ምልከታ ከማደጉ አኳያ የእኛን ሀገር ኳስ በአንዴ እንደውጪ የሚጠብቅበት ሁኔታ በመኖሩና የሃገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳትና ሌላው ነገርም ተጨምሮበት ነው እግር ኳሱ በሚፈልገው መልኩ ላያድግ የቻለው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የአሰልጣኝነት ሙያው ተንቋል ትክክል ነው ብለህ ታምናለህ?
አሰልጣኝ ደግአረገ፡- አዎን፤ በትክክልም ሙያው ተንቋል፤ ሙያው አሁን ላይ የተናቀበት ዋናው ምክንያትም በእኔ ምልከታ መጀመሪያ ሙያውን ማስከበር ያለብን ራሳችን እኛው አሰልጣኞች ስለሆንን ነው፤ ለሙያችን መናቅ የሚጠቀሱት ለስራችን ታማኝ ያለመሆን ስራውን ገንዘብ ለማግኘት እንጂ በፍቅር አለመስራታችን ለስራው የሚገባውን ክብር አለመስጠታችን የአሰልጣኝነት ሙያው የተናቀበት ሰአት ላይ እንድንገኝ አድርጎናል፡፡ ከዛ ውጪም ክለቦች ከአሰልጣኝ ይልቅ ትልቅ የፊርማ ብር ለሚሰጡት ተጨዋቾችም ክብር ያላቸው መሆኑም ሌላው ለሙያው መናቅ ምክንያት ሆኗል፡፡
በእኛ የተጨዋችነት ዘመን ለአሰልጣኞች ትልቅ ክብር ነበረን ዛሬ ላይ ያ የለም፤ በእነዚህ ምክንያቶች ጭምር ሙያው ተንቋል፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ….?
አሰልጣኝ ደግ አረገ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንዲያድግ ሁላችንም የየራሳችንን ስራ ልንወጣ ይገባል፤ በመጀመሪያ አሰልጣኞች ተጨዋቾች ለሙያው ተገዥ ልንሆን ይገባል፤ ዓለም የደረሰበት ደረጃ ላይ ለመገኘት አዳዲስ ነገሮችን ልናመጣ ይገባናል፤ ሚዲያውም እግር ኳሱን ሊያሳድግ የሚችል የመፍትሄ አሳቦችን በመጠቆም በጋራ ከእኛ ጋር የሚሰራ ከሆነ የተሻለ ቦታ ላይ መድረስ ይቻለናል፡፡ ከዛ ውጪ ማለት የምፈልገው ራሴን በተመለከተ በአሰልጣኝነት ሙያው ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ እፈልጋለው፤ ለዛም ራሴን በእውቀት ከማሳደግ አንስቶ ብዙ ነገሮችንም ማወቅ እፈልጋለውና በእዛ ደረጃ ላይ እዘጋጃለው፤ በተረፈ በአሰልጣኝነት ሙያ አሁን ላይ ለምገኝበት ደረጃ የባለቤቴ እገዛ ከፍ ያለም ስለነበር እሷንና ከእኔ ጎን የሆኑትን ሁሉ ለማመስገን እፈልጋለው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P