Google search engine

“መከላከያን የዋንጫው ባለቤትነት ልናደርገው ተዘጋጅተናል” ቴዎድሮስ ታፈሰ /መከላከያ/

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/


በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ 7 ክለቦች ግማሽ ፍፃሜውን ለመቀላቀል ዛሬና ነገ ይጫወታሉ
የ14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬና ነገ በሚደረጉት አራት ግጥሚያዎች የሚጠናቀቁ ሲሆን በእዚሁም መሰረት ዛሬ ቅዳሜ በ8 ሰአት መከላከያ ከወልቂጤ ከተማ የሚያደርጉት እና በ10 ሰአት ደግሞ ባህር ዳር ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል፡፡
የእነዚህ ሁለት ጨዋታዎች ውጤትም ወደ ግማሽ ፍፃሜ የሚያልፉትን ሁለት ቡድኖችም ያሳውቃል፡፡ በእስካሁኑ ጨዋታ መከላከያ ብዙ ጎል አገባ በሚለው ህግ በ4 ነጥብ እና በ1 ግብ ምድቡን ሲመራ ባህር ዳር ከተማ ደግሞ በተመሳሳይ ነጥብና ጎል ተከታዩን ስፍራ ይዟል፡፡ ቅ/ጊዮርገስ በ3 ነጥብና በ1 ጎል ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ወልቂጤ ከተማ ያለምንም ነጥብ 3 የግብ እዳ ኖሮበት የመጨረሻውን ስፍራ ይዞ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የሚያልፍበት እድሉ አክትሟል፡፡
ከሌላው ምድብ ደግሞ ሰበታ ከተማ በ4 ነጥብና በአንድ ግብ ምድቡን ሲመራ ኢትዮጵያ ቡና እና ወልዋሎ አዲግራት በተመሳሳይ ሶስት ነጥብና ያለምንም ግብ ተከታዩን ስፍራ ይዘው ይገኛሉ፤ ኤሌክትሪክም በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን ስፍራ ይዞ ይገኛል፤ በእዚሁም መሰረት ነገ በሚደረጉት የ8 ሰዓቱ የወልዋሎ አዲግራትና የሰበታ ከተማ እንደዚሁም ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናና የኤሌክትሪክ ጨዋታ ጥሩ ውጤት የሚያስመዘግበው ቡድን የግማሽ ፍፃሜውን ይቀላቀላል፡፡
የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ጨዋታዎችን አስመልክተን ከየክለቡ ተጨዋቾች ጋር ያደረግነው ቃለምልልስ በሚከተለው መልኩ ይቀርባል፡፡


ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስን በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ የመክፈቻ ጨዋታ ለማሸነፍ ችላችኋል፤ ግጥሚያው ምን መልክ ነበረው?
ቴዎድሮስ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብን ያሸነፍንበት የቅዳሜው ዕለት ጨዋታ ለእኛ ተጋጣሚያችንን በኳስ ቁጥጥር በልጠን ከመጫወታችን አንፃር እንደዚሁም ደግሞ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ እንደ ቡድን የተጫወትንበት ሁኔታ ስለነበር ግጥሚያው በጣም ጥሩ የሆነልን ነበር፤ ከዛ ውጪም የማሸነፍ መንፈሳችንም ከተጋጣሚያችን አኳያ ሲታይ በጣም ከፍተኛ ስለነበር ጨዋታውን ማሸነፍ መቻላችን የሚገባን ሆኖ ነው ያገኘነው፡፡
ሊግ፡- መከላከያ ቅ/ጊዮርጊስን ሲያሸንፍ ጠንካራ ጎኑ ምን ነበር ? ደካማ ጎኑስ?
ቴዎድሮስ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን ባሸነፍንበት ጨዋታ እኛ የነበረን ደካማ ወይንም ደግሞ ክፍተት ጎናችን ስናጠቃ በቁጥር እናንስ ነበር፤ ያን ማሻሻል አለብን፤ ጠንካራ ጎናችን ደግሞ ኳሱን ተቆጣጥረን መጫወታችን ነው፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስን በጨዋታው በምን መልኩ አገኘሃቸው?
ቴዎድሮስ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ እና ጠንካራ ቡድን ቢሆንም ከእኛ ጋር በነበረው የቅዳሜው ዕለት ጨዋታ ግን በአብዛኛው የጨዋታ እንቅስቃሴ እንደጠበቅናቸው አላገኘናቸውም፤ እነሱ የጨዋታው ሰዓት ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ጥሩ ለመሆን ሞክረው ነበር ያም ሆኖ ግን በጨዋታው እኛ የተሻልን ስለነበርን አሸንፈናቸዋል፡፡
ሊግ፡- መከላከያ ቅዱስ ጊዮርጊስን ባሸነፈበት ጨዋታ የግጥሚያው ኮከብ ተጨዋች ተብለህ ተሸልመሃል፤ ምን ስሜት ተፈጠረብህ?
ቴዎድሮስ፡- ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር በነበረን የሲቲ ካፑ ፍልሚያ የጨዋታው ኮከብ ተብዬ መሸለሜ እንደ ማንኛውም ተጨዋች እኔንም ለቀጣይ ፍልሚያዎች እንድበረታታ ስለሚያደርገኝ ያን ዕለት ሽልማቱ ሲሰጠኝ በጣም ነበር የተደሰትኩት፡፡
ሊግ፡- መከላከያ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያደረገውን የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ሁለተኛ ጨዋታውን በአቻ ውጤት አጠናቋል፤ ይህስ ጨዋታ ምን መልክ ነበረው? ውጤቱስ ለእናንተ በቂ ነው?
ቴዎድሮስ፡- የባህር ዳር ከተማ ክለብን የተፋለምንበትና አቻ የተለያንበት የረቡዕ ዕለት ጨዋታ የመጀመሪያው ቀን ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ስንጫወት ከነበረው ፍልሚያ አኳያ ስናነፃፅረው ሁለታችንም ጨዋታውን በማሸነፍና የግማሽ ፍፃሜውንም ለመቀላቀል ከነበረን ከፍተኛ ጉጉት አኳያ እንደዚሁም ደግሞ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ከነበረው ከፍተኛ ሙቀት የተነሳ በእንቅስቃሴው በኩል በተለይ ለእኛ ቡድን በጣም ከበድ ያለብን ነበር፤ እንዳዛም ሆኖ ግን የሁለተኛው አጋማሽ ላይ የእኛ ቡድን አስቀድሞ በተቆጠረበት ግብ ይመራ ስለነበር እና ተጋጣሚያችንም ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት በማሰብ ወደ ኋላ አፈግፍጎ ሊጫወት በመሞከሩ ቡድናችን ቶሎ ቶሎ ወደፊት አጥቅቶ ስለተጫወተ ግጥሚያውን በአቻ ውጤት ሊያጠናቅቅ ችሏል፤ የተገኘው ውጤትም ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሁለታችንም በቂ ሆኖም ታይቷል፡፡
ሊግ፡- ከወልቂጤ ከተማ ጋር በሚኖራችሁ የዛሬው የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ ማሸነፍና አቻ መውጣት ወደ ግማሽ ፍፃሜ ያስገባችኋል፤ ይህን ውጤት ታሳካላችሁ?
ቴዎድሮስ፡- የወልቂጤ ከተማ ክለብ ጋር የሚኖረንን የዛሬው ጨዋታ የምናከናውነው ተጋጣሚያችን ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ምንም አይነት ዕድል በሌለው ሰዓትና እኛ ደግሞ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ለመሸጋገር ዕድላችን የሚወሰነው ጨዋታውን በማሸነፍ እና አቻ በመለያየት ላይ የተወሰነ በመሆኑ ይህ ለቡድናችን በጣም ጥሩ የሆነ አጋጣሚ ነው፤ ስለዚህም የዛሬውን ጨዋታ በይበልጥ በማሸነፍ ላይ አተኩረን ወደ ሜዳ በመግባት ባለድል እንሆናለን፡፡
ሊግ፡- መከላከያ አሁን ላይ በሲቱ ካፑ የሚወዳደረው ከፕሪምየር ሊጉ በወረደበት ወቅት ነው፤ የውድድር ዓመቱ ዋንኛው እቅዳችሁ ምንድን ነው?
ቴዎድሮስ፡- መከላከያ በእዚህ ዓመት በከፍተኛው ሊግ የሚወዳደር ቡድን ቢሆንም የውድድር ዘመኑ ዋንኛው ዓላማው ይሄን ክለብ ወደነበረበት ፕሪምየር ሊግ መመለስ ነው፤ ለእዛም ነው በዋናነት እየተዘጋጀን የምንገኘው፤ ለእዚህም ሲባል አሁን እያከናወንን ባለነው የሲቲ ካፕ ውድድር ላይ አቋማችንን እየፈተሽን ነው የምንገኘው፤ አሰልጣኞቻችን የቡድኑን እያንዳንዱን ተጨዋቾች ወቅታዊ ብቃትም በሚገባ እየተመለከቱም ነውና ይሄ ግጥሚያ እኛን በጣም የሚረዳን ነው፤ የከፍተኛው ሊግ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ ደግሞ ውጤት ማምጣት ከፈለግን ከወዲሁ የምናደርጋቸው የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ላይም ሆነ የዋናው ውድድር ተሳትፎአችን ላይ ጠንካራ ቡድንን ይዘን መቅረብ ይጠበቅብናልና ያን ለማሳካትም ዝግጁ ነን፡፡
ሊግ፡- መከላከያን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ትመልሱታላችሁ?
ቴዎድሮስ፡- ከፈጣሪ እርዳታ ጋር አዎን፤ ቡድናችን ይህን እልሙን ለማሳካትም አቅሙ አለው፡፡
ሀትሪክ፡- በመከላከያ ክለብ ውስጥ በእዚህ ዓመት አንተን እንዴት እንጠብቅህ?
ሊግ፡- የመከላከያ ክለብ ውስጥ ባለኝ የተጨዋችነት ቆይታዬ ማንኛውም ተጨዋች የተሻለ ነገርን ለማግኘት እንደሚተጋ እና ያለውንም ሲቪ ከፍ ለማድረግ ጠንክሮ እንደሚሰራ ሁሉ እኔም በጥሩ አቋም ላይ በመገኘት በአንድ ዓመት ውስጥ ወደታችኛው ሊግ የወረደውን ክለቤን በጋራ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማሳለፍ በጣሙን ዝግጁ ነኝ፤ ከእዛ ውጪም በግሌም የውድድር ዓመቱ ላይ ምርጥ ተጨዋች ለመባልም ፍላጎቴ ከፍተኛ ነው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…. ?
ቴዎድሮስ፡- መከላከያ በሲቲ ካፑ የውድድር ተሳትፎው አሁን ላይ አቋሙን በሚገባ በመለካት ላይ ይገኛል፤ የመጀመሪያ ጨዋታውንም በድል ተወጥቷል፤ ከዚህ በኋላ በሚኖሩት ጨዋታዎች ደግሞ ለእያንዳንዱ ቡድን እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉ ከፍተኛ ግምት ሰጥተን በመግባት መከላከያን እስከ ፍፃሜው ብሎም ደግሞ እስከ ዋንጫው ባለቤትነት ልናደርሰው በሚገባ ተዘጋጅተናል፡፡ ከዛ ውጪም ዋናው ፍላጎታችን ወደ ፕሪምየር ሊጉም መምጣትም ነውና ያንም የምናሳካው ይሆናል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P