Google search engine

“ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ክለብ ነው፤ ከባድም ፈተና ነው የሚገጥመን፤ በአእምሮም በአካልም ተዘጋጅተን እንጠብቃቸዋለን” አስናቀ ሞገስ /ባህር ዳር ከተማ/

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ዘንድሮ ለተቀላቀለው የባህር ዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ በግራ መስመር የኮሪደር ስፍራ ላይ እየተጫወተ
የሚገኘው አስናቀ ሞገስ ቡድናቸው በሁለተኛው ዙር በሚኖረው የውድድር ተሳትፎ ጥሩ ውጤት
ሊግ፡- የባህር ዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ የዘንድሮውን የፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ውድድር ያጠናቀቀበትን መንገድ እንዴት
ትገልፀዋለህ? በውድድሩ ላይ የነበራችሁ ጠንካራ እና ደካማ ጎንስ ምንድን ነው?
አስናቀ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የተቀላቀልነው ዘንድሮ ከመሆኑና ለሊጉም አዲስ ከመሆናችን አንፃር የመጀመሪያው ዙር የውድድር
ተሳትፎአችን ጥሩ ነው፤ አበረታች የሚባልም ውጤት አስመዝግበንበታል፡፡ በውድድሩ ላይ የነበረን ጠንካራ ጎን የቡድናችን የተጨዋቾች
ስብስብ በአብዛኛው ወጣቶች እና በተመሳሳይ ዕድሜ ላይ ተገኝተን መጫወታችንና ኳስንም እንደ ህብረት በጋራ ሆነንም ለመጫወት
መቻላችን ነው፤ ከዛ ውጪም ለቡድናችን ጥሩነትና ጥንካሬም አሰልጣኛችን ጳውሎስ ጌታቸው /ማንጎ/ በሜዳ ላይ ኳስን ቡድኑን
በሚጠቅም መልኩ በነፃነት እንድንጫወትም ያደርገን ስለነበር እነዚህ የጥንካሬዎቻችን ምንጮች ናቸው፡፡
የባህር ዳር ከተማ ክለብ በመጀመሪያው ዙር ላይ ስለነበረው ድክመት ማንሳት የምፈልገው ነገር ደግሞ ክለባችን የሊጉን ልምድ ያላገኘ ቡድን
ከመሆኑ አንፃር በተደጋጋሚ ጊዜ ለጣልናቸው ነጥቦች ማሳያ ሲሆንም ተመልክተናል፤ ሌላው ደግሞ በውድድሩ ላይ የተወሰኑ
ተጨዋቾቻችንም በከፍተኛ ድካም ላይም ነበሩና ይሄም ክፍተት ጎናችን ላይ የሚጠቀስ ይሆናል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የመጀመሪያ ዙርን በ…..ደረጃ አጠናቃችኋል፤ ሁለተኛ ዙርንስ በምን ውጤት የምታጠናቅቁ
ይመስልሃል?
አስናቀ፡- የባህር ዳር ከተማ ክለብ የፕሪምየር ሊጉን የአንደኛው ዙር ያጠናቀቀበት ውጤት ለክለባችን ከጠበቅነው በላይ ቢሆንም ከዛም
በተሻለ ውጤት ውድድሩን አጠናቀን መጨረስ እንችል ነበር ያ ስለሆነም የአሁኑን የሁለተኛው ዙር ውድድራችንን በአማረ ውጤት
ለማጠናቀቅ ክለባችን በጥሩ ዝግጅት ላይ ስለሚገኝ ይሄንን እውን የምናደርገው ይመስለኛል፤ ባህር ዳር ከተማ በሁለተኛው ዙር ጥሩ ውጤት
ያመጣል ስል ከመሬት ተነስቼ አይደለም አሁን በድካም ላይ የነበሩት ተጨዋቾቻችን በጥሩ ሁኔታ አገግመው ወደ ሜዳ ተመልሰውልናል፤ ከዛ
በተጨማሪም ቴክኒካል በሆኑ ክፍተቶቻችን ላይም በደንብ ተዘጋጅተንበት የመጣንበት አበረታች ጎን ስላለን ከባህር ዳር ጥሩ ነገር ጠብቁ ነው
የምለው፡፡
ሊግ፡- በባህር ዳር ከነማ ውስጥ ያለህን የእዚህ ዓመት የውድድር ጅማሬህ ከዚህ በፊት ከተጫወትክባቸው ጊዜያቶች አንፃር ስትመለከተው
ለአንተ እንዴት ነው የሚገለፀው?

አስናቀ፡- የቡድኑ የጨዋታ ጅማሬዬን በእግር ኳሱ ካሳለፍኳቸው የውድድር ዓመታቶች ሁሉ በአቻነቱ ወደር የማላገኝለት ነው፡፡ ይሄን ስል ግን
በችሎታዬ ከዚ በላይ አልሄድም፤ አልጓዝም ማለት አይደለም፤ ገና ብዙ ወርቃማ ዓመታቶች ይጠብቁኛልና ለዛ ደግሞ ራሴን በብቁ ሁኔታ
አዘጋጃለው፡፡
ሊግ፡- የባህር ዳር ከተማ ክለብ ውስጥ ባለህ ወቅታዊ አቋም ከወዲሁ ማሻሻል አለብኝ የምትለው ነገር ምንድን ነው?
አስናቀ፡- የአሁን ሰዓት ላይ አበረታች የሚባል ብቃቴን እያሳየው ቢሆንም ብዙ ማሻሻል ያሉብኝ ነገሮች አሉ፤ እነዛም ላይ ትኩረት ሰጥቼ
እሰራለው፡፡
ሊግ፡- የባህር ዳር ከነማ ደጋፊዎች እንዴት ይገለፃሉ?
አስናቀ፡- ዎው፤ እነሱ በጣም የሚገርሙ እና አሪፍ የሆኑ ደጋፊዎች ናቸው፤ ለክለቡም ኩራት ናቸው፤ የእነሱ ድጋፍ ታክሎበትም ነው
አበረታች ውጤት እያመጣን የምንገኘው እና ይሄ ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ቆይታክ ላይ ለቡና ከምትጫወትበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በእጅ ውርወራ የሚስተካክልክ የለም
ይባላል፤ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በዚህ የስቶክ ሲቲው ዴላፕ ይታወቃል፤ በውርወራ ከሁለታችሁ ግን ማን ይበልጣል?
አስናቀ፡- /ሳቅ ካለ በኋላ/ በእጅ ውርወራ ማራቁ ላይ ባይገርምህ አንድም ቀን የራሴን ችሎታ ከሌሎች ተጨዋቾች ጋር አወዳድሬም
አስቤም አላውቅም፤ አሁን ስትጠይቀኝ ግን በሀገር ውስጥ ብዙ ጊዜ ከምመለከታቸው ተጨዋቾች አንፃር የራሴን አወራወር ሳየው እንደ እኔ
ጎል ድረስ በማራቅ የሚስተካከልኝ ተጨዋች ያለ አይመስለኝም፤ ከዴላፕ ጋር ያለው ንፅፅር ግን ይቅርብኝ፡፡
ሊግ፡- በአሁን ሰዓት የእግር ኳሱ ላይ የደረስኩበት ደረጃ ተፋጥኗል ብለህ ታስባለህ? ለየት ለየት ክለቦችስ ነው የተጫወትከው? የነበረክስ
ቆይታ ምን ይመስል ነበር?
አስናቀ፡- የእግር ኳሱ ላይ የደረስኩበት ደረጃ እንደጅማሬዬ ከሆነ አዎን ተፋጥኗል ብዬ ነው የማስበው፤ የእግር ኳስን የተጫወትኩባቸው
ክለቦች ደግሞ መጀመሪያ ከሰፈር ደረጃ በመውጣት በአሰልጣኝ ደረጄ ተስፋዬ /አንገቴ/ ይሰለጥን በነበረው የጌታ ዘሩ የታዳጊዎች
የፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ነው፤ ያኔም ከአሰልጣኝ ደረጄ ስልጠና ብዙ ነገሮችን ተምሬያለው፤ እዛም ብዙ ሳልቆይ በአሰልጣኝ ኤፍሬም ደምሴ
ወደሚሰለጥነው የአክረምና ልጆቹ የታዳጊዎች ፕሮጀክት ቡድን ውስጥ በመሰልጠን እና አሰልጣኙም በሚሰጠኝ ስልጠና ጥሩ መሻሻልን
ስላሳየው እኔን ጨምሮ ከቡድናችን ውስጥ በርካታ ተጨዋቾችም በ2004 ላይ ወደ ደደቢት ተተኪ ቡድን ውስጥ የገባንበት አጋጣሚ ስለነበር
በአክረምና ልጆቹ ቡድን ውስጥ የነበረኝም ቆይታ ጥሩ ነበር፤ በክለብ ደረጃም መጀመሪያ የተጫወትኩበት የደደቢት የታዳጊ ቡድን ቆይታዬም
ምርጥ ነበር ለቡድኑ ወሳኝ ተጨዋች ከመሆኔ ባሻገር ለሁለት ተከታታይ ዓመትም ዋንጫ ያገኘንበት ጊዜም ስለነበር ያንንም ወቅት
አልረሳውም፡፡ ያን ጊዜ ሻምፒዮና ስንሆንም እኔ አህመድ ረሺድ /ሺሪላ/ ጌታነህ እና ካሊድም ጥሩ እንጫወት ስለነበርን ወደ ቡና ተስፋ
ቡድን ውስጥ በመግባትም እዛም ጥሩ ልንጫወት ችለናል፡፡
በኋላም ወደ ዋናው ቡድን ካደግኩ በኋላም የመጫወት እድል ያገኘሁባቸው አጋጣሚዎችም ስላሉ በቡናም ቆይታዬ ደስተኛ ነኝ፤ አሁን ደግሞ
በባህር ዳር ከነማ ክለብ በተደጋጋሚ በመሰለፍ የምጫወትባቸው አጋጣሚዎች ስላሉና ጥሩም እየተንቀሳቀስኩ ስለሆነ በኳሱ እየተጓዝኩበት
ያለው አካሄድ የተፋጠነ እና ጥሩ የምለው ነው፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስን በሜዳችሁ ነገ ትገጥማላችሁ፤ ተጋጣሚያችሁን እንዴት ነው የምትጠብቁት? ምን ውጤትስ ትጠብቃለህ?
አስናቀ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ክለብ ነው፤ በነገ ጨዋታችንም ከባድ ፈተና ነው የሚገጥመን፤ እንደ ክለቡ ትልቅነትም እነሱን በአእምሮም
በአካልም ተዘጋጅተን ስለምንጠብቃቸው ጨዋታው ጥሩ ፉክክር የሚደረግበት ይሆናል ሜዳ ላይ ጥሩ የተንቀሳቀሰው እና ብልጫውን
የወሰደም ቡድን ጨዋታውን ያሸንፋል ! ያን ደግሞ የምናሳካው እኛ ባህር ዳሮች ነንና ግጥሚያውን በድል የምንወጣው ይሆናል፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ….
አስናቀ፡- የእግር ኳሱ ላይ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ በብዙ ነገር የረዱኝን ሰዎች አመሰግናለው፤ መካሻ መዳኒቴን፣ አለም ደስታን፣ ሰለሞን
በላይን፣ ደረጄ ተስፋዬን /አንገቴ/ አክረም አብደልቀኒን እና ኤፍሬም ደምሴን እንደዚሁም ቤተሰቦቼን አመሰግናለው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P