ወጣት ነው፤ ዮሴፍ ዩሐንስ ይባላል፤ ይሄ ተጨዋች በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለሲዳማ ቡና የመሀል ሜዳውን በመቆጣጠር እየተጫወተ ይገኛል፤ 6 ቁጥር ለባሹ ሊጉ ውስጥ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን በማሳየት ቡድኑን ሲጠቅም የተመለከትነው ሲሆን ተጨዋቹ በቀጣይ ጊዜ የኳስ ህይወቱ ከሀገር በመውጣት በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ እንደሚጫወትም ከወዲሁ ያልማል፤ ከዛ በተጨማሪም ባለፉት ዓመታት የሊጉ ጠንካራ የዋንጫ ተፎካካሪ የነበረው ቡድናቸው ሲዳማ ቡና የፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮና የሚሆንበት ትክክለኛው ወቅት ዘንድሮ እንደሆነም እየተናገረ ይገኛል፡፡
ከሲዳማ ቡናው የመሀል ሜዳ ተጨዋች ጋር የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ስለ ኳስ ህይወቱና ሌሎች ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ አናግሮት የሰጠው ምላሽ እንደሚከተለው ይቀርባል፤ ተከታተሉት፡፡
ስለ ትውልድ ስፍራው እና እድገቱ
“የተወለድኩት እና ያደግኩት በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሸበዲኖ ወረዳ ወይንም ደግሞ ለኩ በሚባለው ስፍራ ነው፤ እዛም ካደግኩኝ በኋላ ወደ ሐዋሳ ከተማ በመምጣት ልኖር ችያለሁ”፡፡
ስለ እግር ኳስ ጨዋታ አጀማመሩ
“የእግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት ከሕፃንነት ዕድሜዬ አንስቶ ነው፤ ትንሽ እያደግኩ ከመጣው በኋላም ለኳሱ ያለኝ ጥልቅ ፍቅር በጣም ጨመረና ወደፊት ጥሩ እግር ኳስ ተጨዋች ነነለመሆን እንደምችል በጣም አሰብኩ፤ ከዛም በመነሳት አሁን ላይ ያን የልጅነት ዕድሜዬ ምኞቴን ላሳካው ቻልኩ”፡፡
ስለ ቅፅል ስሙ
“ሸጎሌ ተብዬ ነው የምጠራው፤ ይህ ስያሜ ሊወጣልኝ የቻለው በሐዋሳ ከተማ ውስጥ ተዘጋጅቶ በነበረው የሽግግር ውድድር ላይ የከተማው አስተዳደርን ወክለን ኳስን ለመጫወት በተዘጋጀንበት ሰዓት ላይ እኔ ለቱላ ከተማ መጫወትን ፈለግኩ፤ አሰልጣኜ ቾንቤ እና ሌሎቹ ደግሞ ለታቦር ከተማ እንድጫወት ፈለጉ፤ በእዚህ ሰዓት ነው እንግዲህ አሰልጣኝ ቾንቤ ለእሱ ቡድን አለመጫወቴን በነገርኩት ሰዓት አንተ ሸጎሌ ነህ ሊለኝ የቻለውና ስያሜውን በተመለከተ ግን ምን ማለት እንደሆነ እስካሁን ድረስ አላውቅም”፡፡
የእግር ኳስን መጫወት ሲጀምር ተምሳሌቱ /አርአያ/ ስላደረገው ተጨዋች
“ከሲዳማ ብሔራዊ ክልል መጥቼ የሐዋሳ ከተማ ውስጥ በሚገኘው 07 ቀበሌ ወይንም ደግሞ ኮቦኒ ሰፈር መኖር እና ኳስን በፕሮጀክት ደረጃ መጫወት ስጀምር በችሎታው አድንቄው ሞዴሌ /ተምሳሌቴ/ ያደረግኩት ተጨዋች አሁን ላይ በአሰልጣኝነት ሙያ ላይ በመሰማራት የሐዋሳ ከተማ ክለብን በማሰልጠን ላይ የሚገኘውን ሙሉጌታ ምህረትን ነው፤ እሱ ጥሩ ተጨዋች ነበር፤ ለብዙ ተጨዋቾችም ወደ እግር ኳሱ መምጣት ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረገም በመሆኑ አድንቄው ነው ያደግኩት”፡፡
የእግር ኳስን ከመሀል ሜዳ ውጪ በሌላ ስፍራ ላይ ተጫውቶ እንደሆነ
“አዎን ተጫውቻለው፤ ይሄ የሆነውም በፕሮጀክት ደረጃ ላይ እያለው እና በሐዋሳ ከተማ የተስፋ ቡድን ውስጥ በነበርኩበት ሰዓት ላይ ነው፤ ያኔበመሀል ሜዳው ላይ ከእኔ የተሻሉ ጥሩ ተጨዋቾች ስለነበሩም ነው በመስመር ስፍራ ላይ ልጫወት የቻልኩት”፡፡
የእግር ኳስን መጫወቱ ላይ በቤተሰቦቹ አካባቢ ስለነበረው አመለካከት
“በቤተሰቦቼ በተለይ ደግሞ በአባቴ አካባቢ ልጅ በነበርኩበት ሰዓት ትምህርትን እንድማር ነበር የሚፈለገው፤ አባቴ ኳስ በመጫወቴም ይቆጣኝ ነበር፤ በፍጥነት ግን የእኔን ለኳስ የነበረኝን ጥልቅ ፍቅር ከተረዳ እና አስተዳደጌንም ካየ በኋላ ኳስን በደንብ እንድጫወት ፈቀደልኝ በኋላ ላይ ራሱም የህፃናቶች አሰልጣኝ ለመሆን በቃ፤ እናቴም የእኔን ስሜት እያከበረች በመምጣቷ ኳስን ያለምንም ችግር ነው በኋላ ላይ እየተጫወትኩ ለመምጣት የቻልኩት”፡፡
ከቤተሰቦችህ አባላት ውስጥ ከአንተ ውጪ ሌላ የእግር ኳስ ተጨዋች ስለመኖሩ
“በቤተሰባችን ውስጥ እኔን ጨምሮአራት ወንዶች አለን፤ ሁለት እህቶችም አሉኝ፤ አንድ እህታችንን ደግሞ ቀደም ሲል በሞት ልናጣት ችለናል፤ ከእነዚህ የቤቱ አባላት መካከል በአሁን ሰዓት ያለነው እግር ኳስ ተጨዋቾች ሶስት ነን፤ እኔና ሁለቱ ወንድሞቹ እነሱም በሲዳማ ቡና የተስፋ እና ቢ ቡድኑ ውስጥ እየተጫወቱ ይገኛሉ”፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ የእግር ኳስን ስለተጫወተበት ክለብ
“ከፕሮጀክት ተጨዋችነቴ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በክለብ ደረጃ ገብቼ የተጫወትኩበት ክለብ ቢኖር የሐዋሳ ከተማ ወጣት /u-20/ ቡድን ነው፤ እዛም ለሶስት ዓመት ያህል ቆየሁኝ፤ ከእዚህ ቡድን በኋላም ወደ ስልጤ ላንፍሮ /ጦራ/ ቡድን በማምራት ልጫወት ቻልኩ፤ በመቀጠልም ወደ ሀላባ ከተማ ቡድን ውስጥ በመግባት ከተጫወትኩ በኋላ ያሳየሁት እንቅስቃሴ ጥሩ መሆኑን ተከትሎ በቀድሞው የሙገር አሰልጣኝ ግርማ አማካኝነት ለኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን ለመመረጥ ቻልኩኝ፤ ከእዚህ በኋላም ነው የብሔራዊ ወጣት ቡድን ልምምድ ላይ እኔን ይመለከቱኝ በነበሩት የሲዳማ ቡና ክለብ ቡድን አመራር አቶ መንግስቱ ሳሳሞ አማካኝነት ጥሪው ደርሶኝ የአሁኑን ክለቤን ሲዳማ ቡናን ለመቀላቀል የቻልኩት”፡፡
ወደ ሲዳማ ቡና ሲያመራ ስለተፈጠረበት ስሜት
“ሲዳማ ቡናን በወቅቱ ስቀላቀል ባልጠበቅኩበት እና ባላሰብኩበት ሰዓት ስለነበር ወደ ቡድኑ ሳመራ በጣም ነበር ደስ ያለኝ፤ ክለቡ ውስጥ በመግባቴም እስከመገረም ደረጃም ነበር ያደረሰኝ፤ በጊዜው የክለቡ አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ /አሌኮም/ በጊዜው ነበርና ለአንድ ዓመት ለቡድኑ ፈረምኩኝ፤ ለግማሽ ዓመት ያህል ግን ለመጫወት አልቻልኩም፤ ከዛም በአሰልጣኝ ግርማ /መንቾ/ ለሚሰለጥነው ደቡብ ፖሊስ በውሰት ተሰጠውና እዛ መጫወት ጀመርኩ ከእዚህ በኋላም ነው ለሲዳማ ቡና መጫወት በሚያስችለኝ ደረጃ ላይ እንደሆንኩ ራሴን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከ2010 ጀምሮ ለሲዳማ ቡና ለመጫወት የቻልኩት”፡፡
ለሲዳማ ቡና ስላደረገው የመጀመሪያ ጨዋታው
“የመጀመሪያው ጨዋታዬ ከወላይታ ድቻ ጋር ያደረግነው እና 3-1 ያሸነፍንበት ግጥሚያ ነበር፤ ያ ጨዋታም ፈፅሞ የሚረሳኝ አይደለም፤ በተለይ ይህ ግጥሚያ በኳስ ህይወቴ ወደፊት ጥሩ ደረጃ ላይ ለመድረስ እንድችል ትልቁን መንገድ የከፈተልኝ እና ራሴንም በሚገባ ያወቅኩበት ጨዋታ ሆኖ ነው ያገኘሁት”፡፡
ስለ ሲዳማ ቡና እና ስለ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ
“ሲዳማ ቡና በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ትልቁ እና አሪፍም የሆነ ቡድን ነው፤ ይሄ ክለብ በአጭር ጊዜ የቡድን ምስረታውም ለሀገሪቱ እግር ኳስ ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችን በማውጣት እና ለፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮናነትም ባለፉት ዓመታቶች በመፎካከር ለጥቂትም ዋንጫ ያጣበት ጊዜም ስለነበር ለክለቡ ያለኝ አድናቆት ከፍተኛ ነው፤ የቡድኑንአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን በተመለከተ ደግሞ ይሄ ባለሙያለእኔ ትልቅ እና የምወደውም አሰልጣኝ ነው፤ ክለባችንን በኃላፊነት ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮም ቡድኑ ላይ እያሳየ ያለው ለውጥ በጣም ጥሩ ነው፤ አሰልጣኙ በቡድኑ አጨዋወት ውስጥ የሚታይ እና ቅርፅ የሆነ ነገርን እያስመለከተን ይገኛል፤ ከዛ ውጪም ክለቡን በኃላፊነት ሲመራም እኛን ተጨዋቾቹን እንደ አሰልጣኝ ብቻ ሳይሆን እንደ ወንድም እና አባት ጭምር በመቅረብ ብዙም ሳይከብደን እየመከረን ያለበት ሁኔታም አለና ይሄ እሱን ለየት እንዲል ያደርገዋል፤ አሰልጣኝ ዘርዓይ በቡድናችን ቆይታው በእግር ኳሱ የተሻለ ደረጃ ላይ እንድንደርስ በጣም ተግባብቶ ያለውም ከእኛ ተጨዋቾች ጋር ብቻ አይደለም፤በክለቡ /በመስሪያ ቤቱ/ አካባቢም ጥሩ ግንኙነት ነው ያለውና ይሄ መሆን መቻሉ በጣም ያስደስተኛል፡፡
ሲዳማ ቡናን በውጤት ደረጃ ዘንድሮ የት ድረስ ይጠብቁት እንደሆነ
“በፕሪምየር ሊጉ የውድድር ተሳትፎአችን ክለባችን ከእዚህ ቀደም የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ጠንካራ ተፎካካሪ የሆነበትን ጊዜ በተደጋጋሚ ተመልክተናል፤ ካቻምናም በመቐለ 70 እንደርታ በአንድ ነጥብ ተበለጥን እንጂ ዋንጫውን ለማንሳት ተቃርበን ነበር፤ የእዚህ ዓመት ላይ ግን ቡድናችን ከያዛቸው በወጣት የተገነቡ ተጨዋቾቹ አንፃርና የዝግጅት ጊዜ ልምምዳችንንም በጥሩ መልኩ መስራት ከመጀመራችን አኳያ የከዚህ በፊት ቁጭት ስላለብን የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ የምናነሳበት ጊዜ አሁን ነው”፡፡
በኮቪድወረርሽኝ ለወራቶች ከኳስ ርቀው አሁን ላይ ወደ ዝግጅት ስለመመለሳቸው
“የሲዳማ ቡና ክለብ ተጨዋቾች ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላላለፉት ወራቶች ከኳስ በመራቅአሁን ላይ ወደ ዝግጅት ሲገቡ እንደተመለከትኳቸው ሁሉም ተጨዋች አርፈው የመጡ አይመስሉም፤ ብዙዎቹ በሐዋሳ ከተማ እና አካባቢው የሚኖሩ በመሆኑም የእረፍት ወቅቱን ልምምድ በመስራትም ነበር ያሳለፉትና አሰልጣኙ እኛን በማይቸገርበት መንገድ ስላገኘንም ዝግጅቱን ለመጀመር ሳይቸገር ቀርቷል”፡፡
ኮቪድ እሱንና ቤተሰቦቹን ፈትኗቸው እንደሆነ
“ኮቪድ ማንን ያልፈተነው አለ፤ እኛን ብቻ አይደለም የዓለም ህዝብን ጭምር ነው የፈተነው፤ በተለይ ደግሞ ኳስ ተጨዋቾችን ኳሱ ሙያቸው እና እንጀራቸውም ስለሆነ እነሱንና ቤተሰቦቻቸውን በጣም ነው ሊፈትን የቻለው”፡፡
ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ ጊዜውን ስላሳለፈበት መንገድ
“ለእዚህ ክፉ ወረርሽኝ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ነበር በግል እና ወደ ጂምናዝየም ደረጃም በመሄድ ልምምዴን እሰራ የነበረው፤ ከዛ ውጪ ደግሞ ከቤተሰቦቼ ጋርም ነበር በቤት ውስጥ በመዋልም አሳልፍ የነበርኩት”፡፡
ወደ ትዳር ዓለሙ ገብቶ እንደሆነ
“ጓደኛ ብትኖረኝም እስካሁን አላገባሁም፤ የፈጣሪ ፈቃድ ከሆነ ዘንድሮ ልሞሸር እችላለው”፡፡
ስለ ሴት ጓደኛው
“ስለ እሷ ምን ብዬ እንደምነግርህ አላውቅም፤ ሁሌም ለእኔ ትጨነቅልኛለች፤ እንደ ኳስ ተጨዋችነቴም ምን ምን ነገሮችን እንደምፈልግም የምታውቅ ናትና ለእሷ ትልቅ ክብር ነው ያለኝ፤ በጣምም አመሰግናታለው”፡፡
ስለ ቀጣይ ጊዜ የእግር ኳስ ህይወቱ
“በእኛ ሀገር ውስጥ የሚገኙትን ብዙ ተጨዋቾች በአሁን ሰዓት ስለ ቀጣይ ጊዜ የኳስ ህይወታቸው ስትጠይቃቸው መጫወትን የሚያልሙትና የሚያስቡት ቅዱስ ጊዮርጊስ ገብተው ስለመጫወት ነው፤ የእኔ ግን ዋንኛ ዓላማዬ ለሀገሬ ብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ከመጫወት እና አሻራዬንም ጥሎ ከማለፍ ባሻገር ወደ አፍሪካ እና ወደ አውሮፓ ደረጃም በመጓዝ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት መጫወትም ነውና ይሄን እልሜን ለማሳካት ጥረትን አደርጋለው”፡፡
በእግር ኳስ ከአጠገቡ ሲጫወት ምቾት የሚሰጠው እና የመጀመሪያ ምርጫው የሆነው ተጨዋች
“ዳዊት ተፈራ /ኦዚል/ ነዋ!፤ ከእዚህ ተጨዋች ጋር በሲዳማ ቡና ክለብ ውስጥ አብረን እየተጫወትን ይገኛል፤ አጨዋወቱ ቀለል ያለ ስለሆነ የሚመችህ አይነት ነውና እሱ ነው የእኔ ቀዳሚ ምርጫ”፡፡
ከአጠገብህ አብሮ እንዲጫወት የምትመኘውስ ተጨዋች
“የመጀመሪያው ምርጫዬ ፍሬው ሰለሞን /ጣቁሩ/ ነው፤ ከእሱ ጋር እስካሁን ድረስ አብሬው በክለብ ደረጃ ለመጫወት አልቻልኩም፤ ያም ሆኖ ግን ሐዋሳ ከተማ ላይ በእረፍት ወቅት በምንገናኝበት ሰዓት ተሰባስበን የመጫወት አጋጣሚውን አግኝቼ ነበርና ለዛም ነው በችሎታው ስለወደድኩትና አስቀድሜም ስለተመለከትኩት እሱ ነው ምርጫዬ ሊሆን የቻለው፤ ከፍሬው ሌላ አብሬው ልጫወት የምፈልገው ተጨማሪ ተጨዋች ሙሉዓለም መስፍን /ዴኮ/ ነው”፡፡
ከእግር ኳስ ውጪ መዝናኛው
“በካፌ ውስጥ መቀመጥ፤ በቤት ውስጥ ሆኜ የቀድሞ ቅጂ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን መመልከት እና ከቤተሰቦቼ ጋር መሆን እነዚህ ነገሮች ናቸው እኔን የሚያዝናኑኝ”፡፡
ከባህር ማዶ ስለሚያደንቀው እግር ኳስ ተጨዋች እና ስለሚደግፈው ቡድን
“ከተጨዋቾች የክርስቲያኖ ሮናልዶ እና የሴስክ ፋብሪጋዝ አድናቂ ነኝ፤ በክለብ ደረጃ የምደግፈው ደግሞ አርሰናልን ነው”፡፡
የእግር ኳስ ጨዋታ ያለ ደጋፊዎች እየተከናወነ ስለመሆኑ
“በእዛ ደረጃ የእግር ኳስ ጨዋታው መከናወኑ ማራኪ ነው ብዬ አላስብም፤ ከባድ ጊዜንም ነው እያሳለፍን የምንገኘው፤ ያም ሆኖ ግን ከኮቪድ አንፃር የምንጫወተው ለዓላማ እና ጤንነታችንንም ለመጠበቅ ስለሆነ ስራችንን በአግባቡ እየሰራን ጥሩ ጊዜ እንዲመጣልን መጠበቅ ነው”፡፡
የእግር ኳስን ሲጫወት በሜዳ ላይ እለኸኛ ስለመሆኑ
“አዎን፤ ኳስ ስጫወት በጣም እለኸኛ ነኝ፤ እለኸኛ የምሆነውም ከሌላ ነገር ተነስቼ ሳይሆን መሸነፍን ካለመፈለግ ነው፤ ቡድኔ ሁሌም እንዲያሸንፍ ነው የምፍልገው፤ ስለዚህም ሰዎች ይህን ባህሪዬን ሊረዱልኝ ይገባል”፡፡
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስለመመረጥ እና ስለመጫወት
“የዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ ተካትቼ መጫወት ዋንኛ እልሜ ነው፤ ከእዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ለሆናቸው ቡድን በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ አማካኝነት ተመርጬ የነበረ ቢሆንም ከዛ በኋላ ለመመረጥ አልቻልኩም፤ እንደ እኔ እምነት በቀጣይነት ልመረጥ ያልቻልኩት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አድርገነው በነበረው ጨዋታ ላይ የፍፁም ቅጣት ምት ሲሰጥብን ስሜታዊ የመሆን ነገርን አሳይቼ እና ኳሱንም ጠልዤው ነበርና ከዛ መነሻነት ይመስለኛል፤ ስለዚህም ያኔ ለሰራሁት ጥፋት የቡናንም ሆነ ስፖርት አፍቃሪውን ይቅርታ በመጠየቅ ለቀጣዩ ጊዜ ብሔራዊ ቡድን ለመመረጥ ጠንክሬ እሰራለው”፡፡
በመጨረሻ…
“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታው በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ አማካኝነት የሚፈልጋቸውን ተጨዋቾች እሱ ለሚመርጠው የጨዋታ እንቅስቃሴ በመምረጥ ወደ ዝግጅት ገብቷል፤ የወዳጅነት ጨዋታንም እያደረገ ይገኛል፤ አሰልጣኝ ውበቱ በሙያው ከእኛ የተሻለ እና የቆየም በመሆኑ ምርጫውን ልናከብርለት ይገባል፤ ይሄ ብሔራዊ ቡድን የእኛ የሁላችንም ነው፤ ቡድኑን በጋራ ሆነን ልንደግፈው ይገባል፤ ለአፍሪካ ዋንጫም የምናልፍ ይመስለኛል፤ ከዛ ውጪ ሌላ ላስተላልፈው የምፈልገው መልህክት በኳሱ እዚህ ደረጃ እንድደርስ የረዱኝን ቤተሰቦቼን በተለይ ለእኔ የጀርባ አጥንቴ የነበረውን አባቴን፣ እናቴን እንደዚሁም ደግሞ ልጅ እያለው ያሰለጠነኝን ኤፍሬምን እና የአሁኑ አሰልጣኜን ዘርዓይ ሙሉን ለማመስገን እፈልጋለው”፡፡