Google search engine

መከላከያ ከባህርዳር ከተማ ለ15ኛው የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫ ይፋለማሉ”የሲቲ ካፑን ዋንጫ ከማንሳት ባሻገር የተሻለ ቡድን እንዳለንም እናሳያለን”ገናናው ረጋሳ /መከላከያ/”መከላከያን በኳስ በልጠን ዋንጫውን ለማንሳት ዝግጁ ነን”ፉዐድ ፈረጃ /ባህርዳር ከተማ/

መከላከያ ከባህርዳር ከተማ 15ኛው የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫ ይፋለማሉ

“የሲቲ ካፑን ዋንጫ ከማንሳት ባሻገር የተሻለ ቡድን እንዳለንም እናሳያለን”

ገናናው ረጋሳ /መከላከያ/

“መከላከያን በኳስ በልጠን ዋንጫውን ለማንሳት ዝግጁ ነን”

ፉዐድ ፈረጃ /ባህርዳር ከተማ/

የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በገቢ ለማጠናከርና ብሎም ደግሞ የውድድሩ ተሳታፊ ቡድኖች ራሳቸውን ለቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በደንብ እንዲያዘጋጁበት ታስቦ ሲካሄድ የሰነበተው 15ኛው የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫ በነገው ዕለት ፍፃሜውን ያደርጋል፡፡

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊ የሆኑትን አራት የአዲስ አበባ ክለቦችን ጨምሮ በተጋባዥነት የእዚህ ውድድር ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ የተደረገላቸውን ክለቦችን ሲያሳትፍ የነበረው ይኸው ውድድር ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት ሲሆን ከእዛም በተጨማሪ በርካታ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ወጣት ተጨዋቾችንም ልንመለከትበት ችለናል፡፡

ይሄ ውድድር ከሁለት ሳምንት በፊት የምድብ አንድ ተወዳዳሪ የሆኑትን መከላከያን፣ ጅማ አባጅፋርን፣ ኢትዮጵያ ቡናንና አዲስ አበባ ከተማን እንደዚሁም ደግሞ የምድብ ሁለት ተወዳዳሪ የሆኑትን ባህርዳር ከተማን፣ ቅ/ጊዮርጊስን፣ አዳማ ከተማንና ፋሲል ከነማን ባሳተፈበት ሁኔታ ጨዋታዎቹ ተደርገው ከየምድቡ መከላከያንና ጅማ አባጅፋርን ከምድብ አንድ ቅ/ጊዮርጊስንና ባህርዳር ከተማን ከምድብ ሁለት ለግማሽ ፍፃሜው ያሳለፈ ሲሆን ረቡዕ ዕለት በተደረገው ጨዋታም ባህርዳር ከተማ ጅማ አባጅፋርን መከላከያ ቅ/ጊዮርጊስን በማሸነፍ ለነገው የፍፃሜ ጨዋታ ሊያልፉ ችለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ የረቡዕ የቅ/ጊዮርጊስና የመከላከያ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ የመከላከያው ግብ ጠባቂ ክሊመንት ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የእጅ ምልክትን አስፀያፊ በሆነ መልኩ በተደጋጋሚ ጊዜ በማሳየት የተሳደበበት መንገድ ብዙዎቹን ደጋፊዎች ስሜታቸውን እንዳይቆጣጠሩ ባደረገበት ሁኔታ በጣም ያስቆጣቸው ሲሆን ይሄም ድርጊት በመከላከያ በኩል አስፈላጊውን የቅጣት እርምጃ በመውሰድ በኩል ችላ ሊባል እንደማይገባም በመናደድ ጭምር ለክለቡ አሰልጣኞችና አባላቶች ሲገልፁ ታይተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታ ነገ በመከላከያና በባህርዳር ከተማ ከመደረጉ በፊት የደረጃ ጨዋታው በቅ/ጊዮርጊስና በጅማ አባጅፋር ቡድኖች መካከል የሚካሄድ ሲሆን ይኸው የፍፃሜና የደረጃ ውድድርም  ገቢው በጦርነቱ ሳቢያ በአማራ ክልል ለተፈናቀሉት ወገኖቻችን እንዲውል በመታሰቡ ጨዋታው ከአበበ ቢቂላ ስታዲየም ወደ ባህርዳር ስታዲየም እንዲዛወር ተደርጎ ባህርዳር ላይ እንዲካሄድ የአማራ ክልል በጠየቀው መሰረት የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፈቃደኛ ሆኖ በመገኘቱ ጨዋታው እንደሚካሄድ ተወስኗል፡፡ በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ እየተደረገ ባለው የእስካሁኑ ጨዋታም የኮከብ ግብ አግቢነቱን የመከላከያው ቢኒያም በላይ በ4 ግቦች እየመራም ይገኛል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለ15ኛ ጊዜ የሚካሄደውን የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታን በማስመልከት ከመከላከያው የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች ገናናው ረጋሳ እና ከባህርዳር ከተማው አማካይ ፉዐድ ፈረጃ ጋር ያደረግነው ቆይታም እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

 

ስለ አዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ጨዋታ ተሳትፎአቸው፡-

ገናናው፡- “ውድድሩ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ቡድኖች የራሳቸውን አቋም በሚገባ እንዲፈትሹበት ያደረገና ተጨዋቾችም በወቅታዊ አቋማቸው በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ የጠቀማቸው ስለሆነ ጥሩ ተሳትፎ ነበር እስካሁን ሲካሄድ የሰነበተው፤ የእኛን ቡድን በተመለከተም እንደ አዲስ ክለቡን እየገነባን ከመሆኑ አንፃር ብዙ ጨዋታዎችን በማድረግ እስከፍፃሜው ጨዋታ ድረስ መምጣታችንም ቤትኪንጉ ላይ ጠንካራ ቡድን ይዘን እንድንቀርብ ያደርገናልና መሳተፋችን ጠቅሞናል፤  ከዛም ባሻገር ከሜዳ ርቀው የነበሩ የየክለቡ ደጋፊዎችና የስፖርት አፍቃሪዎችም በተገኙበት ፊት ኳስን ለመጫወት መቻላችን ከፍተኛ ደስታንም ሰጥቶናል”፡፡

ፉዐድ፡- “የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ የዘንድሮ ውድድር በጣም ደስ የሚልና ለየት ያለብኝም ነው፤ አዳማ ከተማ እያለው ከዚህ ቀደም በእዚህ ተሳትፎ እኔም የተጫወትኩበትና ተቀይሬ በመግባትም ጥሩ የተንቀሳቀስኩበት ጊዜ ነበር፤ የአሁኑን ውድድር ለየት የሚያደርገው በርካታ ወጣት እና ጥሩ ችሎታን ከማራኪ የኳስ ፍሰት ጋር የሚያሳዩ ተጨዋቾችን የተመለከትንበትም በመሆኑ ነው፤ ወደ እኛ ቡድን ስመጣም በአጨዋወት ደረጃም ጥሩ ለውጦችን ከጨዋታ ወደ ጨዋታም ተመልካችን በሚስብ መልኩ የተመለከትኩበት አጋጣሚ ስላለ ያ መሆን መቻሉ አስደስቶኛል”፡፡

በግማሽ ፍፃሜው ስላደረጉት ጨዋታ

ገናናው፡- “ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር የነበረንን ይህ ጨዋታ ምንም እንኳን እነሱን አሸንፈን ለፍፃሜ የቀረብነው በአምስቱ አምስት የመለያ ምት ቢሆንም በመደበኘው 90 ደቂቃ በነበረው ጨዋታ ግን እኛ በአሰልጣኛችን ዩሃንስ ሳህሌ የተሰጠንን ታክቲክ በመተግብሩ በኩል ከሁሉም ካደረግናቸው ግጥሚያዎች የተሻለው የሚባልና የተደሰትንበት ነበር፤ በጨዋታው ታክቲካል ዲስፕሊን ሆነን ስለተጫወትንም ጎል እንዳይቆጠርብንም አድርጎናል፤ በመጨረሻም በመለያ ምት እነሱን አሸንፈናቸዋል”፡፡

ፉዐድ፡- “የእኛና የጅማ አባጅፋር የግማሽ ፍፃሳ ጨዋታ ሁለታችንም ለፍፃሜው ለመቅረብ ያለን ፍላጎት ከፍተኛ ከመሆኑ አኳያ ውጥረት የበዛበት ነበር፤ ሁሉም ተጨዋቾቻችን እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ ከፍተኛ መስዋትነትን ከፍለው ነበር ሲጫወቱ የነበሩት፤ በእንቅስቃሴ ደረጃ እኛ ብልጫ ነበረን፤ ብዙ ጊዜም ጎል ጋር ደርሰናል፤ በመጨረሻ ሰዓት ላይም የአቻነትን ጎል በማስቆጠር ግጥሚያውን ወደ መለያ ምት በመውሰድ በፍፁም ቅጣት ምት ለፍፃሜ አልፈናል”፡፡

በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ የነገው የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ለመቅረብ በመቻላቸው ስለፈጠረባቸው ስሜት

ገናናው፡- “ጠንካራውን ቅ/ጊዮርጊስ በማሸነፍ ለፍፃሜው ጨዋታ ለመቅረብ በመቻላችን በቡድኑ አባላቶች ላይ ጥሩ የደስታ ስሜትን ፈጥሯል፤ የእኛ ዓላማ ለፍፃሜው ለመቅረብና ዋንጫውንም ለማንሳት ነው፤ አሁን ለፍፃሜው መቅረብ ችለናል፤ ይሄም የስራችን ውጤት ነውና የሚገባን ሆኖም ነው ያገኘነው፤ ምክንያቱም መከላከያ ክለባችን ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እየተሻሻለ ነበር የመጣው፤ በግማሽ ፍፃሜው ጨዋታም በታክቲካሊ ዲስፕሊን በኩል ጥሩ ስለነበር ጨዋታውን ያለ ግብ በማጠናቀቅ በፍፁም ቅጣት ምትም ነው ለነገው የፍፃሜ ጨዋታ የደረሰውና የሚመጥነውን ውጤት ነው እስካሁን ያገኘው”፡፡

ፉዐድ፡- “በሲቲ ካፑ ተሳትፎ ነገ ለሚደረገው የፍፃሜ ጨዋታ ለማለፍ በመቻላችን በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ የእኔን ደስታ ለየት ካደረጉት ምክንያቶች መካከልም ቡድናችን የያዛቸውን ተጨዋቾች በአጭር ጊዜ ውስጥ በማግባባት ኳስን ፖሰስ አድርገው እንዲጫወቱ የተደረገበትና ከጨዋታ ወደ ጨዋታም በእንቅስቃሴው በኩል ለውጦችን እየተመለከትንና ደጋፊዎቻችንንም እያስደሰትን ያለንበት ሁኔታ ስላለ ይሄን በቀጣይነት አጠናክረንም ማስቀጠል እንፈልጋለን”፡፡

የቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን የቡድናቸው ግብ ጠባቂ በእጅ ምልክት ስለመሳደቡ

“በጨዋታው እኔ ቀድሜ ወደ መልበሻ ክፍል ገብቼና በቦታውም ላይ ስላልነበርኩ ስለ እሱ ምንም የምለው ነገር የለኝም”፡፡

በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ካደረጉት ጨዋታዎች ውስጥ ያስቆጨው፡-

ፉዐድ፡- “ከቅ/ጊዮርጊስ ያደረግነውና ሽንፈትን ያስተናገድንበት ጨዋታ ነው በጣም ያስቆጨኝ፤ በፍፃሜው እነሱ ወደቁ እንጂ በድጋሚ ብናገኛቸው ብዬ ተመኝቼም ነበር፡፡ ምክንያቱም ከእነሱ ጋር በነበረን ጨዋታ ቡድናችንን በእንቅሰቃሴው ደረጃ ብዙዎች አስቀድመው እያደነቁትና እያሞገሱት በመጡበት ሰዓት ላይ በዛ ደረጃ በቅ/ጊዮርጊሶች እንሸነፋለን ብለን አልጠበቅንም ነበር፤ ያም ሆኖ ግን እኛ ላይ በጥቃቅን ስህተት የተቆጠረችው የመጀመሪያዋ ግብ ብዙ ነገሮችን ወስዳብንና ተጨማሪም ግብ እንዲቆጠርብን አድርጋ እንድንሸነፍ አስችላለችና ያን እንደ ስህተት በመቁጠርና ሽንፈትም በእግር ኳስ የሚያጋጥም መሆኑን አውቅን በመምጣታችንና ከስህተታችንም በመማራችን አሁን ላይ ለፍፃሜው ጨዋታ ለመቅረብ ችለናል”፡፡

የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫን ማን ያነሳል?

ገናናው፡- “የመከላከያ እግር ኳስ ቡድን የአሁን ሰዓት ላይ ራሱን በወጣት ተጨዋቾች ከመገንባቱ አንፃርና ተጨዋቾቹም የራሳቸውን ችሎታ በማሳደግና በመቀየርም ለትልቅ ደረጃ ለመብቃት እየጣሩ ከመሆናቸው አኳያ ነገ በሚያደርጉት ጨዋታ ባህርዳርን አሸንፈው የሲቲ ካፑን ዋንጫ ለማንሳት በሚገባ ዝግጁ ናቸው፡፡ መከላከያ አሁን ላይ በወጣቶች የተገነባና ጥቂት ደግሞ ሲኒየር ተጨዋቾችን በማጣመር እየሰራ ያለ ቡድን ነው፤ አሰልጣኙ ክለቡን ለፕሪምየር ሊግ በሚመጥን ደረጃም እየሰራም ነው የሚገኘውና ክለባችን የሲቲ ካፑን ዋንጫ ከማንሳት ባሻገር በቤትኪንጉም ፕሪምየር ሊግ ላይ የተሻለ የሚባለውን ቡድን ያሳያል”፡፡

ፉዐድ፡- “ባህርዳር ከተማ በሲቲ ካፕ የውድድር ተሳትፎው ኳስን ፖሰስ አድርጎ በመጫወት የደጋፊውንም ሆነ የስፖርት አፍቃሪውን የኳስ ስሜት ለመግዛት ጥረት እያደረገ ያለ ቡድን በመሆኑ የነገው የፍፃሜም ጨዋታ ላይ ይሄን በማስቀጠልና ተጋጣሚውንም መከላከያን በኳስ በመብለጥ ዋንጫውን ከዓላህ እርዳታ ጋር እንደሚያነሳ እርግጠኛ ነኝ፤ ይሄንንም ዋንጫ አንስተን ምርጦቹን ደጋፊዎቻችንንም እናስደስታለን”፡፡

በመጨረሻ፡-

ገናናው፡- “መከላከያ በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለፍፃሜ በመቅረቡ በጣም ደስ ብሎኛል፤ የእዚህ ውድድር ገቢም ሰሞኑን ተወስኖ በጦርነቱ ለተፈናቀሉት የአማራ ክልል ውድ ዜጎቻችን እንዲውል በመደረጉም ሌላው ያስደሰተኝ ሁኔታ ነውና ይሄ ይበል ያሰኛል፤ በተረፈ የእዚህን ውድድር ዋንጫ ክለባችን አንስቶ እስካሁን እኛን ሲደግፉን የነበሩትንና እያመሰገናቸው ያሉትንም ደጋፊዎቻችንን እንድናስጨፍርም ፈጣሪ ይርዳን ነው የምለው”፡፡

ፉዐድ፡- “ባህርዳር ከተማ አሁን ላይ እየተሰራ ያለ ክለብ ነው፤ ብዙ ወጣት ተጨዋቾችም አሉት፤ ዘንድሮ በሚኖረው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎም ውድድሩን ማራኪ እግር ኳስን ጠንክሮ ከመስራት ጋር  በዓላህ እርዳታ ከ1-3 ለመውጣትም አልሟል፤ ይሄን ካልኩ በሲቲ ካፑም በአንድ ጨዋታ ላይ የግጥሚያው ኮከብ ተጨዋች የተባልኩበት ሁኔታም አለና ያ አስደስቶኛል፤ ኮከብ መባሌም ለነገ ከፍተኛ ተነሳሽነትን ይፈጥርልኛል፤ በ2014ትም ጥሩና ምርጥ ተጨዋች እንደምሆንም አስባለውኝ”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P