በአርባምንጭ ከተማ ውስጥ ነው ተወልዶ ያደገው፤ እግር ኳስን በቤተሰቦቹ ውስጥ ከሚገኙት 5 ወንድሞቹና አንድ እህቱ ውስጥም በአሁኑ ወቅት ብቸኛው ስፖርተኛ እሱ ብቻም ነው፤ በተክለ ሰውነቱ ገዘፍ በማለት የደደቢት የተተኪ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ የኳስ መጫወቻ ጊዜውን የጀመረው እና ዛሬ ላይ ደግሞ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለሐዋሳ ከተማ በተከላካይ ስፍራው ላይ ሲጫወት የተመለከትነው ምኞት ደበበ ከትናንት በስቲያ በተከፈተው የዝውውር መስኮት በበርካታ ክለቦች ተፈልጎ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ቡድን የማምራት ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ እየተነገረ ሲሆን ይህን ተጨዋች የዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ውድድር ከተጠናቀቀ በኋላ በእረፍት ላይ በሚገኝበት ሰዓት ከክለቡ ጋር ስላሳለፈው የውድድር ዘመን፣ ስለ ቡድኑ ተሳትፎ፣ ከኳስ ጋር ስለተገናኘው ሕይወቱና ሌሎችንም ተጨማሪ ጥያቄዎችን ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ለተጨዋቹ አቅርቦለት ምላሹን ሰጥቶበታል፤ ተከታተሉት፡፡
ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በአንተ እይታ እንዴት እንዳለፈ
“ከሁሉም በላይ በቅድሚያ የአጠቃላይ ውድድሩ በዲ. ኤስ.ቲቪ ለመተላለፍ መቻሉ እኛን ተጨዋቾች በራሳችን ጥረት የተሻለ ደረጃ ላይ እንድንደርስ እና ባለን አቅምም እንደከዚህ በፊቱ ቪዲዮን ብቻ እየላክን መጪውን ጊዜ ሳንጠብቅ በቀጥታ ጨዋታዎቻችን በመታየታቸው የሚያስገኝልን ጥሩ ዕድል መጥቷልና ያ አስደሳች ነገር ነው፤ የጨዋታዎቹ መተላለፍም ባለህ አቅም ሁሌም ጥሩ ነገርን እንድትስራም ያስገድድሃልና ይሄ እድል መምጣቱ የሀገራችንን እግር ኳስ አንድ ደረጃ ከፍ እያደረገልንም ይገኛል”፡፡
እንደ ሐዋሳ ከተማ ክለብ ተጨዋችነትህ የእዚህ ዓመትን የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአችሁንስ በምን መልኩ ነው የምትገልፀው?
“ሐዋሳ ከተማ ብዙ ወጣት ተጨዋቾችን ባሳተፈበት የዘንድሮው የውድድር ዘመን የሊጉ ጅማሬ ላይ ቡድናችን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ሲሸነፍ በቃ ይሄ ቡድን ወደ ታችኛው ሊግ ሊሄድ በሚል የመውረድ ስሜት ተሰምቶኝ በጣም ተከፍቼ ነበር፤ ወዲያው ግን ሁላችንም የቡድኑ ተጨዋቾች ከኮቺንግ ስታፉና ከሚመለከታቸው የቡድኑ አካላት ጋር ስብሰባን በማድረግና በችግሮቻችን ዙሪያ በመነጋገር ቡድኑ ጥሩ የውድድር ጊዜን እንዲያሳልፍ አድርገናልና ይሄ ያስደሰተን ጉዳይ ነው፤ በውድድር ዘመኑ ተሳትፎአችን የእኛ ቡድን ምንም እንኳን በሊጉ ጅማሬ ውጤትን ቢያጣም እየተስተካከለ በመምጣት በኋላ ሁለተኛው ዙር ላይ ሊጉን በሁለተኛ ደረጃ ሆነን እስከማጠናቀቅ የሚያደርስ እድሉ ነበረን መጨረሻ ላይ ግን ልጆቻችን ወጣቶችና የተካበተም የጨዋታ ልምዱ ስለሌላቸው እስከመጨረሻው በያዝነው ውጤት ልንቀጥል ስላልቻልን ሊጉን በደረጃው ሰንጠረዥ ወገብ ላይ ሆነን ልናጠናቅቅ ቻልን”፡፡
ሐዋሳ ከተማ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በርካታ ወጣት ተጨዋቾችን ካስመለከቱን ቡድኖች ውስጥ አንዱ ነውና ምን አልክ?
“ወደዚህ ቡድን ሳመራ ከ20 በላይ የሚደርሱ ተጨዋቾችን ነው በስኳዱ ውስጥ የተመለከትኩት፤ ወዲያውም ነበር ከእነሱ ጋርና ሌላም ወጣት አሰልጣኝ ከሆነው ሙሉጌታ ምህረትም ጋር በብዙ ነገሮች ላይ ተግባብቼም ልጫወት የቻልኩት፤ የሐዋሳ ከተማን ወጣት ተጨዋቾች በቆይታዎቼ ስመለከታቸው የሚባሉትን ይሰማሉ፤ የመጫወት ፍላጎታቸውም ከፍተኛ ነው፤ የመጫወት ልምድና ውጤትም በሂደት እንደሚመጣም ያውቃሉና ከእነሱ ጎን ሆነህ ስትጫወት ለአንተም ከፍተኛ እርካታም ይሰጥሃልና ይሄ የቡድኑ የዘንድሮ ጉዞ በፋይናንስ እረገድም ብዙ ወጪዎችን ሳያወጣ የተጫወተበትና አካሄዱም ለሌሎች ክለቦችም በአርአያነት ሊጠቀስ የሚችል ነውና ቡድናችን የተጓዘበትን መንገድ ሳላደንቅ አላልፍም”፡፡
ስለ ፋሲል ከነማ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ማሸነፍና ስለ ኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር የጣምራ የኮከብ ተጨዋችት ተሸላሚነት
“ፋሲል ከነማ ለአራት ዓመታት ያህል ተግባብተው የቆዩ ተጨዋቾችን የያዘና ጠንካራም ቡድን ስለሆነ የዘንድሮ ሻምፒዮናነቱ ሲያንሰው እንጂ የሚበዛበት አይደለም፤ እነሱ ብዙ ለፍተዋልና የሻምፒዮናነቱ ክብሩ ይገባቸዋል፤ አቡበከር ናስርን በሚመለከት ሁሉም ሰው ስለ እሱ የተለያዩ አስተያየቶችንና አባባሎችን እየገለፀ ብዙ ነገርን ብሏል፤ እኔ ለእሱ በቅድሚያ የምመኝለት ግን ከኢትዮጵያ ወጥቶ ተጫውቶ የተሻለ ታሪክን እንዲሰራም ነው፤ ከእሱ ጋርም በዚሁ ጉዳይ ሜዳ ላይ አውርተንበታል፤ እሱ ከእዚህ ሀገር ወጥቶም ይሁን ሳይወጣ ከተጫወተ ጥሩ ነገር እንዲገጥመው የምመኝለትም ተጨዋች ነው”፡፡
ስለ እግር ኳስ ጅማሬው እና ቤተሰብ ጋር ስለነበረው አመለካከት
“የእግር ኳስን ተወልጄ ባደግኩበት አርባምንጭ ከተማ ላይ ነው በሰፈር ደረጃ ተቋቁሞ በነበረው የፕሮጀክት ቡድን ውስጥ መጫወት የጀመርኩት፤ ያኔ ኳሱን ስጫወትም እናቴ ብትፈልግም አባቴ ግን ወደ ትምህርቴ እንዳዘነብል ስለሚፈልግ አይፈቅድልኝም ነበር፤ እኔ ግን የኳስ ፍቅሩ አሸነፈኝና ለአባቴም ከአቅም በላይ ሆኜበት እሱን በሚያሳምን መልኩም ስሜቴን ሊቆጣጠር ባለመቻሉ ኳሱን ገፍቼበት ልጫወት ቻልኩ፤ አባቴም ከዛ በኋላ ጫማና ትጥቅ ሊገዛልኝም ቻለ”፡፡
ወደ እግር ኳስ ተጨዋችነቱ ባታመራ ኖሮ በምን ሙያ ላይ እናገኝህ እንደነበር
“በአርባምንጭ ሳለው ኳስን በሰፈር ደረጃ ከመጫወት ውጪ በላብራቶሪ ቴክኒሺያንነት ሙያ የጤና ትምህርትን እየተማርኩ ነበርኩ፤ ይህን ትምህርትም ደደቢቶች በኳሱ እኔን ፈልገው ሲወስዱኝ ነው ለማቋረጥ የቻልኩትና በኳሱ ባልገፋ ምንአልባት በትምህርቴ ነበር የምቀጥለው”፡፡
ወደ እግር ኳስ ተጨዋችነቱ ህይወት ሲመጣ ተጫውቶ ስላሳለፈባቸው ክለቦች
“መነሻዬ የነበረው የደደቢት ተተኪ /ቢ/ው ቡድን ነበር፤ በወቅቱ የክለቡ አሰልጣኝ የነበረው ዳንሄል ፀሐዬም ነበር እኔን ወደ አርባምንጭ በመምጣት ሊመለምለኝም የቻለው፤ ዳንሄል በጊዜው በእኔ ችሎታ ተደስቶ ካመጣኝ በኋላም ጥሩ ለመጫወት ብችልም የኳስ ህይወቴ እስከዋናው ቡድን ድረስ ሳይዘልቅ ቀረ፤ ከዛ ግን ያለፈው ዓመት ላይ ኮቪድ ወደ ሀገራችን ገብቶ የሊጉ ውድድር እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ለአዳማ ከተማ በመግባት ነው ልጫወት የቻልኩት፤ በአዳማም ለአራት ዓመታት ያህል ቆይታ አድርጌያለው፤ በስተመጨረሻም በዘንድሮ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለሐዋሳ ከተማ ቡድን በመጫወት ከክለቡ ጋር አሳልፌያለው”፡፡
በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኑ ምርጡን ጊዜ ያሳለፈበትና በጣም ደግሞ የተቆጨበት
“በአዳማ ከተማ የነበረኝን ቆይታዬን ነው ጥሩ ቡድን ስለነበረን ምርጡ የምለው፤ የተቆጨሁበትም ከዚሁ ክለብ ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ የምናነሳበት እድሉ ነበረንና ያንን ነው ደግሜ የምጠቅሰው፤ እሱም 2009 ላይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አዲስ አበባ ላይ በነበረን ጨዋታ በተቆጠረብን የፍፁም ቅጣት ምት 1-0 የተሸነፍንበት ግጥሚያ ቀሪዎቹን ግጥሚያዎቻችን ተስፋ በቆረጠ ስሜትና መልኩም ያለ ሞራል ልንጫወት በመቻላችን የሜዳችንን ጨዋታ ጨምሮ ተከታታይ ነጥቦችን ልንጥል ስለቻልን የእዛ ዓመት ላይ ሻምፒዮና ሳንሆን ቀርተን ሊጉን በሶስተኝነት በማጠናቀቃችን ያስቆጨኛል”፡፡
በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ የሊግ ዋንጫን ለማንሳት አለመቻል ስሜቱ ምን ይመስላል?
“በጣም ከባድ ነው፤ ምክንያቱም የትኛውም ተጨዋች ይህን ክብር በጣም ይፈልገዋልና፤ ዋንጫ ስታነሳ እኮ ለጓደኞችህ፣ ለቤተሶቦችህ፣ ወደፊት ለምትመሰርተው ቤተብና ለሚኖርህም ልጅ የምትነግረው ታሪክ ይኖርሃልና በቀጣዩ ጊዜ የግድ ይህን ክብር ዋንጫን አገኝበታለው ከምለው አዲሱ ክለቤ ጋር ስለመጎናፀፍ ነው ከወዲሁ የማልመው”፡፡
በዝውውር መስኮቱ ከሐዋሳ ከተማ ጋር የነበረህን ውል መጠናቀቅ አስመልክቶ ስምህ ከተለያዩ ክለቦች ጋር እየተነሳ ይገኛል፤ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ የምታመራበት እድልም ሰፊ እንደሆነ ይነገራልና በዚህ ዙሪያ የምትለን ነገር ካለ?
“በሐዋሳ ከተማ የነበረኝ የውል ጊዜ የእውነት ነው ተጠናቋል፤ ስሜ ከብዙ ክለቦችም ጋር ተያይዞ እየተነሳም ይገኛል፤ ብዙ ቡድኖች ስላናገሩኝ በድርድር ላይም ነበርኩ፤ እስካሁን ግን በእኔ ዙሪያ ላይ ለቅ/ጊዮርጊስ ፊርማውን አኑሯል ተብሎ ብዙ ሊነገር ቢችልም ይሄ ነው የምለው የተጨበጠ ነገር ስለሌለ ምንም ነገርን ልልህ አልችልም፤ ያም ሆኖ ግን ካለው ድርድር አኳያ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላመራ የምችልበት እድሌ ሰፊ ይመስለኛል፤ የዝውውር መስኮቱም አሁን ላይ ስለተከፈተ አዲሱን ቡድኔንምሰሞኑን የማሳውቃችሁም ይሆናል”፡፡
ቅ/ጊዮርጊስ ከዚህ ቀደም ፈልጎህ እንዳልመጣ ይነገራል….
“ፈልገውኝማ ጥሪያቸውን ተቀብዬ መጥቼ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን በዛን ወቅት ላይ በአንድ አንድ ነገሮች ብቻ አለመስማማት ይኖራልና በዛ ነው ወደ ቡድኑ ሳልገባ የቀረሁት፤ በኳስ ህይወቴ እኔ አይደለም ለቅ/ጊዮርጊስ አክብሮኝ ለሚጠራኝ ማንኛውም ክለብ እኔን ሊወስደኝ ጠይቆኝ እምቢ ያልኩበትን ጊዜ ፈፅሞ አላስታውስም፤ የማናቸውንም ክለቦች ጥሪ እቀበላለው፤ በኳሳዊ መንገድም ሁሉም የተሻለ ነገርንም ይፈልጋልና ከተስማማውም እጫወታለው”፡፡
በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ አሁን ላይ ለትልቅ ስፍራ ደርሻለው ትላለህ?
“በፍፁም ያሰብኩት ደረጃ ላይ አልደረስኩም፤ አቅምና ችሎታዬ እንዳለ ሆኖ ያን ዕድል ለማግኘት እድለኛ መሆንም ጭምር ያስፈልጋልና ገና በዛ ስፍራ ላይ ለመድረስ እየጣርኩኝ ነው ያለሁት”፡፡
በእግር ኳስ ተጨዋችነቱ ለወደፊት ስለሚያልማቸው ነገሮች
“በአሁን ሰዓት ላይ ባለኝ አበረታችና ጥሩ ብቃቴ በመነሳት ስለ ወደፊቱ ማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር የሊግ ዋንጫን አዲስ ከምገባበት ቡድን ጋር ማንሳትን እፈልጋለው፤ ከዛም ወደ ውጪ ሀገር በመውጣት በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት መጫወትን እፈልጋለው፤ ይህን ሁሉ የምታሳካው ደግሞ ቁጭ ብለህ ሳይሆን ጠንክረህም በመስራት ስለሆነ እኔም ከወዲሁ ብዙ እረፍትን ሳላደርግ ለአዲሱ እቅዶቼም ስራዬን ጀምሬያለው፤ በችሎታዬም ብቁ እና ቶፕ ደረጃ ላይ ሆኜም ነው እልሞቼንም ማሳካት የምፈልገው”፡፡
በመጨረሻ…
“በኳስ ጨዋታ ዘመኔ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ ቅድሚያ ፈጣሪ ምስጋናውን ይወስድና ከምኖርበት አርባምንጭ ከተማ እኔን መልምሎ በማምጣት ወደ ጥሩ ጎዳና ያስጓዘኝን አሰልጣኝ ዳንሄል ፀሐዬን በጣም አመሰግነዋለው፤ ከዛ ብዙ ሰዎች አሉ፤ ሌላ ፈፅሞ የማልረሳቸው ቤተሰቦቼም ለእኔ ብዙ ነገሮችን ስላደረጉልኝ ለእነሱም ጭምር ምሳጋና ይገባቸዋል”፡፡