“ለዲስፕሊን ተገዢ መሆኔ የኳስ ሕይወቴን አሳምሮታል“
“ሲዳማ ቡና በጣም ተመችቶኝ እየተጫወትኩበት ያለ ክለብ ነው፤ የሊጉን ዋንጫ ማንሳትና በአፍሪካ የውድድር መድረክ ላይም መጫወት ቀዳሚው እልማችን ነው“
ሳላህዲን ሰይድ /ሲዳማ ቡና/
“ሲዳማ ቡና በጣም ተመችቶኝ እየተጫወትኩበት ያለ ክለብ ነው፤ የሊጉን ዋንጫ ማንሳትና በአፍሪካ የውድድር መድረክ ላይ መጫወት ቀዳሚው እልማችን ነው”
“ጠንክሬ መስራቴ ቅንና ዲስፕሊን ያለው ተጨዋች መሆን ለኳስ ተጨዋችነት ህይወቴ በጣም ጠቅሞኛል” ሳላህዲን ሰይድ /ሲዳማ ቡና/
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ለአሳዳጊው ክለቡ ሙገር ሲሚንቶ ጨምሮ ለቅ/ጊዮርጊስ እንደዚሁም ደግሞ ወደ ግብፅ ሊግ በመሄድ መጫወትን ችሏል። በአሁን ሰዓት ላይ ደግሞ ለሲዳማ ቡና እግር ኳስ ቡድን በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላይ እየተጫወተ ይገኛል። የቤንሻንጉሉ ሀሶሳው ተወላጅ ሳላህዲን ሰይድ የእግር ኳስን ላለፉት 16 ለሚደርሱ ዓመታቶች ሲጫወት አልፎ አልፎ ያጋጥመው ከነበረው ጉዳት በስተቀር በጥሩ ብቃት ላይ ሆኖ በመጫወት ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህን የዋልያዎቹን የቀድሞ ተጨዋች ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ መስከረም 20 ቀን ሊጀመር ስላለው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ቡድናቸው እያደረገ ስላለው ዝግጅት፣ ምን ውጤት ሊያመጡ እንደተዘጋጁ፣ ከቡድኑ ጋር ስላለው ቆይታ እና ሌሎች መሰል ጉዳዮችን በመያዝ ተጨዋቹን ያናገርነው ሲሆን እሱም በቂ የሆነ ምላሹን ሰጥቶናል፤ ተከታተሉት።
ሊግ፦ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሰህ?
ሳላህዲን፦ እንኳን አብሮ አደረሰን።
ሊግ፦ የሲዳማ ቡና የፕሪ-ሲዝን ዝግጅት ምን ይመስላል?
ሳላህዲን፦ በጣም ጥሩ ነው፤ እስካሁንም በቀን ሁለት ጊዜ ልምምዳችንን በደምብ እየሰራን ይገኛል። ዓላ ካለ እንግዲህ ዋናው ግባችን ዋንጫ እስከሆነ ድረስ ይህን ድል ሊያሳካ የሚችል ቡድን መምሰል ስላለበት የፕሪ-ሲዝን ዝግጅታችንን በበቂ ሁኔታ እየሰራን ይገኛል።
ሊግ፦ የአዲሱ ሲዝን ስብስባችሁ ምን መልክ አለው?
ሳላህዲን፦ ቆንጆ ነው፤ ከአምናው ሁለት ልጅ ማለትም ሀብታሙ እና ዳዊት /ኦዚል/ ብቻ ናቸው የለቀቁብን። በእነሱ ምትክም ሌሎች ልጆችን ለመተካት ተሞክሯል። በእያንዳንዱ የመጫወቻ ቦታ ላይ ያለን ስብስብም ሰፍቷል፤ ተመጣጣኝ ችሎታ ያላቸውን ልጆችም እንደ አጠቃላይ ይዘናል። ለቋሚ ተሰላፊነትም አንዱን ተጨዋች በጉዳት ብታጣ እሱን ተክቶ ለመጫወት የሚችል ልጅን በመያዛችን ጥሩ ፉክክርን የያዘ ቡድን ይዘናል።
ሊግ፦ ባሳለፍነው የውድድር ሲዝን የአመቱ ግማሽ ላይ ብትመጣም ለቡድናችሁ ጥሩ ለመንቀሳቀስ ችለህ ነበር፤ አንደኛውን ዙር ደግሞ በልምምድ ነው ያሳለፍከው፤ ዘንድሮስ ከአንተ ምን ይጠበቅ?
ሳላህዲን፦ ከውድድር ስትርቅ በተቻለ መጠን ከብቃትህ /ከሙድህ/ እንዳትወጣ በተቻለ መጠን ጠንክረህ መስራት አለብህና ያን የመጀመሪያው ዙር ላይ ሳደርገው ነበር። በሁለተኛው ዙር ወደ ክለቡ ስመጣ ደግሞ ከጠበቅኩት በላይ ነው ቡድኑን ያገኘሁት። በጣም ጥሩ ቡድን ነበረን። የማውቃቸው ልጆችም ነበሩበት። በእዚህ አጋጣሚ የእነሱ መኖር ተጨምሮበት ከዓላ እርዳታ ጋር ቡድኑን እንድላመድ አድርጎኛል፤ በእዚህ አጋጣሚ የቡድኑን የኮቺንግ ስታፍ አባላቶችና ተጨዋቾችንም ክለቡን እንድላመድ ስላደረጉኝ እና ጥሩ አቀባበልንም ስላደረጉልኝ አመሰግናቸዋለሁ። ዘንድሮ ስለሚኖረኝ የውድድር ቆይታ ደግሞ አሁን ላይ ከክለቡ ጋር ጥሩ ዝግጅትን በመስራት ላይ ስለሆንኩ ክለቡን በመጥቀሙ በኩል ጥሩ ጊዜንም ነው የማሳልፈው።
ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዘንድሮ ምን ውጤትን ከሲዳማ ቡና ክለብ እንጠብቅ?
ሳላህዲን፦ የእኛ ክለብ አሁንም በማሰብ ላይ የሚገኘው ዋናው ግቡን የሊጉን ዋንጫ ማንሳት መቻል አድርጎ ነው። በውጪ የውድድር መድረክ ላይም መሳተፍን ይፈልጋልና ሻምፒዮና ባንሆን እንኳን ሁለተኛ መውጣትም ሌላው ግባችን ነውና እሱን እየጠበቅን ነው። ይኸው ክለብ ከእዚህ ቀደም ሁለተኛ ወጥቷል። አምና ደግሞ ሶስተኛ ሆኖ ጨርሷል። ዘንድሮ ደግሞ ከላይ እንደገለፅኩልህም ዋንጫ ማንሳትን ነው የቅድሚያ ግባችን ያደረግነው።
ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላለፉት በርካታ ዓመታቶች በመጫወት ላይ ትገኛለህ፤ አንተን የተለየ ተጨዋች ካደረጉህ ምክንያቶች መካከልም ይህ የሚጠቀስ ነው፤ ምንአልባት ለእዚህን ያህል ዓመታቶች መጫወትን ለሚፈልጉ ወጣቶች ይህ ትምህርት ሊሆን ስለሚችል የምትለው ነገር ካለ?
ሳላህዲን፦ በእዚህ መልኩ ለመጫወት ዲሲፕሊን ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፤ ከእዛ በተጨማሪ ደግሞ ለእግር ኳሱ የምትሰጠው ቦታ ስራህ እስከሆነ ድረስ ስራህን ማክበር ይኖርብሃል፤ ስራህንም ልትወደው ይገባል። አንዳንዱ ስራውንና ኳሱን ሊወድ ይችላል። ያም ሆኖ ግን ኳሱ የሚፈልገው ነገር ምን አይነት ባህሪይና ዲሲፕሊን ነው የሚለው ነገር ግልፅ ነው፤ ያን መተግበር ነው። ሁለተኛው ነገር ደግሞ ኳሱን መጫወት ስትጀምር ጊዜህን በአግባቡ መጠቀም ነው። ለምሳሌ እኔ የመጣሁበት መንገድ ከፕሮጀክት አንስቶ ነው። በጊዜም ነው በታዳጊ ወጣትነት ዕድሜዬ በብሄራዊ ቡድኖች ደረጃ ላይም በአጋጣሚ ትላልቅ ከሚባሉ ተጨዋቾችም ጋር የተጫወትኩት። ጥሩ ነገርን ከእነሱ ቀስሜያለሁ። እልሜ የነበረውም በኳሱ ለትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስም ነበር። የማስበው ደረጃ ላይ ተገኝቻለሁ ባልልም ከእነ ጉዳቴ አላምዲሊላ /ፈጣሪ ይመስገን/ ለብዙ ዓመታቶች በመጫወት አሁን ያለሁበት ደረጃ ላይ ተገኝቻለሁ። ኳሱን ለብዙ ዓመታቶች ለመጫወት ዋናው ነገር ቅንነት እና ዲስፕሊን መሆን ነው፤ ያም ነው እኔን ለበርካታ አመታት እያጫወተኝ የሚገኘው።
ሊግ፦ ባሳለፍካቸው የእግር ኳስ ህይወትህ ደስተኛ ነህ፤ የቁጭት ስሜትስ አለ?
ሳላህዲን፦ በኳስ ዓለም ጥሩ ነገርም ቁጭትም ይኖራል። ሁለቱንም ነገሮች እኔ አሳልፌያለሁ። አሁን ላይ ደግሞ ወደ ሲዳማ ቡና ቤት ሳመራ በጣም ደስተኛ ሆኜ ነው ኳሱን እየተጫወትኩ ያለሁት። ተጨዋቾቹም ሆኑ አሰልጣኞቹ የሰጡኝ ቦታ እና ያደረጉልኝ አቀባበልም ጥሩም ነውና ላመሰግናቸውም እፈልጋለሁኝ። ክለቡም ተመችቶኛል።
ሊግ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የዲ ኤስ ቲቪ ሽፋንን አግኝቶ መካሄድ ከጀመረ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል። በእዚህ ዙሪያ ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ?
ሳላህዲን፦ በእውነት ጨዋታዎቹ የዲ ኤስ ቲቪ ሽፋንን አግኝተው መካሄድ መቻላቸው ለእግር ኳስ ተጨዋቹ ጥሩ መነቃቃትን ነው የሰጠው። ይህ ሆኖ ሳለ ግን ባለፈው ደግሞ የመጨረሻ ጨዋታዎች አካባቢ እንዴት እንደሆነ ባላውቅም አንዳንድ ግጥሚያዎች በምን መልኩ ከዋንጫው ጨዋታ በኋላ መደረጋቸው እና የዲ ኤስ ቲቪ ሽፋንን አለማግኘታቸው ነገሮችን አስቂኝ ከማድረግ ባለፈ በክፍተትና በጉድለት ደረጃ ያየሁት ነው። ያም ሆኖም ግን እንደ አጠቃላይ ስመለከተው የዲ ኤስ ቲቪ መኖር ወሳኝ ነው። ውድድሩ እንደ አቡኪ አይነት ልጆችን እንዲወጡ እና ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊግ ላይ ሄደውም እንዲጫወቱ ስላደረጋቸውም ሊጉ አሁን ላይ ለውጥ ታይቶበታል።
ሊግ፦ አቡኪ ወደ ደቡብ አፍሪካ በማምራት ለማማሎዲ ሰንዳውንስ እየተጫወተ ይገኛል፤ የእሱን እንቅስቃሴ እንዴት አገኘኸው?
ሳላህዲን፦ አቡኪ አቅም ያለው ልጅ ነው፤ በእዚሁ ከቀጠለም ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሶ ማየት እንችላለን ብዬ አስባለው። ከእሱም ብዙ እጠብቃለሁ።
ሊግ፦ የክረምቱን የእረፍት ወቅት በምን መልኩ አሳለፍክ?
ሳላህዲን፦ የአንድ ወር ጊዜ ነበረን። በእዛም ወቅት ከቤተሰብ ጋር እና አንዳንድ የጂም ስራዎችን በመስራት ነው ያሳለፍኩት።
ሊግ፦ አዲስ ዓመት ሲመጣ ምን ነገርን ሰንቀህ ታሳልፋለህ?
ሳላህዲን፦ አዲስ ዓመት ደስ ይላል፤ አገራችን ሰላም ሆኖ በስራዬ የተሳካ ጊዜን ማሳለፍ ነው የምፈልገው።
ሊግ፦ እናጠቃል?
ሳላህዲን፦ የመጨረሻ መልዕክቴ አገራችን ሰላም ሆና ሁሉም ሰው በፍቅር የሚኖርባት እንድትሆን እንደዚሁም ደግሞ ስፖርተኛውን ጨምሮም ሁሉም ሰው በየድርሻው የሚችለውን እንዲያደርግ ነው የማስተላልፈው።