ለወላይታ ዲቻ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ በመጫወት ጥሩ ብቃቱን አሳይቷል፤ ያሳየው የሜዳ ላይ ብቃትም በብዙ ክለቦች እንዲፈለግ አድርጎታል፤ ያም ሆኖ ግን በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ይህ ተጨዋች ቅ/ጊዮርጊስን በመቀላቀል ፊርማውን ለክለቡ ሊያኖር ችሏል፡፡
ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ያመራው ቸርነት ጉግሳም የቡድኑ ተጨዋች መሆኑን ካረጋገጠ በኋላም “ይህን ትልቅ ክለብ ወደፊት እንጂ በዚህ ጊዜ ውስጥ እቀላቀላለው ብዬ ፈፅሞ አልጠበቅኩም ነበር፤ ያም ሆኖ የክለቡ አመራሮች ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡልኝ ለእዚህ ቡድን የመጫወት ፍላጎት ስለነበረኝና ከሁሉም ቡድኖች ደግሞ የሚሻለው ቡድን ቅ/ጊዮርጊስ ስለሆነ በምርጫዬና በውሳኔዬ ማንንም ሳላማክር አዲሱን ቡድኔን ልቀላቀል ችያለው” በማለት አስተያየቱን ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጧል፡፡
አዲሱ የቅ/ጊዮርጊስ ተጨዋች ወደ ቡድኑ ስላደረገው ዝውውርና በቀድሞ ቡድኑ ስለነበረው ቆይታ እንደዚሁም ደግሞ በሌሎች ጥያቄዎች ዙሪያ አናግረነው የሰጠን ምላሽ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፤ መልካም ንባብ፡፡
ወላይታ ዲቻን ለቅቆ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ስለማምራቱ
“የእውነት ለመናገር ለቅ/ጊዮርጊስ መጫወቱን አጥብቄ ብፈልግም፤ ወደ ቡድኑ በመምጣቴ ደስ ቢለኝም በዚህ ጊዜ ውስጥ ይሆናል ብዬ ግን ፈፅሞ አልጠበቅኩም ነበር፤ እኔ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ አመራለው ብዬ የነበረው ወደፊት ነበር፤ ያም ሆኖ ግን የእነሱ አመራሮች እኔን ለቡድኑ እንድጫወት ሲያናግሩኝ ውሌን ከወላይታ ድቻ ጋር ጨርሼ ስለነበር ቅ/ጊዮርጊስን ምርጫዬ አደረግኩትና ወደ ቡድኑ አመራው”፡፡
ከቅ/ጊዮርጊስ ውጪ በሌሎች ትልልቅ ቡድኖችም ተፈልጎ እንደነበር
“አዎን፤ በተለያዩ ክለቦች የተጫወትልን ጥያቄ ቀርቦልኝ ነበር፤ በዚህም ጉዳይ ላይ ከወንድሞቼ ጋር ተነጋግሬበትም ነበር፤ በመጨረሻ ግን ውሳኔው የእኔ ስለሆነ ከዛ በኋላ ማንንም ሳላማክር ነው በራሴ ፍላጎት ቅ/ጊዮርጊስ ከሌሎች ቡድኖች የተሻለ እና ትልቅ ቡድንም ነው ብዬ ስላሳብኩኝ ለቡድኑ ፊርማዬን ያኖርኩት”፡፡
ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ሲያመራና ፊርማውን ሲያኖር አመራሮቹ ስለ ቡድኑ ምን እንዳሉትና እሱስ ስለ ክለቡ ምን ያህል ያውቅ እንደነበር
“መቼስ የኢትዮጵያ ተጨዋች ሆኖ ስለ ቅ/ጊዮርጊስ ክለብ የማያውቅ ተጨዋችን ማግኘት በጣም ይከብዳል፤ ወደ ቡድኑ ሳመራ አመራሮቹ ስለ ክለቡ ታላቅነትና ውጤታማነት እንደዚሁም ደግሞ ከእኔም ሆነ ከቡድኑ ተጨዋቾች የሚጠበቅ ከባድ ሀላፊነት እንዳለ ብዙ ነገሮችን ሊነግሩኝ ቢችሉም ይሄ ለእኔ አዲስ ነገር አልሆነብኝም፤ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ያመራሁት ሁሉን ነገር አውቄ ነው፤ ይሄ ቡድን ድል የለመደ ነው፤ በእርግጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውጤትን እያጣ መጥቷል፤ ወደ ቀድሞ ስምና ዝናው በፍጥነት መመለስን አጥብቆ ፈልጓልና ከእኔም ሆነ ከቡድኑ ሌሎች ተጨዋቾች የሚጠበቅብንን ነገር በማወቅ ጭምርም ነው ስለ ቡድኑ አውቄ ልመጣ የቻልኩት”፡፡
በቅ/ጊዮርጊስ የተሳካ የኳስ ጊዜን የምታሳልፍ ይመስልሃል?
“አዎን፤ ያለዚያማ ለምን ወደቡድኑ መጣሁኝ! በዚህ ቡድን ውስጥ ሁሉንም ነገሮች ተቋቁሜ በማለፍ ነው ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ክለቤን ለታላቅ ደረጃ የሚያበቃ ውጤትንና ስኬትን በማስመዝገብ ጥሩ ጊዜን አሳልፋለው ብዬ እያሰብኩ ያለሁት”፡፡
ቅ/ጊዮርጊስ ከሚይዘው የተጨዋቾች ስብስብ አንፃር በቋሚ ተሰላፊነት ለመጫወት ስለሚኖረው እድል
“ይሄ የሚወሰነው እንግዲህ በራስህ ጥንካሬና በአሰልጣኙም እምነት ነው፤ ጠንክሮ የሰራና የለፋ ተጨዋች ለክለቡ ሁሌም ጠቃሚ ነውና ያን የመጫወት እድል ያገኛል፤ እኔም ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ስመጣ በቋሚነት ተሰልፌ ለመጫወት እንጂ ዝም ብዬ ለመቀመጥ ስላልሆነ ይሄን የመሰለፍ እድል ለማግኘት በርትቼ እሰራለው”፡፡
ስለወላይታ ዲቻ እና በቡድኑ ውስጥ ስለነበረው ቆይታ
“ወላይታ ዲቻ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ወጣት ተጨዋቾች እዚህ ደረጃ ላይ እንድንደርስ ጥሩ ነገርን ያደረገልን ክለብ ነው፤ ቡድኑን በጣምም ነው የምወደው፡፡ በቆይታዬ ከታች አንስቶ አድጌ የተጫወትኩበት ክለብ ስለሆነም አስደሳች ነገሮችን በመመልከት ላሳልፍበት ችያለው፤ ይሄ ክለብ ለኳስ እድገቴ መነሻዬ የሆነና ራሴን እንዳሳይበት የጥርጊያውን መንገድ ያመቻቸልኝ ክለብ ስለሆነም ስለ ቡድኑ ለመግለፅ ቃላቶች ሁሉ ነው የሚያጥረኝ”፡፡
ወላይታ ዲቻ መጋቢ ሆኖ ብዙ ወጣት ተጨዋቾችን ለተለያዩ ክለቦች ስለማብቃቱ
“ይሄን ክለብ አሁን ላይ በጣም እያሳወቀው ያለው ነገር ይሄ ነው፤ ከስር ጀምሮ የሚያፈራቸው ተጨዋቾቹ ችሎታቸውን ከዕለት ዕለት እያሻሻሉ በመምጣት ወደ ዋናው ቡድን ካደጉና ከተጫወቱ በኋላ በተለያዩ ክለቦች በመፈለግ ወደዛ የሚያመሩበት ሁኔታ መፈጠሩና በተለያዩ የዕድሜ እርከን ደረጃዎች ላይም ለሀገር ብሔራዊ ቡድን በመመረጥ ክለቡ መጋቢ ተጨዋቾችን የሚያፈራ መሆኑን ማስመስከሩም ጭምር ነውና ይሄ ክለብ ለሚሰራው ስራ ከፍተኛ ምስጋናና ሙገሳም ያስፈልገዋል”፡፡
ወላይታ ዲቻ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ስለነበረው ቆይታና ስላስመዘገበው ውጤት
“የውድድሩ አጀማመራችን መልካም ባይሆንም ወደ በኋላ ግን ከፍተኛ መሻሻሎች ነበረን፤ ሊጉን በወገብ ደረጃ ላይም ለማጠናቀቅ ችለናል፤ እንደ አጠቃላይ ተሳትፎአችንም የትኩረት ማጣት ጎዳን እንጂ በደረጃው ሰንጠረዥ በተሻለ ውጤት ላይ ሆነን ሊጉን እናጠናቅቅም ነበር”፡፡
ባሳለፈው የእግር ኳስ ተጨዋችነት ህይወቱ ደስተኛ እንደሆነ
“በኳስ ተጨዋችነት ህይወቴ እኔ የተከፋሁበትን ጊዜ ፈፅሞ አላስታውስም፤ ኳስ የምወደውና የምፈልገው የሙያ ዘርፍ ነው፤ በዛ በመጓዜና ውጤታማም እየሆንኩበት ስለመጣው ደስተኛም ነኝ”፡፡
በእግር ኳስ ተጨዋችነት ባትሰማራ ኖሮ በምን ሙያ ላይ እናገኝህ ነበር…?
“ጥያቄው ከባድ ነው! /እንደ መሳቅ ካለ በኋላ/ ምንአልባት እንደ አንዳንድ ቤተሰቦቼ ነጋዴ ሆኜ በንግዱ ዓለም ላይ ልሰማራ እችል ነበር”፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሶስት ሶስት ወንድማማቾችን ሲጫወቱ ተመልክተናል፤ ከእነዛ ውስጥ አንዱም የእናንተ ቤተሰብ ይጠቀሳልና ማነው ለየት ያለ ባህሪ ያለው
“ከእኛ ቤተሰብ ውስጥ በባህሪው ለየት የሚለው አንተነህ ጉግሳ ነው፤ እሱም በቀልደኝነቱ ነው የሚታወቀው”፡፡
ሶስቱ ወንድማማቾች ሽመክት፣ አንተነህና አንተ ራስህ ተቃራኒ ሆናችሁ በምትጫወቱበት ጊዜ ስለምትባባሉት ሁኔታ
“የወላይታ ዲቻ ተጨዋች የነበርነው እኔና አንተነህ የፋሲል ከነማውን ተጨዋች ወንድማችንን ሽመክት ጉግሳን በተቃራኒ ሆነን በምንገጥምበት ሰዓት ከግጥሚያው በፊት ሁሌም ሰላም ከመባባል በስተቀር የምናወራው ነገር የለም፤ ጨዋታው ካለቀ በኋላ ግን በሜዳ ላይ ስለነበረው እንቅስቃሴ እንነጋገራለን፤ በክፍተታችን ዙሪያም በመወያየት ለነገ ጥሩ ተጨዋች ስለምንሆንበት ነገርም እንማማራለን”፡፡
የእናንተ ቤተሰቦች ከሶስታችሁ ወንድማማቾች ተጨዋቾች ውስጥ ለማን ያደላሉ….?
“ማድላቱና መለያየቱ ላይ እንኳን እነሱን ብዙ አታገኛቸውም፤ ያም ሆኖ ግን ከሶስቱ ውስጥ እኔ ታናሻቸው ስለሆንኩኝ በወጣው በገባው ቁጥር የሚሳሱልኝን ነገር ልመለከት ችያለው”፡፡
በእግር ኳስ ተጨዋችነቱ ማሻሻል ስለሚፈልገው ነገር እና ስለ ቀጣይ ጊዜ ግቡ
“በእግር ኳስ የመስመር አጥቂም በመሀል ከአጥቂዎች ጀርባም ሆኜ እግር ኳሱን እጫወታለው፤ በእነዚህ ቦታዎች ላይ ስጫወት ከሁሉም በላይ ማሻሻል የምፈልገው ነገር ቢኖር ብዙ ጎሎችን ማስቆጠር መቻል ነው፤ እነዚህን እንዳሻሽል ደግሞ ወንድሞቼ ሁሌም ከጨዋታ በኋላ የሚነግሩኝ ነገር ስላለና ጨዋታዎቹም ደግሞ በዲ.ኤስ.ቲቪ የሚተላለፍበት ሁኔታ በመፈጠሩ ያን በማየት በብዙ ነገሮች እንድቀየር ያደርገኛል፤ ይሄን ካልኩ ዘንዳ ስለ ቀጣዩ ጊዜ የኳስ ህይወቴ ማለት የምፈልገው ነገር ከአዲሱ ቡድኔ ቅ/ጊዮርጊስ ጋር የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን አንስቼ ክለቡን ለታላቅ ድል ከማብቃት ባሻገር ለሀገሬም ብሔራዊ ቡድን በመመረጥ እና ጥሩም ውጤት በማስመዝገብ ስሜን በታሪክ ላይ ማስፈርን እፈልጋለውና ይሄን ለማሳካት ነው ጥረትን በማድረግ ላይ የምገኘው”፡፡
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመመረጥ በሴካፋ እያደረገው ስላለው ተሳትፎ
“በቅድሚያ ሀገርን በሚወክል ደረጃ ተመርጦ መጫወት መቻል የብዙ ኳስ ተጨዋቾች ዋንኛው ምኞታቸው ነውና ደስታን ይሰጣል፤ እኔም ይህን እድል ስላገኘው በጣም ደስ ብሎኛል፤ ከእዚህ መነሻነት ወደፊትም ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ስለመመረጥም እያሰብኩኝ ነው”፡፡
የእግር ኳስን ከመጫወት ውጪ ያለህን ጊዜ ስለምታሳልፍበት ጊዜ
“ብዙ ጊዜ የሞባይል አፕሊኬሽን ላይ ያሉ ጌሞችን በመጫወት ነው የማሳልፈው፤ ይሄም ነው የእረፍት ጊዜዬ”፡፡
ምን አይነት ምግብን አጥብቆ ይወድ እንደሆነ
“እኛ አካባቢ ያው ይታወቃል፤ ጥሬ ስጋ ነፍሳችን ነው፤ እሱን ነው አጣጥመንም የምንበላው”፡፡
በዓለም እግር ኳስ ስለሚያደንቀው ተጨዋችና ስለሚደግፈው ክለብ
“የምደግፈው ማንቸስተር ዩናይትድን ነው፤ የማደንቀው ተጨዋች ደግሞ ክርስቲያኖ ሮናልዶን ነው”፡፡
በቅርቡ የተጠናቀቀውን የአውሮፓ ዋንጫ ተመልክቶ እንደሆነና ስለ ጣሊያን ሻምፒዮናነት
“ኳሱን በደንብ ተመልክቼያለው፤ ጣሊያንም የውድድሩ ሻምፒዮና መሆኗ የሚገባት ነው”፡፡
በመጨረሻ….
“ያው ምስጋናን ነው የማቀርበው፤ በቅድሚያ ለእዚህ ላበቃኝ ፈጣሪዬ፣ ከዛም ቤተሰቦቼ እንደዚሁም ከእኔ ጎን ለሆኑት ሁሉ ላቅ ያለ አክብሮትም አለኝ”፡፡