ምንያህል ተሾመ /ቤቢ/ /ኢትዮ-ኤሌክትሪክ/
“እግር ኳስን ጠግቤ አልተጫወትኳትም”
ምንያህል ተሾመ /ቤቢ/ እግር ኳስን ለታዋቂዎቹ ክለቦች ኢትዮጵያ ቡና፣ ደደቢት፣ ቅ/ጊዮርጊስ እና የድሬዳዋ ከተማ ክለቦች ተጫውቶ አሳልፏል።
ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም በመጫወት እስከ አፍሪካ ዋንጫ ላይ መሳተፍም ችሏል። ይሄ ተጨዋች በእግር ኳስ ህይወት ቆይታው ስኬታማ ጊዜያቶችን ያሳለፈ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ወደ ታችኛው ሊግ አስቀድሞ ወርዶ የነበረውን ኢትዮ-ኤሌክትሪክን ከቡድን አጋሮቹ ጋር ዳግም እንዲመለስ በማድረግ አኩሪ ታሪክን ሰርቷል፤ ስሙ በመዝገብ እንዲፃፍም አድርጓል።
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ቡድን ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን መቀላቀሉን በማስመልከት እና ከራሱ የቡድኑ ቆይታዎቹ ጋር በተያያዘ የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ከምንያህል ተሾመ ጋር ቆይታን አድርጎ የነበረ ሲሆን ቃለ-ምልልሱም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል። ተከታተሉት።
ሊግ፦ በቅድሚያ ታሪካዊ የሆነው ክለብ እና የሁለት ጊዜው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮናው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ከሶስት ዓመታት በኋላ ዳግም ተቀላቅሏል እንኳን ደስ አለህ? ወደ ሊጉ በመምጣታችሁ ምንስ ስሜት ተሰማህ?
ምንያህል፦ በመጀመሪያ የመልካም ምኞት መልዕክትን ስለገለፃችሁልኝ እኔም አመሰግናለሁ፤ ወደ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ መቀላቀላችንን በተመለከተ ምን ብዬ እንደምገልፅልህ አላውቅም። በጣም ደስ የሚል ስሜት ነው በውስጤ የተፈጠረብኝ። ምክንያቱም ኢትዮ- ኤሌክትሪክን /መብራት ሀይል/ በተመለከተ የሀገሪቱ ትልቅ ክለብ ከመሆኑ አኳያ በሱፐር ሊጉ መወዳደሩ ደረጃው አልነበረምና አሁን ወደ አዲሱ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ መግባት መቻሉ በጣም ነው ያስደሰተኝ።
ሊግ፦ የከፍተኛው ሊግ /ሱፐር ሊጉ/ ውድድር ሲጀመር ይህን እልማችሁን እናሳካለን ብላችሁ በሙሉ እምነት ጠብቃችሁ ነበር?
ምንያህል፦ በእግር ኳስ ጨዋታ የሚከሰተው ነገር አይታወቅም። ግን በመጀመሪያው ዙር የሀድያ ሆሳዕና ቆይታችን ላይ ውድድሩን በአንደኛነት ስናጠናቅቅና ካለን የተጨዋቾች ስብስብ አንፃርም ስንነሳ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመግባት 70 እና 80 ፐርሰንት እርግጠኞች ነበርን። ያም ሆኖ ግን የሁለተኛው ዙር ላይ የእግር ኳሱ ጨዋታ የሚያመጣው ነገር ስለማይታወቅ የሁለተኛው ዙር ላይ ትንሽ አጣብቂኝ የሆኑ ነገሮች አጋጥመውናል።
ሊግ፦ ወደ ኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከማለፋችሁ በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለብን ጨምሮ የሌሎች ተከታይ የሆኑ ቡድኖች አመጣጥ አላስፈራችሁም ነበር?
ምንያህል፦ በመጀመሪያው ዙር ላይ በነበረን ጉዞ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለቡ ከፈረሰ በኋላ ውድድሩ ገና እየተሳተፈበት ያለና የቅድሚያ ጨዋታዎቹም ስለነበር ብዙም ያስፈራን አልነበረም። የሁለተኛው ዙር ላይ ግን ክለቡ ያስፈረማቸው አዳዲስ ተጨዋቾች ስለነበሩና በፈጣን ለውጥም ይከተሉን ስለነበር አመጣጣቸውን እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ስመለከተው አስጨንቆን እና ሊጉም ወደመጠናቀቁ ሲቃረብ ክለቡ ተፎካካሪያችንም ስለነበር አስፈርቶንም ነበር።
ሊግ፦ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ የሀገሪቱ ስመ-ጥር ክለብ ከመሆኑና በተለያዩ የብሄራዊ ቡድን እርከን ደረጃዎችም ለአገራችን ብዙ ተጨዋቾችን ከእዚህ ቀደም ከማስመረጡ አኳያ በታችኛው ሊግ ላይ ሲወዳደር ነበርና ከስሜት ተነስተህ ያን ስትመለከት ምን አልክ?
ምንያህል፦ እንደሚታወቀው የእኛ ክለብ የሆነው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በሀገሪቱ ከሚገኙት ትላልቅ ቡድኖች ውስጥ አንዱ የነበረ ነው። ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስታመራም እነሱም የሚታወቁ ናቸው። የእኛን ብቻ ሳይሆን የባንክም በዛ ደረጃ አሁን ላይ በሚታየው የውድድር ደረጃ የእነሱን ወደ ታችኛው ሊግ ወርዶ መጫወትን ስታይና የክለቦቹን የኋላ ታሪክም ዳስሰህ ስትመለከት በጣም ነው የሚያሳዝነው። በእዛ ደረጃ መወዳደራቸው ለቡድኖቹ አይመጥናቸውም ነበር፤ በመጨረሻው ላይ ግን የእኛ ቡድን ታሪኩን በመስበር ወደሚመጥነው ሊግ ዳግም ሊቀላቀል በመቻሉ በግሌ በጣም ደስተኛ ነኝ።
ሊግ፦ በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ ለሀገሪቱ ትላልቅ ቡድኖች እና ለብሄራዊ ቡድናችን ተጫውተህ አሳልፈሃል፤ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ከ31 ዓመታት በኋላ ባለፈው የብሄራዊ ቡድናችን ውስጥም ቁልፍ ከነበሩት ተጨዋቾች መካከል አንዱ እንደነበርክም ይታወሳልና ብዙዎች አንተን በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ደረጃ ሲጠብቁ አንተ ግን ከሜዳ ጠፍተህ ነበር፤በኋላ ላይ ደግሞ ከቆይታ በኋላ ወደታችኛው ሊግ በመውረድ ነው ለኢትዮ-ኤሌክትሪክ ለመጫወት የቻልከው ይሄ እንዴት ነው ሊሆን የቻለው? በእታችኛው ሊግ ስትጫወትስ ይሄ ለእኔ አይመጥነኝም የሚል ስሜትስ ሊሰማህ ችሏል?
ምንያህል፦ ባሳለፍኩት የእግር ኳስ ህይወት ከላይ እንደገለፅከው ለትላልቅ ቡድኖችና ለብሄራዊ ቡድናችን ተጫውቼ አሳልፌያለሁ። ወደ ድሬዳዋ ከተማ ክለብ ካመራው በኋላ ግን ደርሶብኝ የነበረው የእግር ጉዳት እኔን ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ለሚደርስ ጊዜ ከሜዳ አርቆኝ ስለነበር ከሜዳ መጥፋቴ የእውነት ነበር። በላይኛው ሊግ ላይ ብቻ ሳይሆን በታችኛው ሊግ ላይም የባለፈውን ዓመት ጭምር ለኢትዮ-ኤሌክትሪክ እንድጫወት በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና አማካኝነት ተፈልጌም በቀጣዩ ጊዜ የኳስ ህይወቴ በደንብ ለመጫወት እንድችል ከጉዳቴ ማገገም አለብኝ በሚል ውሳኔዬ እና ሀገሪቱ ላይ ተፈጥረው ከነበሩት የፖለቲካው አለመረጋጋትና ከኮቪድ ወረርሽኙም ጋር በተያያዘ ትርምሶች ስለነበሩ ትንሽ ራሴን ላረጋጋው ከሚል ውሳኔዬ ላይ በመድረሴም ነው ከሜዳ ማረፍን በመፈለጌ ልጠፋ የቻልኩት። ከቆይታ በኋላ ግን በፕሪምየር ሊግ ደረጃ መጫወትን እየቻልኩ ወደታችኛው ሊግ ወርጄ ለኢትዮ-ኤሌክትሪክ ልጫወት የቻልኩት እግር ኳስን ስራዬና እንጀራዬ ነው ብለህ ካሰብክ በየትኛውም ሊግ ላይ መጫወት ግዴታህ ነውና እኔም አዲሱ ክለቤን ከቡድን አጋር ጓደኞቼ ጋር የሆነ ቦታ ማድረስ አለብኝ ከሚል ውሳኔ ላይ በመድረሴ ነው ራሴን አሳምኜው ለቡድኑ በመፈረም የተጫወትኩትና ክለቡንም ለስኬት እንዲበቃም የራሴን አስተዋጽኦ ያበረከትኩት።
ወደታችኛው ሊግ ላይ ሄጄ መጫወቴን በተመለከተ ለእኔ ብዙም አልከበደኝም። በሰራከው ልክ ደግሞ የምታገኘው ነገር ይኖራልና ያም ነበር እኔን ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማሳለፉ ላይ ድርሻው ስለነበረኝ ያ ስኬት የገጠመኝ።
ሊግ፦ ወደ ታችኛው ሊግ ወርዶ ከመጫወቱ ጋር በተያያዘ ከላይ ውድድሩ ለእኔ አይመጥነኝም የሚል ስሜት ሊሰማህ ችሏል? የሚል ጥያቄን አቅርቤልህ ነበር። አንዳንዶችም ያን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ምንያህል አዎ ከእዚህ በፊት ወርዶ መጫወቱን አይመጥነኝም ብሏል የሚሉህም አሉና ከእዛ በመነሳት የምትተነፍሰው ነገር ካለ?
ምንያህል፦ በመጀመሪያ ደረጃ እኔ ሲጀመር እንደዛ የምል አይነት ተጨዋች አይደለሁም። እንደዛ አይነት ቃላቶችን ከአንደበቴ ባወጣም ኖሮ በዘንድሮ ከፍተኛው ሊግ ላይ አልጫወትምም ነበር። ከአፌ እንደዛ አይነት ቃል ሊወጣኝም አይችልም። ለምንድን ነው እኔ መጫወት ከፈለግኩና ካመንኩበት ምንም ነገር ሊያግደኝ አይችልም ለየቱም ክለብ በታችኛው ሊግ ደረጃ መጫወት እችላለሁ ብዬም ነው ወርጄ ልጫወት የቻልኩት።
ሊግ፦ ለኢትዮ-ኤሌክትሪክ በአብዛኛዎቹ ጨዋታዎች ዘንድሮ ለመጫወት ችለሃል፤ ያመለጡህ ግጥሚያዎች የትኞቹ ናቸው?
ምንያህል፦ በመጀመሪያው ዙር ላይ በጉዳት ሶስት ግጥሚያዎችን ብቻ ነው ያልተጫወትኩት። በሌላዎቹ ላይ መሳተፍ ችያለሁ።
ሊግ፦ አንተን ጨምሮ በኳሱ የእውቅና ስም ያላቸው እንደ እነ ሳሙኤል ታዬና ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ ኢትዮ-ኤሌክትሪክን ለመቀላቀል መቻል ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያልፍ በደንብ አግዞታል?
ምንያህል፦ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች በአንድ ቡድን ውስጥ መኖር መቻላቸው ውጤትን ከማምጣት አኳያ የቡድን መንፈስን /ቲም ስፕሪትን/ በደንብ አድርጎ ያሳድግልሃል። ከላይ እንደገለፅከው በእኛ ክለብ ውስጥ ስማቸውን የጠቀስካቸው ስም ያላቸውና ሌሎች ተጨዋቾች ነበሩ ከእነዛ መካከልም በብሄራዊ ቡድን ደረጃ አብሬ ከተጫወትኳቸው ተጨዋቾች ውስጥም ግብ ጠባቂው ዘሪሁንም የሚጠቀስ ተጨዋችም ነበርና እሱን ጨምሮ በትላልቅ ቡድኖች ደረጃ የተጫወትነው ልጆች በእዚህ ቡድን ውስጥ ለመገኘት መቻላችን የቡድኑን እና የየራሳችንንም ክፍተቶች እንድናውቅም ስላደረገን የእኛ በቡድኑ ውስጥ መገኘት ክለቡን በጣም ነው ተጠቃሚ ያደረገው።
ሊግ፦ ወደ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ክለብ ከማምራትህ በፊት ባለፉት ጊዜያቶች ከሜዳ መጥፋትህን ተከትሎ በሻላ የጤና ቡድን ውስጥ ስትለማመድ ነበር? ከእዛም የጤና ቡድን ቆይታህ በኋላም ነው ወደ ኢትዮ- ኤሌክትሪክ ቡድን ያመራከው እና አንዳንዶች ኤልፓ ብሎ ብሎ ከጤና ቡድን ተጨዋች ማስፈረም ጀመረ በሚል የስሞታ ነገርም ቀርቦበት ነበርና በእዚህ ጉዳይ ላይ የምትለው ነገር ካለ?
ምንያህል፦ ይሄን ጉዳይ በሚመለከት እኔ ሁኔታውን የማየው አንዳንድ ሰዎች እንደሚያወሩት አይደለም። የሻላ የጤና ቡድን ውስጥ እኔ ስለማመድ የነበረው ከምስረታው ጊዜ ጀምሮ የጤና ቡድኑ የክብር አምባሳደር ስለሆንኩና ቡድኑም በአካባቢዬ የሚገኝ ስለነበር ከእዛም ውጪ በጉዳት ላይ በነበርኩበት ሰዓት ይሄ የጤና ቡድን ከጉዳቴ ተመልሼ ዳግም ወደ መደበኛው የእግር ኳስ ጨዋታም እንድመለስ እና ራሴንም በደንብ አድርጌ እንድጠብቅ ያደረገኝ እና በርትቼ ሰርቼም ዳግም ወደ ኳሱ እንድመለስ ትልቁን አስተዋጽኦም ያደረገ ቡድኔም ነውና በእዚሁ አጋጣሚ እነሱን በጣም አድርጌ አመሰግናችኋለሁ። አከብራቸዋለሁም። በጤና ቡድን ደረጃ ብዙ ተጨዋቾች ኳስን በክለብ ደረጃ ለተወሰነ ጊዜ ሲያቆሙና በእዛ የጤና ቡድን ደረጃም ሲጫወቱ ብዙ ነገሮች እንደሚባሉ አውቃለሁ። ያም ሆኖ ግን በእዛ ደረጃ መለማመድና መጫወት መቻል ራስህን ወደ ዋናው መደበኛ ክለባት ውስጥ ገብተህ እንድትጫወት ራስህን በአካልም ሆነ በአህምሮ ረገድም ዝግጁ /አክቲቭ/ እንድትሆን ስለሚያደርግህ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነውና እኔም ከእነሱ ጋር ልምምዴን በመስራቴ በጣም ነው ተጠቃሚ ያደረገኝና የእኔ በእዛ ደረጃ ለመለማመድ መቻል እንዳላርፍ አድርጎኝም ነበርና ለሌሎች ተጨዋቾችም ማስተማሪያቸውም ነው የሆንኩት። ይሄን የጤና ቡድን በሚመለከትም እንደ መደበኛ የጤና ቡድን ብቻ የምትመለከተው አይደለም። አንዳንድ የጤና ቡድኖች እድሜያቸው የገፋ ተጨዋቾችን በማካተት ስፖርትን እንዲሰሩ ያደርጋሉ። በእኛ የጤና ቡድን ውስጥ ደግሞ እኔን ጨምሮ እንደ እነ ታፈሰ ተስፋዬ፣ አሉላ ግርማ፣ በሀይሉ አሰፋ /ቱሳ/፣ ተስፋዬ አለባቸው /ቆቦ/ እና መንግስቱን /ማሲንቆ/ የመሳሰሉ በትላልቅ ቡድኖች ደረጃ የተጫወቱና እየተጫወቱ ያሉም ተጨዋቾች የሚገኙበትም ነውና በእዛ ደረጃ ውስጥ ሆነን መለማመዳችንና መጫወታችን ጠንክረን ለክለብ የውድድር ደረጃ እንድንቀርብም አድርጎናል።
ሊግ፦ ምንያህል ተሾመ በኢትዮጵያ ቡና ሳለህ ከአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጋር በተጨዋችነት ዘመኑ ተገናኝቷል፤ አሁን ደግሞ በኢትዮ- ኤሌክትሪክ ክለብ ውስጥ ዳግም ሊገናኙ ችለዋል። የመገናኘት ግጥምጥሞሹን እንዴት ተመለከትከው? ስለ አሰልጣኙስ ምን ትላለህ?
ምንያህል፦ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና በኢትዮጵያ ቡና እያለሁ ከስር ቡድኑ ወደ ላይ ያሳደገኝ ጥሩ የእግር ኳስ ባለሙያ ነው። ከቡና ከወጣ በኋላ በየትኛውም ቡድን ደረጃ ባንገናኝም በኖርማል ህይወት ደረጃ ግን አልፎ አልፎ እንገናኝ ነበር እና በአሰግድ ተስፋዬ የመታሰቢያ ውድድር ላይ ነው እኔ ለሻላ የጤና ቡድን ስጫወት ተመልክተውኝ ከነበሩት የስፖርቱ ሰዎች መካከል አንዱ ነበርና እዛ ላይ ተመልክቶኝ ነው እኔን ወደ ቡድኑ በማምጣት ሊጠቀምብኝ የቻለው። በኤልፓ ቆይታዬ እኔ ሳላሳፍረው ነው በቡድኑ ውስጥ ልቆይ የቻልኩት። እሱን ብቻ ሳይሆን የክለቡን የኮቺንግ ስታፍንና አመራሮችንም ጭምር በማሳመንም ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲገባም አድርገነዋልና በእዚህ አጋጣሚ ክፍሌንም ሌሎቹንም ለማመስገን እወዳለሁኝ።
ሊግ፦ ወደ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዘንድሮ እንድትሸጋገሩ ያስቻላችሁ ጠንካራው ጎናችሁ የትኛው ነበር፤ የክፍተት ጎናችሁስ?
ምንያህል፦ ያን ስኬት እንድናስመዘግብ ጠንካራው ጎናችን የነበረው ውድድሩ ሀይል የተቀላቀለበት ጨዋታ ይበዛበት ስለነበር እና የአሰልጣኛችን የኳስ ፍልስፍና ደግሞ ቡድኑ ኳስ ይዞና መስርቶ የሚጫወት ቡድን በመሆኑ ያን እንቅስቃሴ በመከተላችን ነው አብዛኛዎቹን ጨዋታዎች አሳማኝ በሆነ መልኩ በማሸነፍ ተጠቃሚ እንድንሆን ያደረገን። በክፍተት ጎን የተመለከትኩት ነገር ደግሞ በውድድር ዘመኑ ቆይታችን የመጀመሪያው ዙር ላይ ቀሎን ስለተጫወትን በሁለተኛው ዙር ላይም ይሄን ጠብቀን ነበር። ያም ሆኖ ግን ብዙ ጎናችን ጠንካራ የነበረ ቢሆንሞ በአንዳንድ ተጨዋቾችን ላይ የነበሩት ድክመቶች ይኸውም የልምድ ማነስና የመቻኮል ሁኔታዎች ግን ወደ ዋንጫው ግስጋሴ በምንሄድበት ጊዜ አጋጥሞን ነበርና ያን ብቻ ነው በክፍተት ደረጃ የተመለከትኩት።
ሊግ፦ ለኢትዮ-ኤሌክትሪክ ዘንድሮ ፈታኙ ጨዋታ የቱ ነበር?
ምንያህል፦ ሁለት ፈታኝ ግጥሚያዎች ናቸው የገጠሙን፤ የመጀመሪያው ከተከታያችን አርሲ ነገሌ ጋር ባደረግነው ጨዋታ 1-0 ከመመራት አንሰራርተን 2-1 ያሸነፍንበት ጨዋታ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በወራጅነት ቀጠና ላይ ከሚገኙ ቡድኖች ጋር ስትጫወት እነሱን አቅልሎ የመግባት ነገር አለና መውረዱን ካረጋገጠው አምቦ ከተማ ጋር ስንጫወት አቻ የተለያየንበትን ነው። በእዛ ጨዋታ ለእኛ ግጥሚያው ፈታኝ የሆነብንም እነሱ በመከላከል ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴን ሊከተሉ ስለቻሉም ነው ሊያስቸግሩን የቻሉት።
ሊግ፦ ከላይ ባለፉት ጊዜያቶች ከሜዳ ለመራቅህ ጉዳትን በምክንያትነት ጠቅሰህ ነበር፤ የሰውነትህ መጨመርስ ሌላው ምክንያት ሊሆን ይችላል?
ምንያህል፦ አዎን፤ በእግር ኳሱ ከሜዳ በጉዳት ስትርቅ መጀመሪያ ላይ ራስህን ለማስተካከልና ጤናህንም ለመመለስ ስለምትፈልግ እረፍት ስለምታደርግና ከስፖርቱም ስለምትርቅ የሰውነት መጨመር ያጋጥምሃል፤ እኔንም ያ ሁኔታ ስፖርት ከመስራት አርቆኝ ስለነበር እና የተወሰነም ኪሎ ስለጨመርኩ ከሜዳ አጥፍቶኝ ነበር። በኋላ ላይ ግን የዝግጅት ጊዜዬን በደንብ አድርጌ በአግባቡ ለመስራት ስለቻልኩና ከጨዋታ ወደ ጨዋታም በአካል ብቃቱ በኩል እየተሻሻልኩኝ ለመምጣት ስለቻልኩ ወደ በፊቱ አቋሜ ልመለስ ችያለሁ።
ሊግ፦ የእግር ኳስ ጨዋታን ጠግበኸው ተጫውተሃል?
ምንያህል፦ እግር ኳስን አትጠግባትም፤ እኔም ተጫውቼ አልጠገብኳትም። ያም ሆኖ ግን በየቀኑ በሜዳ ላይ የምታሳያቸው አዳዲስ ነገሮች ከመለያየታቸው በተጨማሪ ስኬቶችም ከልጅነቴ እድሜም አንፃር ስለመጡ አንዳንድ ሰዎች ኳሱን ጠግቤ የተጫወትኩና የጨረስኩ ይመስላቸዋል። ለእኔ ግን ስኬቶቹ ናቸው እንጂ ቀድመው የመጡት እግር ኳሱን ገና ተጫውቼ አልጠገብኳትም። በእኔ አስተሳሰብም እግር ኳስ አትጠገብም ብዬም አስባለሁ።
ሊግ፦ የምንያህል ተሾመ ምርጡን ስምና ዝና ዳግም የምንመለከት ይመስልሃል?
ምንያህል፦ አዎን፤ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር አሁን ያለኝ የተጨዋችነት ቆይታና ግንኙነት በጣም ጥሩ ነው። ከዛ በመነሳትም በመጪው የውድድር ዘመን ላይ በሚኖረኝ የቡድኑ ቆይታም ከእግዚአብሔር እርዳታ ጋር የቀድሞውን ምንያህል ተሾመን እናየዋለን።
ሊግ፦ እናጠቃል…….?
ምንያህል፦ በጉዳት ከእግር ኳሱ ርቄና ስራ አጥቼ በነበረበት ሰዓት ቤተሰቦቼ፣ ባለቤቴ፣ ጓደኞቼ፣ በአካባቢዬ የሚገኙ ወዳጆቼ እና የሻላም የጤና ቡድን አባላቶች ለእኔ የቴክስት መልህክት በመላክ ጭምር አይዞን እያሉ ያበረታቱኝ ነበርና በእዚህ አጋጣሚ ለእነሱ ያለኝን አክብሮትና ምስጋናን መግለፅ እፈልጋለሁኝ።