በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ መክበብ ደገፉ ጥሩ እንቅስቃሴን ካሳዩ ግብ ጠባቂዎች መካከል ስሙ ይጠቀሳል፤ ይህ በረኛ ሁሉም አሰልጣኞች ለኢትዮጵያን ግብ ጠባቂዎች የመሰለፍ እድልን የሚሰጡ ከሆነ አገራችን ብዙ ምርጥ በረኞች አሏት ሲልም ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ ጋር በነበረው ቆይታ አስተያየቱን ሰጥቷል።
ሲዳማ ቡና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የደረጃው ሰንጠረዥ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን የቡድኑን የዘንድሮ የሊግ ጉዞን በተመለከተ እና ስለ ራሱ ወቅታዊ አቋም እንደዚሁም ደግሞ በሌሎች ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ከግብ ጠባቂያቸው መክብብ ደገፉ ጋር የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ሰፋ ያለ ቆይታን አድርጎ ተጨዋቹ ለጋዜጣው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል፤ ተከታተሉት።
ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዘንድሮ የነበራችሁን የውድድር ቆይታ እንዴት አገኘኸው?
መክብብ፦ የዘንድሮ የሊጉ ቆይታችን የተለያየ መልክ የነበረው ነው። የመጀመሪያው ሐዋሳ ላይ እያለን በውጤት ደረጃ ትንሽ ተቸግረን ነበር። ይሄ የሆነውም ያኔ ደጋፊዎቻችንን በውጤት ለማስደሰት ብዙ ጥረንና ለፍተን የነበረ ቢሆንም ከጉጉት ስሜት የተነሳ በመጨናነቃችንና በጫና ጭምር የምንፈልገውን ስኬት ሳናስመዘግብ መቅረታችን ሊያስቆጨን ችሏል፤ የመጨረሻው ግጥሚያ ላይ ግን ወላይታ ድቻን በማሸነፍ ወደምንፈልገው አቋም ከመጣን በኋላ የድሬዳዋ ተሳትፎአችን ላይ ጥሩ ጊዜን አሳለፍን፤ በድሬ ቆይታችን አሰልጣኛችን በሚሰጠን ጥሩ ስልጠናም ነው የያዝነው ውጤት ወደ ዋንጫው ፉክክር ውስጥ እንደሚያስገባን በማሰብ ከአንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ለመውጣት ተዘጋጅተን የነበረው አዳማ ላይ የነበረው ተሳትፎአችን ደግሞ ራሱን የቻለ ለየት ያለ የውድድር ቆይታ ነበረው። ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ከነበረን ጨዋታ ጀምሮ በውጤት ደረጃ እየቀነስን መጣን፤ ባህርዳር ከመጣን በኋላ ደግሞ ምንም እንኳን የተወሰነ ሽንፈት ቢያጋጥመንም ለእኛ ቡድን በውጤት ደረጃ ጥሩ ጊዜን ያሳለፍንበት ነው። በእዚህ ከተማ የውድድር ቆይታችን ጊዜም እስከ ሁለተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ወደ ኢንተርናሽናል ውድድር ለማለፍ ብንጥርም በአንድአንድ ተጨዋቾቻችን ላይ መጨነቅ ስለነበር እልማችንን ለማሳካት ሳንችል ቀረን። አሁን ባለንበት ደረጃ ደግሞ አንደኛነቱንና ሁለተኝነቱን ባናገኝም ቡድናችን ከእነ ጥሩነቱ የሶስተኛ ደረጃን ይዞ የሚፈፅምበት ዕድሉ ስላላው ይሄም በመልካምነቱ የሚጠቀስ ነው። ይህን ደረጃ ደግሞ በእርግጠኝነት ይዘን እንፈፅማለን።
ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዘንድሮ የነበራችሁ ጠንካራ እና ክፍተት ጎናችሁ ምንድን ነበር?
መክብብ፦ ጠንካራው ጎናችን እንደ ቡድን ከበረኛ አንስቶ እስከ አጥቂው ክፍል ድረስ ኳስን ይዘን መጫወት መቻላችን ነው፤ በእዚህ በኩል ምንም አይነት ችግር የለብንም። አሰልጣኙ የሚፈልገው በእዛ መልኩ እንድንጫወትም ነው። ሌላው ጥንካሬያችን ፕላን ቢም ስላለን የሚያጠቃም ቡድን ነው ያለን። ሁሉም በየቦታው የሚጫወቱ ተጨዋቾቻችንም ኳስን ይዞ በመጫወቱ በኩል ጥሩ ናቸው። እንደውም በሊጉ ላይ እኛ ጋር ያለው ኳስ ይዞ የመጫወት ብቃት ሌሎች ጋር ያለም አይመስለኝም። ክፍተቱ ጎናችን ደግሞ የምንዘናጋው ነገር ነበር፤ ያ በአሰብነው መልኩ ውጤት እንዳናመጣ አድርጎናል።
ሊግ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሲጀመር ምን ውጤትን ለማምጣት ነበር ያቀዳችሁት?
መክብብ፦ የአመቱ ውድድር ሲጀመር ክለቡ ቅድሚያ እኔን ጨምሮ 15 የሚደርሱ ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችን አስፈርሞ ስለነበርና ዝግጅቱንም በጊዜ በመጀመር ከሌሎች ቡድኖች ቀድሞም ስለነበር ዋንጫን እንጂ ሌላ ውጤትን እናመጣለን ብለን ፈፅሞ አላሰብንም ነበር። ያም ሆኖ ግን ወደ ውድድሩ ከገባን በኋላ በውጤት ደረጃ እንዳሰብነው አልሆነልንም። የሶስተኛ ደረጃን ግን ከላይም እንደገለፅኩት ይዘን እንፈፅማለን።
ሊግ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በአንተ እይታ እንዴት ይገለፃል?
መክብብ፦ የዘንድሮ ውድድርን ለየት የሚያደርገው ብዙ ነገሮች አለ። ፉክክሩ ከአምናው በጣም ይሻላል። ሻምፒዮናውንና ወራጁን ቡድን ለማወቅ ጨዋታዎቹ እስከ መጨረሻዎቹ ሳምንት ድረስ የተከናወኑበት ሁኔታ ሊጉን ለየት እንዲል አድርጎታል። ሌላው የዘንድሮን ውድድር የተለየ ያደረገው ከሁለት ዓመት በፊት የነበሩት የሊጉ የደርሶ መልስ ውድድሮች ተጨዋቹ ያለውን አቅም በደንብ የማያውቅበት ነበርና አሁን ላይ የዲ ኤስ ቲቪ መምጣት በኳሳችን እድገት ላይ ብዙ ነገሮችን ቀይሯል። የስፖርቱ አፍቃሪም የቱ ተጨዋች ምን አይነት አቋም እንዳለው በደንብ አድርጎ ማወቅ ጀምሯል። ተጨዋቹም ያለውን አቅሙን ጨዋታዎቹን ደግሞ የሚመለከትበት ዕድሉ ስላለውም በጥሩ ሁኔታ እንዲያውቅም አድርጎታል። ከእዚህ በኋላም የአገራችንን እግር ኳስ የበለጠም ያሳድገዋልና ጥሩ የእግር ኳስ ፉክክርንም ነው ዘንድሮ የተመለከትነው።
ሊግ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በመጪው ሳምንት ይጠናቀቃል፤ ዋንጫውን ማን ከፍ አድርጎ ያነሳል?
መክብብ፦ ይሄ እግር ኳስ ነው፤ በቅ/ጊዮርጊስ እና በፋሲል ከነማ መካከል ካለው የጠበበ የነጥብ ልዩነት አኳያ ሻምፒዮናውን ቡድን መለየት ከባድ ቢሆንም ቅ/ጊዮርጊሶች ዋንጫውን ለማንሳት የተሻለ እድል አላቸው።
ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዘንድሮ ስለነበረህ ወቅታዊ አቋም ምን ትላለህ? በቀጣይነትስ ከአንተ ምን ይጠበቅ?
መክብብ፦ ሲዳማ ቡናን ከወላይታ ድቻ በመምጣት ከተቀላቀልኩ በኋላ የመጀመሪያው ሰሞን አካባቢ ትንሽ ከቤተሰቤ ጋር በተፈጠረ ግጭት ለሶስት ወራቶች ያህል የተረጋጋ ጊዜን አላሳለፍኩም ነበር። ኳስን እስከማቆም ደረጃም ሁሉ ደርሼ ነበር። በኋላ ላይ ግን የነበረብኝ ችግሬ ተፈቶና ወደ ራሴም ልመለስ ስለቻልኩ በአዲሱ እና ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብን በያዘው የአሰልጣኝ ገብረ መድህን ሀይሌ ቡድን ውስጥ ሌሎች ጥሩ ጥሩ ግብ ጠባቂዎች ስላሉና ተፎካክሮ መሰለፍም ስለሚያስደስተኝ ያንን ሁሉ ፈተና በማለፍና ለረጅም ጊዜም የተክለማሪያም ሻንቆም ተጠባባቂ ከሆንኩ በኋላ አሁን ላይ በጥሩ አቋም ላይ ለመገኘት ችዬ ለቡድኔ ለመሰለፍ ስለቻልኩ ደስ ብሎኛል። በእዚሁ አጋጣሚ የእኛን ቡድን ግብ ጠባቂዎች በተመለከተም አንድ ነገርን ብልም ደስ ይለኛል። በሊጉ ውስጥ አሉ ከሚባሉት የ16ቱ ክለብ ግብ ጠባቂዎች በቂ ስብስብን የያዘው የእኛ ቡድን ነው። እነሱም አራቱ ሲኒየሮቹ ተክለማሪያም ሻንቆ፣ እኔ፣ አዱኛ ፀጋዬ፣ ፍቅሩ ወዴሳ ሲሆኑ አንዱ ታዳጊው ደግሞ ሀብታሙ መርመራ ነው። እነዚህ በየቡድኑ ገብተው መጫወትም ይችላሉ።
ሊግ፦ በሲዳማ ቡና የዘንድሮ የውድድር ቆይታ ላይ የተክለማሪያም ተጠባባቂ በነበርክበት ሰዓት በሁለታችሁ መካከል የነበረው ግንኙነት ምን ይመስል ነበር?
መክብብ፦ መጀመሪያ ተክለማርያም ጎበዝ ግብ ጠባቂ መሆኑን መናገር እፈልጋለሁ። እኔ ወደ ሲዳማ ቡና የመጣሁት በቋሚነት ተሰልፌ ከምጫወትበት ወላይታ ድቻ ነበር። በአዲሱ ክለቤ ውስጥ ለስድስት ወራት ያህል ሳልጫወት በመቅረቴ በአቋም ደረጃ ያጣሁት ነገር ነበር። በኋላ ላይ ግን
እነዛን ነገሮች ወደ ኋላ በመርሳትና ልምምዴንም በግሌ ጠንክሬ በመስራት እንደዚሁም ደግሞ የውጪ በረኞች የሚሰሩትን ልምምዶችንም ከቪዲዮ ላይ ዳውን ሎድ እያደረግኩኝ በማየትና በቋሚነት ይሰለፍ ከነበረውም ከተክለማሪያም የተማርኳቸው አንድ አንድ ነገሮች ስለነበሩም የሚጎድሉኝን ነገሮች አውቄ አሁን ላይ በቋሚነት እየተጫወትኩ ነው። በሲዳማ ቡና ቆይታዬ በእኔና በተክለማሪያም መካከል ጥሩ ግንኙነት ነበረን እኔ ከእሱ የተማርኩት ነገር አለ። እሱም ከእኔ የሚማረው ነገር ይኖራል። በእዛ ላይ እኔ ተሰልፌ ስጫወት ደስ እንደሚለው ሁሉ እኔም እሱ ተሰልፎ ሲጫወት ደስ የሚለኝ ጊዜ ነበርና መልካም የሚባል ጊዜን ነው ያሳለፍነው።
ሊግ፦ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ቆይታ ለውጪ ሀገር እንጂ ለእኛ ሀገር ግብ ጠባቂዎች ብዙ ጊዜ የመሰለፍ እድልን አይሰጥም ነበር፤ በእዚህ ዙሪያ ምን አልክ? የእኛዎቹ እንዴትስ ከእነሱ ጋር ይነፃፀራሉ?
መክብብ፦ የኢትዮጵያ ግብ ጠባቂዎች እና የውጪ ሀገር ግብ ጠባቂዎችን በሚመለከት እኔ ነገሮችን በሁለት መልኩ ነው የማያቸው። በአጋጣሚ በተጨዋችነት ዘመኔ ከውጪ ግብ ጠባቂዎች ጋር በሐዋሳ ከተማ እና በአዳማ ከተማ ቡድን ውስጥ ሆኜ አብሬ ሰርቻለሁ። አምና ደግሞ በግማሽ ሲዝን ከዳንኤል አጃዬ ጋርም፤ በእዚህ ጊዜ ቆይታዬ ከእነሱ የተማርኳቸው ብዙ ነገሮች አሉ። እኛ በዋናነት ከእነሱ የምንማረው በተሻለ ሊግ ላይ ተጫውተው ስለመጡ ያላቸውን ልምድ ሁሉ ያካፍላሉ። ከእነዛም መካከል አንድ ግብ ጠባቂ ከአጥቂ ጋር አንድ ለአንድ ሲገናኝ እንዴት አድርጎ ኳስን ሊያድን እንደሚችል፤ የአየር ላይ ኳስን በምን መልኩ ሊይዝ እና ሊያወጣ እንደሚችል የተማርኩት ነገር አለ። ይሄን ደግሞ አሁን አሁን የእኛዎቹ ግብ ጠባቂዎችም እያደረጉት ይገኛሉ። የእኛ ሀገር ግብ ጠባቂዎችን ከውጪዎቹ ማነፃፀሩ ላይ የአሰልጣኞች የእምነት ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በችሎታ አንሰው አይደለም። ሁሉም አሰልጣኞች በሀገር ውስጥ በረኞች ላይ እምነት ቢያሳድሩና የመሰለፍ ዕድሉን ቢሰጡ ሀገራችን ምርጥ በረኞች አሏት።
ሊግ፦ ከልጅነት ዕድሜህ አንስቶ ግብ ጠባቂ ነበርክ፤ ፈልገኸው ነው?
መክብብ፦ አዎን፤ ከፕሮጀክት ተጨዋችነት ዘመኔ ጀምሮ ነው ግብ ጠባቂነትን በጣም እወድ ስለነበር የሆንኩት። ያኔም ለደቡብ ክልል ለአራት ጊዜ ያህል ተመርጬም ተጫውቻለው። ከዛም ችሎታዬን እያሻሻልኩ በመምጣት ይኸው ለዛሬ ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ ቻልኩ።
ሊግ፦ ወደ ስፖርቱ ዓለም የመጣከው በየት አካባቢ ተወልደህ በማደግ ነው ?
መክብብ፦ በዱራሜ አካባቢ ተወልጄ በማደግ ነው የስፖርት ዓለሙን የተቀላቀልኩት።
ሊግ፦ ዱራሜ ሲጠራ ከዚህ ቀደም የእዚሁ ክልል ተወላጅ ደስታ ጊቻሞ በሴቶች እግር ኳስ ደግሞ የሎዛ አበራ ስም በተደጋጋሚ ጊዜ ተነስቷል። ስለ እነሱ የምታውቀው ነገር አለ? ከእዚሁ ክልል ሌሎች በርካታ ተጨዋቾችን ማግኘት ይቻላል ?
መክብብ፦ አዎን። ደስታ ጊቻሞን በተመለከተ እሱ ከእኛ ክልል ቀድሞ የወጣና ለብሄራዊ ቡድንም መጫወት የቻለ ነው። አምና አዳማ ነበር። አሁን ደግሞ ለወራቤ ከተማ እየተጫወተ ይገኛል። ጥሩ አቅም ያለው ተጨዋች ነው። በሴቶቹ ደግሞ ሎዛ ሎዛ ነች። እጅግ በጣም ብዙ አቅም ያላት ልጅ ነች። አሁን ደግሞ እነ አስረስን የመሰሉ ተጨዋቾችን ከተማዋ ለብሄራዊ ቡድን ተጨዋችነት አፍርታለች። ለአዳማ ከተማ የሚጫወተው እነ ሚሊዮንም አሁን ላይ ለብሄራዊ ቡድን እስከ መመረጥ ደረጃም የደረሱ አሉና ክልሉ ሌሎች አቅም ያላቸው ተጨዋቾች ለምሳሌ እንደ እንዳለ ዩሃንስን የመሳሰሉ ዕድሉን ያላገኙ በርካታ ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች ስላሏት አሰልጣኞች በቂ ትኩረት ቢያደርጉባት ተጠቃሚዎች ይሆናሉ።
ሊግ፦ የልጅነት ዕድሜህ ላይ ወደ ተጨዋችነት ዓለሙ ስትመጣ ቤተሰቦችህ ፍላጎት ነበራቸው?
መክብብ፦ እንደ አብዛኛው ቤተሰብ እነሱም ኳስ ኤንድጫወት ፍላጎት አልነበራቸውም። አባቴ የቢዝነስ ሰው ነው። ነጋዴ ስለሆነ እሱን ጨምሮ ሌሎቹም ቤተሰቦቼ እንድማርም ነበር የሚፈልጉት። ከረጅም ጊዜ ጭቅጭቅ በኋላ ግን ወደ ወላይታ ድቻ ቡድን ሳመራና ኮከብ ግብ ጠባቂም ስሆንና ዋንጫም ስናገኝ በቃ ይጫወት ወደሚል ነገር አመሩና ይኸው የእነሱ ፍላጎትም ተቀይሮ ኳሱን በመጫወት ላይ አገኛለሁ።
ሊግ፦ በቤተሰቡ ስፖርተኛው አንተ ብቻ ነህ? ስንት ወንድም እና እህትስ አለ?
መክብብ፦ ሰባት ወንድሞች እና አራት እህቶች አሉኝ። ከቤተሰቡ ስፖርተኛው ደግሞ እኔ ብቻ አይደለሁም። አሁን ላይ ለዱራሜ ከተማ የሚጫወት ዘሪሁን ደገፉ የሚባል ወንድም አለኝ።
ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አቡበከር ናስር አምና ጎልቶ ወጥቷል። ዘንድሮስ ምርጥ ሆኖ የተመለከትከው ማንን ነው?
መክብብ፦ ለእኔ አሁንም ምርጡ ተጨዋች አቡበከር ናስር ነው።
ሊግ፦ አሁን ላይ ለሲዳማ ቡና እየተጫወትክ ነው፤ ስለ ቀጣይ ጊዜ የኳስ ህይወትህ ከወዲሁ ምን እያሰብክ ነው?
መክብብ፦ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የግብፅ አቻውን ብዙዎች ባልጠበቁበት ሁኔታ ካሸነፈ በኋላ የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የዋልያዎቹን ስብስብ ተቀላቅሎ መጫወትን እኔን ጨምሮ የማይመኝ ተጨዋች የለም። ሁሉም የእዚህ ቡድን አባል መሆንን እያለመም ይገኛል። እኔም ፈጣሪ ረድቶኝ ይሄን ቡድን ባገለግል እና ከፍ ባለ ስፍራም ላይ ብገኝ ደስ ይለኛል። ይሄን ለማሳካት ከበፊቱ የኳስ ቆይታዬ አኳያም ጠንክሬም እሰራለሁ።
ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ አንድ ጨዋታ ላይ ፂምና ፀጉርህን ቀለም በመቀባት መጫወትህ ታይቶ ነበር?
መክብብ፦ አዎን፤ ይህን ያደረግኩት ዕለቱን ካስታወስክ የአባቶች ቀን ነበርና እኔም የልጅ አባት ስለሆንኩ እና ደግሞም በመቀባቱ ስለሚያምርብኝ ያንን በማሰብና ለየት ለማለትም ስለፈለግኩ ነው።
ሊግ፦ የግል ባህሪህን በተመለከተ ምን ትላለህ?
መክብብ፦ ከሰዎች ጋር እግባባለሁ። ትምክተኛ አይነት ሰው አይደለሁም። ለሰዎች ክብር እሰጣለው። በአኗኗርም ሆነ በሌላ ሁኔታ እታች ካለ ሰው ጋርም ወርጄ አብሬ መዋል እና መጫወት የሚያስደስተኝ አይነት ሰው ነኝ። በአለባበሴና በስራዬም ለየት ማለትም የሚያስደስተኝ ነኝ።
ሊግ፦ በመጨረሻ?
መክብብ፦ በእስካሁኑ የኳስ ዘመን ቆይታዬ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ ጥሩ አስተዋፅኦን ያደረጉልኝ አካላቶች አሉ። በቅድሚያ ፈጣሪዬና ቤተሰቦቼን አመሰግናለሁ በተለይም ደግሞ እናቴን ላቅ ባለ ሁኔታ አመሰግናታለሁ። ሲቀጥል ደግሞ በእኔ ስር ሆነው ያሰለጠኑኝንም አመሰግናለሁ።