Google search engine

“መቐለ 7ዐ እንደርታ በሜዳው ብቻ ሳይሆን ከሜዳው ውጪም ማሸነፍ የሚችል ቡድን ነው፤ የሊጉን ዋንጫ እናነሳለን” ዮናስ ገረመው /መቐለ 70 እንደርታ/

የመቐለ 70 እንደርታ እግር ኳስ ክለብን በአማካይ ስፍራ ላይ እያገለገለ የሚገኘው ተደናቂው የመሀል ሜዳ ተጨዋች ዮናስ ገረመው /ሀላባ/
የዘንድሮውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ክለባቸው እንደሚያነሳ እና ቡድናቸው ግጥሚያዎችን በሜዳው ብቻ ሳይሆን ከሜዳው ውጪም ማሸነፍ
እንደሚችል አስተያየቱን ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ ሰጥቷል፡፡
የመቐለ 70 እንደርታ ክለብ የፕሪምየር ሊጉን የውድድር ተሳትፎው ደደቢትን 4-1 ካሸነፈ በኋላ ከተከታዩ ክለብ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ
ልዩነት ወደ 8 ቢያሰፋም ይሄ ልዩነት እንደማያኩራራቸው እና ቀጣይ ስራቸው ላይ በማተኮር የሀገሪቱን ዋንጫ ለማንሳት እንደተዘጋጁም ሀሳቡን
ጨምሮ ጠቅሷል፡፡
የመቐለ 70 እንደርታን የሊግ ጉዞ እና ለሻምፒዮናነትም ስለሚኖራቸው እድል የቡድኑ ተጨዋች የሆነውን ዮናስ ገረመውን አናግረን የሰጠን ምላሽ
የሚከተለውን ይመስላል፡፡

ሊግ፡- የመቐሌ 70 እንደርታን የፕሪምየር ሊግ ጉዞ እንዴት ትገልፀዋለህ? ሊጉን በሰፊ የነጥብ ልዩነት ከመምራታችሁስ አኳያስ ዋንጫውን
ለማንሳት የሚኖራችሁ እድል የቱን ያህል ነው?’

ዮናስ፡- በፕሪምየር ሊጉ ክለባችን እየሄደበት ያለው የውድድር ጉዞ በ8 የነጥብ ልዩነት ተከታያችንን በመምራት ላይ በምንገኝበት ደረጃ ላይ ስለሆንን
ለእኛ ጥሩ የሚባል ነው፤ በዚህ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ የቻልነውም ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችን ስለያዝን እና ጠንክረንም ስለሰራን ነው፤ ያም ሆኖ ግን
ውድድሩ ገና ያላለቀ እና በርካታ ጨዋታዎችም የሚቀሩት ከመሆኑ አንፃር በ8 ነጥብ መራን ብለን የምንኩራራበት አንዳችም ምክንያት ስለሌለ
ለቀጣይ ጨዋታዎቻችንን ትኩረት ሰጥተን ግጥሚያዎቻችንንም በማሸነፍ የዘንድሮ የውድድሩ ሻምፒዮና እንሆናለን፡፡

ሊግ፡- የመቐለ 70 እንደርታን ለውጤታማነት እያበቃው ያለው ዋናው ጥንካሬው ምንድን ነው?
ዮናስ፡- የሊጉን ውድድር ለመምራትና 10 ተከታታይ የሆኑ ጨዋታዎችንም በማሸነፍ በአሁን ሰዓት በጥሩ አቋም ላይ ለመገኘት የቻልንበት ዋነኛው
ጥንካሬያችን እያንዳንዱን ጨዋታዎቻችንን እንደ ቡድን በመጫወት ስለምንንቀሳቀስ ነው፡፡ ከዛ ውጪ የአሰልጣኛችንን ገ/መድህን ኃይሌን የጨዋታ
ታክቲክ በሚገባ ስለምንተገብርለት እንደዚሁም ደግሞ እሱ እያንዳንዱን ተጨዋቾች ማኔጅ የሚያደርግበት የተለየ መንገድ ስላለው ይህ ለውጤታማነት
ሊያበቃን ችሏል፡፡

ሊግ፡- መቐለ 70 እንደርታ በሊጉ የተለየ አጨዋወት አለው?

ዮናስ፡- እንደዛ ብዬ ነው የማስበው፡፡ የተለየ አጨዋወት ስላለንም ነው ሊጉን እየመራን የምንገኘው፡፡ የእኛ አጨዋወትም ኳስን መቆጣጠርና
በፍጥነትም አጥቅቶ መጫወቱ ላይ ነው፡፡ አላማ ያለው ኳስም ነው የምንጫወተው፡፡ ሁሌም ጎሎችን በማስቆጠር ግጥሚያዎችን ለማሸነፍም
የምንጫወት ስለሆነ ይሄ ይለየናል፡፡

ሊግ፡- መቐለ በመሪነት ላይ የተቀመጠው ብዙ የሊጉ ጨዋታዎችን በሜዳው ስላሸነፈ ነው 2ኛው ዙር ላይ ከሜዳው ሲወጣ ይቸገራል የሚሉ አሉ…
ዮናስ፡- ይሄን አባባል አልስማማበትም፡፡ በመጀመሪያው ዙርም ከሜዳችን ወጥተን አሸንፈናል፡፡ አሁንም ከሜዳችን ስንወጣ አሸናፊ የሚያደርገንን
ጠንካራ ቡድን ስለገነባን በዚህ በኩል ምንም አይነት ስጋት የለብንም፡፡

ሊግ፡- ለመቐለ 70 በሊጉ ቀጣይ ውድድሮች ምን አይነት አስተዋፅኦ ታበረክታለህ?

ዮናስ፡- የሊጉን ዋንጫ አምና ከጅማ አባጅፋር ጋር ማንሳት ችያለሁ፡፡ ያኔ ጥሩ እና ምርጥ የሆነ ብቃቴን ማሳየት ችያለሁ፡፡ ዘንድሮ ደግሞ የሊጉን
ዋንጫ ዳግም ማንሳት ስለምፈልግ ለክለቤ መቐለ ከፍተኛ አስተዋፅኦን በሜዳ ላይ በማድረግ ቡድኔን ለውጤት አበቃለሁ፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ

ዮናስ፡- የመቐለ ደጋፊዎች ዘንድሮ ባደረግነው የሊጉ ውድድር እንደ 12ኛ ተጨዋች በመሆን ለእኛ ምርጥ ድጋፋቸውን እየሰጡን ነው፡፡ የእነሱን ድጋፍ
በከፍተኛ ሁኔታ እንድንነሳሳ ስላደረገን በጣሙን ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P