የፋሲል ከነማ የአማካይ ክፍሉ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን ከሚያሳዩት ተጨዋቾች መካከል አንዱ የደሴ ከተማ ተወላጁ ኤፍሬም ዓለሙ ነው፤ ይህ
ተጨዋች በሜዳ ላይ በሚያሳየው ብቃት በብዙዎቹ የስፖርት አፍቃሪዎች አድናቆትን እያተረፈ ሲሆን በቁመቱ አጠር የሚለው ይኸው ተጨዋች በሊጉ
የውድድር ዙሪያ ቡድናቸው የአሁን ሰዓት ላይ ካለው ወቅታዊ አቋሙ እና ከያዙት የተጨዋቾች ስብስብ አንፃር በቀጣዮቹ የስድስት ሳምንታት
ጨዋታዎቻቸው የሊጉን መሪ መቐለ 70 እንደርታን በልጠው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ሻምፒዮና እንደሚሆኑ ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ
ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሹን ለጋዜጣው ሰጥቷል፡፡
የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ሊጠናቀቅ የስድስት ሳምንታት ጨዋታዎች በቀሩበት የአሁን ሰዓት ላይ በደረጃው ሰንጠረዥ ከመሪው መቐለ 70
እንደርታ በሁለት ነጥብ በማነስ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከእዚህ በኋላ የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎችም የዋንጫ ያህል በመመልከት እና
ለግጥሚያዎቹም ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የሊጉ ሻምፒዮናነትን ማንም እንደማይነጥቃቸውም አማካዩ ኤፍሬም ዓለሙ እየተናገረ ይገኛል፡፡
የፋሲል ከነማው የአማካይ ስፍራው ተጨዋች ኤፍሬም ዓለሙ ለክለቡ ተሰልፎ እየተጫወተ ባለበት የአሁን ሰዓት ላይ እስካሁን ለቡድኑ ውጤት
ማማር 4 የሊግ ጎሎችን ለማስቆጠር የቻለ ሲሆን ይህን ተጨዋች በቡድናቸው የሊግ ተሳትፎ እና አቋማቸው ዙሪያ፣ የሊግ ዋንጫውን ማን
እንደሚያነሳ፣ በራሱ አቋም እና ሌሎችንም ተያያዥ የሆኑ ጥያቄዎችን አንስተንለት የሚከተሉትን ምላሾች ሊሰጠን ችሏል፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ ወልዋሎ አዲግራትን ማሸነፍ መቻሉ ከመሪው ክለብ መቐለ 70 እንደርታ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት እንዲያጠብ አድርጎታል፤
ድል ያደረጋችሁበት ጨዋታ ምን ይመስል ነበር፤ ውጤቱንስ እንዴት አገኘኸው?
ኤፍሬም፡- የወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲን ያለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በሜዳችን ገጥመን ድል ያደረግንበት ጨዋታ እኛ ከተጋጣሚያችን
በተሻለ ጥሩ እንቅስቃሴን ያደረግንበት እና በጨዋታውም ለመከላከል የመጣውን ቡድን በማሸነፍ ከሜዳ የወጣንበት ጨዋታ ሲሆን በተመዘገበው
ውጤትም ለዋንጫው ፉክክር ከመጫወታችን አንፃር በጣም ደስተኛ የሆንበትም ነበርና ውጤቱ የሚገባን ሆኖ ነው ያገኘነው፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲን ለማሸነፍ እንዲችል የረዳው ዋናው ጉዳይ ምን ነበር?
ኤፍሬም፡- የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎው ላይ ወልዋሎ አዲግራትን ብቻ ሳይሆን በርካታ ክለቦችን ለማሸነፍ
የቻለበት ዋንኛው ጥንካሬው ቡድኑ በሜዳውም ሆነ ከሜዳው ውጪ ሲጫወት በማጥቃት ላይ የተመረኮዘን እንቅስቃሴን ስለሚከተል እና
የጨዋታውም አካሄድ እንደ ግል ሳይሆን እንደ ቡድንም በመጫወት በተደጋጋሚ የተጋጣሚዎቹ የግብ ክልልም ጋር የሚደርስ በመሆኑ ነውና ይሄ
ለውጤታማነቱ በሚገባ ሊጠቅመው ችሏል፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማ ብዙዋን ተጨዋቾች ጎንደር ላይ በሚደረግ ጨዋታ በተጋጣሚዎቻቸው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ደስተኛ አይሆኑም ይባላል፤ ይሄ
ሁኔታ ምንድን ነው?
ኤፍሬም፡- አዎን፤ እኔም ተጋጣሚዎቻችን በሚከተሉት አጨዋወት ደስተኛ አይደለውምና የቡድኔን ተጨዋቾች ሀሳብ እጋራለው፤ የሊጉ የውድድር
ዘመን ተሳትፎ ላይ ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን እንደተመለከትኩት ወደ ጎንደር የሚመጡት ሁሉም ክለቦች ግጥሚያቸውን ከእኛ ጋር ሲያደርጉ
የመከላከል አጨዋወትን በመምረጥ አንድ ነጥብን ለመውሰድ ስለሚጫወቱ ይሄ አጨዋወታቸው ብዙም አይመቸኝም፤ ያም ሆኖ ግን መጨረሻ ላይ
የብዙዎቹ ክለቦች እጣ ፈንታም ሲሆን የሚታየው ሽንፈትንም ሲያስተናግዱም ነውና የሚመርጡት አጨዋወት ለእኛ የጠቀመበት ጊዜም በብዛት
ታይቷል፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማ እግር ክለብ ዘንድሮ እያሳካቸው ላሉት ውጤቶች ሌሎች የሚጠቀሱ ምክንያቶችስ የሉትም?
ኤፍሬም፡- አሉት እንጂ፤ ከላይ ከጠቀስኳቸው በሜዳውም ሆነ ከሜዳው ውጪ ሲጫወት አጥቅቶ እንደ ቡድን ከመንቀሳቀሱ በተጨማሪ ቡድኑ
ውስጥ ያለው የአንድነት እና እያንዳንዳቸውን ጨዋታዎች ስናደርግ ወደ ሜዳ ይዘን የምንገባው የአሸናፊነት መንፈስ እንደዚሁም ደግሞ እርስ በራሳችን
ያለን የመከባበር ስሜት እና ተጨዋቹ ተሰለፈም አልተሰለፈም ቅድሚያ ለራሱ ሳይሆን ለቡድኑ የሚሰጥበት ጉዞ በጣሙን የጠቀመን ሆኗል፤ ከዛ
ውጪ ሌላው ቡድናችን በወጣት እና ጥሩ ችሎታ ባላቸው ተጨዋቾችም መገንባቱ እና አሰልጣኙ የሚሰጠን ልምምድም ጥሩ መሆኑ እነዚህ ስኬታማ
ሊያደርጉን ችለዋል፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ በአንደኛው ዙር የሊግ ተሳትፎው ጎል ማግባት ላይ ተቸግሮ ነበር፤ አሁን ግን ይሄን ችግሩን ቀርፏል፤ ይሄ ለውጥ እንዴት መጣ?
ኤፍሬም፡- የእውነት ነው፤ የፕሪምየር ሊጉን ውድድር በአንደኛው ዙር ላይ ስናከናውን ግቦችን በተደጋጋሚ የሚያስቆጥርልን ሁነኛ አጥቂ ስላልነበረን
ብዙ ጎሎችን አናገባም ነበር፤ ይሄ ደግሞ ዋንጫውን ለሚያስቡት ፋሲሎች አደጋ አለውና ይሄንን ችግራችንን የግድ መቅረፍ አለብን ብለን በመነጋገር
እና ጠንክረን በመስራት አሁን ላይ ክፍተቱን በመድፈን ጎሎችን እያስቆጠርንና ግጥሚያዎችንም እያሸነፍን እንገኛለን፡፡
የፋሲል ከነማ ክለብ የአጥቂው ክፍል ላይ የነበረበትን ክፍተት ሊሞላ የቻለው የቡድኑን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት የተከላካይ ስፍራ ላይ
የሚጫወተውን ሙጂብ ቃሲምን የሁለገብ ተጨዋችነት ሚና ስላለው እሱን ወደፊት በማምጣቱና ከዛ ውጪ ደግሞ የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ
የጨዋታ ታክቲክ ሁሉንም የቡድኑን ተጨዋቾች የሚያሳትፍ እና የሚያደርጉትም የጨዋታ እንቅስቃሴ ጎሎችን ለማስቆጠርም የሚያመች ስለሆነ
ሁሉም ጎልን ስለሚያስቆጠር በእዚህ በኩል ለውጥን ልናመጣ ችለናል፤ ፋሲል አሁን ጎል እያገባ የሚገኘው በአጥቂ ክፍሉ ብቻ አይደለም፤ አማካኙ
ያገባል፤ የመስመር ተጨዋቹ ያገባል፤ እንዲሁም ተከላካዩም ጎል ያገባልና ይሄ ደግሞ ለአንድ ቡድን ውጤታማነት በጣምም ወሳኝ ነውና ይሄ
ጥንካሬያችን እና የለውጣችንም ሚስጥር ወደፊትም አብቦ ይቀጥላል፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ በቅርቡ ከደቡብ ፖሊስ ጋር ባደረገው የሜዳው ላይ ጨዋታ አቻ በመለያየት ነጥብ ጥሎ ነበር፤ ያን ውጤት ስታጡ የተፈጠረባችሁ
ስሜት ምን ይመስል ነበር? ከዋንጫው ፉክክር ወጣን አላችሁ? ወይንስ ሌላ ተስፋ እንዳላችሁ ሰነቃችሁ?
ኤፍሬም፡- ፋሲል ከነማ ከደቡብ ፖሊስ ጋር ባደረገው ጨዋታ ተጋጣሚያችን የወራጅ ቀጠናው ላይ የሚገኝ በመሆኑና ይከብደናልም ብለን
ስላላሰብን ወደ ሜዳ እርግጠኛ ሆነን የገባነው ከግጥሚያው ሶስት ነጥብ ይዘን ስለመውጣት እንጂ የአቻ ውጤትን ፈፅሞ አልጠበቅንም ነበር፤
ያም ሆኖ ግን የኳስ ነገር ሆኖ ነጥብን ተጋርተን ልንወጣ ችለናል፤ የአቻነቱን ውጤት ስናስመዘግብም አሰልጣኛችን አስቀድሞ ደቡብ ፖሊስ ሊከብደን
እንደሚችል ነግሮን ነበርና የምንፈልገውን የድል ውጤት ባለማግኘታችን በጣም አዝነን ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ከጨዋታው በኋላ የሊጉ መሪ መቐለ 70
እንደርታም በባህር ዳር ከተማ ሽንፈትን አስተናግዶም ስለነበር አሁንም ከሊጉ የዋንጫው ፉክክር አልወጣንም፤ ከዚህ በኋላ ስለቀጣዩ
ግጥሚያዎቻችን እናስብ ብሎ ስለነገረን እና የደቡብ ፖሊስ ጨዋታችንም ትምህርት ሆኖ ስላገኘነው ከመከላከያው የአዲስ አበባው ጨዋታ አንስቶ
ያሉትን ግጥሚያዎች በማሸነፍ አሁን ላይ ከመሪው ክለብ ጋር ያለንን የነጥብ ልዩነት በማጥበብ ዋንጫ የማንሳት እድላችንን እያሳመርነው ይገኛል፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማ ቀጣዩ የሊግ ጨዋታ ነገ ይካሄዳል፤ ለጨዋታው ምን አይነት ዝግጅት አድርጋችኋል፤ ምን ውጤትስ ይኖራችኋል?
ኤፍሬም፡- የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ በሜዳው እና በምርጦቹ የቡድኑ ደጋፊዎች ፊት በመታጀብ ነገ ከጅማ አባጅፋር ጋር የሚያደርገው ጨዋታ
በወሳኝነቱ አቻ ከማይገኝላቸው ግጥሚያዎች መካከል አንዱ ነው፤ ጅማ የአምናው የሊግ ሻምፒዮና ነው፤ ከዛም ባሻገር አሁን ላይ ተከታታይ
ጨዋታዎችን በማሸነፍም ሆነ ነጥብ በመጋራት ወደፊት እየገሰገሰ ይገኛልና ለእዚህ ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን ነው ግጥሚያውን እየተጠባበቅን
የምንገኘው፡፡
የፋሲል ከነማ ክለብ ከጅማ አባጅፋር ጋር በሚኖረው ጨዋታ ወደ ሜዳ የሚገባው ለዋንጫው ባለቤትነት የሚጫወት ከመሆኑ አኳያ ግጥሚያውን
ለማሸነፍ ነው፤ ደግሞም ጨዋታውን እናሸንፋለን፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ የፕሪምየር ሊጉ አሸናፊ ለመሆን ከመሪው መቐለ 70 እንደርታ እና ከራሱ ስር ካለው ሲዳማ ቡና ጋር እየተፎካከረ ይገኛል፤ ከ6
ጨዋታዎቻችሁ በኋላ ሊጉ ሲጠናቀቅ ይሄ ዋንጫ ወደየት ያመራል?
ኤፍሬም፡- የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ የሊግ ውድድሩ ሊጠናቀቅ የስድስት ሳምንታት ጨዋታዎች በቀሩበት የአሁን ሰዓት ላይ ዋንጫውን
ለማንሳት የሚፎካከረው ከላይ እንደጠቀስከው ከሊግ መሪው መቐለ 70 እንደርታና ከሲዳማ ቡና ክለቦች ጋር ቢሆንም ይሄ ዋንጫ ዘንድሮ የእኛ
ቡድን ከያዘው ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብ እና በየሜዳውም ላይ ካሳየው ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ አንፃር ድሉ የሚገባን ለእኛ ስለሆነ በእርግጠኝነት
የእዚህ የውድድር ዘመን አሸናፊ የምንሆነው እኛ ፋሲሎች ነን፡፡
ሊግ፡- የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እኮ የመቐለ 70 እንደርታን ነጥብ መጣል እና እናንተም ያላችሁን ቀሪ ግጥሚያዎች ማሸነፍ የግድ
ይላችኋል ይሄ ይሳካል?
ኤፍሬም፡- ፋሲል ከነማ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ያነሳል ስንል ያለምክንያት አይደለም፤ ቡድናችን ከመሪው ክለብ ጋር የነበረውን የ10 ነጥብ ልዩነት
አጥቦ አሁን ላይ ወደ ሁለት ማድረግ መቻሉ አንድ ነገር ከፊታችን እንደሚጠብቀን ምልክት ስለሰጠን ነው ሻምፒዮና እንሆናለን እያልን የምንገኘው፤
የሊግ ዋንጫውን ለማንሳት አሁን ላይ እኛ እያሰብን የምንገኘው የራሳችንን የቤት ስራ ስለመወጣት ብቻ ነው፤ ይህም ቀሪዎቹ 6 ጨዋታዎቻችን
የዋንጫ ያህል የምናደርጋቸው ስለሆኑ እነሱን ማሸነፍ ከቻልን ሻምፒዮና እንሆናለን፤ ቡድናችን አሁን ስለመሪው ክለብ እያሰበ አይደለም የሚገኘው፤
ቀሪዎቹን ጨዋታዎች እኛ የምናሸንፍ ከሆነ መቐለ ካሉት የሜዳው ውጪ ጨዋታዎቹ አንፃር ነጥብ መጣሉ አይቀሬ ስለሆነ ነው ሻምፒዮናነታችን
በእርግጠኝነት ይሳካል እያልን የምንገኘው፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብን ከፕሪምየር ሊግ ክለቦች የሚለየው የተለየ ነገር አለ?
ኤፍሬም፡- አዎን፤ የፋሲል ከነማ ክለብን ከሌሎች ቡድኖች ይለየዋል ብዬ የምናገረው በመጀመሪያ በየግጥሚያው ጥሩ እግር ኳስን የሚጫወት እና
በሜዳውም ከሜዳውም ውጪ አጥቅቶ የሚጫወት መሆኑ ነው፤ ከዛ ውጪ ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ተጨዋቾች ከወጣቶች ጋር አጣምሮ እያጫወተ
ይገኛል፤ ሌላው ቡድኑ ውስጥ ማንም ተሰለፈ አልተሰለፈም ሁሉም
ቅድሚያ የሚሰጠው ለቡድኑ ውጤት ማማር ነው፤ ከዛ ባሻገር በእያንዳንዱ የሊግ ጨዋታዎቻችን ላይ ለክለባችን ማን ጎል እንደሚያስቆጠር
አታውቀውምና ይሄ እኛን ይለየናል፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማ ደጋፊዎችን እንዴት ትመለከታቸዋለህ?
ኤፍሬም፡- የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ሁሌም ቢሆን በሚሰጡት ድጋፍ ለእኛም ሆነ ለሚመለከታቸው ሁሉ ልዩ መስህብ ያላቸው ናቸው፤ ስለ እነሱ
ለማውራት ቃላቶችም ናቸው የሚያንሱኝ፤ የእነሱ ድጋፍ ለውጤታማነታችን ብርታት ሲሆነንም ተመልከተናልና እነዚህ እንደ ቤተሰብ ሆነው
የሚቀርቡንን ደጋፊዎች በእዚሁ አጋጣሚ ላመሰግናቸው ነው የምፈልገው፤ ከዛ ባሻገር ለእነዚህ ምርጥ ደጋፊዎችም ዘንድሮ ዋንጫ
ስለሚያስፈልጋቸው የሊጉን ዋንጫ አንስተን እናስጨፍራቸዋለን፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን ማሳየት ብትችልም ካለፈው ዓመት አንስቶ ለብሔራዊ ቡድን መመረጥ አልቻልክም በዚህ
ዙሪያ ምን ትላለህ?
ኤፍሬም፡- የፋሲል ከነማ እግር ክለብ ውስጥ ሊጉ ላይ ከማሳየው ጥሩ እንቅስቃሴ አንፃር ለብሔራዊ ቡድን እስካሁን አለመመረጤ በጣም
ይቆጨኛል፤ ከዚህ በፊት በነበሩት ምርጫዎች ላይ በስኳዱ አለመካተቴም ለእኔ አሁን ድረስም አልገባኝም፤ እንደ አሰልጣኞቹ አመለካከትም
ለብሔራዊ ቡድን ያልተመረጥኩት ምንአልባት በእነሱ ጥሩ ላልሆን ቀርቼ ሊሆን ይችላልና በቀጣዩ ጊዜ ምርጫ ግን የበለጠ ጠንክሬ ሰርቼ
በመምጣት የሀገሬን ብሄራዊ ቡድን ማገልገል ዋንኛው ፍላጎቴ ነው፡፡