በመሸሻ ወልዴ
ኢትዮጵያ ቡና ሲዳማ ቡናን በአቡበከር ናስር ሶስታ /ሀትሪክ/ ግቦች እንደዚሁም ደግሞ በአስራት ቶንጆ እና በሀብታሙ ታደሰ ተጨማሪ ግቦች 5-0 በማሸነፍ በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ የደረጃው ሰንጠረዥ ሁለተኛ ስፍራ ላይ ሊቀመጥ ችሏል፤ ፋሲል ከነማ ደግሞ ሊጉን እየመራ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ሲዳማ ቡናን ድል ባደረገበት ጨዋታ ሌሎችም ግብ ሊሆኑ የሚችሉ እድሎችን ያልተጠቀመባቸው ሲሆን በተጋጣሚው በኩልም ከርቀት የተደረጉ የግብ ሙከራዎች በጨዋታው ላይ ሊታዩ ችለዋል፤ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ልቀው በታዩበት በእዚህ ጨዋታ አቡበከር ናስር ሀትሪክ መስራቱን ተከትሎምየኳስ ስጦታ የተበረከተለት ሲሆን ለተጨዋቹ ሀትሪክ ሲሰራ የአሁኑ ሁለተኛውም ሊሆን ችሏል፤ ኢትዮጵያ ቡና እንደ ቡድን ጥሩ በነበረበት ጨዋታ ላይ የኮሪደር ስፍራው ተጨዋች አስራት ቶንጆም ጎል ከማስቆጠሩ ባሻገር ለሁለት ግቦች መገኘትም ኳስ ለጓደኞቹ በማቀበል የተዋጣለት እንቅስቃሴን ሊያሳይ ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናውን ስኬታማ ተጨዋች አስራት ቶንጆን ሲዳማ ቡናን ድል ካደረጉበት ጨዋታ በኋላ የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በጨዋታው ዙሪያና ሌሎችንም ጥያቄዎች አቅርቦለት ተጨዋቹ ምላሽን ሰጥቷል፡፡
ሊግ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና 5 ሲዳማ ቡና 0 የሚል ውጤት ተመዝግቧል፤ ጨዋታው እንዴት ይገለፃል…..ስለ ጎሉስ ብዛት?
አስራት፡-ሲዳማ ቡናን የተፋለምንበት ጨዋታ ለእኛ በጣም ጥሩ የነበረና ተጋጣሚያችንንም በኳስ ቁጥጥር በልጠን የተጫወትንበት ነው፤ ይህን ጨዋታ ለማሸነፍ እንድንችልም የረዳን ባለፉት ሁለት ግጥሚያዎቻችን ላይ በወላይታ ድቻ ተሸንፈንና ከባህር ዳር ከተማ ጋር ደግሞ አቻ ተለያይተን ስለነበር ከእነዚህ ሁለት ጨዋታዎች ክፍተቶቻችን ብዙ የተማርናቸው ነገሮች ስለነበሩ ነው፤ ከዛ ውጪ በተጋጣሚያችን ላይ በርካታ ጎሎችን ለማስቆጠር እንድንችልም ያገዘን ነገር ቢኖር የሁላችንም ተጨዋቾች በጥሩ አቋም ላይ መገኘት መቻላችንና አጥቅተንም በመጫወታችን ነው፡፡
ሊግ፡-ሲዳማ ቡናን ድል ስታደርጉ ጠንካራ እና ደካማ ጎናችሁ ምን ነበር?
አስራት፡- በጨዋታው ላይ የነበረን ጠንካራው ጎን ከፍተኛ ተነሳሽነታችንና የማሸነፍ ፍላጎታችን ነበር፤ በተለይ ደግሞ ወደፊት አጥቅተን ስንጫወት እንደ ቡድንም እንንቀሳቀስ ስለነበር ይሄ ለስኬት አብቅቶናል፤ በድክመት ሳይሆን ክፍተት ደረጃ የማነሳው ደግሞ ከእዚህ በፊት የኳስ ሂደቱን ከኋላ በምንጀምርበት ሰዓት ራሳችን በምንሰራቸው ስህተቶች ከሜዳው ለጨዋታ አስቸጋሪ ከመሆኑ ጋርም ተዳምሮ ጎሎች ይቆጠሩብን ነበር፤ ይሄን ለማስተካከል ጥረት እናደርጋለን፤ በሲዳማ ቡናው ጨዋታም ላይ ጎል ሳይቆጠርብን መውጣታችንም እንደ ጥሩ ነገር የሚታይ ነው፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና በጨዋታው ላይ የድል ጎልን አስቆጥረሃል፤ ሌሎች ግቦች እንዲቆጠሩም ምክንያት ሆነሃል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን ማለት ይቻላል?
አስራት፡-ከሲዳማ ቡና ጋር በነበረን ጨዋታ ጥሩ በመጫወቴ እና ጎል በማስቆጠሬ ከፍተኛ ደስታ ነው የተሰማኝ፤ በተለይ ደግሞ ይሄ ጨዋታ ቡድናችንን ወደ አሸናፊነት መንፈስ እንዲመለስ ያደረገ እና ለእኔም ከጅማው ግጥሚያ በኋላ ሌላ የድል ግብን ያስቆጠርኩበት ስለሆነምጨዋታው ለቀጣይ ጨዋታዎቻችንም ከፍተኛ ተነሳሽነትን የሚፈጥርልን ነው፡፡
ሊግ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ኢትዮጵያ ቡናን ከሌሎች ቡድኖች የሚለየው የተለየ ነገር አለ?
አስራት፡-ሁሉም ቡድን በሚፈልገው እና ያዋጣኛል የሚል የራሱ እንቅስቃሴ ቢኖረውም የእኛ ቡድንን ደግሞ ከሌሎች ይለየዋል ብዬ ልናገርለት የምፈልገው በኳስ ቁጥጥር ላይ ያተኮረን እንቅስቃሴ ከኋላ በማስጀመር መጫወት መቻሉ ነው፤ ይሄ እንቅስቃሴውም ለውጤት እያበቃው ነው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡናን ወቅታዊ አቋም እና ስለ ቀጣይ ጊዜ የሊግ ተሳትፎአችሁ በተመለከተ ምን ትላለህ?
አስራት፡- ኢትዮጵያ ቡና ሁሌም በግለሶቦች ላይ ተንጠልጥሎ የሚሰራ ሳይሆን እንደ ቡድን ተሰርቶም በመቅረብ ጥሩ እግር ኳስን የሚጫወት ክለብ ነው፤ እስካሁን ያለን ወቅታዊ አቋምም በጥሩ መልኩምየሚገለፅ ነው፤ ጥሩ ቡድን፣ ብዙ ተፅህኖ ፈጣሪ ተጨዋቾችና ምርጥ አሰልጣኝ ስላለን ይሄ ለእኛ ኩራታችንም ነው፤ የዘንድሮ ውድድርም ምንም እንኳን ለድካም የሚዳርግ ቢሆንም ከአሁን የበለጠውን ምርጡን ቡና ግን ለጨዋታ በጣም አመቺ በሆነው የባህር ዳር ከተማ ላይ የምናየው ይሆናል፤ እዛም ጠብቁንም ነው የምለው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና የውድድር ዓመቱ ሲጠናቀቅ በየት ደረጃ ላይ ይቀመጣል?
አስራት፡-እንደ ትልቅ ቡድንነታችን የምንጫወተው ለሻምፒዮናነት ነው፤ በአሁን ሰዓት የቡድን መንፈሳችንም በጣም ጥሩ ስለሆነ ከፈጣሪ እርዳታ ጋር በአንደኛ ስፍራ ነው የውድድር ዓመቱን ማጠናቀቅ የምንፈልገው፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ጎል ስታስቆጥር ምን አይነት ስሜት ይሰማሃል?
አስራት፡-የተለየ ደስታ ነዋ! ከእዚህ በፊት ውሌን በጨረስኩበት አካባቢ ጎሎችን አገባ ነበር፤ ዘንድሮም ደግሞ ከጅማ አባቡና ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ እንዲሁ ጎል ላገባ ችያለው፤ ጎሎቹ በተለይ ቡድኑን ለድል የሚያበቁ ሲሆን በከፍተኛ ሁኔታም ነው የምደሰተው፡፡
ሊግ፡- በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ስር እየሰለጠንክ ነው፤ ስለ እሱ ምን ትላለህ…እንዴትስ አገኘኸው?
አስራት፡-ካሳዬ አራጌ ጎበዝ እና ለየት ያለ አሰልጣኝ ነው፤ ከማሰልጠን ችሎታው ባሻገርም ያለው ስብህና በጣም ይገርማል፤ የራሱ የሆነ የአሰለጣጠን መንገድም ያለው ባለሙያ ስለሆነ በእሱ ስር መሰልጠኔን እንደ እድለኛ አድርጌ ነው ራሴን የምቆጥረው፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመመረጥ ችለሃል፤ መመረጥህ ዘግይቷል?
አስራት፡-እኔ እንደዛ ብዬ አላስብም፤ ምክንያቱም አንድ አሰልጣኝ ተጨዋቾቹን ሲመርጥ ጥሩ ስለሆንክና ስላልሆንክ ብቻ አይደለም፤ ለሚፈልገው አጨዋወት ይሆነኛል የሚለውንና ለአጨዋወቱ ጥሩ የሚለውን ተጨዋች ነው የሚመርጠው፤ ከእዚህ በፊት ለነበሩት አሰልጣኞች እኔ ለአጨዋወታቸው ስላልሆንኩ አልተመረጥኩም፤ አሁን ደግሞ ጥሩ ስለሆንኩ እና ለአሰልጣኙ አጨዋወት ትሆናለህ ስለተባልኩ ተመረጥኩኝ፤ ይሄ እግር ኳስ ነው፤ ሁሉንም ነገር እንደአመጣጡ ልትቀበል የግድ ይልሃል፤ እኔ አሁን የቡድኑ አባል ሆኛለሁ፤ ለብሔራዊ ቡድን በመመረጤም ተደስቻለው፡፡
ሊግ፡- በተለያዩ የማህበራዊ ድረ-ገፆች ላይ የቡና ደጋፊዎች እና አድናቂዎችህ “ዝምተኛው ገዳይ” ብለው እያሞካሹክ ይገኛል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለ?
አስራት፡-የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችም ሆኑ አድናቂዎቼ ሁሌም ለሚሰጡኝ ማበረታታት መጀመሪያ ከልብ ላመሰግናቸው እፈልጋለው፤ የእነሱ ብርታትና ድጋፍም ለእኔ ትልቅ የሞራል ስንቅም ነው የሚሆነኝ፡፡
ሊግ፡- በኳሱ አድናቂዎችህ ዝምተኛው ገዳይ ብለውካል፤ ግን ዝምተኛስ ነህ?
አስራት፡-አላውቅም፤ የሚቀርበኝ ሰው ሲኖር በደንብ ነው የማወራው፡፡
ሊግ፡- አቡበከር ናስር ለኢትዮጵያ ቡና በርካታ ጎሎችን እያስቆጠረለት ይገኛል፤ በአቡበከር ዙሪያ የምትለው ነገር አለ?
አስራት፡-አዎን፤ አቡኪ ለቡና ጎል እያስቆጠረ ያለው እንደ ቡድን ስለምንጫወት ነው፤ እሱ በእንቅስቃሴ ደረጃ ሁሌም ቢሆን ካለው የግል ችሎታ በመነሳት ኳስ እንድታቀብለው ያስገድድሃል፤ ለቡና በጣም ወሳኙ ተጨዋችም ነው፤ እንዳለው ምርጥ ችሎታም ገና ልጅ ስለሆነም ወደ ባህር ማዶ ወጥቶም መጫወት ይችላል፡፡
ሊግ፡- በመሀል ተጨዋችነት ነበር የምትታወቀው፤ ለኢትዮጵያ ቡና ግን በርካታ ጨዋታን የምታደርገው የመስመር ላይ ተጨዋች ሆነህ ነው፤ ቦታው ተስማምቶሃል?
አስራት፡- አዎን፤ ከእዚህ በፊት በነበረኝ የኳስ ህይወቴ ለጅማ አባጅፋርም ሆነ ለሰበታ ከተማ ስጫወት የነበርኩት በአማካይ ስፍራ ላይ ነበር፤ በቡናም በእዚህ ስፍራ ላይ የተጫወትኩበት ጊዜ ነበር፤ በቡድኑ ቆይታዬ አብዛኛውን ግልጋሎቴን የሰጠሁት ግን በመስመር ላይ በመጫወት ነው፤ እኔ በየቱም ስፍራ ላይ ልጫወት የሚስማማኝ አይነት ተጨዋች ነኝ፤ ለአሰልጣኜም ታክቲክ ተገዥ እና በሚያጫውተኝ ቦታ ሁሉ ለመጫወት ራሴን ሁሌ አዘጋጀዋለው፡፡
ሊግ፡- በትዳር ህይወት ውስጥ እንዳለህ እናውቃለን፤ ከኳስ ህይወትህ ጀርባ የባለቤትህን እገዛ እንዴት ትገልፀዋለህ? ባለቤትህ ማንስ ትባላለች?
አስራት፡-ባለቤቴ መሰረት ጣሰው ትባላለች፤ ለስድስት ዓመት በፍቅር ስንቆይ ካገባዋት ደግሞ አሁን ሁለተኛ ዓመቴ ነው፤ ከእሷ ጋር ትውውቅን ካደረግንበት ጊዜ ጀምሮ ዛሬ ላይ ለደረስኩበት የኳስ ደረጃ የእሷ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፤ ሁሌም ከጎኔ ሆናም ብዙ ነገሮችንም ትረዳኛለች፤ ታግዘኛለችም፤ በእዚህ አጋጣሚ ይህቺን መልካም እና ልዩ የሆነችውን ባለቤቴን ላመሰግናት እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- በኳስ የመጨረሻ ግብህ የት ድረስ መጓዝ ነው?
አስራት፡-እንደ ማንኛውም እግር ኳስ ተጨዋች ዕድሉን ካገኘው ከሀገር ወጥቼ መጫወትን እፈልጋለው፤ ኳሳችን አሁን ላይ በዲ.ኤስ.ቲቪም እየተላለፈ ስለሆነም ይሄን አጋጣሚ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
ሊግ፡- እግር ኳስ ለአንተ ምንህ ነው?
አስራት፡-ህይወቴ፣ መዝናኛዬ እና ስራዬ ነው፤ ይሄን እድል ያላገኙም ብዙ አሉና ኳስ ተጨዋች በመሆኔ እድለኛ ነኝ፤ ኳስንም በጣም አከብራታለው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ….?
አስራት፡-የእግር ኳስ ጨዋታን መጫወት ስጀምር ቤተሰቦቼ ብዙም ሊጫኑኝ ያልቻሉና ለእኔም በጣም ጥሩ የነበሩ ስለሆኑ ለእዚህ ደረጃ መድረሴ ከፈጣሪ ቀጥሎ ትልቅ አስተዋፅኦን ሊያደርጉልኝ ችለዋልና ምስጋና ይገባቸዋል፤ ፈጣሪዬንም ለእዚህ ስላበቃኝ አመሰግነዋለው፤ ከዛ በተረፈ ሁሌም እኔን ለሚያበረታቱኝ አድናቂዎቼም ሆኑ የቡና ደጋፊዎችም ምስጋናን አቀርባለው፡፡