የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሩዋንዳ አቻውን አሸንፎ ለቻን የአፍሪካ ዋንጫ ያለፈ ሲሆን ይህን ድል አስመልክቶና ከቡድኑ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የቡድኑ ተጨዋች ሚሊዮን ሰለሞን ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርቦለት ምላሽን ሰጥቷል።
የሩዋንዳ አቻቸውን ስላሸነፉበት ጨዋታና ለቻን የአፍሪካ ዋንጫ በማለፋቸው ስለተሰማው ስሜት
“ለጨዋታው ወደ እነሱ የተጓዝነው ግጥሚያውን በግዴታ እናሸንፋለን ብለን ነበር። ጠንክረን ለመጫወት ስለቻልንም ባለድል ሆነናል። ለቻን የአፍሪካ ዋንጫውም ስናልፍ በተለይ ለእኔ የመጀመሪያዬ ስለሆነም በጣም ደስ ብሎኛል፤ ፈጣሪ ስለረዳንም ለእሱ ክብርና ምስጋና ይግባው”።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለቻን ሲያልፍ በቋሚነት ተሰልፈህ ተጫውተህ ነበር። ተሰልፎ መጫወት እና ከውጪ ሆኖ ግጥሚያን በማድረግ እና ባለድል በመሆን ዙሪያ ያለውን ልዩነት እንዴት ተመለከትከው
“እንደ እኔ አመለካከት ገብቶ መጫወትም ሆነ ከውጪ ሆኖ ይህን ድል ለማሳካት መቻል ዞሮ ዞሮ ድሉ የሀገር ደስታ ነውና ነገሮችን በጥሩ መልኩ ነው የማየው። ተሰልፈህ የምትጫወተውም የምትቀመጠውም እንደ አሰልጣኙ ውሳኔም ነው”።
የሩዋንዳን ብሄራዊ ቡድን ለማሸነፍ ስለቻሉበት ሚስጥር
“ምንም ሚስጥር የለውም። ከእዚህ ውድድር ከራቅን ስድስት ዓመት አልፎናልና የግጥሚያው ውጤት ለእኛ ያስፈልገን ነበር። ተጋግዘንና ተባብረን ስለተጫወትንም ነው ለውድድሩ ልናልፍ የቻልነው”።
አልጄሪያ ላይ በሚኖረን የውድድር ተሳትፎ ከዋልያዎቹ ምን ውጤት ይጠበቅ?
“ከእዚህ በኋላ ይህ ቡድን የሚቆም አይደለም። ጥሩ ቡድን አለን። ከምድብ በማለፍም ታሪካዊ ውጤትን እናስመዘግባለን”።
ወደ አፍሪካ ዋንጫው ስለማለፍ ተስፋችን
“አሁን ላይ ጥሩ አቋም አለን፤ የሚከብደን ነገርም የለም። ለአፍሪካ ዋንጫው እናልፋለን”።
የዋልያዎቹን መለያ ለብሶ ስለመጫወት
“በጣም ነው ደስ የሚለው። የሀገርን መለያ ለብሶ መጫወት የማንኛውም ተጨዋች እልሙም ነውና የእዚህ ዕድል ባለቤት ስለሆንኩ ፈጣሪዬን አመሰግነዋለሁ”።
የአዲስ ዓመትን ስለሚቀበልበት ሁኔታ
“ከቤተሰብ ጋር ነው የበዓሉን ጊዜዬን የማሳልፈው”።
በመጨረሻ
“ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ እላለሁ”።