Google search engine

 “መሀል ሰፋሪ ሆነን እንጨርሳለን ብለን ነበር፤ አሁን ግን ለደረጃ ተፎካካሪነት እንጫወታለን” “አቡበከር ናስር የጨዋታ ጫና በዛበት እንጂ አሁንም በሊጉ የተሻለው ተጨዋች እሱ ነው” ምንይህሉ ወንድሙ /ወላይታ ድቻ/

 “መሀል ሰፋሪ ሆነን እንጨርሳለን ብለን ነበር፤ አሁን ግን ለደረጃ ተፎካካሪነት እንጫወታለን”

“አቡበከር ናስር የጨዋታ ጫና በዛበት እንጂ አሁንም በሊጉ የተሻለው ተጨዋች እሱ ነው”

ምንይህሉ ወንድሙ /ወላይታ ድቻ/

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው  የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ትናንት ድሬዳዋ ከተማ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከሐዋሳ ከተማ እንደዚሁም ደግሞ ሲዳማ ቡና ከባህርዳር ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ የተጀመረ ሲሆን ይኸው ውድድር ዛሬ፣ ነገና ሰኞ በሚደረጉት ግጥሚያዎችም ቀጥሎ ይውላል፤ በእዚህ ሳምንት ከሚደረጉት ግጥሚያዎች መካከልም ቅ/ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማና ወላይታ ድቻ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታም በጉጉት ተጠብቋል፡፡ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በእዚህ ሳምንት ሲደረግም በደረጃው ሰንጠረዡ በሰባተኛ ስፍራ ላይ የሚገኘው ወላይታ ድቻ በሊጉ ድሬዳዋ ከተማ ላይ ስለሚኖረው ቆይታ፣ በአጠቃላይ የሊጉ ጉዞ እንደዚሁም ደግሞ ከቡድናቸው ተሳትፎ ጋር በተያያዘ እና ሌሎችንም ጥያቄዎች ለቡድኑ ተጨዋች ምንይህሉ ወንድሙ አቅርበንለት ተጨዋቹ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቶናል፤ ተከታተሉት፡፡

ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሐዋሳ ከተማ ላይ የነበራችሁ ቆይታ ምን መልክ ነበረው?

ምንይህሉ፡- ውድድሩ እስኪቋረጥ ድረስ ጥሩ ቆይታ ነው  የነበረን፤ ቡድናችን በስኳዱ ከያዘው የተጨዋቾች ስብስብ አንፃርም ያስመዘገብነው ውጤት መልካም የሚባል ነው፡፡

ሊግ፡- በዘጠኝ ሳምንታት የውድድር ጉዞአችሁ የነበራችሁ ጠንካራና ደካማ ጎንስ ምን ነበር?

ምንይህሉ፡- የእኛ ጠንካራ ጎን ጥሩ የቡድን መንፈስ ያለን መሆኑና በከፍተኛ ፍላጎትም ኳሱን መጫወታችን ነው፤ በደካማነት የማነሳው ጎን ደግሞ የትኩረት ማነስ ችግር ነበረብን፤ ለራሳችን ያስቀመጥነው ቦታ ከፍ ያለ መሆኑና በግምት ደረጃም የተቃራኒን ቡድን የማውረድ ሁኔታ ስለነበረብን እነዚህ ሁኔታዎች ሊጎዱን ችለዋል፡፡

ሊግ፡- በድሬዳዋ ከተማ ላይ ለሚኖራችሁ ተሳትፎስ ካለፉት ግጥሚያዎቻችሁ ምን ነገሮችን ለማሻሻል ተዘጋጅታችኋል?

ምንይህሉ፡- እንደ ቡድን መከላከላችንና ማጥቃታችን ጥሩ ሆኖ ሳለ አንድ አንድ ጊዜ ስህተቶች ሲፈጠሩ ይሄ ችግር የእኔ አይደለም በሚል ሀላፊነትን የመውሰድ ነገር የለም፤ ስለዚህም ክፍተቶች ሲኖሩ ሀላፊነቱን ሁሉም ተጨዋች ነው ሊወስድ የሚገባው፡፡

ሊግ፡- ቤትኪንጉ ሲጠናቀቅ ወላይታ ድቻ ውድድሬን በምን ስፍራ ላይ አጠናቅቃለው ነው ያለው?

ምንይህሉ፡- እንደ እቅድ ካለን ስብስብና 14 የሚደርሱ ታዳጊ ተጨዋቾችንም ከመያዛችን አንፃር ውድድሩን ስንጀምር በደረጃው ሰንጠረዥ የመሀል ሰፋሪ ሆነን እንጨርሳለን ነበር ያልነው፤ አሁን ላይ ደግሞ ውጤታችንን ስንመለከተውና ሜዳም ላይ በከፍተኛ የጨዋታ ፍላጎት መንቀሳቀሳችንን ሳይ የደረጃ ተፎካካሪ ሆነን የምንጨርስበት እድሉም ይኖረናል፡፡

ሊግ፡- ወላይታ ድቻ ላይ ምን ለውጥን ተመልክተሃል?

ምንይህሉ፡- ይሄ ቡድን ከሊጉ ላለመውረድ የሚጫወት ቡድን ነበር፤ አሁን ደግሞ አሰልጣኙ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም በሚሰጠን የጨዋታ ታክቲክና ልምድ ያለው ደጉ ደበበም በአንድ አንድ በሚረዳን ምክሮቹ  በመመራትና በቁርጠኝነትም ስራችንን ስለምንሰራ በቡድኑ ላይ ከፍተኛ ለውጦችን ልመለከት ችያለው፡፡

ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ወላይታ ድቻን በምትፈልገው መልኩ እየጠቀምከው ነው?

ምንይህሉ፡- እስካሁን በምችለው አቅም ቡድኑን እያገለገልኩት ቢሆንም በበፊቱ ምርጥ አቋሜ ላይ ግን ገና አልተገኘሁም፤ ለወላይታ ድቻ አሁን እየተጫወትኩ የምገኘው በምታወቅበት ቦታዬ ላይ አይደለም፤ በእርግጥ አንድ ተጨዋች አሰልጣኙ በሚሰጠው ቦታ ሁሉ ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባልና በቀጣይነት እንግዲህ ለቡድኑ ከእኔ የሚጠበቀውን ነገር ሁሉ ለመስጠትና ቡድኑንም ውጤታማ ለማድረግ እየተዘጋጀው ነው የምገኘው፡፡

ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የዘጠኝ ሳምንታቶቹ ጨዋታዎች ለአንተ ለየት ያለውና ምርጡ  የነበረው ቡድን ማን ነው?

ምንይህሉ፡- ለየት ያለብኝ ቡድን እንኳን የለም፤ ያም ሆኖ ግን አዳማዎች ምንም እንኳን ውጤት ባይቀናቸውም ባሳዩት አጨዋዋት እነሱ ከሌሎቹ የተሻሉ ነበሩ፡፡

ሊግ፡- ባሳለፍነው ዓመት የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር /አቡኪ/ በየጨዋታዎቹ ጎልቶ ወጥቶ ነበር፤ አሁንስ በእሱ ደረጃ የተመለከትከው ተጨዋች አለ?

ምንይህሉ፡- የለም፤ አሁንም እሱ የጨዋታ ጫና ስለበዛበት እንጂ ተሸሎ የሚገኘው ተጨዋች እሱ ነው፡፡

ሊግ፡- ወላይታ ድቻን አጠር ባለ ቃላት ግለፀው ብትባል ምላሽህ ምን ይሆናል?

ምንይህሉ፡- አንድነትና ፍቅር ያለው ጥሩ ቡድን ነው፤ ከቦርድ አንስቶ ኮቺንግ ስታፉና ተጨዋቾቹ ጋር ያለው መግባባትም ደስ ይላል፤ ጥሩ ድጋፍንም ክለቡን ከሚወዱት ደጋፊዎቻችን እያገኘንም ይገኛልና ይሄ ለቡድኑ ቀጣይ ጉዞ በጣም ይጠቅማል፡፡

ሊግ፡- ከካሜሮኑ ውድድር ስለተሰናበቱት ዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ እናምራ፤ እንዴት አገኘካቸው?

ምንይህሉ፡- በውድድሩ ጥሩ ቡድን እንዳለን አሳይተናል፤ ተጨዋቾቹ የሚችሉትንና ያላቸውን አቅምም አውጥተው ተጫውተዋል፤ ቴክኒኩም ላይ ጥሩ ነን፤ ያም ሆኖ ግን በተቃራኒነት እንደ ተጋጣሚዎቻችን  በሁሉም መልኩ አንድ ፕሮፌሽናል ተጨዋች ሊያሟላ ከሚፈለጉት ነገሮች ውስጥ አንድ አንዱ እኛ የሌለን መሆኑና እንደ እነሱ ፐርፌክት አለመሆናችን እንደዚሁም ደግሞ ትላልቆቹን የጨዋታውን ሰራማም ሜዳም ያለመላመድ ችግሮች እኛን ሊጎዱን ችለዋል፡፡

ሊግ፡- በዋልያዎቹ የአፍሪካ ተሳትፎ ዙሪያ ሌላስ የእኛ ችግር አልነበረም?

ምንይህሉ፡- ጥሩ ኳስ እንጫወት እንጂ ችግርማ አለ እንጂ፤ ከላይ ከገለፅኩት በተጨማሪ  በመከላከል አደረጃጀት ላይ፣ በመከላከል አቋቋም ላይና ግብ ጠባቂም ከጊዜ አጠባበቅ ጋር በተያያዘ የታዩ ችግሮች ስላሉ እነዚህን መቅረፍ ከቻልን ወደፊት ዋልያው ጠንካራና አስፈሪ ቡድንን መገንባት ይችላል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P