Google search engine

“ሸገር ደርቢውን ከማሸነፍ ባሻገር የሜዳ ላይ ፉክክሩን ልናደምቀው ተዘጋጅተናል”
ጋዲሳ መብራቴ /ቅ/ጊዮርጊስ/

በመሸሻ_ወልዴ

ሊግ፡- በድሬዳዋ ስታዲየም ነገ ምሽት ስለምታከናውኑት የሸገር ደርቢው ጨዋታ በቀጥታ ከማምራቴ በፊት አንድ ነገርን ልጠይቅህ እስኪ?

ጋዲሳ፡- ይቻላል የፈለግከውን ጥያቄ ጠይቀኝ፡፡

ሊግ፡- ይሄ ዓመት ለአንተ ደስታንም ትካዜንም እያሳለፍክበት ነው ልበል?

ጋዲሳ፡- አዎን፤ በትክክልም ነው የገለፅከኝ፤ ምክንያቱም አንድን እግር ኳስ ተጨዋች በህይወት ዘመኑ እንዲህ ያሉ ነገሮች ያጋጥሙታልና እኔንም ስላጋጠመኝ ነው፤ የእዚህ ዓመት ላይ እግር ኳስን ስጫወት በህይወቴ ላሳካቸው ከምፈልጋቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ ለሀገሬ ብሔራዊ ቡድን በመመረጥ ከዚህ ቀደም ወደ አፍሪካ ዋንጫ ዋልያዎቹን ካሳለፉትና ታሪክ እንደሰሩትም ተጨዋቾች አንዱ መባልን እፈልግና እመኝ ስለነበር ያን ላሳካና በጣም ልደሰት ችያለሁ፤ ወደ ክለቤ ቅ/ጊዮርጊስ ስትመጣ ደግሞ በዚሁ ቡድን ቆይታዬ ምናለ በብሔራዊ ቡድን ተጨዋችነቴ እየተደሰትኩ እንዳለሁት ሁሉ በክለቤም ውጤትን አምጥተን ደስ ባለኝም እያልኩ እየተመኘው ባለሁበት ሰዓት እስካሁን ይሄን እያሳካው ባለመሆኔ እየተከዝኩና እያዘንኩም ነው የምገኘውና በዚህ ቡድን ደስታን የማገኝበትና አህምሮዬንም አረፍና ዘና የማደርግበትንም ጊዜ እየጠበቅኩኝ ነው፡፡

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈችበት የደስታ ስሜት አሁንም ድረስ በውስጥህ እንዳለ ነው?

ጋዲሳ፡- አዎና! ደስታው እንዴትስ ይጠፋል ብለህ ነው? ምክንያቱም ይሄ ደስታ መላው የሀገራችን ህዝብ የተደሰተበት እና ይህን እልም ያሳካነው ደግሞ ከ8 ዓመታት ቆይታ በኋላ ስለሆነ እንዲህ ያሉ ስኬቶችን ደግሞ ሀገራችን ከዚህ ቀደምምቢሆን ያገኘችበት ጊዜ በርካታ ዓመታቶችንም ማለትም 31 ዓመታትን ጠብቃ ስለነበርም የእዚህ ታሪክ ባለቤት መሆን መቻል ደግሞ እንደ አንድ ተጨዋች ልዩ ስሜትንም ስለሚሰጥም ነው በእኔም የተጨዋችነት ዘመን ላይ ይህን ጣፋጭ ድልን ስለተጎናፀፍን ደስታዬ መቼም ቢሆን ከውስጤ ሊወጣ ያልቻለውምና ይህን ስመለከት በክለቤም እንዲህ ያለ ታሪክን ማግኘት በጣሙን እያጓጓኝም ነው የሚገኘው፡፡

ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስ ክለብህን በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ብዙዎች ውጤት ከማምጣት ጋር በተያያዘ እንደጠበቁት አላገኙትም?

ጋዲሳ፡- የእውነታቸውን ነው፤ የእኛን ቡድን በተመለከተ ብዙዎች ብቻ ሳይሆኑ አጠቃላይ የእግር ኳስ አፍቃሪውና ስፖርተኛውም ጭምር ነው እንዲህ ትሆናላችሁ ብሎ ስላልጠበቀን የውጤት ማጣታችን አስገራሚ ሊሆንባቸውም የቻለው፤ ቅ/ጊዮርጊስ እኮ የሚታወቀው በውጤታማነቱ እና በተደጋጋሚ ጊዜ የሊግ ዋንጫውን በማንሳቱ ነው፤ አሁን አሁን ግን ይህን ውጤት ማግኘት እየራቀን ነው፤ የማይመጥነንንም ውጤት እያስመዘገብን ነው፤ በተለይ ዘንድሮ ደግሞ ከመሪው ክለብ ፋሲል ከነማ ጋርም ሰፋ ባለ ነጥብም የራቅንበት አጋጣሚ ስላለም ለክለባችን ገፅታ ጥሩ አይደለምና በቀጣይ ጊዜ የሊጉ ግጥሚያዎቻችን ላይ ምንም አይነት ነጥብን ሳንጥልና በነጥብ በመቃረብም በክለቡ ታሪክ የራቀንን ግስጋሴያችንን ዳግም ለማሳየት እየተዘጋጀን ነው የሚገኘው፡፡

ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስን ውጤት እያሳጣው ያለው ጉዳይ ምንድን ነው?

ጋዲሳ፡- የራሳችን ድክመትና ችግር ነዋ ውጤትን ያሳጣን፤ ከአምናው ቡድን አንፃር የአሁኑ ቡድን ደከም ብሎብኛል፤ ለዛም ማንም ላይ ማሳበብን አልፈልግም፤ ለውጤት ማጣታችንም ከራሳችን ውጪ ማንንም መውቀስም አልፈልግም፤ በርካታ ነጥቦችን ነበር የጣልነው፤ አንዳንዶቹ የጣልናቸው ነጥቦች የማይሆኑ ናቸው፤ አንድአንዶቹን ጨዋታዎች ስናሸንፍ ደግሞ ተቸግረንም ጭምር ነው ስናሸንፍ የነበርነውና በእዚህ ዓመት ላይ ይዘን የቀረብነው ቡድን የሚዋዥቅ አይነትና ወጥ የሆነ አቋምም የሌለው ስለነበር ለዛም ጭምር ነው ውጤትን ዘንድሮ እያጣን ልንጓዝ የቻልነው፡፡

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን በሸገር ደርቢው ጨዋታ እሁድ ምሽት ትገጥማላችሁ፤ ምን ነገርን ከጨዋታው እንጠብቅ?

ጋዲሳ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎአችን የቡድናችንን የውጤት ማጣት መነሻ በማድረግ የበፊቱ አሰልጣኝ ከኃላፊነቱ ተነስቶ በአሁን ሰዓት በአዲስ አሰልጣኝ እየተመራን ይገኛል፤ አዲሱ አሰልጣኝም የቡድኑን አቋም ለማስተካከልና ክለቡ ወደሚታወቅበት ውጤታማነትም ሊመልሰን እያዘጋጀን ይገኛልምና በሸገር ደርቢው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለንን ጨዋታ አሸንፈን ከሜዳ ለመውጣት በሁሉም መልኩ ተዘጋጅተናል፤ ከቡና ጋር የሚኖረን የሸገር ደርቢ ጨዋታ ለእኛ በጣም የምንፈልገው ግጥሚያ ነው፤ በመጀመሪያው ዙር ከእኛ ግብ ጠባቂያችን በቀይ ካርድ ወጥቶ እነሱ አሸንፈውናል፤ ያም ቢሆን ግን በጎዶሎ ልጅ ሆነን ጥሩ ተጫውተናል፤ አሁን ግን እኩል አስራአንድ አስራአንድ ሆነን የምንጫወትበት አጋጣሚ ስላለና ይሄ ጨዋታ ደግሞ ወደፊት ለምናደርገው የውጤታማነት ጉዞም ዋናው ፍልሚያ ስለሆነ አሸናፊ እንሆናለን፡፡

ሊግ፡- የሸገር ደርቢው ያለ ደጋፊ የሚከናውን መሆኑ ጨዋታውን ያቀዘቅዘዋል ተብሏል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን አልክ….ከእናንተ ተጨዋቾችስ ከእዚህ ጨዋታ ምን ይጠበቅ?

ጋዲሳ፡- ይህን ጥያቄ እንኳን አነሳክልኝ እኛና ቡናዎች የምናደርገው የሸገር ደርቢ ጨዋታው እንደከዚህ በፊቱ በደጋፊዎቻችን የምናደርገው አይደለም፤ እነሱ ቢኖሩ ጨዋታው ይበልጥ ይደምቅ ነበር፤ አሁንም ቢሆን ግን ያለ እነሱ ይህን ጨዋታ እንዳሉ አድርገን በመቁጠር ጨዋታውን ልናደምቀው እና ስፖርታዊ ጨዋነትም በተሞላበት መልኩ ግጥሚያውን ልናደርግ ተዘጋጅተናል፤ ይሄን ጨዋታ ዲ.ኤስ. ቲቪም በቀጥታ ስለሚያስተላልፈው ሁሉም በያለበት ሆኖም በመመልከት ቡድኑን በጥሩ ሁኔታ ሊያበረታታም እንዲችል መልህክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለው፡፡

ሊግ፡- በሸገር ደርቢው የመጀመሪያ ጨዋታ ጥሩ ተንቀሳቅሰሃል፤ ይሄ ይደገማል?

ጋዲሳ፡- አዎን፤ በትክክልም ነው የምደግመው፡፡

ሊግ፡- ፋሲል ከነማ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን በሰፊ የነጥብ ርቀት ከመምራቱ አኳያ አሁንም ዋንጫውን የማንሳት እድላችን አልተሟጠጠም ብላችሁ እያሰባችሁ ነው?

ጋዲሳ፡- እንደ ሂሳብ ስሌት ለምን አናስብም፤ ደግሞም በእግር ኳስ ጨዋታ የሚመጣውን ነገር አታውቅም፤ክለባችን ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ከዚህ ቀደም በሰፊ የነጥብ ልዩነት ተበልጦ ዋንጫ ያነሳበት ጊዜ ስለነበርና ለጥቂትም ዋንጫ ያጣበትም ወቅት ስላለ ለዛም ነው ያለንን የከዚህ ቀደም ልምድ በመጠቀምና እስከመጨረሻው ጨዋታ ድረስም የሌላ ቡድንን ውጤት ባለመጠበቅ ከራሳችን የሚጠበቀውን የአሸናፊነት ውጤት በማስመዝገብ የሚመጣውን እድልም የምንጠባበቀው፤ ይሄ ባይሳካ እንኳን ጨዋታዎችን እያሸነፉ መጓዙም በአፍሪካ መድረክ ለሚያወዳድረው የኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳትፎም ውጤቱ ይረዳናልና ለዛም ጭምር ነው ቀሪዎቹን ግጥሚያዎች የምናደርገው፡፡

ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስ ዋንጫ ማንሳትን ለምዷል፤ ከመሪው ካላችሁ የነጥብ ርቀት አኳያዘንድሮ በቤትኪንግ ተሳትፎአችሁ ሁለተኛ ብትወጡ ያስከፋችኋል?

ጋዲሳ፡- ለምን ያስከፋናል፤ በእርግጥ የእኛ ቡድን ካለው ስምና ዝና አንፃር ከዛ በተጨማሪ ደግሞ ከትልቅ ክለብነቱ አኳያ እያመጣንለት ያለው ውጤት የሚመጥነው ባይሆንም፤ ይህን ደግሞ ደጋፊው የሚያውቅ ቢሆንም የውድድር ዘመኑ ሲጠናቀቅ ክለባችን ቤትኪንጉን ሁለተኛ ሆኖ ቢያጠናቅቅ እንደበፊቱ ጊዜ አያስከፋንም፤ ምክንያቱም ቡድናችን ወደ ኢንተርናሽናል የውድድር መድረክ መመለስን አጥብቆ ይፈልጋል፤ ለዛም የሌላ ክለቦችን ውጤት ሳንጠብቅናበራሳችን ግጥሚያ ውጤት ብቻ በመወሰን ይህን ውጤት ለማምጣትም ነው እየተጫወትን የምንገኘው፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ… ?

ጋዲሳ፡- ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችን ሁላችንንም አስደስቶናል፤ ሀገራችን በብዙ ነገሮች ጭንቀት ላይም ነበረችና ይህ ውጤት መምጣቱ የሰውን አህምሮ በብዙ ነገር ቀይሮት አረጋግቶታል፤ የመጣው ድል ከምንም በላይ አይደለም እኛ የቡድኑ አባል ለሆንነው ለሁሉም ሰው ታሪኩ ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ሲደሰትን ማየት የበለጠ የሚያረካ ነገር የለምና በዛ እኔም ደስ ብሎኛል፤ ይህን ካልኩ የመጨረሻ መልዕክቴ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን ነው፡፡

https://t.me/Leaguesport

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P