Google search engine

“ምርጥ ስብስብ አለን፤ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እንጫወታለን” ኤፍሬም ዘካሪያስ /አዳማ ከነማ/

 

ሊግ፡- ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በሜዳችሁ እና በደጋፊዎቻችሁ ፊት ተጫውታችሁ አቻ ተለያይታችኋል፤ ግጥሚያውን እንዴት አገኘኸው?
ኤፍሬም፡- ቅዱስ ጊዮርጊስን የተፋለምንበት ጨዋታ ለክለባችን ብቻ ሳይሆን በቅርቡ ከጉዳት ርቄ ለመጣሁት ለእኔም ጥሩና ተጋጣሚያችንንም በልጠን የተጫወትንበት ነበር፡፡ በረቡዕ ጨዋታችን ያለንን አቅም ሁሉ አውጥተን ተጫውተናል፤ ያም ሆኖ ግን ያገኘናቸውን የጎል አጋጣሚዎች ለመጠቀም ስላልቻልን ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስን በሁለቱ 45 ደቂቃዎች ስትፋለሙ የነበራችሁን የጨዋታ እንቅስቃሴ ብትገልፅልን?
ኤፍሬም፡- አዳማ ከነማ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ በነበረው ጨዋታ እኔን የመስመር ተጨዋች አድርጎ ስለተጠቀመብኝ በዚህ ጊዜ የነበረን እንቅስቃሴ በተጋጣሚያችን ላይ ብዙም ጫና የፈጠርንበት አልነበረም፤ የሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግን ከነበርኩበት ዳር ወጥቼ ወደመሃል ስገባ እና የቡድናችንም አሰልጣኞች የአጨዋወት ታክቲካቸውን ሲቀይሩ በጣም ጥሩ ሆንና ተጋጣሚያችንን በእንቅስቃሴ ልንበልጥ ቻልን፤ በዚህ አጨዋወት ውስጥ ከነሃን ማርክነህ ከመስመር /ዳር/ ሲነሳ ሲነሳ ጥሩ ስለነበርም በዚህ ጎል የማስቆጠር እድሎችን ፈጥረን ባንጠቀምበትም ቀኑ ጥሩ የተጫወትንበት ነበር፡፡
ሊግ፡- 0ለ0 የተጠናቀቀው የአዳማ ከነማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ውጤቱ ለሁለታችንም ተገቢ ነው ትላለህ?
ኤፍሬም፡- ለእኔ በበኩሌ ውጤቱ ጥሩ ነበር ብዬ አላስብም፤ ካገኘናቸው የጎል እድሎች አንፃር ጨዋታውን ቢያንስ 2ለ1 ማሸነፍ ይገባን ነበር፤ እነሱ ጎል የማስቆጠር ንፁህ የጎል እድል ያገኘሁት መጨረሻ ላይ ሀሜ የሞከራት ናት፤ የእኛ ቡድን ግን ሁለት ጎል ሊሆኑ የሚችሉ እድሎችን አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡
ሊግ፡- የአዳማ ከነማ የዘንድሮ አቋም እንዴት ይገለፃል? በቀጣይነትስ ከቡድናችሁ ምን ይጠበቅ?
ኤፍሬም፡- አዳማ ከነማ እስካሁን የመጣበት መንገድ ጥሩ የሚባል ነው፤ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እየተሻሻለም ይገኛል በሊጉ ውድድር ባለፉት 7 ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ አልተሸነፍንም፡፡ የአቻ ውጤትና የድል ውጤትን እያስመዘገብንም ይገኛልና በቀጣይነት ደግሞ ማሸነፍን በማስቀጠል ለሻምፒዮናነቱ የመፎካከር ተስፋው በጣሙን አለን፡፡
ሊግ፡- አዳማ ከነማ ፕሪምየር ሊጉ ላይ ባለው አቋም ጥሩ ጎኑና ሊያስተካክለው የሚገባው ምንድነው?
ኤፍሬም፡- የፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ ክለባችን ሊያስተካክለው የሚገባው ዋናው ነገር ወደ ተቃራኒ ቡድን የሜዳ ክልል ከደረስን በኋላ ግብ የማስቆጠር ችግር አለብን እና ያን መቅረፍ ይጠበቅብናል፤ በቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታም የታየው ይሄ ነው፤ ግብ ጋር ስንደርስ የመረጋጋት ችግር አለብን፡፡ ይሄ ሊስተካከል ይገባል፡፡ በጥሩ ጎኑ የምጠቅሰው ደግሞ ኳስ ተቆጣጥረን መጫወታችንን ነው፡፡
ሊግ፡- የአዳማ ከነማ የተጨዋቾች ስብስብ በአንተ እይታ ሲገለፅ? የሁለተኛው ዙር ላይስ ምን አይነት አቋም ይኖራችኋል?
ኤፍሬም፡- የክለባችን የተጨዋቾች ስብስብ በአብዛኛው በወጣቶች ከመገንባቱ በተጨማሪ ምርጥ እና ጥሩ የሚባል ነው፤ ኳስን በሚገባ መጫወት የሚችሉ ልጆችንም የያዝንበት ነው፤ በቀጣይነት ደግሞ ለሁለተኛው ዙር የውድድር ተሳትፎአችን ቡድናችንን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ልጆችንም ክለባችን ሊያስፈርም የተዘጋጀበት እና የቀድሞውን ተጨዋች ብሩክ ቃልቦሬንም በመሀል ሜዳው ላይ እንዲያገለግለን ያስፈረመበት ሁኔታ ስላለ በሁለተኛው ዙር ላይ አዳማን ከመጀመሪያው ዙር በበለጠ በጣም ጠብቁት፤ ጥሩ ጨዋታን ከውጤታማነት ጋር ያሳያችኋል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፉክክር በተቀራረበ ነጥብ ላይ ይገኛል፤ ከዚህ አንፃር እንዴት አገኘኸው?
ኤፍሬም፡- የፕሪምየር ሊግ ፉክክሩ በጣም ነው ደስ የሚለው፤ አሁን ላይ ወደፊት ነጥሮ የወጣ ክለብም ስለሌለ ከመሪው ክለብ ጋር በተቀራረበ ነጥብ ላይም ነው የምንገኘው፤ ብዙ ክለቦች በነጥብ ተጠጋግተው ይገኛሉ፤ የሁለተኛው ዙር ላይ ይሄ ከቀጠለ ሊጉ አዲስ ሻምፒዮና ያገኛል ብዬ አስባለሁ፡፡
ሊግ፡- የአዳማ ከነማን ደጋፊዎችን እንዴት ነው የምትገልፃቸው?
ኤፍሬም፡- የአዳማ ከነማ ደጋፊዎች ለሚሰጡን ድጋፍ ሁሌም ነው የማመሰግናቸው፤ በየጨዋታው እያበረታቱን ይገኛል፤ ከዚህ በላይም ከጎናችን ሊቆሙ ይገባል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P