በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና የሲዳማ ክልል ለሆነችው ሐዋሳ ከተማ ተጫውቶ ጥሩ የውድድር ጊዜን አሳልፏል፤ ከዛ በፊት በነበረው የሊጉ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው ደግሞ ለደደቢት፣ ለሽሬ እንደስላሴ እና ለሀድያ ሆሳዕና ሊጫወት ችሏል።
ይህ ወጣት ተጨዋች በኮሪደር ስፍራው ላይ በመጫወት አበረታች የኳስ ብቃቱን የሚያሳየው መድሃኔ ብርሃኔ ሲሆን ተጨዋቹ ከሊግ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር በነበረው ቆይታ ስላሳለፉት የውድድር ዘመን ቆይታቸው፣ ስለ ራሱ የኳስ ዘመን ጉዞው እና ስለመጪው ጊዜ የኳስ ህይወቱ ተጠይቆ ምላሾቹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል። ተከታተሉት።
ሊግ፦ ውልደትህ እና እድገትህ የት አካባቢ ነው?
መድሃኔ፦ ተወልጄ ያደግኩት በአዲስ አበባ ከተማ ቄራ አካባቢ ነው።
ሊግ፦ የእግር ኳስ ተጨዋች መሆን እልምህ እና ፍላጎትህ ነበር?
መድሃኔ፦ አዎን፤ ከልጅነቴ አንስቶ ነው ኳስ ተጨዋች የመሆን ፍላጎቴ የነበረው፤ ያንንም እልሜ አሳካሁት። በጣምም ነው ደስ ያለኝ።
ሊግ፦ የእግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮ በምን ሙያ ላይ እናገኝህ ነበር?
መድሃኔ፦ ከኳስ መጫወት ውጪ ምንም አይነት ስራን ሰርቼ ስለማላውቅ በሌላ ሙያ ላይ ስለመሰማራት እና ስለመገኘቴ ለመመለስ በጣም ይከብደኛል። ከበፊት አንስቶ ኳስ ተጨዋች መሆንን ነበር የፈለግኩት፤ ኳስ ተጨዋች ሆኛለሁ።
ሊግ፦ በቤተሰቦችህ በኩል ኳስ በመጫወትህ ዙሪያ የነበረው ፍላጎት የቱን ያህል ነበር?
መድሃኔ፦ ወደ ኳስ ተጨዋችነቱ ውስጥ ጠልቄ እና ዘልቄ እንድገባ በቤተሰቦቼ ዘንድ በጣም ነበር ግፊቱ የነበረው። በተለይም ደግሞ እናቴ በብዙ ነገሮች ታግዘኝ እና ትደግፈኝ ነበር።
ሊግ፦ ከቤተሰባችሁ ውስጥ ከአንተ ውጪ ሌላ ስፖርተኛ አለ? ስንት ወንድም እና እህትስ ነው ያለህ?
መድሃኔ፦ በእኛ ቤት ውስጥ ሌላ ስፖርተኛ የለም፤ የቤቱ ስፖርተኛም እኔ ብቻ ነኝ፤ ሶስት ወንድሞች ሲኖሩኝ፤ የመጨረሻው ልጅም ነኝ።
ሊግ፦ የኳስ መነሻህ በፕሮጀክት ወይንስ በክለብ ደረጃ የተጀመረ ነው?
መድሃኔ፦ በፕሮጀክት ደረጃ ነው ኳሱን መጫወት የጀመርኩት፤ የቡድን መጠሪያ ስማችንም አክረምና ልጆቹ ይባል ነበር። በእዛ ደረጃም ኳሱን ከተጫወትኩ በኋላ ወደ ክለብ ደረጃ ተሸጋገርኩኝ።
ሊግ፦ እስኪ ስለ ትውልድ አካባቢህ እና ስለ ክለብ ተጨዋችነትህ አውጋኝ?
መድሃኔ፦ የእኔ የትውልድ ስፍራ ማንም እንደሚያውቀው የስፖርት አካባቢ ነው። በፈጣሪ ፈቃድ ከዛም አካባቢ ነው የወጣሁት። ሰፈሩ ትንሽ ወጣ ቢልም እንደ እነ መስዑድ መሀመድን እና አስራት መገርሳን የመሳሰሉትን ተጨዋቾች እንደዚሁም ደግሞ ከእኛ በቅርብ ርቀት ላይ ያሉትን እንደ እነ ሄኖክ ኢሳያስንና አንዳርጋቸው ይላቅን እና የቀድሞ ተጨዋቹን ጌታቸው ካሳ የመሳሰሉትን ያፈራም አካባቢ ነው።
ሊግ፦ ወደ ክለብ ተጨዋችነት ያመራህበት መንገድ ምን ይመስላል?
መድሃኔ፦ በእዛ ደረጃ ለመጫወት መጀመሪያ ላይ ነገሮች ለእኔ ከባድ ነው የነበሩት፤ ሌሎቹ ተጨዋቾች ግን ወደ ክለብ ገቡ። እኔ ወደ ክለብ ያልገባሁበት መንገድም በዕድሜዬ ልጅ ስለነበርኩና ትምህርቴም ላይ ትኩረትን ስለማደርግ ነበር። ከጥቂት ቆይታ በኋላ ግን ራዕይ ወደሚባል የቸርች ቡድን ለመጫወት አመራው፤ እዛም ሄጄ ነገሮች ከሰመሩልኝ በኋላ የደደቢት ክለብን ተቀላቀልኩ።
ሊግ፦ ደደቢትን የተቀላቀልክበት መንገድ በተተኪው ቡድን ውስጥ ነው?
መድሃኔ፦ አዎን፤ በተተኪው ቡድን ላይ ቢያንስ ለሶስት ዓመታት ያህል ቆይታን አድርጌያለሁ። በአራተኛው ዓመት ላይ ደግሞ የዋናውን ቡድን በመቀላቀል ጥሩ ጊዜን ላሳልፍ በቅቻለሁ።
ሊግ፦ ሌሎች የተጫወትክባቸው ክለቦች የትኞቹ ናቸው?
መድሃኔ፦ በደደቢት በነበርኩበት ሰዓት ራሴን በሚዲያ ደረጃ ካስተዋወቅኩኝ በኋላ የተጫወትኩባቸው ቡድኖች ለግማሽ ሲዝን ለስዑል ሽሬ እንደስላሴ እና ለሀድያ ሆሳዕና ሲሆን የአሁን ሰዓት ላይ ደግሞ የሐዋሳ ከተማ ተጨዋች ሆኜ ከዘንድሮ ሲዝን ጀምሮ እየተጫወትኩ ነው የሚገኘው።
ሊግ፦ ባሳለፍከው የኳስ ዘመን ምርጡ የጨዋታ ጊዜዬ የምትለው የትኛውን ነው?
መድሃኔ፦ ምርጡ ጊዜዬ የምለው ቡድኑ በአሁን ሰዓት ባይገኝም የልጅነቴም ቡድን ስለሆነ በደደቢት ሆኜ ያሳለፍኩትን ነው። ቡድኑን በጣምም ነበር የምወደው። አሁን ላይ ደግሞ ልክ እንደ ደደቢት ሁሉ ሌላ በምወደው ሐዋሳ ከተማ ክለብ ውስጥ እያሳለፍኩት የሚገኘው ቆይታ አሪፍ ነውና ይህንን ነው ማለት የምፈልገው።
ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በሐዋሳ ከተማ ቡድን ውስጥ ተጫውተህ እያሳለፍክ ነው፤ ስለዘንድሮ የሊጉ ቆይታችሁ ምን የምትለው ነገር አለ?
መድሃኔ፦ የውድድር ተሳትፎአችን በዋንጫ የታጀበ ባይሆንም በጣም ነበር ደስ የሚለው። ለሻምፒዮንነትም ነበር የተዘጋጀነው። ከተጨዋቾቻችን ጋር ጥሩ ጊዜን አሳልፈንም ነበር። ጥሩ አሰልጣኝም ነበረን በመጨረሻ ላይ ግን ያሰብነው ዋንጫ ባይሳካልንም ውድድሩን በአራተኛ ደረጃ ላይ ሆነን በማጠናቀቅ አሪፍ ጊዜን ልናሳልፍ ችለናል።
ሊግ፦ የውድድር ዘመኑን በሻምፒዮናነት ለማጠናቀቅ እንዳትችሉ ያደረጋችሁ ዋናው ነገር ምንድን ነበር?
መድሃኔ፦ የስኳዳችን ጠባብ መሆን ነው፤ ያ ባይሆን ኖሮ ለሻምፒዮናነቱ ፉክክር እንጫወት ነበር።
ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊ ሆናችሁ ነበር፤ ስብስባችሁ በምን መልኩ ይገለፃል?
መድሃኔ፦ ቡድናችን በወጣት ተጨዋቾች የተገነባ ነበር። ያ መሆኑም ጥሩ ነው። በተለይ ደግሞ በእዛ ደረጃ መሰራቱ ሁሉም ተጨዋች ለአሰልጣኙ ፍልስፍና ታዛዥ እንዲሆን ስላደረገው ለተከተልነው ታክቲክ ጥሩ ነበር። በሲኒየር ደረጃም እንደ እነ ዳንሄል ደርቤ፣ አዲስዓለም ተስፋዬ፣ በቃሉ ገነነም የመሳሰሉ ተጨዋቾችን አጣምረን እስከ ፍፃሜ እንጓዛለን ብንልም ፈጣሪ ሳይፈቅድ ቀርቶ ሊጉን በአራተኛ ደረጃ ላይ ለማጠናቀቅ ችለናል።
ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ ምርጡ ጨዋታችሁ የቱ ነው፤ ያስቆጫችሁ ጨዋታስ?
መድሃኔ፦ በጣም ያስደሰተን ግጥሚያ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያደረግነው ነው፤ ከመመራት ተነስተን ባለቀ ሰዓት ወደ 3-2 ውጤቱን የቀየርንበት እና የሄድንበትም ነው፤ ያ ጨዋታ አስደሳች እና የማልረሳው ነበር። ያስቆጨን ግጥሚያ ደግሞ በቅ/ጊዮርጊስ 2-1 የተሸነፍንበትን ነው።
ሊግ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በአንተ እይታ እንዴት ይገለፃል?
መድሃኔ፦ የውድድሩ ፉክክር እና ሁኔታ በአሁን ሰዓት ላይ በአሪፍ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። ለእዛ እንዲበቃም ያደረገው የጨዋታዎቹ የቀጥታ ስርጭት አግኝቶ በዲ ኤስ ቲቪ መተላለፍ መቻሉ ነው። ሌላው ጨዋታዎቹን ስትመለከት እንደ ቀድሞው ይሄ ክለብ አስቀድሞ ያሸንፋል የምትለው ነገር የለም። ከእዛ ውጪ በብሄራዊ ቡድናችን ደረጃም ላይ ተፅህኖን አምጥቷል። የብሄራዊ ቡድናችን አሪፍ እየሆነ ነው። እግር ኳሱም እያደገም ነው የሚገኘው። ሌላው ደግሞ ለሻምፒዮናነት የነበረው ፉክክር እና ላለመውረድ የነበረው ጨዋታም አጓጊ ነበር፤ እጅ የሚሰጥ ቡድን አልነበረም። በጥሩ መልኩም ነው የሊጉ ጨዋታዎች ሲደረጉ የነበሩት። ከእዚህ በኋላም ውድድሩ የበለጠ እያደገም የሚሄድ ይመስለኛል።
ሊግ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በቅ/ጊዮርጊስ ሻምፒዮናነት ተጠናቋል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን አልክ?
መድሃኔ፦ እነሱ ጥሩ የውድድር ጊዜን ነው ያሳለፉት፤
ም እየተከተልናቸውና በተወሰነም መልኩም እየተፎካከርናቸው ነበር። በተመለከትኩት ነገር ድሉ ለእነሱ የሚገባቸው ነው።
ሊግ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላይ ለአንተ ምርጡ ተጨዋች ማን ነው?
መድሃኔ፦ የእኛውን ብሩክ በየነን በቅርበት ስላየሁት እና ከአጠገቡ ጋርም ሆኜ ስለምጫወት እሱን ነው ዘንድሮ ምርጡ ተጨዋች ያልኩት።
ሊግ፦ ሐዋሳ ከተማ የውድድር ዘመኑን ያሳለፈበት ሂደት ምን ይመስላል፤ ጠንካራ እና ክፍተት ጎኑ ምን ነበር?
መድሃኔ፦ ጥሩ ጎናችን ህብረታችን ነበር። እንደ ወንድም በመተያየትም እንተሳሰብም ነበር። ከዛ ውጪም ከአንድ ቀን በፊት ማንም ጣልቃ ሳይገባ የራሳችን ዝግ ስብሰባ አለንና ማንም ቢመጣ እንደማይከብደንና ግጥሚያዎችን እንዴት ማሸነፍ እንዳለብንም እንነጋገር ነበር። በክፍተት ጎን የማነሳው ደግሞ ስኳዳችን ጠበብ ይል ነበር። ልምድ ያላቸው ልጆችም ብዙ አልነበረንም ነበርና ያ ለሻምፒዮናነቱ እንዳንፎካከር አድርጎናል።
ሊግ፦ በመጪው የውድድር ዘመን ወሳኝ ተጨዋቾቻችሁ ወደ ሌላ ክለብ መዘዋወራቸውን አስመልክተህ የምትለው ነገር ካለ?
መድሃኔ፦ የልጆቹ ከእኛ ጋር አለመኖር ቢጎዳንም አዳዲስ የመጡትን ልጆች በክረምቱ ዝግጅት በማዋቀር አዲስ ቡድን ስለምንገነባ ለዋንጫው ባለቤትነት ተፎካክረን ለአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ለማለፍና በእዛ ካልተሳካልን ደግሞ ሁለተኛ በመውጣት ለኮንፌዴሬሽን ካፑ ለማለፍ ጥረትን እናደርጋለን።
ሊግ፦ በእግር ኳሱ ዋናው ራዕይህ ምንድን ነው?
መድሃኔ፦ እንደማንኛውም ተጨዋች ክለቤን በሚገባ አገልግዬ ለሀገሬ መጫወት እፈልጋለሁ፤ ከዛ ውጪ ደግሞ ወደ ውጪም በመውጣትም በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት መጫወትም ዋናው እልሜ ነው።
ሊግ፦ በእግር ኳሱ ተጨዋችነትህ ራስህን የቱን ያህል ነው የምታዘጋጀው?
መድሃኔ፦ ሁሌም ጨዋታ ባለን ሰዓት ራሴን ነፃ በማድረግ ለግጥሚያዎቹ ትኩረት እሰጣለሁ። ከዛ ውጪ ደግሞ ስልኬ ላይ ኤርፎን በመሰካትም አህምሮዬን ጥሩ የሚያደርግልኝን ነገሮች እሰማለሁ።
ሊግ፦ ሙዚቃ መስማትን ጨምሮ ነው?
መድሃኔ፦ አዎ፤ ሙዚቃማ ዋናው ነው። በእዛ መንፈሴን አድሳለሁ።
ሊግ፦ ቤትኪንግ ከተጠናቀቀ በኋላ የእረፍቱን ጊዜ እንዴት አሳለፍክ?
መድሃኔ፦ ብዙም ከቤት አልወጣም ነበር። በቤቴ ውስጥም ነው ስፖርትን በመስራት ሳሳልፍ የነበረው። ከዛ ውጪ ደግሞ የፕሌይስቴሽን ጌሞችንም እጫወት ነበር። አሁን ላይ ደግሞ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የተጀመረ የሸገር ሰመር ካፕ ግጥሚያም ስላለ በአቋም ደረጃ የቱጋ ነኝ ለማለት ስለሚጠቅም በእዛ በመጫወት እያሳለፍኩኝ ነው የሚገኘው። በእዚህ አጋጣሚ ይሄ ውድድር ለእኔ ብቻ ሳይሆን በክለብ ደረጃም ለማይጫወቱ ተጨዋቾች ጥሩ መታያም ስለሚሆናቸው ይህን ውድድር ላዘጋጀውና ለብዙ ሰዎችም ፈለግ ለሆነው የኔነህ በቀለ ከፍተኛ ምስጋናዬን አቀርብለታለው።
ሊግ፦ በእግር ኳሱ ሜዳ ላይ በጣም ፈጣን ነህ፤ ከእዚህ ጋር በተያያዘ የምትለው ነገር ካለ?
መድሃኔ፦ ፍጥነቴ የተፈጥሮ ነው። ፈጣሪ ልጅ እያለሁ ጀምሮ የሰጠኝም ስጦታ ነው። ከእዛ ውጪ ደግሞ በልምምድም ያዳበርኩትም አለ።
ሊግ፦ በእናንተ ቡድን ውስጥ ቀልደኛው እና አስቂኙ ተጨዋች ማን ነው?
መድሃኔ፦ አስቂኙ ተጨዋች ባሲጥ ነው የእሱ ስራውና አጠቃላይ ሁኔታው ሁሉ ያዝናናል።
ሊግ፦ ዝምተኛው ተጨዋችስ?
መድሃኔ፦ ዝምተኛው ዳንሄል ደርቤ /ዳኒ/ ነው። እሱ ቁጥብ ሰው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ አይነት ካፒቴን አይቼ አላውቅም። በጣም ሰው አክባሪ ነው። አንድ ቡድን እንዴት መያዝ እንዳለበትም የሚያውቅ ነው። ቡድናችን ለእዚህ የውድድር ፉክክር መድረሱም እሱ ቁልፉ ሰውም ነበር።
ሊግ፦ የአንተስ ባህሪ እንዴት ይገለፃል?
መድሃኔ፦ ከሜዳ ውጪ ከሰው ጋር እጫወታለሁ፤ እስቃለሁ። አንዳንዴ ደግሞ ሜዳ ውስጥ ሰውም ይነግረኛል መሸነፍን ስለማልፈልግ ልጣላም እችላለሁ፤ ያልሆነ አክሽንም ላሳይ እችላለሁ እና ይህን ማሻሻል እፈልጋለሁ።
ሊግ፦ ባሳለፍከው የኳስ ህይወት ደስተኛ ነህ?
መድሃኔ፦ በጣም ደስተኛ ነኝ።
ሊግ፦ ተከፍተህ ታውቃለህ?
መድሃኔ፦ በኳሱ ብዙም ተከፍቼ አላውቅም። ከእዛ ውጪ ባለው ህይወቴ ግን ለእኔ ብዙ ነገሮችን ማለትም ትጥቅና ጫማ ጭምር በመግዛት ጥሩ ነገሮችን ያደርግልኝ የነበረውን የምወደውን ወንድሜን በሞት ሳጣ ተከፍቻለው፤ በጣም አዝኛለሁም።
ሊግ፦ በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ ግጥሚያን ካደረግክና ጨዋታን ካሸነፋችሁ በኋላ የመጀመሪያውን ስልክ የሚደውልልህ ሰው ማን ነው?
መድሃኔ፦ እናቴ ነች የምትደውልልኝ። በመጀመሪያም እንኳን በሰላም ከሜዳ ወጣ ትለኝና ውድድሩን በሰላም ጨረስክ ትለኛለች። ከእሷ ውጪ ደግሞ ኤፍሬም ክፍሌ የሚባል ጓደኛ አለኝ ጨዋታን ቁጭ ብሎ ጨርሶ አስተያየት የሚሰጠኝም አለና በእዚህ አጋጣሚ ሁለቱንም አመሰግናችኋለሁ።
ሊግ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን በምን መልኩ እንጠብቀው?
መድሃኔ፦ ቤትኪንጉን ከዕጣ አወጣጡ ጀምሮ አይቼዋለሁ፤ ቀላል የሚባል ነገር አይደለም። የሚከብድ የውድድር ዘመን የምናሳልፍ ይመስለኛል። እኛም አዲስ ቡድን እንደመስራታችን ፉክክሩ ቀላል አይሆንም። ለተመልካችም የሚያምር ውድድር ነው የሚኖረው።
ሊግ፦ ለብሄራዊ ቡድን ተመርጦ በመጫወቱ ዙሪያስ ምን አልክ?
መድሃኔ፦ ለብሄራዊ ቡድን የመጠራት ዕድሉ ገጥሞኝ አያውቅም። ተመርጦ መጫወት ግን የልጅነት እልሜ ነበር። አሁን ግን በእዛ ደረጃ ላይ ተመርጦ ለመጫወት በቂ ነኝ ብዬ ስለማስብ የመመረጥ ፍላጎቴ ጨምሯል። ሀገርን ወክሎ መጫወት ደግሞ የማይፈልግ ሰው የለምና በአሰልጣኙ ታምኖብኝ ለመመረጥ ጥረትን የማደርግ ነው የሚሆነው።
ሊግ፦ ኢትዮጵያ ግብፅን ባሸነፈችበት ጨዋታ ቀን ስሜትህ እንዴት ነበር።
መድሃኔ፦ ጨዋታውን ተሰብስበን ነበር ያየነው። ግጥሚያውንና ውጤቱን ስንመለከት ሀሳባችን ሊገለባበጥ ችሏል። ከብዙ አቅጣጫ ግጥሚያውን ስናይ ደስ የሚል ነበር። አሳምነን ነው ያሸነፍናቸው። ጎሉ ያንሳቸዋል አራትም አምስትም አይበቃም እያልንም ነበርና ያን ጨዋታ ሳይ ምናለ በእዚህ ቡድን ውስጥ በኖርኩም ያስብላል።
ሊግ፦ የእግር ኳሳችንን ደረጃ ከሌሎች ከፍ ካሉት ጋር አነፃፅረህ ምን ብንሰራ እነሱ ላይ መድረስ ይቻላል ትላለህ?
መድሃኔ፦ መጀመሪያ ከስር ታዳጊዎች ላይ በደንብ ተከታትለን መስራት አለብን። ከእዛ ውጪ ደግሞ ሜዳዎች ሊኖረን ይገባል። ሜዳን በተመለከተ ኢትዮጵያን በሚያክል ሀገር ላይ ሜዳ አለመኖርና ግጥሚያዎቻችንን በባህርማዶ ማድረጋችን ይከብዳልና በእዚህ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል።
ሊግ፦ ጎሎችን ከማስቆጠር ጋር በተያያዘ ምን ትላለህ?
መድሃኔ፦ በዘንድሮ ውድድር ላይ ባላገባም በአምናው ውድድር ላይ ግን በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተጫውቼ አገባ ነበር። አሁን ላይ ከጎሎች ርቄያለሁ። ይህን ጎል የማስቆጠር ችግሬን ደግሞ በመጪው ዓመት የምቀረፈው ነው የሚሆነው።
ሊግ፦ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ምሽቱን ተጀምሯል፤ የማን ደጋፊ ነህ? ዘንድሮ ምን ትጠብቃለህ?
መድሃኔ፦ የአርሰናል ደጋፊ ነኝ፤ ክለቡን በጣም ነው የምወደው። ሲያሸንፍ ደስ ይለኛል። ሲሸነፍ ደግሞ ምግብ ሳልበላ የምተኛበት ጊዜ አለ። ይሄ ቡድን ጥሩ መጣህ ስትለው የሚቀርበት ጊዜም አለና ዘንድሮ ግን ጥሩ ውጤት የሚያመጣ ይመስለኛል።
ሊግ፦ በልጅነት ዕድሜህ የማን ተጨዋች አድናቂህ ነበርክ?
መድሃኔ፦ ከሀገር ውስጥ ከአጠገቤ ደደቢት ውስጥ ሆኜም ስላየሁት የስዩም ተስፋዬ አድናቂ ነኝ። እሱ የተለያዩ ቦታዎች ላይ መጫወት ይችላል። ያኔም ነው አይኔ ውስጥ ገብቶ ያደነቅኩት። እኔንም እነሱ ሲያሳድጉኝ በእሱ ቦታ እንድጫወትም ጭምር ነውና ይሄን ነው የምፈልገው። ከውጪ የማደንቀው ደግሞ ሊዮኔል ሜሲን ነው። በጣም ነው የምወደው። በእኔ ቦታ በመጫወት ደግሞ የዳንሄል አልቬስ አድናቃ ነኝ።
ሊግ፦ እናጠቃል?
መድሃኔ፦ በኳስ ህይወትህ ብዙ ሰው ይኖራል። በመጀመሪያ ፈጣሪዬን ማመስገን እፈልጋለሁ፤ ሲቀጥል ደግሞ እዚህ ደረጃ ላደረሰኝና ብዙም ነገር ላደረገልኝ አክረም አብዱልቃድር ምስጋናን አቀርብለታው። ከእሱ ውጪ ወንድሜ ሳሙኤል ብርሃኔንና እናቴን እንደዚሁም የራዕይ አሰልጣኜን ኤፍሬምን በማመስገን ፈጣሪ ሁሉንምን ያክብርልኝ ነው የምለው።