Google search engine

“የእዚህ ዓመት የሻምፒዮናነቱ ፉክክር እንደ ዓምናው እስከ መጨረሻው አይጓዝም” “አንድ ክለብ ሁለትና ሶስት ጨዋታ ሲቀር  የእዚህ ዓመትን ዋንጫ ያነሳል”  ስንታየሁ መንግስቱ /ወላይታ ድቻ/

 

በፕሪምየር ሊጉ ለወላይታ ድቻ በአጥቂ ስፍራ በመጫወት በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል። ፈጣን ነው፤ ጎል ጋርም ቶሎ ቶሎ ይደርሳል። ቀደም ሲል የደረሰበት ጉዳት  ዘንድሮ ከጎል ማስቆጠር አርቆት የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ወደ መልካም ጤንነቱ የተመለሰ ስለሆነ እንደ በፊቱ ለክለቡ ጎል በማስቆጠር ስኬታማ ግልጋሎቱን እንደሚሰጥ ስንታየሁ መንግስቱ ከሊግ ስፖርቱ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል።

ሊግ ስፖርት ከወላይታ ድቻው አጥቂ ስንታየሁ መንግስቱ ጋር በሊጉ ተሳትፎአቸው እና ከራሱ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የነበራቸው አጠቃላይ ቆይታም የሚከተለውን ይመስላል። ተከታተሉት።

በእዚህ ዓመት ሊጉ ላይ እያደረጉት ስላለው ተሳትፎ

“ቆይታችን ሁለት አይነት ገፅታ የነበረው ነው፤ ባህርዳር ላይ ትንሽ  ጥሩ ጊዜን አላሳለፍንም። ወደ ድሬዳዋ ስንጓዝ ግን ጠንክረን ሰርተን የተሻለ ውጤት ልናመጣ ችለናል”።

የእዚህ ዓመት ተሳትፎአቸው ላይ ምን ውጤትን ለማምጣት እንዳለሙ

“እኛ በእያንዳንዱ ጨዋታዎች ላይ ከእዚህ በፊት ከነበረን አቋም በተሻለ መልኩ በመቅረብ ከአምናው በጣም ከፍ ያለ ውጤት ለማምጣት ነው እየተጫወትን የሚገኘው”።

የውድድሩ ጉዞአችሁ ላይ ጠንካራና ማሻሻል ያለባችሁ ጎን

“ማሻሻል ያለብን ጎን አለ፤ እነዛም  ለአሰልጣኞቻችን የሚታዩ በመሆናቸው የሚታረሙ ናቸው። ጠንካራ ጎናችንን በተመለከተ ህብረታችንና አንድነታችን በዋናነት ይጠቀሳል። ይህ ገፅታም የክለባችን መገለጫም ሆኗል።

ጎል ከማስቆጠር ጋር በተያያዘ ቡድኑን ለመጥቀም እያደረገ ስላለው ቅድመ ዝግጅት

“ከጎል ማስቆጠር ጋር በተያያዘ አሁን ላይ ስሜ እየተነሳ አይደለም። እንደ አንድ አጥቂ የእኛም ክለብ ከእኔ ጎል ይፈልጋልና በግሌ በጣም እየተዘጋጀው ስለሆነ ወደ ጎል ማስቆጠሩ በቅርቡ የምመለስ ይሆናል”።

ወላይታ ድቻ  በፊት በፊት ከሊጉ ላለመውረድ የተጫወተበት እና መሀል ሰፋሪም ሆኖ የቆየበት ጊዜ ነበር፤ ያን ሂደት ስለማሻሻሉ

“እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ከእዚህ በፊት አጋጥመውን የነበሩ ቢሆኑም አሁን ላይ  ሁኔታዎቹ ሊሻሻሉ ችለዋል። ይሄ የሆነውም አንድ እና አንድ ጠንክረን ልንሰራ በመቻላችን ነው”።

በፕሪምየር ሊጉ ለየት ባለ መልኩ /ሰርፕራይዝ/ ሆኖ የቀረበብህ ቡድን

“ኢትዮጵያ መድን ነዋ! ይሄ ክለብ በሊጉ ተሳትፎው ከተገመተው በላይም ነው እየተጓዘ የሚገኘው”።

በውድድሩ የእስካሁኑ ጉዞ ለእናንተ አስቆጪ የሚባለው ግጥሚያ የቱ እንደሆነ

“አስቆጪው ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ያደረግነው ነው፤ ከእዚህ ግጥሚያ ነጥብ መውሰድ እየተገባን ባለቀ ሰዓት በተቆጠረብን የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ቢያንስ ነጥብ መጋራት እየቻልን ተሸንፈንበታል”።

የእዚህ ዓመትን የሊግ ዋንጫ ማን ሊያነሳ ይችላል?

“ሊጉ ገና 18 ጨዋታዎች ይቀሩታል። አሁን ላይ ሆነህ ግን ይህ ቡድን ዋንጫውን ያነሳል ብሎ መገመት  ከባድ ነው”።

የዘንድሮው  የሊጉ ፉክክር እንደ አምናው አንገት ለአንገት ተያይዞ ይጓዝ እንደሆነ

“ጥሩ ፉክክር ይኖረዋል፤ እንደ አምናው ግን በተቀራረበ ነጥብ /ታይት/ ሆኖ ይጓዛል ብዬ ፈፅሞ አላስብም። ከእዛ ይልቅ እኔ የማስበው አንድ ቡድን ሁለትና ሶስት ጨዋታዎች ሲቀሩት ዋንጫውን የሚያነሳ ይመስለኛል”።

ስላሳለፍከው የኳስ ህይወት፤ በጣም ደስተኛ ነህ?

“ሁሌም ሙሉ ለሙሉ ደስተኛ አትሆንም። የምትደሰትባቸው ጊዜ አለ፤ እንደዛውም የምትከፋባቸው። የምከፋው ገና በመምጣት ላይ ያለው ተጨዋች ስለሆንኩኝ አንድ ነገርን ማድረግ እየፈለግኩ በጉዳት ከሜዳ ስርቅ ይቆጨኛል። ይህን ቁጭቴንም ወደፊት በሚኖሩት የውድድር ጊዜ ቆይታዎች የምቀርፋቸውና በጣም የምደሰትባቸው ጊዜያቶችም ይኖሩኛል”።

የወደፊቱ የሀገሪቱ ምርጥ ተጨዋች ይሆን እንደሆነ

“ፈጣሪ ይመስገነው እና የእኔ ሀሳቤ ከእዛም  በላይ ስለመሆን እና ታሪክ ሰርተው እንዳለፉት ተጨዋቾች መሆንንም ነው የምፈልገው”።

በኳስ ተጨዋችነቱ ወደፊት መድረስ ስለሚፈልግበት ስፍራ

“በዋናነት ለሀገሬ ብሄራዊ ቡድን ተመርጬ  ማገልገል እፈልጋለሁ። በሁለተኝነት ደግሞ የጎል ቁጥሬን ማሳደግ እፈልጋለሁ። ሌላው ደግሞ ብቃቴን አሳድጌና በውጤት ደረጃ ለክለቤ ወላይታ ድቻ ጥሩ ነገርን ከሰራው በኋላ  ወደ ውጪ ወጥቼ መጫወትንም እፈልጋለሁ”።

በተለያዪ ምክንያቶች ከሜዳ ሲራቅ የሚሰማው ስሜት

“ለአንድ እግር ኳስ ተጨዋች እንዲህ ያሉ ነገሮች ሲያጋጥሙ ስሜቱ ከባድ ነው። ይሄም ክለብህን ሜዳ ገብተህ የማታገለግልበት እና የማትጠቅምበት ሁኔታ ስላለም ነው። ሜዳ ገብተህ የምታገለግለው ፈጣሪ ሲፈቅድ ነው። በተለይ ጉዳቶች ደርሶብህ ከሜዳ ስትርቅ ከብዙ እቅዶችህ ወደ ኋላ ያስቀርሃልና ሁሉንም ነገር ለበጎ ብሎ ማለፉ ጥሩ ነው”።

በህይወትህ ስትኖር በጣም የሚቆጭህ

“ቁጭቶች ይኖራሉ፤ የምትቆጨውም አንዳንዴ  ነገሮች  አንተ  እንዳሰብከው ሳይሄዱልህ ሲቀሩም  ነው፤  በተለይ የእግር ኳሱ ህይወትህ ላይ  የስራው ባህሪው  ቁጭትም ደስታም አለውና  ነገሮችን እንዳመጣጣቸው መቀበል ጥሩ ነው”።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አልጄሪያ ላይ እያደረገ ስላለው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎው

“ውጤቶች ሊመጡ ወይንም ደግሞ ላይመጡ ቢችሉም ቡድናችን ላይ ጥሩ ነገሮችን እየተመለከትን ነው የሚገኘው።  ይሄን ጥሩነት አስቀጥለን ልናስጉዘው ይገባል። በውድድሩ ላይ ማሸነፍ የምንችልበትን ጨዋታ ከሞዛምቢክ ጋር ነጥብ ተጋርተንበታል። ከአልጄሪያ ጋር ስንጫወት ደግሞ ከግጥሚያው በፊት የተባለውና ቡድናችን ሜዳ ከገባ በኋላ ነገሮችን በተቃራኒነትም አስመልክቶናልና ጥሩ ቡድን እንዳለን  እያሳየን ነው። ስለ ቡድኑ አጠቃላይ አቋም ለመናገር ግን  እኔ ኳስ ተጨዋች ስለሆንኩ ብዙ የምለው ነገር የለኝም። በእዚህ ላይ የስፖርቱ ባለሙያዎች አስተያየት ይስጡበት”።

በመጨረሻ

“በእግር ኳሱ ሙያዬ ከፈጣሪ ቀጥሎ ብዙ ሰዎች ከጎኔ ሆነው እያገዙኝ ነው፤ ወደፊትም ያግዙኛል። ፈጣሪን ጨምሮ እነዚህን አካላቶች በጣም ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ”።

 

 

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P