Google search engine

“ምን ያህል ሳኒታይዘር ተጠቅመካል ነው ያልከኝ፤ መጠቀም ግድ ስለሆነ እጄ ራሱ ሳኒታይዘር ሆኗል”ታደለ መንገሻ /ሰበታ ከተማ/

“ምን ያህል ሳኒታይዘር  ተጠቅመካል ነው ያልከኝ፤  መጠቀም ግድ ስለሆነ  እጄ ራሱ  ሳኒታይዘር ሆኗል”

“ጥሬ ስጋ ተከልክሎ ብዙ ሰው ነው የሚጠቀመው፤ ሰዉ መብላትም አላቆመም፤ ይሄ ጊዜ ሲያልፍ እኮ አይደለም ጥሬውን በሬውንም መብላት ይችላሉ”

በመሸሻ_ወልዴ
 
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና  በሰበታ ከተማ ክለብ ውስጥ በአማካይ ስፍራ ላይ በአሁን ሰዓት የሚጫወተው  ታደለ መንገሻ በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑ ባለው ችሎታ ብዙዎች የሚያደንቁት ሲሆን በሜዳ ላይ የሚያሳየው የአጨዋወት ስታይልም ከፍተኛ አድናቆትን ተጫውቶ ባሳለፈባቸው ዓመታቶች ላይ አሰጥቶታል፤ ይሄን ተጨዋች የሊግ ስፖርት ጋዜጣ   ኮሮና ቫይረስ  ለዓለም ከፍተኛ ስጋት ሆኖና ወደ ሀገራችንም  ገብቶ  የእግር ኳሱን  እስከማቋረጥ ስላደረሰበት ደረጃ፣  ውድድሩ ከተቋረጠ በኋላ እና አሁን ደግሞ ጭራሽ እንዲሰረዝ ስለተደረገበት ሁኔታ እንደዚሁም  ደግሞ እሱ በእዚህ ጊዜ ውስጥ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝና ሌሎችን ተያያዥ የሆኑ ጥያቄዎችን ስልክ ቁጥሩ ላይ በመደወል አነጋግረነዋል፤ ታደለም ላቀረብንለት ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽን ሰጥቶናል፤ ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- በኮሮናው ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የዓለም እግር ኳስ ጨዋታዎች ተቋርጠዋል፤ ከእነዛም መካከል የኢትዮጵያ  ፕሪምየር ሊግ አንዱ ነው፤ እሱም ሰሞኑን በተላለፈው ውሳኔና መመሪያ መሰረትም እስከ መሠረዝ ደርሷል፤ በእዚህ ዙሪያ የምትለው ነገር ካለ?
ታደለ፡- የኮሮና ቫይረስ /ኮቪድ 19/ ወረርሽኝ  በአሁን ሰአት በአለም ላይ  በሚገኙ በርካታ ሀገራቶች  ብዙ ሰዎችን በሞት እየነጠቀንና  ለከፍተኛም  ህመም እየዳረገ ያለ በመሆኑ የበሽታው ከባድነቱና አስከፊነቱ  በግልፅ የሚታይ ነገር ነው፡፡ በእዚህም ሳቢያ  ወረርሽኙ ዓለም አቀፋዊ ስለሆነም እግር ኳስን ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገሮችንም ሊያስቆምም  ችሏል፤  የቫይረሱ መስፋፋትም  ሰዎችን እቤታቸው እስከማስቀመጥ ደረጃና  ት/ቤቶችን እስከማስቆምም ደረጃ ደርሷል፤ አሁን ላይ  ጊዜው ሁሉም ነገር ከባድ  ስለሆነም  እግር ኳሱ እንደ ሁሉም ነገር ነው መታየት ያለበት፤  ስለዚህም ይህን  ወቅት ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ለማለፍ   ሁሉም  አካል ተባብሮና  አንድ ሆኖም ሊሰራ ይገባል፤ ያኔም ወደ ምንወደው እና በጣም ወደምናፍቅረው እግር ኳሳችን  ተመልሰን መምጣታችን የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡
ሊግ፡-  ኮቪድ 19 ወደ አገራችን ከገባ ወደ  2 ወራትን  አስቆጥሯል፤ ያን ለመጀመሪያ ጊዜ ስትሰማ  ምን አይነት ስሜት ነው የተፈጠረብህ? ወረርሽኙን አስመልክቶስ አሁን ከምትመለከተው ነገር በመነሳት ምንስ ነው የምትለው?
ታደለ፡- የኮሮናው  ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አገራችን ገባ ሲባል እኔም እንደሌላው ማህበረሰብ ሁሉ  በጣም ነው ቅር ያለኝ፤ ከበድ ያለ  እና ጥሩ ያልሆነም ስሜት ነው የተሰማኝ፤ የእዚህን ወረርሽኝ መግባትን አስመልክቶም ወዲያውኑም  በአሁን ሰዓት ታላላቅ ሃገራቶች   ያልቻሉትን  ነገር እኛ እንዴትስ  እንቋቋማዋለን ብዬም  ምንም አይነት ተስፋንም  አላደረግኩም ነበር፤ ሆኖም ግን ቫይረሱ ገባ ከተባለ በኋላ  በፈጣሪ እርዳታ በተወሰነ ደረጃ ከፍተኛ እና  ብዙ ስጋቶች እንዳይፈጠሩብን የተደረጉ ነገሮች ቢኖሩም አሁንም ግን በጥንቃቄዎቻችን ዙሪያ ከምመለከታቸው ነገሮች በመነሳት  በጣም መሻሻሎችን ማሳየት አለብን፤  በመመሪያ ደረጃም የሚባለውን  ነገር መስማት አለብን፤  የእውነት ለመናገር ጥንቃቄውን  አሁን ላይ እያደረግነው አይደለም፤  አንተ ጋር  የሆነ ሰው ካልጎደለ ወይንም ደግሞ ካልሞተ በስተቀር  ጥንቃቄው  ላይ በጣም ጥሩ አይደለንም፤ ስለዚህም  በእዚህ አጋጣሚ አንዳችን ለአንዳችን በማሰብና በመጨነቅ   ልንጠነቀቅ ነው የሚገባን፡፡
ሊግ፡- በኮሮናው  ቫይረስ የእግር ኳስ ውድድሮች  ተቋርጠዋል፤ አሁን ደግሞ ጭራሽ ቆመዋል፤ ብሎም ደግሞ ውድድሮች ተሰርዘዋል፤   ከኳስ መራቁ ምን አይነት ስሜትን ይፈጥራል?
ታደለ፡-  እንደእኛ ሙያችን ለሆኑ ሰዎች ከእግር ኳስ መራቅ በጣም  ከባድ ነገር ነው፤ ያሳምምካልም፤  ያውም ለእንደዚህን  ያህል ቀናቶች፤ አይደለም በሙያው ላይ ላለነው ሰዎች  ከኳሱ ሙያ  ውጪ ላሉት ሰዎች ራሱ የውጪ ሀገራትንና የእኛንም ሀገራት ኳስ የሚመለከቱበት ሁኔታም ስላለ እነሱም ጭምር ናቸው በጣም  የሚጨነቁት፤  እኛን ስታስብ ደግሞ ከእነሱ  በላይ ኦቨር በሆነ ሁኔታም  ነው ስሜታችን የሚጎዳው፤ ምክንያቱም ኳስ ለእኛ ህይወታችን ነውና፤   በተለይ የለመድነውንና ህይወታችን የሆነውንም  ነገር ማጣት በጣም ይከብዳልና ፈጣሪ ጥሩ ጊዜን እንዲያመጣልን በየእምነታችን  ልንፀልይ ነው የሚገባን፡፡
ሊግ፡-  በኮሮናው ቫይረስ  አሁን ላይ  በቤት ውስጥ ትውላለክና በምን በምን ሁኔታዎችን ነው ጊዜህን የምታሳልፈው?
ታደለ፡-  እንደ እግር ኳስ ተጨዋችነቴ  በአሁን ሰዓት ጊዜዬን የማሳልፈው በሰውነቴ ላይ ውፍረት  እንዳያጋጥመኝ የተለያዩ ስፖርቶችን በቤት ውስጥ  በመስራት  እና ብሎም ደግሞ  እንደ አዲስ የቀድሞ ጊዜ ያለፉ የዓለም ዋንጫና  የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎችን በማየት ነው፤ ይሄን የማደርገው ከኳስ መራቅና መለየት በጣም ከባድም ስለሆነ  ከናፍቆትም አንፃር  ነው፤ ሌላ ጊዜ እኮ ኳስ ውስጥ ስትሆን እንዲህ ያሉ  የሚተላለፉ ጨዋታዎችን አታይም፤ ለኳሱ ካለህ ፍቅር  ነው ጨዋታዎችን በድጋሚ የምትመለከተውና  ደስ ብሎኝ ቁጭ ብዬ ነው የማየው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ በጣም የምታደንቀው ማንን ነበር?
ታደለ፡- ሁሌም  ሮናልዲንሆ ጎቾን ነው የማደንቀው፤ በተለይ ከሪያል ማድሪድ ጋር  በኤልክላሲኮ ሲጫወቱ ያሳየው እንቅስቃሴ ስሜቴን በጣም  ይገዛዋልና ያንን ደጋግሜ ሳየው ሁሌም  ነው ደስ የሚለኝ፡፡
ሊግ፡- የዓለም ዋንጫ የድሮ ጨዋታዎችን  ባየህበት አጋጣሚ  የቱን ጨዋታ አደነቅክ?
ታደለ፡- ብራዚል ከፈረንሳይ የተጫወተችውንና ዚዳን ሁለት ግቦች ያገባበትን ግጥሚያ  በጣም ወድጄዋለው፤ የማልረሳውም ጨዋታ ነው፡፡
ሊግ፡- ኮሮና ቫይረስ ከመግባቱ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘኸው ሠው ማንን ነበር?
ታደለ፡-  ኮሮና ቫይረስ ወደ አገራችን ገባ የተባለ ጊዜ  ክለባችን ሰበታ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ  ጋር ጨዋታ ነበረው፤ ያን ጨዋታ ተጫውተን ካበቃን በኋላም በነጋታው  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጥሪን እንድንቀላቀል ከተነገረን በኋላ ወደዛ ልናመራ ስንል በበሽታው ምክንያት ጥሪው ተራዝሟል ተብሎ ሲነገር ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘሁት ሰው የቡድናችንን ተጨዋች አንተነህ ተስፋዬን ነው፤ እሱም የክልሌ አርባምንጭ ልጅም በመሆኑ  አብረንም ነው በቀጥታ ወደ ትውልድ ክልላችን ልንጓዝ የቻልነው እዛም እንገናኛለን፡፡
ሊግ፡-  አሁን ላይ እንደ እግር ኳስ ተጨዋችነትህ የተለያዩ ልምምዶችን ከመስራት  ውጪ ሌላስ   የምታደርጋቸው ነገሮች አሉ?
ታደለ፡- አዎን፤  የአማርኛን ጨምሮ አንድ አንድ ፊልሞችን እመለከታለሁ፤ ከዛ ውጪም  በሞባይሌ ላይ ያሉ  የስፖርት እንቅስቃሴዎችንም ፊልም እንደ ስፖርተኝነቴ የሚጠቅመኝ ነገር አለና ደጋግሜ እመለከታለሁ፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ጨዋታ ከፍተኛ  የደስታ ስሜትን እንደሚሰጥ ይታወቃል፤  አሁን ያ ቀርቶብህ እቤት ውስጥ  ቁጭ ብለህ የሜዳ ላይ ሁኔታውን  መለስ ብለህ ስታስብ  አይከብድም? ምን ምን ነገሮችስ ናቸው ትዝ የሚሉህ?
ታደለ፡-  በቤት ውስጥ  መዋል አሁን የግድ ስለሆነ እንጂ  በጣም ነው የሚከበደው፤  ይጨንቃልም፤  ምክንያቱም መዋሉን እንደ እኛ ላሉ ስፖርተኞች  ያላስለመድነው ነገርም ስለሆነ ነው፤ እኛ እንደውም በእዚህ በኩል ከሌላው ማህበረሰብ ወጣ ብለን ስፖርትን የምንሰራበት አጋጣሚም ስላለ የተሻልን ሆንን እንጂ  ቤት መዋሉ ከባድ ነው፤ ለዛም ነው ቁጭ ማለቱን ስለማንወደው    እንቅስቃሴ አድርገን ጭንቅላታችንን ፍሪ  በማድረግ ወደ ቤታችን  የምንገባው፡፡ያን ካልኩ ትዝ ስለሚሉኝ ነገሮች ደግሞ  ኳስ ህይወቴ ነው፤ የእውነቴንም ነው የምልህ  አሁን ላይ ቤት ስውል ብዙ ነገርን ነው ወደ ኋላ ተመልሼም ስለማስታውስ  ያን ስሜት ማጣት ከባድ ስለሆነ በአህምሮዬ ነው ነገሮችን እንዲህ አድርጌ  ይሄን ተጨዋች ባልፈው  ከእዚህ ቡድን ጋር ብንጫወት ምን ማድረግ አለብኝ  እያልኩ ሌት ከእሌት የማስበውና እነዚህን ትዝታዎች በአህምሮዬ ደጋግሜ አመላልሳቸዋለው፡፡

ሊግ፡- ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ እስካሁን  ስንት ሳኒታይዘር ጨረስክ?
ታደለ፡-  /ሳቅ ካለ በኋላ/ ሳኒታይዘር ነው ያልከው፤ እጄ ራሱ  ሳኒታይዘር ሳይሆን ይቀራል ብለህ ነው፤ ሆኗልም በለው፤  በቃ እጄ ተቀይሯል ሌላም ሆኗል፤ ያን መጠቀምም ግድ ነው፤ የእውነት ለመናገር ሳኒታይዘር  ምን እንደሆነ አላውቅም ነበር፤ አሁን  በሽታው ሲመጣም  ነው ያወቅኩት፤ ሳኒታይዘርን አሁን ለምጄዋለው ስወጣም ስገባም በስርዓቱም   እቀባዋለው፤ ተቀብተህ ስለማትችለውም እየተቀባህ ፈጣሪንም ትለምነዋለህ፡፡
ሊግ፡- በቀን እጅህን ለስንት ጊዜያት ያህል ትታጠባለህ?
ታደለ፡-  ቆጥሬው ባላውቅም በየሰአቱ ነው ከቤት  ስወጣም ስገባም አንድአንድ ነገሮችን ስሰራና  ምግብ ለመብላትም በምንዘጋጅበት ሰዓት እጄን የምታጠበው፤ ከታጠብኩ በኋላም  እጄን እያደረቅኩ ሳኒታይዘርን እቀባለው፤ የወጣውን መመሪያም አከብራለው፡፡
ሊግ፡- ከቤተሰቦችህ ጋር   ያለህ የአዋዋል ሁኔታ አሁን ላይ ምን ይመስላል?
ታደለ፡- በአሁን ሰዓት በቤታችን ውስጥ የወንድሜ እና የእህቴ ልጆች አሉ፤ እናታችንም አለች፤  እኔ ደግሞ እንደ ስፖርተኝነቴ  ወደ ውጪ ለስራ የምወጣበት ሁኔታና ከሰዎች ጋርም  ልገናኝ የምችልበት ሁኔታ  ሊኖር ስለሚችል ቅድሚያ  ለእነሱ  ተጨንቄ ነው አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ አብሬያቸው የምውለው፤  ከዛ ውጪም  በጣም  ስለምጨነቅላቸው ወደ ውጪ አትውጡም እላቸዋለው፡፡
ሊግ፡- በተለይ ደቡቦች በጥሬ ስጋ አትታሙም፤  አሁን ላይ ግን ለኮሮናው ቫይረስ  ጥሬ ስጋ አትብሉ እየተባለ ጥንቃቄ እያደረጋችሁ አይደላችሁም?
ታደለ፡- የእውነት ልክ ብለሃል፤  እኔ  አሁን እንዳየሁት እንደውም   ብሉ  የተባሉም  ነው የሚመስለው፤ ጥሬ ስጋን  ብዙ ሰውም ነው የሚጠቀመው፤ መበላቱም አልቆመም፤  አንዳንዶች ስጋውን  በፌስ ቡክ ላይ ፖስት እስከማድረግ ደረጃም ደርሰዋል፡፡  ከዛ ውጪም እኛ ጋር  ምንም አይነት ችግር የለውምም ይሉሃል፤ ችግር ስላለው ስለሌላው ሳይሆን  በቃ የተባለውን ነገር ማድረግ ነው፤ ይሄ ጊዜ ሲያልፍ እኮ አይደለም ጥሬውን  በሬውንም መብላት ይችላሉ፤ በተለይ  በጣም የሚገርምህ አንተን የሚመክርህ ሰው ነው ሲባላም የምታየው፤ ታዲያ ማን ከማን ይማር የሚለውን ነገር ታስባለክና በዚህ በኩል ጥንቃቄ ቢደረግ ጥሩ ነው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን በተለያዩ  ክለቦች ውስጥ ተጫውተህ አሳልፈሃል፤ ምርጥ  ጥምረቶቼ የምትላቸው እነማን  ናቸው?
ታደለ፡- የደደቢት ክለብ ውስጥ ሻምፒዮና በሆንበት ሰዓት የነበረውን ነው ስጫወት ነው የእኔን ምርጥ ጥምረት ያየሁት፡፡ እኔ መሃል ላይ ሁኜም ጌታነህ ከበደ እና ዳዊት ፍቃዱ ከፊት በነበሩበት ሰአት ያ ይገርማል፡፡
ሊግ፡-  በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑ እንዳሰበው አልደረሰም ብለህ የሚቆጭህ ተጨዋች አለ?
ታደለ፡- አዎን፤ የአርባምንጭ ከተማ እግር ኳስ ቡድን ውስጥም  አብረን ተጫውተናል፡፡ ትልቅ አቅም ያለው ተጨዋችም ነው፤  ወንድሜነህ ዘሪሁን /ኦኪቲ/ በሁለት እግሩም ይጫወታልና ይሄን እንደወንድሜ  የማየው እና የእሱንም ብቃት የምመለከትለትንና የምወድለትን  ተጨዋች ከማንም በላይ ሆኖ ለማየት አለመቻሌ በጣም ይቆጨኛል፡፡
ሊግ፡- በኮሮናው ቫይረስ የኢትዮጵያን  እግር ኳስ ቀጣይ ጊዜ አስበህ ምን ማለት ትችላለህ?
ታደለ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ  ሳሳልፍ  አሁን የመጣው በሽታ በጣም ከባድ ነው፤ ይሄን ወረርሽኝ ሳስብም አሁን ላይ አንድ የሆነ ነገር በውስጤ ፈጥሮብኛል፡፡ ባለፉት ዘመናት ኳስን ስንጫወት   አስቀያሚና ደስ የማይል ነገሮችን  ስንመለከት ነው  የነበርነው፤ በብሄር እስከመጣላትና ሰው እስከመሆናችንም  ድረስ  ዘንግተን ነበር፡፡ በእዚህ ወቅት ግን  በሽታው ሲመጣ ሁላችንም  ስለ ብሄርተኝነት እያነሳን ከማውራትና  እና ስለሌላም ክፋቶች ከመናገር ተቆጥበንና እንደአንድ ሆነን አንዱአንዱን ሲረዳ አንዱአንዱን ሲያግዝ እና የሰዎችንም ማንነት የምንመለከትበት  ሁኔታ ነው  ያለውና ይሄ ነው መሆን ያለበት፤ ከእዚህም ብዙ ነገር ልንማር ይገባናል፡፡
ሊግ፡- በኮሮናው ቫይረስ የበጎ አድራጎት ተግባራት  ላይ ተሰማርተሃል?
ታደለ፡-  አዎን፤ ኮሮናው ከገባ በኋላ እዚህ አርባምንጭ ከሚገኘው ዞንና ከተማ አስተዳደር  ጋ የመጣልን ጥያቄ ነበር፤ ይህም እግር ኳስ ተጨዋቹ ትልቅ አቅም ስላለው እናንተ ስፖርተኞች እንደመሆናችሁ እዚህ ለሚገኙት ጎዳና ተዳዳሪዎች  መሰብሰብ  ስላለባቸው የሚቻላችሁን አንድአንድ ነገር አድርጉ የሚል ነበር፤ ከዛም  ባላንበት ስፍራ በእዚሁ ክልል ተወልደን ለተለያዩ ክለቦች የምንጫወትና እዛው ለአርባምንጭ የሚጫወቱ አስር የምንደርስ ተጨዋቾች ተነጋገርንና አንድ አይሲዙ ሙሉ ፉሩኖ ዱቄት፣ ፓስታ፣ ሩዝ፣ ዘይት፣ ሶፍት የመሳሰሉ ነገሮችን በመግዛት እንደየአቅማችን ነገም እኛን አይቶ እንዲረዳ   የሚጠበቅብንንም  አድርገናል፡፡
ሊግ፡- ከኮሮናው ቫይረስ በኋላ እንደ ስፖርተኝነትህ  የምግብ አጠቃቀምህ ተቀይሯል? ምን አይነት ስፖርትስ ነው የምትሰራው…
ታደለ፡-  አመጋገቤ የተለየ ሳይሆን  ኖርማል ነው፤ ያገኘሁትንም ነገር አልበላም፤ ስፖርትን በተመለከተ  የኪሎ መዛባት እንዳያጋጥመኝ  ልምምድን እንደ ክለብ  እንደምሰራው ባይሆንም ራሴ  ይበቃኛል እስከምል ድረስ በተወሰነ መልኩ  እሰራለውኝና  በእዚህ አጋጣሚ  በጥሩ ሁኔታ ነው ያለሁት፡፡
ሊግ፡- በአሁን ሰዓት በጣም የናፈቀህ  ነገር ምንድን ነው…
ታደለ፡-  እግር ኳስ ነው የናፈቀኝ፤ የእውነት ለመናገር ናፍቆቱ አስቸግሮኝ የመጀመሪያው ሰሞን አካባቢ የሰራነው ስራ ትክክል ባይሆንም  እኔና አበባው ቡታቆን ጨምሮ  ወጥተን መጫወት ስንጀምር ፖሊሶች ከለከሉን፤ ስንከለከል ሌላ ሰፈር ሄድን እዛም ልንጫወት ስንል  ተከለከልን፤ አሁንም ሌላ ሰፈር ሄደን ልንጫወት ስንል እናንተ ምን እየሰራችሁ ነው ትክክልም አይደላችሁም ሲሉን ምን እናድርግ ለእኛ ኳሱ ህይወታችን ነው አላስችልም ብሎንም  ነው ካልናቸው በኋላ ባለው ሁኔታ ለመግባባትም ስለቻልንና እኛም ወደራሳችን መመለስ ስላለብንም ሁሉንም ነገር ትተን በቤታችን የስፓርት ስራዎችን እያከናወንን ነው የምንገኘው፡፡   
ሊግ፡- በመጨረሻ….
ታደለ፡- ስለኮሮና  ቫይረስ ያልሠማ የለም፤ እንጠንቀቅ ሰዎችን እንርዳ፤ እንተጋገዝ፤  ወደ ኳስ የምንመጣበት ጊዜም ሩቅ አይደለም፡፡
https://t.me/Leaguesport

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P