ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን በጉጉት እንዲጠበቅ ከሚያደርጉት ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የሸገር ደርቢ ፍልሚያ ከአዲስ አበባ ውጪ አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ ሊካሄድ ነው፤ ቅ/ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና የሸገር ደርቢ ፍልሚያቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ ያደረጉት በ1993 በናዝሬት ከተማ ላይ ሲሆን አምና ደግሞ ከክልሉ ውጪ በሁለተኛው ዙር ሊፋለሙ ችለዋል፡፡
ቅ/ጊዮርጊስን ከኢትዮጵያ ቡና ከ1991 ዓ.ም አንስቶ ሲያፋልም የነበረው ይኸው ተጠባቂ ጨዋታ በሁለቱም ክለብ ደጋፊዎችና ተጨዋቾች ዘንድ በቂ ትኩረት ተሰጥቶት የጨዋታውን የመዳረሻ ቀናት እየተጠባበቁ ሲሆን ሁለቱ ክለቦች ይህንን ፍልሚያ የሚያደርጉትም በመጀመርያ ሳምንት ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ግጥሚያዎቻቸውም ከተጋጣሚዎቻቸው ሲዳማ ቡናና ሰበታ ከተማ ነጥቦችን ተጋተው የሚገናኙበት አጋጣሚ ስለሆነ እኩል የስነ-ልቦና ዝግጅት አድርገው በመምጣት ጨዋታውን የሚያደርጉት ይሆናል፡፡
ቅ/ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና በሸገር ደርቢ የእስከዛሬ ግንኙነታቸው በአብዛኛው ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ቅ/ጊዮርጊስ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናም እንደ ቅ/ጊዮርጊስ አይሁን እንጂ እሱም ተጋጣሚውን የረታባቸው አጋጣሚዎች አሉ፤ ሁለቱም ቡድኖች በሚያደርጉት በዚህ ተጠባቂ ጨዋታ ከኢትዮጵያ ቡና ወገን በመጀመርያ ግጥሚያ ከአምናው በተላለፈ አምስት ቢጫ ካርድ ያልተሰለፈው አጥቂው አቡበከር ናስር በዚህ ጨዋታ ላይ የሚሰለፍ ሲሆን ሌሎቹ የቡድኑ ተጨዋቾችም በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፤ በቅ/ጊዮርጊስ በኩልም በተመሳሳይ የተጨዋቾች ጉዳት እስካሁን የሌለ በመሆኑ የሁለቱም ቡድኖች በተሟላ መልኩ ለጨዋታው መቅረብ መቻል አንዱን አንዱን አሸንፎ ለመውጣት ብርቱ ትግል ያደርጉበታል ተብሎም ይጠበቃል፡፡