በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/
ወጣት ነው፤ መስፍን ታፈሰ ይባላል፤ በክለብ ደረጃ እግር ኳስን ለሐዋሳ ከተማ በመጫወት ላይ ሲገኝ በክብደቱ ደግሞ 72 ኪ.ግራም ይመዝናል፤ በቁመቱም 1.80 ሜትር ይረዝማል፤ ይኸው ተጨዋቹ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተወዳዳሪ ለሆነው የሐዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንንም የተጨዋቾች ስብስብ ከቅርብ ጊዜያቶች ወዲህ በመቀላቀል ተስፋ ሰጭ የሆነን እንቅስቃሴም እያሳየ ይገኛል፤ የሐዋሳ ከተማ ቄራ ሰፈር ያፈራው ይኸው ተጨዋች ለክለቡም ሆነ ለሀገሩ የወጣትና የብሄራዊ ቡድን ተጨዋችነት ተመርጦ የመሰለፍ እድልን ባገኘበት ጨዋታዎችም ጎሎችን እስከማስቆጠር ደረጃ ላይ ደርሶ ብዙዎች ከወዲሁ አድናቆትን እየሰጡትም ይገኛል፡፡ ከእዚሁ የወደፊቱ የአገራችን ተስፋ ሰጪ የአጥቂ ስፍራ እግር ኳስ ተጨዋች ጋር ሊግ ስፖርት በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ቆይታን አድርጋ የነበረች ሲሆን ከእሱ ጋር ያደረግነውም ቃለ ምልልስ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፤ ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ጨዋታ ጅማሬህ ምን ይመስላል?
መስፍን፡- የእግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት ተወልጄ ባደግኩበት የሐዋሳ ከተማ ቄራ አካባቢ ነው፤ ያኔ በፕሮጀክት ደረጃም ነው ልጅ ሆኜ ኳሱን ስጫወት የነበረው፡፡
ሊግ፡- በቤተሰቦችህ ዘንድ ኳሱን ስትጫወት ተፅዕኖ አልነበረብህም?
መስፍን፡- በፍፁም፤ ቤተሰቦቼ እንደውም ልጅ ሆኜ ጀምሮ ነው ኳስን እንድጫወት ይፈልጉ የነበረው፤ ወላጅ አባቴም እናቴም ሁሌም ከጎኔ ነበሩና የእነሱም ድጋፍ ነው ዛሬ ላይ ለትልቅ ደረጃ እያበቃኝ የሚገኘው፡፡
ሊግ፡- ከቤተሰቦችህ ውስጥ ስፖርተኛው ወይንም ደግሞ የእግር ኳስ ተጨዋቹ አንተ ብቻ ነህ? ስንት ወንድምና እህትስ አለ?
መስፍን፡- አዎን፤ ስፖርተኛውም ኳስ ተጨዋቹም እኔ ብቻ ነኝ፤ 1 እህት ብቻም አለኝ፤ እሷም ገና ልጅ ናት፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን መጫወት ስትጀምር ማንን አድንቀህ ነው ያደግከው?
መስፍን፡- ከሀገር ውስጥ ጌታነህ ከበደን ሲሆን ከባህር ማዶ ደግሞ ሊዮኔል ሜሲና ክርስቲያኖ ሮናልዶን ነው፤ እነዚህን ተጨዋቾችም በጣም ስለምወዳቸው ተምሳሌቴ እና /ሞዴሌ/ም አድርጌ ነው እያደነቅኳቸው ያደግኩት፡፡
ሊግ፡- በፕሮጀክት ደረጃ የእግር ኳስን መጫወት ስትጀምር የትኞቹ አሰልጣኞች ናቸው አንተን ሊቀርፁህ የቻሉት?
መስፍን፡- የእግር ኳስ ተጨዋች ሆነህ ለጥሩ ደረጃ ስትበቃ መጀመሪያ ሁሌም አንተ ላይ መሰረቱን የጣሉልህን ባለሙያዎች ልትረሳ አይገባምና የታዳጊነት እድሜዬ ላይ ኳስን በፕሮጀክት ደረጃ መጫወት ስጀምር ለእኔ ትልቁን አስተዋፅኦ ያደረጉልኝ አሰልጣኞች አዲሴ ካሳ፣ ባርዬ፣ ሙሉጌታ ምህረትና ታምራት ሲሆኑ በአራቱም ፕሮጀክቶች የሰራዋቸው ጥሩ ስራዎች ነው ዛሬ ላይ ለእኔ ትልቁን መሰረት የጣሉልኝና ያ መሆን መቻሉ እስከብሄራዊ ቡድን ተጨዋችነት ደረጃ ሊያደርሰኝ ችሏል፡፡
ሊግ፡- ለሐዋሳ ከተማ የዋናው ቡድን ከማደግህ በፊት ለወጣት ክለቡ ተጫውተህ ነበር፤ ወደዛ እንዴትና በምን መልኩ አመራህ?
መስፍን፡- የሐዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብን በወጣት ቡድን ደረጃ ተቀላቅዬ ልጫወት የቻልኩት በጊዜው የተሰጠኝን የሙከራ እድል ለማለፍ በመቻሌ ነው፤ በጊዜው ግን ከሐዋሳ ከተማ ወጣት ቡድን በፊት መጀመሪያ ልጫወት የነበርኩት የሙከራ እድሉ ለተሰጠኝ የአዲስ አበባውና የሀሠላው የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ቡድን ነበርና ያኔ ለአሰላው የወጣቶች አካዳሚ ቡድን ተጫወት ስባል ያን ባለመፈለጌ ወደ ሐዋሳ ቡድን በምን መልኩ ነው ለመቀላቀል የቻልከው፤ የቡድኑ የእስካሁኑ በመምጣትና ሙከራን በማድረግ ነው የቡድኑ ተጨዋች ልሆን የቻልኩት፡፡
ሊግ፡-የሐዋሳ ከተማን የዋናው ቆይታህስ ምንድነው የሚመስለው?
መስፍን፡- የሐዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ ካለፈው ዓመት አጋማሽ አንስቶ የቡድኑ ተጨዋች ልሆን የቻልኩት በወጣት ቡድኑ ውስጥ በነበረኝ የሁለት አመታት ቆይታዬ እንደ ቡድንም እንደግልም ስጫወት ጥሩ አቋሜን ለማሳየት በመቻሌ ነው፤ በቡድኑ ውስጥ ስጫወት በግል የመጀመሪያ ዓመት ላይ 8 ግቦችን የሁለተኛው አመት ላይ ደግሞ 16 ግቦችን ማስቆጠር ችያለሁ፤ ለቡድኑ ደግሞ ከጓደኞቼ ጋር በጋራ በመሆን ለሁለት ተከታታይ ዓመታትም ዋንጫን ያነሳሁባቸው ጊዜያቶችም አሉና የእስካሁኑ የተጨዋችነት ቆይታዎቼ ገና ጀማሬ ላይ ያሉ ቢሆንም ለእኔ ጥሩና የሚያበረታታኝ ነው፤ ወደፊት ደግሞ ከአሁን የበለጠ መልካም የሆኑ ስራዎችን በመስራት ጥሩ ጊዜን እንደማሳልፍ ፈፅሞ አልጠራጠርም፡፡
ሊግ፡- ከሐዋሳ ከተማ የወጣት ቡድን ጋር ተደጋጋሚ ዋንጫን ለማንሳት ችለሃል፤ ይሄን ድል ከዋናው ቡድንስ ጋር የምታሳካው ይመስልሃል?
መስፍን፡- አንድ ቀን የማይቀር ነው፤ ይሄን የድል ዋንጫ ክለባችን ለሶስተኛ ጊዜ አንስቶ የቀድሞ የቡድኑን ስምና ዝናን የምንመልሰው ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- በሐዋሳ ከተማ ክለብ ውስጥ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች ሆነህ ልንመለከትህ ችለናል፤ በእዚህ ስፍራ ላይ ትጫወት የነበረው ከበፊት አንስቶ ነው?
መስፍን፡- አዎን፤ የእግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት አጥቂ ሆኜ ነው፤ አሁንም በእዚያ ስፍራ ላይ ነው ቦታ ሳልቀይር እየተጫወትኩ ያለሁት፤ ከአጥቂ ውጪ ተጫውቼም አላውቅም፡፡
ሊግ፡- የሐዋሳ ከተማ ክለብን እንዴት ትገልፀዋለህ?
መስፍን፡- ሐዋሳ ከተማ አሁን ላይ ጥሩ ቡድን ነው፤ ለታዳጊዎች እና ለወጣት ተጨዋቾች ከፍተኛ ትኩረትን የሚሰጥ እና ከሌሎቹ ክለቦችም በእዚህ በኩል ከፍተኛ እምነትንም በመጣል የሚለይ ቡድንም ነውና የእዚህ ክለብ አንዱ አባል ተጨዋች በመሆኔ የተለየ የደስታ ስሜት ነው የሚሰማኝ፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን እየተጫወትክ ባለህበት የአሁን ሰአት በጣም የተደሰትክበት እና ያዘንክበት አጋጣሚዎች የትኞቹ ናቸው?
መስፍን፡- በሐዋሳ ከተማ ክለብ ውስጥ ባለኝ የተጨዋችነት ቆይታዬ በጣም የተደሰትኩበት ጊዜ ከወጣት ቡድኑ ጋር ተደጋጋሚ ዋንጫን ስናነሳ ሲሆን የተከፋሁበት አጋጣሚ ደግሞ በእግሬ ላይ ጉዳት የደረሰብኝ ወቅት ነው፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ወጣትም ለዋናው ብሄራዊ ቡድንም ከመመረጥ አልፎ እየተጫወትክ ይገኛል፤ ያን ስሜት እንዴት አገኘኸው?
መስፍን፡- ለኢትዮጵያ ወጣትና የዋናው ብሄራዊ ቡድን የመመረጥ እድሉን ሳገኝ የእነዚህ ቡድኖች አባል እና ተጨዋች ለመሆን በመቻሌ የተሰማኝ የደስታ ስሜት በጣም ከፍ ያለ ነበር፤ ይህን ስልም ያለምክንያትም አይደለም፤ የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ሁሌም ቢሆን ሃገርህን እንድታገለግላት የሚፈጠርልህ እድል ነውና ያ የተለየ ስሜት በውስጥህ እንዲፈጠርብህም ያደርግሃል፤ ያኔ ደግሞ የመመረጥ እድሉን ባገኘሁባቸው የእነዚህ ቡድኖች ቆይታዬም ጎሎችን በጅቡቲ ብሄራዊ ቡድንና በሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን ላይም እስከማስቆጠር ደረጃ የደረስኩባቸውም አጋጣሚዎች ነበሩና ይሄ ለእኔ ለወደፊቱ ትልቅ ተጨዋች እንድሆንና የተሻለም ደረጃ ላይ እንድደርስ ከፍተኛም መነሳሻ ይሆነኛልና በእዚህ ሁኔታ ላይ መገኘቴ ደስ ብሎኛል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአጠቃላይ ውጤት በሩዋንዳ አቻው ተሸንፎ ለቻን የአፍሪካ ዋንጫ ሳያልፍ ቀርቷል..ስሜታችሁ እንዴት ነበር?
መስፍን፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሩዋንዳን በተፋለመበት የቻን አፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታው ጥሩ ሆኖ ቢቀርብም እድል ከእኛ ጋር ስላልነበር ብቻ ለካሜሮኑ ውድድር ሳያልፍ ቀርቷል፤ ሩዋንዳን ጥለን አለማለፋችንም በጣሙን እንድንቆጭና እንድናዝንም አድርጎናል፡፡
ሊግ፡- የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለወደፊቱ ተስፋ አለው ብለህ ታስባለህ?
መስፍን፡- አዎን፤ ቡድኑ በአዲሰ መልክ እየተገነባ ያለና ኳስንም ተቆጣጥሮ በመጫወቱ በኩል አዲስ የጨዋታ ታክቲክን ለመከተል ጥረት እያደረገ ያለ ስለሆነ ስብስባችን ለወደፊቱ ተስፋ እንደሚኖረው አምናለሁ፤ ለዛ ደግሞ አሁን የያዝነውን እንቅስቃሴ አጠናክረን መቀጠልም ግድ ይለናል፡፡
ሊግ፡- የሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድንን በገጠማችሁበት ሰአት እነሱ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምን መልኩ የተሻሉ ነበሩ? እኛስ?
መስፍን፡- ሩዋንዳዎች ከእኛ የተሻሉት በጉልበትና የቆሙ ኳሶችን በመጠቀም ነው፤ እኛ ደግሞ ኳስን ተቆጣጥረን በመጫወት በኩል ሙሉ ለሙሉ ተሽለን ነው የታየነው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ካለፈው አመት አንስቶ ባደረጋቸው የተለያዩ የማጣሪያ ጨዋታዎቹ ሽንፈቶችን በማስተናገድ ከውድድሮቹ ሁሉ ውጪ ሆኗል፤ ይሄ አሳዛኝ ነው?
መስፍን፡- በጣም እንጂ፤ በተለይ ደግሞ እኔ ስለነበርኩበት እና በቅርቡም ከሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን ጋር የመጫወት እድሉን ስላገኘሁበት ጨዋታ እኛ ዋልያዎቹ ወደካሜሩን የቻን የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እድሉና ተስፋው እያለን ያንን ስላላሳካንን ተቆጭተናል፤ የብሄራዊ ቡድናችን በዚህ ውድድር ያጠፋው የሜዳው ላይ ጨዋታን ሊጠቀም አለመቻሉ ነው፤ ሃገራችን ላይ ሁሉን ነገር መጨረስ ነበረብን፤ ያ ባለመሆኑ ውጤቱን ልናጣ ችለናል፤ ያም ሆኖ ግን ከሜዳችን ውጪ የነበረን ፍልሚያ ጥሩና አበረታች ስለነበር እንደዚያ አይነት እንቅስቃሴ ለወደፊቱም ቢሆን ሊጠቅመንና ውጤታማም ሊያደርገን ስለሚችል አንድ አንድ ሊያጠናክረን የሚችሉ ነገሮችን በመጨመር ልንጓዝበት ነው የሚገባን፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከመጪው ወር አንስቶ የተለያዩ የአፍሪካና የአለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ያደርጋል፤ በእነዚያ ፍልሚያዎች ውጤታማ እንድትሆኑ በምን መልኩ መቅረብ ይጠበቅባችኋል?
መስፍን፡- የመጀመሪያውና ዋናው ጉዳይ ብዬ የማስበው የብሄራዊ ቡድናችን የአሁኑ ሰአት ላይ የያዘውን እንቅስቃሴ እና ያለውን ጥሩ ነገር አጠናክሮ ማስቀጠል ይኖርበታል፤ ያን ማድረግ ከቻልን በየውድድሮቹ መድረክ ጥሩ ውጤት ማምጣት የምንችል ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሁን ላይ ያለውና የያዘው ነገር ምንድነው?
መስፍን፡- የብሄራዊ ቡድናችን አሁን ላይ ኳስ ይዞ የሚጫወት ቡድን ነው፤ ሌሎች ተጋጣሚዎቻችን ደግሞ ብዙ ጊዜ በእዚህ መልኩ አይታወቁም፤ ስለዚህ በእዚህ ውስጥ መገኘታችን ለእኛ ጥሩ ጎን አለውና ያለን ብቃት ላይ በተደጋጋሚ ጠንክረን በመስራት ውጤታማነትን ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡
ሊግ፡- ከእግር ኳሱ ውጪ የእረፍት ጊዜህን በምንድነው የምታሳልፈው?
መስፍን፡- የእረፍት ጊዜዬን ሁሌም የማሳልፈው በመተኛት ነው፡፡
ሊግ፡- ሙዚቃ ትወዳለህ?
መስፍን፡- አይ በእሱ አልታወቅም፤ መዝሙር በማድመጥ ግን እታወቃለሁ፤ ያኔም ጥሩ ስሜት ነው የሚሰማኝ፡፡
ሊግ፡- ከምግቦች የአንተ ቀዳሚ ምርጫ የቱ ነው?
መስፍን፡-የተለየ ምንም አይነት የምግብ ምርጫ የለኝም፤ ያገኘሁትን ሁሉ እመገባለሁ፡፡
ሊግ፡- የወደፊት ምኞትህ እና ግብህ ምንድነው?
መስፍን፡- የእግር ኳስን ስትጫወት የራስህ ግብና ዓላማ ይኖርሃል፤ የእኔም የወደፊት ምኞት በኳስ ተጨዋችነቱ እስከ ፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ ላይ መድረስ ነው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነት ጉዞ ላይ በአሁን ሰዓት ማሻሻል ያለብህ ነገር ምንድነው?
መስፍን፡- እንደ አጥቂ ስፍራ ተጨዋችነቴ በወጣትነት እድሜዬ በርካታ ግቦችን ማስቆጠር እፈልጋለሁ፤ ለእዛ ደግሞ በክፍተት ጎኖቼ ላይ ያሉብኝ ነገሮች ላይ ጠንክሬ ከመስራት ባሻገር ጎሎችን ማስቆጠሩም ላይ ራሴን ማሳመን ስላለብኝ እነዛን ነው የማሻሽለው፡፡
ሊግ፡- የሐዋሳ ከተማ ክለብ የፕሪ ሲዝን ልምምዱን ጀምሯል፤ ቡድናችሁን ዘንድሮ እንዴት እንጠብቀው?
መስፍን፡- ሐዋሳ ከተማ የፕሪ ሲዝን ዝግጅቱን በጣም በተጠናከረ መልኩ ከመስራቱ አኳያ የአሁን ሰዓት ላይ ያለበት ሁኔታ ጥሩ ነው፤ ይሄን ልምምድ ሰርተን ስንጨርስና የአቋም መለኪያ ጨዋታን ስናደርግ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ አቋማችንን በሚገባ የምናውቅበት ሁኔታ ስለሚኖር ያኔ ያለንበትን ሁኔታ በተግባር እናሳያለን፤ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፏችንን በተመለከተ ቡድናችን ከዚህ ቀደም የሁለት ጊዜ የሊጉ ሻምፒዮና ነበር፤ ዘንድሮ ደግሞ እንደፈጣሪ ፈቃድ ዋንጫን እናነሳለን ብለን ተስፋን ሰንቀናል፡፡
ሊግ፡- ከመስፍን ውጪ ሌላ የመጠሪያ ስም አለህ? ለምንስ ተባልክ?
መስፍን፡- አዎን፤ የሰፈሬ ሐዋሳ ከተማ ቄራ ልጆች ያወጡልኝና የሚጠሩኝ ጩኒ የሚል መጠሪያ ስም አለኝ፤ ስሙን ግን ለምን እንዳወጡልኝ አላውቅም፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ….?
መስፍን፡- የእግር ኳስን ስጫወት ከልጅነቴ አንስቶ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ አካላቶች አስተዋፅኦ አድርገውልኛል፡፡ በመጀመሪያ ቀዳሚውን ስፍራ የሚወስደው ፈጣሪዬ ነው፤ ከዛ ቀጥሎ ደግሞ ቤተሰቦቼ፤ ወደፊት እያልኩ ስጓዝም ከፕሮጀክት አንስቶ ያሰለጠነኝ ታምራት፣ ባርዬ፣ አዲሴ ካሳ፣ ሙሉጌታ ምህረት፣ ብርሃኑ ወርቁ /ፈየራ/፣ ዮሴፍ ተስፋዬ፣ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እና የሰፈሬ ቄራ አካባቢ ልጆችን ለማመስገን እፈልጋለሁ፡፡