በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ታሪክ ጥሩ እግር ኳስን ከሚጫወቱ ቡድኖች መካከል አንዱ ለሆነው መከላከያ በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ፊርማውን ያኖረው አስናቀ ሞገስ በአዲሱ የውድድር ዘመን ለቡድኑ ስኬታማ ግልጋሎትን እንደሚሰጥና ክለቡም ጥሩ ውጤት እንደሚያመጣ ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ አስተያየቱን ሰጥቷል፤ የባህር ዳር ከተማ ክለብ ውስጥ የነበረውን የውል ጊዜ የጨረሰው እና ወደ መከላከያም ያመራው አስናቀ ስለ አዲሱ ቡድኑም ጠይቀነው በሰጠን ምላሽ “መከላከያ ጥሩ ቡድንና ኳስንም በአማረ መልኩ የሚጫወት ነው፤ ጥሩ የተጨዋቾችንም ስብስብ ይዟል፤ በስኳዱ የያዛቸው ተጨዋቾችም ወጣቶችና በጥሩ ፍላጎትም ልምምድን የሚሰሩ ናቸው” ካለ በኋላ በእግር ኳስ ተጨዋችነቱ ስላሳለፋቸው ጊዜያቶች እንደዚሁም ደግሞ በአዲሱ ቡድኑ ስለሚኖረው ቆይታና ሌሎችንም ጥያቄዎች አቅርበንለት ምላሾቹን ከዚህ በታች ሰጥቷል፡፡
ከልጅነት ዕድሜው አንስቶ እስከ አሁን ተጫውቶ ስለመጣባቸው ዓመታቶች
“የእግር ኳስን ተጫውቼ የመጣሁባቸው የእስካሁን ዓመታቶች ለእኔ ትልቅ ግብአት የሆኑኝና ጥሩ ትምህርትም ሰጥተውኝ ያለፉ ናቸው፤ በታዳጊነት ዕድሜዬ ኳስን በአሰልጣኝ ደረጀ ተስፋዬ /አንገቴ/ በሚሰለጥነው የጌታ ዘሩ የታዳጊ ፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ስጫወትም ሆነ በኋላ ላይ ለአክረምና ልጆቹ ቡድን ስጫወት ጠንክሬ መስራት ከቻልኩ ወደ ክለብ ደረጃ ገብቼ መጫወት እንደምችል አስብኩና ያን በተግባር ላይ በማዋል ህልሜን ማሳካት ቻልኩ፤ በክለብ ደረጃም የደደቢት የታዳጊና የወጣት ቡድን ውስጥ እንደዚሁም ደግሞ ለኢትዮጵያ ቡናም የተስፋው ቡድን ስጫወት በቀጣይነት በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ለመጫወት የሚያስችለኝ አቅም እንዳለኝ ተረዳውና ይሄንን ለማሳካት መንገዱን በመጀመር ለቡና በመቀጠል ደግሞ ለባህር ዳር ከተማ ክለቦች ልጫወት ቻልኩ፤ በእነዚህ ቡድኖች የተጨዋችነት ቆይታዬም ኳሱን ስጫወት የገጠሙኝ ጥሩም ሆነ አስቸጋሪ የነበሩ ጊዜያቶችን ተመልክቻለሁና ሁኔታዎቹን እንደ አጠቃላይ ስመለከታቸው አሁን የደረስኩበትን ደረጃ በጥሩ መልኩ ነው የምገልፀው”፡፡
የእግር ኳሱን ሲጫወት በጥሩ መልኩና በአስቸጋሪነቱ ስለላሳለፋቸው ጊዜያቶች
“የእግር ኳስ ተጨዋቾች በጨዋታ ዘመናቸው ጥሩ ጊዜያቶችን እንደሚያሳልፉ ሁሉ ሁሌም ደግሞ ነገሮች አልጋ በአልጋ አይሆንላቸውም፤ እኔም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከመጣሁበት ሰአት አንስቶ ለኢትዮጵያ ቡና ስጫወት በመሰለፍና ባለመሰለፍ ዙሪያ የተቸገርኩበት አጋጣሚ ስለነበር በውሰት ለባህር ዳር ከተማ እስከመሰጠት ደርሻለሁና ያን የምረሳው አይደለም፤ ዳግመኛ ወደ ቡና ተመልሼ ከመጣሁ በኋላም የመጫወት ዕድል ያገኘሁባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም መልሶ ተሰልፎ የመጫወት አጋጣሚውን ሳጣ ደግሞ አቋሜን ለማስተካከል በጣም የጣርኩበትና በኋላም ላይ ከቡና ጋር የተለያየሁበት አጋጣሚም ነበርና እነዚህ የኳስ ባህሪያቶች ናቸው፤ የኳሱ ሕይወቴ ላይ በቡና ቆይታዬ እንደፈለግኩት በተሳካ መልኩ ጊዜዬን ባላሳልፍም ወደ ባህር ዳር ከተማ ክለብ ካመራሁበት ጊዜ አንስቶ ግን እንደ ግልም እንደ ቡድንም ጥሩና የተሳካ የውድድር ዘመን ቆይታን ያሳለፍኩበት ጊዜ ስለነበር ይሄ በጣም የሚያስደስተኝ ነው”፡፡
ስለቀጣይ ጊዜ የኳስ ህይወቱ
“የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ሁሌም ኳስን ስትጫወት የመጀመሪያ እልምና ምኞትህ ለብሄራዊ ቡድን በመመረጥ በሀገር ደረጃ መጫወት መቻል ነው፤ ያን እድል ካገኘህ በኋላ ደግሞ ሌሎችን ማለትም ከሀገር ውጪ ወጥተህ ስለመጫወትም ታስባለህ”፡፡
ከባህር ዳር ከተማ ወደ መከላከያ ስለማምራቱና በቡድኑ ስለሚኖረው ቆይታ
“መከላከያን በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ከባህር ዳር ከተማ ክለብ በመምጣት የተቀላቀልኩት ቡድኑ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሜዳ ላይ የሚያሳየው እንቅስቃሴ ጥሩ በመሆኑና የእኔ የትወልድ ስፍራዬም አዲስ አበባ ከመሆኑ አኳያ የቡድኑ መገኛ ለቤተሰቦቼ ቅርብ ሆኜ የምጫወትበት አጋጣሚ ስለተፈጠረልኝ ነውና በእዚህ ቡድን በሚኖረኝ ቆይታዬም ጥሩና የተሳካ የውድድር ዘመንን ለማሳለፍ ተዘጋጅቻለሁ፤ መከላከያንም ለውጤት ማብቃት ቀዳሚው ግቤ ነው”፡፡
ስለ አዲሱ ቡድኑ መከላከያ እና ምን ውጤትን ለማስመዝገብ እንደተዘጋጁ
“መከላከያ ጥሩ ቡድን ነው፤ መልክ ያለው ኳስን ይጫወታል፤ ጥሩ የተጨዋቾችን ስብስብም ይዟል፤ ከዛ ውጪም አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች ወጣቶችና በጥሩ ፍላጎትም ልምምድን የሚሰሩ ናቸውና ስለ ክለቡ ይሄን ነው ማለት የምፈልገው፤ ቡድኑ ዘንድሮ ስለሚያመጣው ውጤት ደግሞ አሁን ላይ የፕሪ ሲዝን ዝግጅታችንን በጥሩ መልኩ ጀምረናል፤ ክለቡ ዓምና የሚመጥነውን ውጤት አላስመዘገበም፤ ዘንድሮ ግን ይሄ አይደገምም፤ የተሳካ ውጤትን በእዚህ ዓመት እናስመዘግባለን”፡፡
በእግር ኳስ ተጨዋችነቱ አሁን ላይ ስላለው ወቅታዊ አቋም
“በእግር ኳሱ አሁን ላይ ስለምገኝበት አቋም ስለራሴ እንዲህ ነኝ ብዬ አላወራም፤ ስለ እኔም መግለፅ የሚችሉት የቡድን አጋር ጓደኞቼና አሰልጣኞቼ ናቸው፤ ይሄ ደግሞ በደንብ ሊታወቅ የሚችለው አሁን ሳይሆን በፕሪ ሲዝን በምናደርገው ዝግጅት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ስናደርግ ነውና ለእዛ ያድርሰን እላለው”፡፡
በመጨረሻ……
“የኢትዮጵያ እግር ኳስ ባሳለፍናቸው ጥቂት ዓመታቶች ከፍተኛ የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰቶች እየታዩበት የመጡና እግር ኳሱንም ወደአላስፈላጊ ነገሮች እየወሰዱት ነውና በቅድሚያ ሁላችንም ከእንደዚህ አይነቶቹ ድርጊቶች ልንቆጠብ ይገባል፤ ይሄን ካልኩ የሊጉ የውድድር ጉዞ ዓምናም ሆነ ከዚህ በፊት ከፍተኛ ችግሮች እየተፈጠሩበት በመሆኑ አሁን ላይ ሊጉ በየቱ የውድድር ፎርማት እንደሚካሄድ እስከአሁን ድረስ የታወቀ ነገር የለምናስለ ውድድሩ እንደተጨዋችነቴ እኔ ማለት የምፈልገው ቅድሚያ ለሃገራችን የእግር ኳስ ስፖርት እድገት ሊበጅ የሚችል እና ከምንም ነገርም የፀዳ ሰላማዊ የሆነ ውድድር ይሁን እንጂ በሌላ ነገር ችግር የለብኝም፤ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከዚህ ቀደም ከመባሉ በፊት ክለቦች በየክልላቸው ከተጫወቱ በኋላ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና የሚባል ውድድር እንደነበር ሰምቻለው፤ በእዚያ ላይ ይሳተፉም ነበር፤ ያኔ ውድድሩ መልካምም መጥፎም ሆኖ ሊሆን ይችላል፤ እግር ኳስ ግን ሁሌም መዝናኛ ስፖርት ስለሆነ ለእኛ ምርጫችን ሊሆን የሚገባው የእግር ኳስ ስፖርት አፍቃሪው ከስጋት ነፃ ሆኖ ጥሩ ኳስን የሚመለከትበትና ሀገራችንም ልታድግ የምትችልበትን ውድድር ነውና ያን ለማየት ያብቃን ፈጣሪም ይርዳን”፡፡