Google search engine

“መከላከያን ለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን የሲቲ ካፑንም ዋንጫ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል” /የአብስራ ተስፋዬ /ቅ/ጊዮርጊስ/

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬ ቅ/ጊዮርጊስ ከመከላከያ ባህር ዳር ከተማ ከወልቂጤ ከተማ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል


የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በገቢ ለማጠናከር ከዛ ውጪ ደግሞ ተወዳዳሪ ቡድኖች የራሳቸውን አቋም እንዲለኩበት ታስቦ የሚዘጋጀው ዓመታዊው የሲቲ ካፕ ዋንጫ ዘንድሮም ለ14ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ይኸው ውድድር ከዛሬ አንስቶም በድምቀት ይከናወናል፤ የሲቲ ካፑ ዋንጫ ሊጀመር የነበረው ባለፈው ሳምንት ቢሆንም በሀገሪቱ ከሚታየው የፀጥታ ችግር አኳያ ውድድሩ ለዛሬ ሊተላለፍ ችሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬ በይፋ ሲጀመርም የመጀመሪያ ተጋጣሚ ሆነው የሚቀርቡት ቡድኖች የምድብ አንድ ተፎካካሪ ክለቦች የሆኑት ተጋባዦቹ ባህር ዳር ከተማና ወልቂጤ ከተማ ሲሆኑ ጨዋታቸውንም ከ8 ሰዓት አንስቶ ያደርጋሉ፤ በቅዱስ ጊዮርጊስና በመከላከያ ክለቦች መካከል የሚካሄደው ሌላው የእዚህ ምድብ ተጠባቂ ጨዋታም ከቀኑ 10 ሰዓት አንስቶ ይከናወናል፡፡
የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫ የሌላው ምድብ ጨዋታም ነገ የሚቀጥል ሲሆን ከምድብ ሁለት በ8 ሰዓት ኢትዬ-ኤሌክትሪክ ከተጋባዡ ክለብ ወልዋሎ አዲግራት ጋር በ8 ሰዓት ጨዋታውን ሲያደርግ በ10 ሰዓት ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና ከሌላው ተጋባዥ ቡድን ሰበታ ከተማ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ የሚጠበቅ ሆኗል፡፡
የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ የዘንድሮ ውድድር ከፀጥታም ሆነ ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ውድድሩ በሰላም ተጀምሮ በሰላም የሚጠናቀቅበትን ነገር በሜዳ ላይ ለማሳየት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከየክለቦቹ የደጋፊ አስተባባሪዎች ጋር የቅድመ ዝግጅትን ውይይት ያደረጉ ሲሆን የእዚህ ዓመት ውድድርም በጥሩ መልኩ እንዲጠናቀቅም ሁሉም የስፖርት አፍቃሪም የየራሱን ድርሻ እንዲወጣም መልዕክት ሊተላለፍ ችሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ /ሲቲ/ ካፕ ዋንጫን ጅማሬ በማስመልከት ከተሳታፊ ክለባት አንድ አንድ ተጨዋቾች ጋር ቡድናቸው በሚያደርገው ጨዋታ ዙሪያና ስለ ዘንድሮ አጠቃላይ የውድድር ዘመን የዝግጅት ጊዜ ቆይታቸው ያናገርናቸው ሲሆን ተጨዋቾቹም የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፤ ተከታተሏቸው፡፡

“መከላከያን ለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን የሲቲ ካፑንም ዋንጫ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል”
/የአብስራ ተስፋዬ /ቅ/ጊዮርጊስ/
የእስካሁን የፕሪ ሲዝን ዝግጅታቸውን በተመለከተ
“ቅ/ጊዮርጊስ በቢሾፍቱ ከተማ ተቀምጦ ላለፉት ሁለት ወራት ሲሰራ የነበረው የቅድመ ሲዝን ዝግጅቱ በጣም ጥሩ ሲሆን በቆይታችንም መልካም የሚባል ጊዜያትንም ነው ያሳለፍነው፤ በእዚህ ዝግጅትም በአዲሱ የክለባችን አሰልጣኝ እየተሰጠን ያለው ልምምድም እሱ ውጤታማና ጥሩ ቡድን ከመስራት ባሻገርም ኳስንም በሚገባ እንድጫወት የሚፈልግ ባለሙያ በመሆኑ የእዚህ ዓመት የውድድር ተሳትፎአችንን በስኬታማነት ውጤት የምናጠናቅቅም ይመስለኛል”፡፡
ቅ/ጊዮርጊስን ስለተቀላቀሉት የውጪ ሀገር ተጨዋቾች
“ቅ/ጊዮርጊስ በፕሮፌሽናል ደረጃ ያስመጣቸው የውጪ ሀገር ተጨዋቾች ከሞላ ጎደል በፊት አጥቂነት ሚና የሚጫወቱ ተጨዋቾች በመሆናቸው የእነሱ እኛን መቀላቀል የክለባችንን ክፍተት ከመሸፈን ባሻገር በዚህ አመት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ጠንካራ እና የተሟላ ውጤታማ ቡድንን እንድንፈጥር እገዛን ያደርጉልናል ብዬ አስባለሁ”፡፡
የቅ/ጊዮርጊስ የተጨዋቾች ስብስብን በተመለከተ እና ቡድኑ የት ድረስ እንደሚጓዝ
“የእዚህ ዓመት የተጨዋቾች ስብስባችንን በፕሪ ሲዝን ጅማሬ ዝግጅታችን ላይ እንደተመለከትኩት በጣም አሪፍ ነበር፤ በመሃል ላይ ግን በአንድ አንድ ተጨዋቾቻችን ላይ ማለትም በሳላህዲን ሰይድ፣ በናትናኤል ዘለቀ እና በያቤል ያለው ላይ የደረሱት ጉዳቶች አሁን ላይ ለጊዜው ተፅዕኖን ሊፈጥርብን ቢችልም እነሱ ሙሉ ለሙሉ ከጉዳታቸው አገግመው ሲመለሱ መልሶ በምርጥ ስብስባችን ላይ እንደምንገኝ አምናለውኝና በእዚያ በኩል ብዙም ስጋት የለብንም፤ አሁን እንደውም ሳላህዲን ከጉዳቱ ድኖ የተመለሰልን የመጀመሪያው ተጨዋችም ሊሆን ችሏል፤ ሌሎቹም በቅርቡ ይመለሱልናል”፡፡
ቅ/ጊዮርጊስ በዘንድሮው የፕሪምየር ሊጉ የውድድር ዘመን ተሳትፎው አስፈሪ ይሆናል?
“አዎን፤ ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ ነው፤ ጉዳት ላይ ያሉት ተጨዋቾች ሙሉ ለሙሉ አገግመው በፍጥነት ወደሜዳ የሚመለሱ ከሆነ በሁሉም ነገር የተሻለ የሚባል ቡድንን ነው በልምምዳችን ላይ ከሰራነው ጠንካራ ልምምድ አኳያ ይዘን ለመቅረብ የተዘጋጀነውና ይሄን ነው ለመናገር የምፈልገው”፡፡
ቅ/ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ስለሚኖረው የውድድር ተሳትፎውና እሱም በእዚህ ውድድር ላይ ከዚህ ቀደም ተካፍሎ እንደሆነ
“የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጀው የሲቲ ካፕ ውድድር ላይ ከዚህ ቀደም ነፍሱን ይማረውና የቡድናችን አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ በነበረበት ዘመን የደደቢት ተጨዋች ሆኜ ተካፍያለሁ፤ የአሁኑ ተሳትፎዬም ዳግመኛ ነው የሚሆነውና የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን መለያ አጥልቄ በምጫወትበት የእዚህ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ተሳትፎዬ ላይ ይሄን ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳት ነው የምጫወተው፡፡ ቡድኔም ከሰራው ጠንካራ ልምምድ አንፃር ይሄን ዋንጫ ለማግኘት በጣሙን ዝግጁ ነው”፡፡
ቅ/ጊዮርጊስ የአ/አ ከተማ ዋንጫን የመክፈቻ ጨዋታ ከመከላከያ ጋር ያደርጋል፤ቡድናችሁ በግጥሚያው ምን ውጤትን ያስመዘግባል? የአ/አ ስታድየምስ ናፍቆሃል?
“የአዲስ አበባ ስቴድየም አዎን ናፍቆኛል፤ ምክንያቱም በእዚህ ሜዳ ላይ የደደቢት ክለብ ተጨዋች ሆኜ ከተጫወትኩ ረጅም ያለ ጊዜያትን ስላስቆጠርኩ ነው፤ ደደቢት መቀመጫውን መቀሌ ካደረገበት ጊዜ አንስቶ የአዲስ አበባ ስቴድየም ሜዳ ላይ ኳስን የተጫወትኩት ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ከኢትዮጵያ ቡናና ከመከላከያ ጋር ብቻ ነው፤ ይህ ደግሞ ረዘም ያለ ጊዜን ስላስቆጠረ ከብዙ ጊዜያት በኋላ ዳግመኛ በእዚህ ሜዳ ላይ መጫወቱ በጣሙን አጓጉቶኛልና የዛሬውን የቅዳሜ ጨዋታ በጥሩ ብቃት ጭምር ለመጫወት ዝግጁ ሆኛለሁ፡፡
ከመከላከያ ጋር የሚኖረንን የመክፈቻ ጨዋታ በተመለከተ ግጥሚያውን ለማሸነፍ በሚገባ ተዘጋጅተናል፤ የእኛ ዋንኛው አላማም መከላከያን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን የሲቲ ካፑንም የአቋም መለኪያ ውድድር ማሸነፍ ነውና ያን እየጠበቅን ነው፤ በውድድሩ ደግሞ ይሄን ዋንጫ እኛ አገኘን ማለት ለፕሪምየር ሊጉም የውድድር ሻምፒዮንነት መነሻ ይሆንልናልና የጨዋታው መጀመር በጣሙን አጓጉቶናል”፡፡
በቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ልትጫወት ተዘጋጅተሃል፤ እነሱን በምን መልኩ ነው የምትገልፃቸው?
“የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን በተመለከተ ከእዚህ ቀደም በጣም እንደምወዳቸውና እንደማከብራቸውም ነግሬያለሁ፤ ከእነሱ ጋር በተቃራኒነት ሆኜም ስጫወት በአደጋገፋቸው የሚስቡኝም ናቸውና አሁን ላይ ደግሞ በእነሱ ፊት ቆሜ ልጫወት ስለተዘጋጀው በጣሙን ነው ደስ የሚል የመንፈስ ስሜት እየተሰማኝ የሚገኘው፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ክለባቸውን ሲያበረታቱ በጣም ነው ደስ የሚሉት በዚህ ዓመትም በልዩ እና በአማረ ድጋፋቸው ስለሚያበረታቱን የተለያዩ ዋንጫዎችን እንድናነሳ ትልቁን አስተዋፅኦ ነው የሚያደርጉልን”፡፡
የቅ/ጊዮርጊስ ተጨዋች ሆነሃል፤ ከእዚህ በኋላስ ምን አይነት ተጨዋች ሆነህ ነው የምትቀርበው?
“የእግር ኳስ ጨዋታን አሁን ላይ ገና ጀምሬዋለሁ፤ ከእዚህ በኋላ ደግሞ ለትልቅ ቡድን ልጫወት እየተዘጋጀሁ ከመሆኔ አንፃር የሀገሪቱ ምርጥ ተጨዋች በሚባል ደረጃ ላይ ለመድረስ እና ብሎም ደግሞ ብቃቴን በየጊዜው በማሻሻል ለብሄራዊ ቡድን ልጠራ የምችልበትንም ጠቋሚ መንገድ ለመፈለግ ሁኔታዎችን እያመቻቸው ነው የምገኘው”፡፡


spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P