Google search engine

“ለካሳዬ አራጌ አጨዋወት ምቹ እሆናለው፤ ከዮርዳኖስ በላይም ጥቅም ለመስጠት ወደ ቡድኑ መጥቻለው” ሰይፈ ዛኪር አባጊዲ /ኢትዮጵያ ቡና/


በመሸሻ ወልዴ

ኢትዮጵያ ቡና በክረምቱ የተጨዋቾች
ዝውውር መስኮት ካስፈረማቸው
ተጨዋቾች መካከል በከፍተኛው ሊግ
ለፌዴራል ፖሊስ በአጥቂው ስፍራ
ላይ ሲጫወት የነበረው ሰይፈ ዛኪር ስሙ
ይጠቀሳል፤ ይሄ ተጨዋች ወደ ቡድኑ
መምጣቱን ተከትሎም ካለው የሜዳ ላይ
ብቃት አንፃር አዲሱ ዮርዳኖስ አባይ የሚል
ስያሜ እያሰጠውም ይገኛል፡፡
የእግር ኳስ ተጨዋችነት ህይወቱን
ከአባቱ አቶ ሰይፈ ዛኪር አባጊዲና
ከእናቱ ወ/ሮ እቴነሽ በቀለ አብራክ
በመፈጠርና በተወለደበት ጅማ ዞን ጌራ
ወረዳ ላይም ኳስን የልጅነት ዕድሜው
ላይ በማንከባለል የጀመረው ይኸው 62
ኪሎ ግራም የሚመዝነውና 1 ሜትር ከ77
ሜትር ቁመት ያለው ወጣት ተጨዋች
የእግር ኳስን በወረዳ ከዛም በመቀጠል
በክለብ ደረጃ ለአርሲ ነገሌ፣ ለቱሉ ቦሎና
ለፌዴራል ፖሊስ በመጫወት ችሎታውን
ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሻሻልና ለውጥንም
በማምጣት አሁን ለቡና ለመጫወት
ፊርማውን ያኖረ ሲሆን በቡና በሚኖረው
የቀጣይ ጊዜ ቆይታውም የተሳካ የውድድር
ዘመንን እንደሚያሳልፍና ለአዲሱ የቡድኑ
አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌም የጨዋታ
ፍልስፍና ምቹ ሆኖ እንደሚቀርብ
እየተናገረ ይገኛል፤ ከእዚህ ተጨዋች ጋር
ወደ ቡና ክለብ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘና
አጠር ስላለው የኳስ ህይወቱ አናግረነው
ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፤
ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና መፈረምህን
ተከትሎ ከወዲሁ “አዲሱ ዮርዳኖስ አባይ”
ወደ ቡድኑ መጥቷል እየተባልክ ነው፤
ስያሜው ያስማማሃል?
ሰይፈ፡- አዎን፤ በእሱ ስም
መጠራቴም ለእኔ ትልቅ ክብርና ብዙ
ነገር እንደሚጠበቅብኝም የሚያመላክት
ነው፤ ዮርዳኖስ አባይ በጣም የማደንቀውና
የምወደው አይነት የቀድሞ የኢትዮጵያ
ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች ነው፤ ልጅ
ሆኜም ስለ እሱ ችሎታ እሰማና ለአገራችን
ብሄራዊ ቡድን ሲጫወትም የእሱን እንቅስቃሴ
በቴሌቪዥን መስኮት እከታተልም ስለነበር እሱ
ጥሩ ችሎታ ያለውና ልዩ ተጨዋችም ነው፤
እኔም ለቡና ስፈርም አዲሱ ዮርዳኖስ አባይ ወደ
ቡድኑ መጥቷል የተባልኩት ያለ ምክንያት
አይደለም፤ ወደ ቡና የመጣሁት ለክለቡ
ውጤታማነት ትልቅ ነገሮችን ለመስራት
ነው፤ ዮርዳኖስ አባይ በቡድኑ ቆይታ ጥሩ
ችሎታውን ከማሳየት አልፎ በርካታ ጎሎችንም
በማስቆጠር ነው የክለቡን ቆይታ ያጠናቀቀው
አሁን ደግሞ እኔ በቡድኑ በሚኖረኝ የወደፊት
ቆይታዬ አዲሱ ዮርዳኖስ አባይ ብቻ እንድባል
ሳይሆን ከእሱም በበለጠ ለቡና ጥሩ ነገሮችን
ለመስራት ነው የመጣሁትና ለእዛ በርትቼና
ጠንክሬ ነው የምሰራው፤ ከፈጣሪ እርዳታ ጋር
ዮርዳኖስ አባይ ከሰጠው ጥቅም በላይም ቡናን
ለማገልገልም መምጣቴንም በእዚሁ አጋጣሚ
መናገር እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- ወደ ኢትዮጵያ ቡና የመጣህበትና
ፊርማህን ያኖርክበት የዝውውር ሂደት ምን
ይመስላል?
ሰይፈ፡- ወደ ኢትዮጵያ ቡና ልመጣና
ፊርማዬን ላኖር የቻልኩት በከፍተኛው ሊግ
የፌዴራል ፖሊስ ቡድን ቆይታዬ ከሶስት
ጨዋታዎች በስተቀር ዓመቱን ሙሉ በጥሩ
አቋሜ ላይ ልገኝ በመቻሌና ቡድናችን
ባደረጋቸው ትላልቅ በሚባሉ ግጥሚያዎችም
ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ቡና የላካቸው
የተጨዋቾች መልማዮች የእኔን እንቅስቃሴ
በአግባቡ የተመለከቱ በመሆናቸው በክለቡ
በጥብቅ ተፈልጌና በችሎታዬም ታምኖብኝ
ነውና የእኔ የዝውውር ሂደት በእዚህ መልኩ
ነው የተከናወነው፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮ-ኤሌክትሪክ ለመፈረም
ፈልገህ ወደ ኢትዮጵያ ቡና እንዳመራህ
ተነግሯል፤ የእውነት ነው?
ሰይፈ፡- አዎን፤ መጀመሪያ ላይ የከፍተኛ
ሊግ ተወዳዳሪ ለሆነው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ
ለመጫወት ነበር የፈለግኩት፤ በእዛም
የታችኛው ሊግ የቡድኑ ቆይታዬ የራሴን
ብቃት በደንብ ካዳበርኩ እና ካሻሻልኩ በኋላም
የፕሪምየር ሊጉ ላይ ከአንድ ዓመት በኋላ
ገብቼ ለመጫወት ነበር እቅዴ የነበረው ያም
ሆኖ ግን የእኔን በቡና ክለብ መፈለጌን
የሰሙት ጓደኞቼ በእኔ ውሳኔ ተበሳጭተው
እና ደስተኛ ሳይሆኑ ቀርተው በመምጣታቸው
አንተ ጫና ቢኖረውም ለቡና ነው መጫወት
ያለብህ፤ እዛም ይሳካልሃል ሲሉኝና
የቡድናችን አሰልጣኝ የሆነው መሳይ በየነም
ከፌዴራል ፖሊስ ክለብ ጋር ያለኝ የውል ጊዜ
መጠናቀቅን ካወቀ በኋላና ከሁለቱ ክለቦች
የመጣልኝንም ጥሪ በተረዳ ሰዓት እኔ ለየቱ
ቡድን ብጫወት የበለጠ ጥሩ እንደሚሆንልኝ
በጠየቅኩት ሰዓት መጀመሪያ ራስህ ወስን
ካለኝ በኋላ ለኢትዮጵያ ቡና ብትጫወት
በፍጥነት ለመታወቅም ሆነ ችሎታህን በአንዴ
ለማሳደግ የሚኖርህ የተለየ ነገር ይኖራል
ስላለኝ የጓደኞቼ ውትወታና የአሰልጣኝ
መሳይ ምክርም ነው ከኤሌክትሪክ ይልቅ ወደ
ኢትዮጵያ ቡና እንድመጣ ያደረገኝ፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና ከ15 ዓመታት
በኋላ ባስመጣው የቀድሞ አሰልጣኙ ካሳዬ
አራጌና ለየት ባለም የጨዋታ ፍልስፍና
ነው የመጪው ዓመት ላይ ወደ ውድድር
የሚገባው፤ ለክለቡ ፊርማህን ስታኖር እነዚህን
ነገሮች አውቀህ ነው? በቡና በሚኖርህ ቆይታስ
ይሳካልኛል ብለህ ታሳባለህ?
ሰይፈ፡- አሁን ላይ ለኢትዮጵያ ቡና
እየፈረሙ ያሉት ተጨዋቾች ወደ ክለቡ
እየመጡ ያሉት ቡድኑ ከአሜሪካን ሀገር
ላስመጣው የቀድሞ የቡድኑ ተጨዋችና
አሰልጣኝ ለነበረው ካሳዬ አራጌ የጨዋታ
ፍልስፍና ይሆናል ተብለው የታመነባቸውን
ነው፤ እኔም ከፌዴራል ፖሊስ እንድመጣ
የተደረግኩት ለአሰልጣኙ የጨዋታ ፍልስፍና
ትሆናለህ ተብዬ ስለሆነ ይህንን አውቄ ነው ወደ
ቡድኑ የመጣሁት፤ ለዛም የጨዋታ ፍልስፍና
ራሴን ከወዲሁ በምን መልኩ ማቅረብና
መምጣት እንዳለብኝም በሚገባ እያዘጋጀሁት
ነው፤ ከአሰልጣኞች የጨዋታ ፍልስፍና ጋር
በተያያዘ እኔ ምንም ችግር የለብኝም፤ ከእዚህ
በፊት በተጫወትኩባቸው ክለቦች ውስጥ
ለሁሉም አሰልጣኞች የጨዋታ ፍልስፍናም
ሆነ ታክቲክ ምቹ ሆኜ ቀርቤያለው፤ በቡና
የመጪው ዓመት ቆይታዬም ለአሰልጣኝ
ካሳዬ አራጌ የአጨዋወት ፍልስፍና በጣም
ምቹ እንደምሆንና በቡና ክለብ ቆይታዬም
የተሳካ ጊዜን እንደማሳልፍ እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሊግ፡- ለፌዴራል ፖሊስ ስትጫወትም
ሆነ ከእዛ በፊት በነበረህ የክለብ ተጨዋችነት
ቆይታህ አንተ ምን አይነት ተጨዋች ነበርክ?
ለፌዴራል ፖሊስስ ስንት ግብ አስቆጠርክ?
ሰይፈ፡- የእግር ኳስን በተጫወትኩባቸው
የከዚህ ቀደም የክለብም ሆነ የአካባቢ የወረዳ
ውድድሮች ላይ የእኔ ተጨዋችነት ችሎታ
የሚገለፀው ጎል በማስቆጠርና ከእዛ በላይ
ደግሞ እኔ ከማስቆጥራቸው ግቦች በላይ
ጣጣቸውን የጨረሱ ኳሶችንም ለጓደኞቼ
በማቀበል የምታወቅ አይነት ተጨዋች ነኝ፤
ስለዚህም ጎል ማግባት እችላለው፤ ኳሶችንም
በሚገባና በትክክለኛው መንገድም አቀብላለው፡
፡ የፌዴራል ፖሊስ ክለብ ውስጥ በነበረኝ
የዘንድሮ ቆይታዬ ለክለቡ ያስቆጠርኩት ጎል
6 ነው፤ ብዙ ኳሶችን ግን አቀብያለው፡፡
ሊግ፡- የፌዴራል ፖሊስ ቡድን
ውስጥ የነበረህን ቆይታ በምን መልኩ ነው
የምትገልፀው?
ሰይፈ፡- በከፍተኛው ሊግ ተሳትፎአችን
በፌዴራል ፖሊስ ውስጥ የነበረኝ ቆይታ
በጣም ጥሩና ጣፋጭም የነበረ ነው፤ ለክለቡ
ተጫውቼ ማለፌም ራሴን እንደ ዕድለኛ
አድርጌም ነው የምቆጥረው፤ ቡድናችን ብዙ
ደጋፊ ባይኖረውም ጥሩ ፍቅር ያለው ቡድን
ነው፤ በውድድር ዘመኑ ተሳትፎአችንም
ጠንካራ ተፎካካሪዎች ባሉበት የእነ ሰበታ
ከተማ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ እና የኤሌክትሪክ
ምድብ ውስጥ ሆነን እልህ አስጨራሽ
ፍልሚያን ስናደርግ የነበርንበት ጊዜም
ስለነበር ይሄንን የምረሳው አይደለም፤
በክለቡ በነበረኝ የዘንድሮ የውድድር ዘመን
ቆይታም ለእኔ ብዙ ነገሮች ጥሩ ሆነውልኝም
አልፈዋል፤ ለክለቡ ጥሩ በመጫወቴም ነው
የቡድኖችን ትኩረት እንድስብና በእነሱም
እንድፈለግ ያደረገኝና ፌዴራል ፖሊስ አሁን
ላይ ወደ ኢትዮጵያ ቡና እንድገባ የጥርጊያውን
መንገድ የከፈተልኝ ቡድን ስለሆነ ክለቡን፤
አመራሮቹን፤ ለእኔ እንደ አባት ያህል
የምቆጥረውንና በአሰልጣኝነቱ ችሎታም
የማደንቀውና ለችሎታዬም መሻሻል ከፍተኛ
አስተዋፅኦ ያበረከተልኝን የቡድኑ አሰልጣኝ
መሳይ በየነን ከዛ ውጪም ረዳቶቹን
ኢብራሂምና ጁማሀን እንደዚሁም የቡድን
መሪውን በየነን ለማመስገን እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- ወደ እግር ኳስ ተጨዋችነት
ህይወቱ ባትመጣ ኖሮ በምን ሙያ ላይ
እናገኝህ ነበር?
ሰይፈ፡- ምንም መዋሸት አልፈልግም፤
የመንግስት ሰራተኛ ስለመሆን ሳይሆን
የማስበው ከመጀመሪያው አንስቶም
የቤተክርስቲያን አገልጋይ ሆኜ በመምጣት
ዘማሪ ወይንም ደግሞ ሰባኪ ሆኜ ነበር
የምታገኙኝ፤ ያም ሆኖ ግን እግር ኳሱን
አጥብቄ እወደው ስለነበር ኳስ ተጨዋች
ልሆን ችያለው፡፡
ሊግ፡- ከቤተሰባችሁ አንተ ብቻ ነህ
ስፖርተኛው?
ሰይፈ፡- አንድ ወንድምና አንድ እህት
ቢኖረኝም አሁን ላይ ስፖርተኛው እኔ ብቻ
ነኝ፤ ወንድሜ ካሳሁን ግን በፊት ተማሪና
የመንግስት ሰራተኛ ከመሆኑ በፊት ኳስን
በአካባቢ ደረጃ ይጫወት ነበር፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳሱ ማንን አድንቀህ ነው
ያደግከው?
ሰይፈ፡- የልጅነት ዕድሜያችን ላይ
ኳስን ስንጫወት ስለ ኢትዮጵያ ብሄራዊ
ቡድን የምንሰማቸው ነገሮች ነበሩ፤ ያኔም
ከምነሰማው ነገር በመነሳትና በቴሌቪዥን
መስኮትም ከምንከታተለው ነገር በመነሳት
ስለ እነ ዮርዳኖስ አባይ፣ ሰብስቤ ሸገሬና ደያስ
አዱኛን ስለመሳሰሉት ተጨዋቾች እናውቅ
ስለነበር እነሱን አድንቀን ነው ያደግነው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P