በመሸሻ ወልዴ /ጂቦይስ/
የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሰበታ ከተማ በማገናኘት ነገ ይጠናቀቃል
የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለ14ኛ ጊዜ ያዘጋጀው የከተማው የዋንጫ ውድድር ነገበድምቀት ይጠናቀቃል፡፡
የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በገቢ ለማጠናከር እና ክለቦችም የራሳቸውን አቋም እንዲለኩበት ታስቦ የተካሄደው ይኸው ውድድር ነገ ሲጠናቀቅም ሰበታ ከተማን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ለፍፃሜ የሚያገናኝ ሲሆን ሁለቱ ቡድኖች ለፍፃሜ ደረሱትም ሰበታ ከተማ መከላከያን 3ለ1 ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናን 2ለ0 በማሸነፍ ነው፤ የደረጃው ጨዋታ ደግሞ ዛሬ ኢትዮጵያ ቡናን ከመከላከያ ጋር በ10 ሰዓት ያገናኛል፡፡
የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታን አስመልክተን ከሰበታ ከተማው ታደለ መንገሻ እና ከቅ/ጊዮርጊሱ አቤል ያለው ጋር ቆይታን ያደረግን ሲሆን ተጨዋቾቹም ምላሻቸውን በሚከተለው መልኩ ሰጥተውናል፡፡
ሊግ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፋችሁ ለፍፃሜው አልፏችኋል፤ ግጥሚያውን በምን መልኩ አሸነፋችሁ…? በድሉስ ምን ስሜት ተሰማህ?
አቤል፡- ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የነበረብንን የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ቡድናችን ለማሸነፍ የቻለው ሁላችንም የቡድኑ ተጨዋቾች ያለንን አቅም አውጥተን ልንጫወት በመቻላችን እና ግጥሚያውንም ለማሸነፍ ከፍተኛ መነሳሳት ስለነበረን ነው፤ በጨዋታው ቡናን ለማሸነፍ የእነሱን ኳስ ተቆጣጥሮ የመጫወት እንቅስቃሴ ልናውቅ መቻላችንና በመልሶ ማጥቃት አጨዋወትም ልንጫወት መቻላችን ጠቅሞናል፤ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ በጎዶሎ ተጨዋች የተጫወትንበትም አጋጣሚ ስለነበር ወደ ኋላ በመከላከሉ አፈግፍገን ተጫውተን ቆይተናልና በአጠቃላይ ድሉን ከፈጣሪ እርዳታ ጋር የሚገባን ሆኖ አግኝተነዋልና የጨዋታው አሸናፊ በመሆናችን በጣም ደስ ብሎናል፡፡
ሊግ፡- በቅ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ላይ ጥሩ የስታድየም ድጋፍም አስደሳች ድባብም ታይቷል፤ እንዴት ተመለከትከው?
አቤል፡- በጣም ነበር ደስ የሚለው፤ ይሄ አይነት ድጋፍም ቢቀጥል ለእግር ኳሱ በጣምም ነበር ጥሩ የሚሆነውና በዛ የድባብ ስሜት ውስጥ ሆነን ጨዋታውን ስላሸነፍንም ደጋፊዎቻችንንም ስላስደሰትንም ጥሩ ስሜት ሊሰማኝ ችሏልና በእዚሁ አጋጣሚ ደጋፊዎቻችንንም እንኳን ደስ አላችሁ ማለትም እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን በጨዋታው እንዴት ተመለከትካቸው?
አቤል፡- የኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረን ጨዋታ የራሳችን አጨዋወት ላይ ብቻ ትኩረት አድርገን ስለነበር ስለ እነሱ ብዙ የምለው ነገር የለም፤ ያም ሆኖ ግን ለእነሱ ጨዋታ ተዘጋጅተንና እንቅስቃሴያቸውንም አውቀን ስለነበር ልናሸንፋቸው ችለናል፡፡
ሊግ፡- የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታን ከሰበታ ከተማ ጋር ነገ እሁድ ታደርጋላችሁ፤ ምን ውጤት ይመዘገባል?
አቤል፡- የሰበታ ከተማ ጋር ያለንን የፍፃሜ ጨዋታ አሸንፈን የውድድሩ ሻምፒዮና ለመሆን በሚገባ ተዘጋጅተናል፤ ይሄን የነገ ጨዋታን የምናደርገውም በደጋፊዎቻችን ምርጥ ድጋፍ ታጅበን ስለሆነም ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ድሉ የእኛ ነው የሚሆነው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን ስታሸንፉ የጨዋታው ኮከብ ተብለሃል፤ ምን ስሜት ተሰማህ?
አቤል፡- ጨዋታው ኮከብ ተብዬ በመሸለሜ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ይሄ ሽልማትም የእኔ ብቻ ሳይሆን የቡድኑ የጋራ የስራ ውጤት ነውና ይሄን ነው ለማለት የምፈልገው፡፡