test
Google search engine

“ምርጥ ብቃቴን በተደጋጋሚ ጊዜ ማሳየትና ወደ ውጪ ወጥቶ መጫወት ምኞቴ ነው”ሱሌይማን ሃሚድየኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የኮሪደር ስፍራው ተጨዋች ሱሌይማን ሃሚድበእግር ኳስ ተጨዋችነቱ ለሀገር ብሔራዊ ቡድን በተደጋጋሚ ጊዜ ከመጫወት አልፎ ምርጥ ብቃቱን ለማሳየት እንደዚሁም ደግሞ እስከ ፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃም ወደ ውጪ ወጥቶ ለመጫወት ከፍተኛ ምኞት እንዳለው ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረገው ቆይታ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
በቤተሰቡ ውስጥ ከሚገኙት አምስት እህቶቹ እና ሶስት ወንድሞቹ መካከል ብቸኛው ስፖርተኛ የሆነው ሱሌይማን ጋር በኳስ ህይወቱ ዙሪያና ሌሎችንም ጥያቄዎች ጨምረን አናግረነዋልና የእሱ ምላሽ በሚከተለው መልኩ ይቀርባል፤ ተከታተሉት፡፡
ስለ ትውልድ ስፍራው እና አስተዳደጉ
“የተወለድኩት እና ያደግኩት በቤንሻንጉልአሶሳ ከተማ ውስጥ ነው፤ የልጅነት አስተዳደጌም ኳስን በመጫወት ነው፤ ከዛም ትንሽ ከፍ ስል አዲስ አበባ ወደሚገኘው የኢፌዲሪ ወጣቶች አካዳሚ ቡድን ውስጥ በመግባት ይሄን የእግር ኳስ ተጨዋችነት ጉዞዬን አጠናክሬ ልቀጥልበት ቻልኩ”፡፡
የእግር ኳስን በልጅነት ዕድሜው መጫወት ሲጀምርበቤተሰቡ አካባቢ ስለነበረው አመለካከት
“በእዛን ወቅት የእግር ኳስንእንዳልጫወት ቤተሰቦቼ ምንም አይነት ተፅህኖን አያሳድሩብኝም ነበር፤ እነሱ ትምህርትህን በደንብ ተማር ኳስንም ተጫወት ነበር የሚሉኝ፤ ከዛ ውጪ ደግሞ ሁሌም ዲስፒሊን ያለኝ ልጅ እንድሆንና ሰዎችንም እንዳከብርም አድርገውም ነበር ያሳደጉኝና በእዚህ አጋጣሚ ዛሬ ላይ ለደረስኩበት ደረጃ የእነሱ ትልቅ አሻራ ስላለበት ላመሰግናቸው እፈልጋለውኝ”፡፡
በቤተሰቡ ውስጥ የእግር ኳስን የሚጫወተው እሱ ብቻ እንደሆነ
“አዎ፤ ኳስ ተጨዋቹ እኔ ብቻ ነኝ፤ ወንድሞቼና እህቶቼ ተማሪዎች ናቸው፤ በጥሩ ደረጃም ላይ የሚገኙ”፡፡
የልጅነት ዕድሜው ተምሳሌቱ ስለነበረው ተጨዋች
“የእግር ኳስን እስከዛሬ ድረስ አብሬው ባልጫወትም የልጅነት ዕድሜዬ ላይተምሳሌቴ እና ሞዴሌ አድርጌው የነበረው ተጨዋች ሳላህዲን ሰይድ ነው፤ ሳላን በእዛ ደረጃ ላይ ልገልፀው የቻልኩትም የዛሬ 8 ዓመት አካባቢ ወደተወለደበት ወደ እኛ ክልል ለእረፍት በመጣበት እና በአሶሳ ስታድየም ላይም ኳስን በሚጫወትበት ሰዓት ነው ያለውን ችሎታ ተመልክቼ እና ስለ ገናና ስሙና ዝናውም በአግባቡ ተረድቼ እሱን አርአያዬ ላደርገው የቻልኩት”፡፡
የቤንሻንጉል ክልልለተለያዩ ክለቦችና የብሔራዊ ቡድናችን ብቁተጨዋቾችን እያፈራች ስላለችበት ጉዞዋ
“ከክልላችን ከእዚህ በፊት ብዙ ተጨዋቾች ይወጡ ነበር፤ አሁን እንደውም ተቀዛቅዟል፤ ስለዚህም በእዚህ ጊዜ የእኔና የረመዳን በብሔራዊ ቡድን ደረጃ መገኘት መቻል እንደ እድለኛነትም ይቆጠራልና ሌሎች የክልላችንም ተጨዋቾች እንደዚህ ያለውን አጋጣሚዎች ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረትን ሊያደርጉ ይገባል፡፡ የእግር ኳስ ተጨዋች ስትሆን ሁሌም በእዚህ ደረጃ ላይ ለመገኘት የዓላማ ፅናትን ይጠይቃል፤ በርትተህ ከሰራህም የትም መድረስ ይቻላልና ከእኛ በታች ያሉት ታዳጊ ተጨዋቾች ፈለጋችንን ከተከተሉ ጥሩ ደረጃ ላይ ሊደርሱም ይችላሉና እኛም ልናግዛቸው ይገባል”፡፡
በአዳማ ከተማ ውስጥ አንተን ጨምሮ ሁለት ሱሌይማን የሚባሉ ተጨዋቾች ስለመኖራቸው
“አዳማ ከተማን አሁን ለቀቅኩኝ እንጂ ሱሌይማን የምንባለው ተጨዋቾች ሁለት ነበርን፤ አንዱ እኔ ስሆን ሌላው ደግሞ ለብሔራዊ ቡድናችንና ለተለያዩ ክለቦች የተጫወተው ሱሌይማን መሐመድ ነበር፤ ቡድኑ ውስጥ እኛ እንለይ እና እንጠራ የነበረውም እንደ ቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለቱ ተጨዋቾች አንዋሮች አይነት ትንሹ ሱሌይማንና ትልቁ ሱሌይማን በመባልም ነበር፤ በእዚህ አጋጣሚ ሱሌይማን እኔን በጣም የሚመክረኝ ነው፤ እንደእሱም እግር ኳስን ለረጅም ዓመታትም እንድጫወት ልምዱን እያካፈለኝም ይገኛልና ላመሰግነው እፈልጋለው”፡፡
ስለ ረመዳን ናስር
“ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመመረጥ በአሁን ሰዓት ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ እያሳየ የሚገኘው ረመዳን ናስር ለእኔ የትውልድ ክልሌና የሰፈሬ ልጅ ነው፤ ከልጅነታችን ዕድሜም ጀምሮ ነው በመተዋወቅ ጭምር አብረን ነው ያደግነው፤ እሱ ጥሩ ችሎታ ያለውና ወደፊትም ትልቅ ደረጃ መድረስ የሚችል ነው”፡፡
ስለመጀመሪያ ክለቡ እና የቡድኑ ቆይታ
“በክለብ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የእግር ኳስን የተጫወትኩት በወጣት ቡድን ደረጃ ለኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ ቡድን ነው፤ እዛም በነበረኝየሶስት ዓመት ቆይታዬ ጥሩ ስንቀሳቀስ ነበር፤ ከዛም ውጪ ያንን የተመለከቱ ቡድኖችም እኔን የቡድናቸው አካል ለማድረግም በወቅቱ ፍላጎትን አሳድረውም ነበር”፡፡
ወደ አዳማ ከተማ ስላደረገው ዝውውር
“በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ወደ ሚወዳደረው የአዳማ ከተማ እግር ኳስ ቡድን ላመራ የቻልኩት በጊዜው ከመከላከያ፣ ከደደቢት፣ ከባንክ እና ከቡና የቀረቡልኝን ጥያቄዎች ካጤንኩ በኋላ መጀመሪያ ለእዚህ ቡድን ልጫወት በሚል ከውሳኔ ላይ ልደርስ ስለቻልኩ ነው፤ በአዳማ ከተማ ውስጥ በነበረኝ የአራት ዓመት የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬም ከቡድኑ ጋር ጥሩ ጊዜን ነበር ያሳለፍኩት፤ አዳማ ከተማ ለእኔ ትልቁን ውለታ የዋለልኝ ቡድኔ ነው፤ ዛሬ ላይ እስከ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ እንድጫወትም የጥሪጊያውን መንገድ አመቻችቶልኛልና የቀድሞ ክለቤን ሳላመሰግን አላልፍም”፡፡
በእግር ኳስ ተጨዋችነቱ አሁን የደረሰበት ደረጃ ፈጣን እንደሆነ
“አዎን፤ የእኔ እድገት በጣም ነው የፈጠነው፤ የእግር ኳስን በፕሮጀክት ደረጃ በአሶሳ ውስጥ ስጫወት እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ጉዞዬ ሩቅ ይሆናል ብዬ ነበር ያሰብኩት፤ የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ግን ጠንክሬ ስለሰራው፣ ነገሮች ስለቀለሉልኝ እና ፈጣሪዬም ዓላ ስላለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለጥሩ ደረጃ ልበቃ ችያለሁ፤ ለእዚህ ላበቃኝ አምላኬም አላምዲሊላሂ በማለት አመሰግነዋለሁ”፡፡
በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ስላደረገው ጨዋታ
“የአዳማ ከተማ ተጨዋች በነበርኩበት ሰዓት የመጀመሪያዬን የሊግ ጨዋታ ያደረግኩት ከወላይታ ድቻ ጋር በነበረው እና በእኛ የ2-1 አሸናፊነት ውጤት በተጠናቀቀው የሜዳችን ውጪ ፍልሚያ ላይ ነበር፤ ያኔ ተቀይሬም ነበር የገባሁት፤ በወቅቱ ከወጣትነቴ እና ልምድ የሌለኝ ተጨዋች ከመሆኔ አኳያ ግጥሚያው በወቅቱ ከፍተኛ ጫና የነበረው ቢሆንም እኔ ግን ጥሩም ልንቀሳቀስ ችያለሁ፤ በጊዜው ይሄን የመሰለፍ እድልም ስላገኘው በጣምም ተደስቻለሁ”፡፡
ከአጥቂነት ወደ መስመር ስፍራ ተጨዋችነት ስላመራበት መንገድ
“የእግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት አጥቂ ሆኜ ነው፤ ይሄን ስፍራ በመቀየር ወደ መስመር /ፉል ባክ/ ተጨዋችነት ላመራ የቻልኩት በአዳማ ከተማ ክለብ የተጨዋችነት ቆይታዬ በእዛ ስፍራ ላይ የሚጫወተው ተስፋዬ ነጋሽ በቀይ ካርድ የወጣበት እንደዚሁም ደግሞ አንዳርጋቸው ይላቅ /ማቲ/ በጉዳት ያልተሰለፉባቸው ሁኔታዎች በመፈጠራቸው በእነሱ ቦታ ላይ ነው ገብቼ እንድጫወት እድሉ ስለተፈጠረልኝ በእዛ ስፍራ ላይ ልጫወት የቻልኩት”፡፡
አዳማ ከተማን ለቅቆ ወደ ሀድያ ሆሳህና ስለማምራቱ እና ዘንድሮ በምን መልኩ ለመቅረብ እንደተዘጋጀ
“የአዳማ ከተማን ለመልቀቅ የቻልኩት ሀድያ ሆሳህና ባቀረበልኝ ጥሪ እና በሰጠኝም ጥሩ ጥቅም ለቡድኑ ለመጫወት ስለፈለግኩኝ ነው፤ የእዚህ ቡድን የተጨዋችነት ቆይታዬም እንደ አዳማ ከተማ ሁሉ ጥሩ ይሆንልኛል ብዬ አስባለው፤ በሊጉ ዘንድሮ ጥሩ ብቃቴን በማሳየት ክለቡን ለስኬታማነት ለማብቃትም ከፍተኛ ጥረቴን አደርጋለው”፡፡
ዲ.ኤስቲቪ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታችንን ሊያስተላልፍ ስለመሆኑ
“ይሄ ለኳሳችን እድገት በጣም ጥሩ እና የሚያስደስትም ነገር ነው፤ የእኛ ሊግ ከእዚህ በፊት እንደዚህ ያለን የሚዲያ ሽፋን ባለማግኘቱ ተጎድቶ ነበር፤ አሁን ግን ጨዋታዎቹ ዲ.ኤስ.ቲቪን በሚጠቀሙ የዓለም ሀገራት ላይ ሲተላለፉ ብዙ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች እንዲኖሩን ያደርጋልና ለእዛ ሁላችንም ጠንክረን ልንሰራ ይገባል”፡፡
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ስለመጫወቱ
“የልጅነት እልሜ ለነበረው ለዋልያዎቹ ተመርጦ መጫወት መቻል ለእኔ ከምነግርህ በላይ ከፍተኛ ደስታን እየሰጠኝ ይገኛል፤ ይሄን እድል ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘሁትም ከዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በተደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ነው፤ በእዛ ግጥሚያ መጀመሪያ ላይ ተደናግጬ ነበር፤ ከዛም የብሔራዊ ቡድናችን ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች አይዞህ እያሉ ስላበረታቱኝ ያ ግጥሚያ ለእኔ ትልቅ ትምህርትን የሰጠኝም ሆኗል”፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የኒጀር አቻውን ስለማሸነፉ እና ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ስለሚኖረው እድል
“ከኒጀር ጋር ባደረግነው የሜዳችን ላይ ጨዋታ እኛ ያስመዘገብነው የድል ውጤት በጣም የሚገባን ነው፤ አይደለም በሜዳችን በእነሱም ሀገር ላይ የነበረንን ግጥሚያ ተሸነፍን እንጂ አሸናፊነቱ ለእኛ ነበር የሚገባን፤ ግን ምን ታደርገዋለህ፤ በፈጣሪ ስራ መግባት አይቻልምና ያ ውጤት በጣም ነው የቆጨን፤ በኒያሚው ፍልሚያችን ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዘን ብንመጣ ኖሮ ለአፍሪካ ዋንጫ የምናልፍበት እድላችን ሰፊ ይሆን ነበር፤ አሁንም ቢሆን ግን በቀጣይ በሚኖረን ሁለት ጨዋታዎች እድላችንን የምንወስነው በራሳችን ስለሆነ በልበ ሙሉነት የምናገረው ይሄ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫው እንደሚያልፍ ነው”፡፡
ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጨዋቾች ስብስብ እና ስለ ቡድኑ መንፈስ
“የዋልያዎቹ ስብስብ በጣም ጥሩ እና በወጣት ተጨዋቾች ጭምር የተገነባ ነው፤ ጥሩ የቡድን መንፈስ እኛ ጋር አለ፤ ሁላችንም ተጨዋቾች ከአንድ እናት ማህፀን የወጣን ያህልም ነው የምንተያየው፤ አሰልጣኛችን የሚሰጠንን ልምምድም በአግባቡ እየሰራንም ነው የቆየነው፤ ይሄ ቡድን በቀጣይነት ጥሩ ነገርን ለመስራት የተዘጋጀም ስለሆነ ወደፊት ጠንካራ እና ውጤታማ የሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን እናያለን”፡፡
ስለ ወደፊት እልሙ
“ፈጣሪ ይርዳኝ እንጂ የእኔ የኳስ እልም ለሀገሬ ብሔራዊ ቡድን በተደጋጋሚ ጊዜ ተመርጬ ከመጫወት ባሻገር ወደ ውጪ ሀገርም ወጥቶ መጫወት ነው ይሄን ማሳካቴ ደግሞ የማይቀርም ነው”፡፡
ከባህር ማዶ ስለሚያደንቃቸው ተጨዋቾች እና ስለሚደግፈው ቡድን
“ከውጪ የአርሰናልና የሪያል ማድሪድ ደጋፊ ነኝ፤ የማደንቀው ተጨዋች ደግሞ ክርስቲያኖ ሮናልዶን ነው”፡፡
ስለ ትዳር አጋሩ
“ከአራት ወራት በፊት ያገባዋት ባለቤቴ ለእኔ በጣም መልካም ሰው ነች፤ ለስኬቴም እገዛዋን አበርክታለች፤ የመጀመሪያ እናት በማንም ስለማትተካም እሷ ሁለተኛዋ እናቴም ነች፤ በጣምም ነው የምወዳት”፡፡
በመጨረሻ
“በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ ዛሬ ላይ ለደረስኩበት ደረጃ ከፈጣሪ ቀጥሎ ከእኔ ጎን ሆነው ላበረታቱኝ፣ ለመከሩኝ እንደዚሁም ደግሞ ከልጅነት እድሜዬ አንስቶ አሁን ድረስ ላሰለጠኑኝ በሙሉ ምስጋናዬን አቀርባለው፤ በተለይ ደግሞ ቤተሰቦቼ ለእኔ ብዙ ነገሮችን አድርውልኛልና መቼም ቢሆን አልረሳቸውም፤ ሌላው በፕሮጀክት ደረጃ ስጫወት ያሰለጠነኝ ማቴዎስ በፍቃዱ እንደዚሁም ደግሞ በአዳማ ከተማ ውስጥ በነበርኩበት ሰዓት የመጫወት እድሉን የሰጠኝን አሸናፊ በቀለን በጣም ነው ላመሰግነው የምፈልገው፤ ሀገራችንን ሰላም እንዲያደርግልንም ምኞቴን እገልፃለው”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

P