Google search engine

“ሻምፕዮን የመሆን ሕልማችን ይሳካል” አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)መሸሻ ወልዴ /G.BOYS
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ25ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ዐርብ፣ ቅዳሜ እና እሁድ ዕለት በተደረጉት ግጥሚያዎች ቀጥሎ
የዋለ ሲሆን ከእነዚህ ጨዋታዎች መካከል ተጠባቂ ከነበሩት መሀል አንዱ የሆነውን ጨዋታ ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ ቡናን
በአዲስ ግደይ እና በሀብታሙ ገዛኸኝ ሁለት ግቦች 2ለ0 በማሸነፍ ከመሪው ክለብ ፋሲል ከነማ በሶስት እንደዚሁም
ደግሞ ከተከታዩ ቡድን መቐለ 70 እንደርታ በሁለት ነጥቦች በማነስ ወደ ዋንጫው ፉክክር ሊቃረብ ችሏል፡፡
የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ኢትዮጵያ ቡናን ባሸነፈበት ጨዋታ ከተጋጣሚው ተሽሎ የታየበት ሲሆን የቡድኑ ስኬታማው
የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች አዲስ ግደይም በኢትዮጵያ ቡና ላይ የድል ጎል ከማስቆጠሩ ባሻገር ጥሩ ችሎታቸውን ካሳዩት
የቡድኑ ተጨዋቾች መካከልም አንዱ ስለነበር ስለ ክለብ ውጤታማነት ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ ጋር በነበረው ቆይታም
ይናገራል፡፡
የሲዳማ ቡና ስኬታማው የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች አዲስ ግደይ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎአቸው ላይ ለክለቡ
እያስቆጠራቸው ያሉት ተደጋጋሚ ግቦች እና ከጓደኞቹም ጋር በሜዳ ላይ የሚያሳየው ጥሩ እንቅስቃሴ ክለቡን ለፕሪምየር
ሊግ ሻምፒዮናነትም ሊያበቃው ይችላል በሚል በብዙዎቹ የክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ አደራም የተጣለበት ተጨዋች ሲሆን
ከዛ ባሻገርም የሀገሪቱ የኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር ውስጥ ከመገኘቱ እና በመሪነት ደረጃም ላይ ከመቐለ 70
እንደርታው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ጋርም በጋራ ከመፎካከራቸው አንፃር ክብሩን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜም ያገኛል
ተብሎ ግምትም ተሰጥቶታል፡፡
የሲዳማ ቡናውን አዲስ ግደይ በክለባቸው ውጤታማነት ዙሪያ እና ሌሎችንም ጥያቄዎች የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ
ወልዴ /G.BOYS/ ጠይቆት ተጨዋቹ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቶናል፤ ተከታተሉት፡፡


ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን በሜዳው እና በደጋፊው ፊት 2ለ0 አሸንፋችኋል፤ ጨዋታው ምን መልክ ነበረው? በድሉስ ምን
ስሜት ተሰማህ?
አዲስ፡- ኢትዮጵያ ቡናን በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ድል ያደረግንበት የእሁዱ ጨዋታ ተጋጣሚያችን የሀገሪቱ ትልቅ
ቡድን ከመሆኑ አንፃር እኛ ያስመዘገብነው ውጤት በጣም ጥሩ የሚባል ነው፤ ጨዋታው ጥሩ ፉክክር ተደርጎበታል፤
ከግጥሚያው በኋላም በክለባችን ማሸነፍ እኔ ብቻ ሳልሆን የቡድናችን ተጨዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ አመራሮች እና
ደጋፊዎቻችን በጣም ተደስተውበትም አልፏል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን እንረታለን ብለህ ገምተህ ነበር?
አዲስ፡- አዎን፤ ምክንያቱም ክለባችን አሁን ላይ እየተጫወተ የሚገኘው የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ነው፤ እንደዚህ ያሉ
ምኞቶችን እና ህልሞችን ለማሳካት ደግሞ የግድ ከአጠገባችን ወደሚገኙት መቐለ 70 እንደርታ እና ፋሲል ከነማ ጋር
በነጥብ መቀራረብ ስላለብን እና እኛም ደግሞ በዛ ደረጃም በተወሰነ የነጥብ ልዩነት ርቀት ላይ የምንገኝ በመሆናችን
የእነሱን አንገት ለመያዝ እንዲቻል እንዲህ ያሉ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ስላለብን በከፍተኛ የአሸናፊነት ስሜት
ላይ ሆነን ወደ ሜዳ በመግባታችን ነው ተጋጣሚያችንን በማሸነፍ ባለድል ለመሆን የቻልነውና በእሁዱ ጨዋታ ኢትዮጵያ
ቡናን አሸንፈን ከሜዳ በመውጣታችን በጣም ነው የተደሰትኩት፡፡
ሊግ፡- የእሁዱ ጨዋታ ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ለማሸነፍ እንድትችሉ የረዳችሁ ዋንኛው ጥንካሬያችሁ ምን ነበር?
አዲስ፡- የፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎ ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊትም በነበሩት ግጥሚያዎች ላይ ሌሎችን
ክለቦች ለመርታት የቻልንባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች እና ጥንካሬዎች ያለን አንድነት እና ህብረት ከፍተኛ ስለሆነ ነው፤
ለዛም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ስንጫወትም ግጥሚያውን ለማሸነፍ በህብረት ምን ማድረግ እንዳለብን እንነጋገርና
እንተጋገዝም ስለነበር ይሄ ጉዞአችን የጨዋታው አሸናፊ እንድንሆን አድርጎናል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን እሁድ የነበረው ጨዋታ ላይ እንዴት አገኘኸው?
አዲስ፡- የኢትዮጵያ ቡናን የከዚህ በፊት ጨዋታዎች ብዙ ባላይም የእኛን ቡድን እሁድ ዕለት በተፋለሙበት ጨዋታ ላይ
ግን በመጀመሪያው አጋማሽ ትንሽ ጫና ፈጥረውብን ሊጫወቱ ቢችሉም ያን ዕለት ብዙም ጥሩ የሚባሉ አልነበሩምና
ቡናን የተፋለምነው በዚሁ መልኩ ነው፡፡
ሊግ፡- መቐለ 70 እንደርታ በሐዋሳ ከተማ በመሸነፉ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መሪነትን ጅማ አባጅፋር ላሸነፈው
ለፋሲል ከነማ አስረክቧል፤ እናንተ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፋችሁ ሁለቱንም በነጥብ ተጠግታችኋል፤ ከእዚህ
አንፃር የሊጉን ዋንጫ የማንሳት እድላችሁ የቱን ያህል ይሆናል?
አዲስ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ ቡድናችን ባለፉት አመታቶችም ሆነ ዘንድሮ እየተካፈለ
የሚገኘው ሻምፒዮናነትን አስቦ ነው፤ ስለዚህም አሁን ላይ ይህንን ፍላጎታችንን ለማሳካት ከወዲሁ ስለቀሪዎቹ 5
ጨዋታዎቻችን በማሰብ ለግጥሚያው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን እና ጨዋታዎቹንም በማሸነፍ ውጤቱ የሚያስቀምጠን
ቦታ ላይ ልናርፍ ተዘጋጅተናልና ዘንድሮ ሻምፒዮና የመሆን ህልማችን ይሳካል፡፡

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሊጠናቀቅ የ5 ሳምንታት ጨዋታዎች ይቀሩታል፤ የዘንድሮውን ፉክክር አሁን ላይ እንዴት
አገኘኸው?
አዲስ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፉክክርን አሁን ላይ ሁላችንም እንደተመለከትነው ወራጁንም ሻምፒዮናውንም
ክለብ ለመለየት የከበደበት የውድድር ዘመን ላይ ሆኖ ያገኘሁት ሲሆን፤ በዚህ የሻምፒዮናም ውድድር የሊጉን መሪ
መቐለ 70 እንደርታን ከሰፊ የነጥብ ልዩነት ተከታዮቹን መምራት በኋላ አሁን ተደጋጋሚ ነጥቦችን በመጣሉ ምክንያት
ወደመንሸራተት የመጣበት እና ፋሲል ከነማ እና እኛ ደግሞ የነጥብ ልዩነቱን በማጥበብ ዋንጫ የማንሳት እድል
እንዲኖረን ያደረግንበት የውድድር ዘመን ስለሆነ ያለው የሊጉ ፉክክር ጥሩ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ተሳትፎአችሁ በዋንጫው ፉክክር ውስጥ ቆይታችሁ
ተመልሳችሁ ከፉክክሩ ወጥታችሁ ነበር፤ አሁን ላይ ሊጉ ወደመጠናቀቁ ሲቃረብ ደግሞ በድጋሚ ወደ ፉክክሩ ውስጥ
ልትገቡ ችላችኋል፤ ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ?
አዲስ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዙር ግጥሚያዎች ሲጀመሩ ቡድናችን በሶስት ተከታታይ የሜዳው ውጪ
ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ውጤትን ሊያስመዘግብ ባለመቻሉ ከዋንጫው ፉክክር ሊወጣና እና ሊንሸራተትም ችሎ ነበር፡፡
ሆኖም ግን ከእነዚያ ግጥሚያዎች በኋላ አቋማችንን በማስተካከል መልሰን ወደ ዋንጫው ፉክክር ውስጥ ልንገባ
ችለናልና በዚህ ደረጃ ላይ ለመገኘት ያስቻለን ዋናው ጉዳይ የነበሩብንን ችግሮች በፍጥነት ልናርም በመቻላችን ነው፤ ይሄ
ጥንካሬያችንን ያሳየን ሆኖም አልፏል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክሩን አንተና አማኑኤል በመምራት ላይ ትገኛላችሁ፤ ዘንድሮ
በዚህ ደረጃ ላይ እገኛለው ብለህ ጠብቀህ ነበር? ከሁለታችሁ ማንስ ኮከብ ግብ አግቢ ይሆናል?
አዲስ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር ውስጥ ዘንድሮ ለክለቤ ተደጋጋሚ ጎሎችን ከማስቆጠሬ
አንፃርና ለውጤታማነታችንም ማማር ቡድኔ ከእኔ በርካታ ጎሎችን የሚፈልግ ስለነበር በግብ አግቢነት ፉክክሩ ውስጥ
እንደምኖርበት እገምት ነበርና አሁን ላይ በዛ ደረጃ ላይ መገኘቴ ብዙም የሚያስገርም አይደለም፡፡
የሲዳማ ቡና የጨዋታ ዘመን ቆይታዬ ላይ እስከዛሬ ለቡድኑ ስንቀሳቀስ እና ስኬታማ ስራዎችን ስሰራ የነበረው ለኮከብ
ግብ አግቢነቱ ብቻ አስቤ አልነበረም፤ የእኔ ዋንኛው ምኞቴና ዓላማዬ በቅድሚያ ቡድኔን ውጤታማ ማድረግ ነው፤
ሌላው የኮከብ ግብ አግቢነቱ ደግሞ ቀጥሎ የሚመጣ ነውና ዘንድሮ የጣምራ ሽልማት ባለቤት ለመሆን
እስከመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ድረስ በርትቼ ነው የምሰራው፡፡
ሊግ፡- የሲዳማ ቡና ደጋፊዎችን እንዴት ነው የምትገልፃቸው?
አዲስ፡- የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች አሁን ላይ የሚሰጡን ድጋፍ ከወትሮው ማለትም ከዚህ በፊት ከነበረው አይነት የሚለይ
እና በጣምም የአማረ ነው፤ የድጋፉ ዋናው ልዩነትም በፊት በብዛት ሆነው በሜዳቸው ነበር የሚደግፉን አሁን ላይ ግን
ጥሩ ውጤትን እያስመዘገብን ከመሆናቸው አኳያ ከክልላቸው እና ከሜዳቸው ውጪ ያሉትን ጨዋታዎችም በርካታ
ሆነው የሚያበረታቱን ስለሆነ በዚህ ሊመሰገኑ ነው የሚገባው፤ ከሚሰጡን ጥሩ የሆነ ድጋፍ አኳያም እነሱን በውጤት
ልናስደስታቸውም ተዘጋጅተናል፡፡
ሊግ፡- የመቐለ 70 እንደርታው አማኑኤል ገ/ሚካኤል በኮከብ ግብ አግቢነቱ የአንተ ተፎካካሪ ከመሆኑ አኳያ ብቃቱን
እንዴት ነው የምትገልፀው? ስለ አንተ የቡድን አጋርህ ሀብታሙ ገዛኸኝስ ምን ትላለህ?
አዲስ፡- የመቐለ 70 እንደርታው አማኑኤል ገ/ሚካኤል የአጥቂው ስፍራ ላይ የሚያገኛቸውን የግብ እድሎች
በመጠቀምም ሆነ ባለው የግል ችሎታ ጎበዝ የሆነ ተጨዋች ነው፤ ከእሱ ጋር በክለብ ደረጃ አብረን ባንጫወትም
የብሄራዊ ቡድን ላይ የተወሰነ ቆይታ አድርገናልና የማደንቀው ተጨዋች ነው፤ ሌላው የቡድናችን ተጨዋች የሆነውን
ሃብታሙ ገዛኸኝን በተመለከተ ደግሞ ሀብታሙ ለቡድናችን ውጤት ማማር በጣም የሚለፋ እና ታታሪ የሆነም ተጨዋች
ነው፤ በሜዳ ላይ እንዳለው ኳሊቲም ብዙ ያልተወራለት እና ያልተዘመረለትም ተጨዋች ነውና ወደፊት ከዚህ በላይም
ጥሩ ነገርን ይሰራል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P