በመሸሻ ወልዴ
ወላይታ ድቻ በፕሪምየር ሊጉ እያደረጋቸው ባሉት የዘንድሮ የውድድር ተሳትፎዎቹ አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ ለቡድኑ ስኬታማ ጎሎችን እያስቆጠረለት ይገኛል፤ እስካሁንም 7 ግቦችንም ከመረብ አሳርፏል፤ የዓመቱ ውድድር መጀመሪያ ላይ ጥሩ ውጤት እንደማያመጣ ሲነገርለት የነበረው ይኸው ቡድን አሁን ላይ በአራተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ አጥቂው ባዬም ዘንድሮ ለዋንጫ የማንፎካከርበት ምንም አይነት ምክንያትም የለም ሲልም ይናገራል፤ ከባዬ ገዛኸኝ ጋር ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አጠር ያለ ቆይታን አድርጎ ነበር፤ በሚከተለው መልኩም ቀርቧል፡፡
ወላይታ ዲቻ ባህርዳር ከተማን በአንተ ብቸኛ ግብ አሸንፏል፤ ጨዋታው ምን መልክ ነበረው?
“ወላይታ ድቻ ከባህርዳር ከተማ ጋር ያደረገው ጨዋታ ጥሩ ነበር፤ እኛ አጥቅቶ በመጫወቱ እነሱ ደግሞ ኳስ ሲቆጣጠሩ ጥሩና የተሻሉ ነበሩ በኋላ ላይ ግን ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት በዕለቱ በነበረን ጥሩ ጎናችን ማለትም በተከላካይ ክፍሉ እና በመስመር ክፍሉ ላይ በነበሩት የአጥቂ ስፍራ ተጨዋቾቻችን የተጠቀምንበት የአጨዋወት ስልት ረድቶን ውጤት ይዘን ልንወጣበት ችለናል፤ በተለይ ደግሞ የመስመር ላይ ተጨዋቾቹ ሰብረው ወደ ውስጥ ሲገቡና ድሪብል ሲያደርጉም ጥሩ ስለነበሩ በስተመጨረሻም እኔ ባገባሁት ብቸኛ ግብ ጨዋታውን ለማሸነፍ ችለናል፤ በውጤቱም በጣም ተደስተናል፡፡
ስለ ወላይታ ዲቻ የፕሪምየር ሊግ ጉዞ
“ወላይታ ዲቻ የአሁን ሰአት ላይ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እየሄደበት ያለው የውድድር ጉዞ ጥሩ እና ከፍተኛ መሻሻልንም እያሳየበት ያለ ነው፤ ከዚህ ወቅታዊ አቋማችንም በመነሳት አሁን በአራተኛ ደረጃ ላይ ብንገኝም ከዚህ በኋላ በሚኖሩን ጨዋታዎች የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እንጫወታለን”፡፡
ወላይታ ዲቻን ብዙዎች ዘንድሮ በእዚህ ውጤትና ደረጃ ላይ ትገኛላችሁ ብለው አልጠበቃችሁም ነበር….
“አዎን፤ እንዳንጠብቅ ያደረገን በራሳችን አንድአንድ ችግሮች እንጂ ቡድናችን ምንም አንሶትና ጥሩ ሳይሆን ቀርቶ አይደለም፤ ጥሩ ቡድን ነው ያለን፣ ወጣት እና ጥሩ ችሎታ ያላቸውንም ተጨዋቾች ይዘናል፤ የቡድናችንም መንፈስ ጥሩ ስለሆነም ነው በብዙ ነገሮች ተሻሽለን ለእዚህ ደረጃ ልንበቃ የቻልነው”፡፡
ለወላይታ ድቻ የውጤት ለውጥ የአሰልጣኝ ቅያሪ ማድረግ መቻሉ ጠቅሞታል ማለት ይቻላል?
“አዎን፤ እኔ እንደዛ ብዬ ነው የማስበው፤ ምክንያቱም ውጤት እምቢ ሲልህ ወደዛ አማራጭ መሄድ የግድ ነው የሚልህና በዛም ነው እኛ ለውጥ በማድረጋችን እና ለተጨዋቾቻችንም የሚሰጠውን የአጨዋወት ታክቲካችንንም ልንቀይር በመቻላችን ውጤታችን እየተስተካከለ የመጣው”፡፡
የወላይታ ዲቻ ጥሩ እና ጠንካራ ጎኑ?
“ከሁሉም በላይ የፊት መስመር ላይ ያለነው ተጨዋቾች ጥሩ አቅም ያለንና ወጣት ተጨዋቾችም ስላሉበት በእዚህ በኩል ጠንካራ ጎን አለን፤ ከዛ ውጭ ደግሞ እንደ እነ ደጉ ደበበ እና ተስፋዬ አለባቸው ቆቦን የመሳሰሉ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾችም መኖራቸው ጥሩ ነገርን እንድንሰራ አድርጎናል”፡፡
የወላይታ ዲቻ ወቅታዊ አቋሙና የያዘው የተጨዋቾች ስብስብ የሊጉን ዋንጫ እስከማንሳት ደረጃ ያደርሰዋል?
“በእኔ እምነት አዎን ዋንጫ የሚያነሳ ስብስብ አለን፤ ባለን ወቅታዊ አቋምም ከቀጠልን ምንም ነገርንም ከማድረግ የሚያግደን ነገርም የለም ብዬም አስባለው”፡፡
ወላይታ ዲቻ በሜዳው እና ከሜዳው ውጭ ሲጫወት ልዩነት አለው?
“ቡድናችን የትም ይጫወት ብዙም ልዩነት የለውም፤ አጨዋወታችንም ተመሳሳይ ነው፤ እያንዳንዱን ጨዋታም ለማሸነፍ ነው በሜዳችን ብቻ ሳይሆን የትም ስንሄድም የምንጫወተው፤ በዛ ላይም ደጋፊዎቻችንም ሁሌም ከጎናችንም ነው ያለው”፡፡
ወላይታ ዲቻን ዘንድሮ ያስቆጨው ጨዋታ
“ከሐዋሳ ከተማ ጋር ያደረግነው ነዋ! በጨዋታው 1-1 ከሆንን በኋላ ባለቀ ሰአት ነው ግብ ተቆጥሮብን የተሸነፍነው”፡፡
በጣም የተደሠትክበትስ?
“ሁሌም ጨዋታዎችን ስናሸንፍ በጣም ደስ ይለኛል፤ ያም ሆኖ ግን እኔ ተቀይሬ ገብቼና በባህርዳር ከተማ ላይ ግብ በማስቆጠር ያሸነፍንበት የሜዳችን ላይ ጨዋታ ከሁሉ በላይ ሊያስደስተኝ ችሏል”፡፡
ለወላይታ ተደጋጋሚ ጎል ስለማስቆጠሩና ስለወቅታዊ አቋሙ?
“የእግር ኳስን ስጫወት ጉዳት በሚደርስብኝ ሰዓት ትንሽ የመቀዛቀዝ ሁኔታ ይታይብኝ ነበር፤ ከመከላከያ ቡድን ተጨዋችነቴ አንስቶም የደረሰብኝ ጉዳት በችሎታዬ የበለጠ ወደፊት እንዳልጓዝም አድርጎኝ ነበር፤ አሁን ላይ ግን ሙሉ ጤነኛ ሆኜ ስለምጫወት በወቅታዊ አቋሜ ጥሩ ነኝ፤ የበፊቱን ባዬም ለመመለስ ጥረትን እያደረግኩኝ ነው የምገኘው፤ በሁሉም ነገር የተሳካ የውድድር ጊዜን እንደማሳልፍም እርግጠኛ ነኝ”፡፡
ለሲዳማ ቡና በመጫወት ላይ የሚገኘው የወንድምህ ሀብታሙ ስኬታማ ተጨዋችነትን በተመለከተ
“ሀብታሙ ታናሼ እና ጥሩ ስነ-ስርዓት ያለው ተጨዋች ነው፤ ከብዙ ተጨዋቾችም ጋር በፍቅርና በመግባባትም ጥሩ የሆነ የውድድር ዘመንን እያሳለፈ ይገኛል፤ በስራው ይለፋል፤ ይጥራል፤ እኔም እመክረዋለው፤ ከእሱ ጋር ብዙ ጎሎችን እንዲያስቆጥር እና የተሻለም ደረጃ ላይ እንዲደርስ የምንመካከርበት ነገር አለና ሁሌም ከእሱ ጎን መሆኔና እሱን ለማገዝም ዝግጁ ነኝ”፡፡
ለወላይታ ድቻ ከዚህ በኋላስ ብዙ ጎሎችን ታስቆጥርለታለህ?
“አዎን፤ በምገባባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ግብ አስቆጥሬ የቡድኔን ውጤት ከዚህ የበለጠ እንዲሻሻል ከፍተኛ ጥረትን አደርጋለው”፡፡
የዘንድሮ ፕሪምየር ሊግ በአንተ እይታ ሲገለፅ?
“ውድድሩ በጣም ጥሩ ፉክክር እየተደረገበት ነው፤ ቡድኖችም በነጥብ ተቀራርበዋል፤ ሻምፒዮና የሚሆነውም ሆነ የሚወርደው ክለብንም ለመለየት አሁን ጊዜው አይደለም፤ ከዛ በላይ ደግሞ የተለየ ሆኖ ያገኘሁት የትም ሄደህ ብትጫወት በነፃነት ተጫውተህ የምትመለስ እና ግጥሚያዎችንም ማሸነፍ የምትችልበት ሁኔታ መኖሩ ነው፤ ሌላው ዳኞችም መፍራት ትተዋልና ይሄ ደስ ያሰኛል ይበልም ያሰኛል”፡፡