Google search engine

“ቅ/ጊዮርጊስ ያለምንም ጥርጥር የሊጉ ሻምፒዮንና ምርጥ ቡድን ነው” “በፍፁም አንወርድም፤ ኮከብ ግብ አግቢነቱን አቡበከር ቢያነሳ ደስ ይለኛል” በላይ ገዛኸኝ /አርባምንጭ ከተማ/

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የእዚህ ሳምንት ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ሐዋሳ ከተማን  2-1 በማሸነፍ ባለድል ሆኗል፤ ክለቡ ስኬታማ በሆነበት ጨዋታ የድሉን ጎል በላይ ገዛኽኝ አስቆጥሯል፤ ለአርባምንጭ ከተማ ሌላዋን ግብ አሸናፊ ፊዳ ሲያስቆጥር ለተሸናፊው ክለብ ሐዋሳ ከተማ ደግሞ  ወንድማገኝ ኃይሉ ሊያስቆጥር ችሏል፡፡

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የእዚህ ሳምንት ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ  ባለድል መሆኑን ተከትሎ  በ30 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ለቡድኑ እስካሁን 3 ግቦችን ያስቆጠረው በላይ ገዛኸኝ በቀሪዎቹ የሊጉ ግጥሚያዎች ቡድናቸው ጥሩ ውጤት እንደሚያስመዘግብና ከሊጉም በፍፁም እንደማይወርዱ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጿል፤ በላይ ገዛኸኝ ከሊግ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ ጋር በነበረው ቆይታ ስለ ኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክርም ጥያቄ ቀርቦለት የነበረ ሲሆን ተጨዋቹ ሲመልስ “እኔም የማገኛቸውን እድሎች ብጠቀም ኖሮ ፉክክሩ ውስጥ እኖርበት ነበር፤ ካለ በኋላ ዘንድሮ ኮከብ ግብ አግቢነቱን አቡበከር ናስር ቢያነሳ ደስ ይለኛል” ሲልም ሀሳቡን አክሎ ተናግሯል፡፡

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ አርባምንጭ እያደረገ ስላለው ተሳትፎና በሌሎች ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ከተጨዋቹ በላይ ጋር ያደረግነው ቆይታ ይህን ይመስላል፡፡

ሊግ፡- ሐዋሳ ከተማን በማሸነፍ ባለድል ሆናችዋል፤ ጨዋታውና ድሉ እንዴት ይገለፃል?

በላይ፡- ወደ ግጥሚያው ስናመራ እነሱ ተቀዛቅዘው ነበር የመጡት፤ ያንን ታሳቢ በማድረግም ከጨዋታው በፊትም ሆነ በኋላ ላይ በሜዳ ላይ ተነጋግረን ለመግባት በመቻላችን አሸናፊ ለመሆን ችለናል፤ ያገኘነው ድልም ትልቅ የደስታ ስሜትን ሊፈጥርብንም ችሏል፡፡

ሊግ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በአራት ከተሞች ላይ ነበር ሲካሄድ የቆየው፤ የቱ ይመቻል?

በላይ፡- የባህርዳር ሜዳ ነዋ! በእርግጥ አንድአንዴ አስቸጋሪ የሚሆንበት ጊዜም አለ፤ ያም ሆነ ግን ጥሩ እግር ኳስን ለመጫወት እና ብዙ ነገርን ለማድረግ ምቹ ስለሆነ ያን ተመራጭ ከማድረጌ ባሻገር ጥሩ ቆይታንም እያደረግንበት ነው፡፡

ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ምን ውጤትን ማምጣት ነበር ያለማችሁት፤ ከእዚህ በኋላስ ምን ውጤት ይገጥማችኋል?

በላይ፡- ሊጉን ስንጀምር ከአንደኛ እስከ አራተኛ መውጣን ነበር፤ እንደውም እስከ ሁለተኛ ደረጃ በመውጣትም በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የውድድር መድረክ ላይ መሳተፍንም አልመን ነበር፤ አሁንም እስከ አራተኛ ደረጃ መውጣትን ነው እያሰብን የምንገኘው፡፡

ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ አርባምንጭ ከተማ እንዴት ይገለፃል?

በላይ፡- የእኛ ቡድን እንደሚታወቀው በአብዛኛው ጀማሪ ተጨዋቾችን ነው የያዘው፤ በአንድነታችን እና በህብረታችንም እንታወቃለን፤ አሰልጣኛችን የሚሰጠንን ስልጠናም በአግባቡ ስለምንቀበል ይሄም ሌላው መለያችን ነው፡፡

ሊግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮ ምን ትሆን ነበር?

በላይ፡- ለአንድም ቀን ይሄን ሁኔታ አስቤው አላውቅም፤ ከልጅነት እድሜዬ አንስቶ ኳስ ተጨዋች ስለመሆን ነው ሳስብ የነበርኩት፡፡

ሊግ፡- በእግር ኳስ የት ደረጃ ላይ መድረስ ነው ግብህ?

በላይ፡- በሀገር ውስጥ ከዚህ ቀደምም ተናግሬዋለሁ ለቅ/ጊዮርጊስ መጫወት ነው እልሜ፤ ከዛ ውጪ ደግሞ ለብሔራዊ ቡድን ተመርጦ መጫወትም ሌላው ግቤ ነው፡፡

ሊግ፡- በዘንድሮ የውድድር ዘመን የሊጉ ምርጥ ቡድን ማን ነው?

በላይ፡- ቅ/ጊዮርጊስ ያለምንም ጥርጥር የሊጉ ምርጥ ቡድን ነው፤ ስኳዱ ጥሩ ነው በዛ ላይ እያሸነፈም ነው፡፡

ሊግ፡- ባሳለፍነው የውድድር ዘመን አቡበከር ናስር ከኢትዮጵያ ቡና የሊጉ ምርጥ ተጨዋች ነበር፤ ዘንድሮ ለአንተ ምርጡ ተጨዋች ማን ነው?

በላይ፡- የባህርዳር ከተማው ፍፁም ዓለሙ ነዋ! ጥሩ የውድደር ጊዜን እያሳለፈም ይገኛል፡፡

ሊግ፡- ከቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላለመውረድ የሚኖር ፉክክር አለ፤ የእናንተን ቡድን ይህ ያሰጋዋል?

በላይ፡- በፍፁም፤ ከሊጉ አንወርድም፤ ቅድምም ነግሬያለሁ የእኛ ቡድን አላማ ሊጉን ስንጀምር ከአንድ እስከ አራት መውጣት ነው፤ ያን ለማሳካትም እንጫወታለን፤ ስለዚህም ስለመውረድ አንሰጋም፡፡

ሊግ፡- በእዚህ የውድድር ዘመን ላይ ምን የተለየ ነገርን ተመለከትክ?

በላይ፡- ለሊጉ አዲስ ብንሆንም እግር ኳሱ ላይ ለውጦችን እየተመለከትን ነው፤ የተጨዋቾች የመጫወት ፍላጎት ጨምሯል፤ ዳኝነቱ ላይ መጠነኛ ስህተቶች ቢኖሩም ወዲያው ውሳኔዎች መሰጠታቸው መልካም ጎኑ ነው፡፡

ሊግ፡- በእግር ኳሱ ላይ ተምሳሌትህ ማን ነው?

በላይ፡- ሳላህዲን ሰይድ ነው፡፡

ሊግ፡- በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የማን ደጋፊ ነህ?

በላይ፡- የማንቸስተር ዩናይትድ፡፡

ሊግ፡- ፕሪምየር ሊጉ እሁድ ይጠናቀቃል፤ ዋንጫውን ማን ያነሳል?

በላይ፡- ሊቨርፑል ቢያነሳ ደስ ይለኛል፤ ግን ሲቲ ጠንካራ ቡድን ከመሆኑ ባሻገር ነጥብ ይጥላል ብሎ ማሰብም ከባድ ስለሆነ የዋንጫው ባለቤት የሚሆን ይመስለኛል፡፡

ሊግ፡- ሻምፒዮንስ ሊጉንስ ዋንጫ ማን ያነሳል? ሊቨርፑል ወይንስ ሪያል ማድሪድ?

በላይ፡- ሊቨርፑል ነዋ! ይሄን ዋንጫማ አይምሩትም፡፡

ሊግ፡- በባህሪህ እንዴት ትገለፃለህ?

በላይ፡- ሰው አከብራለሁ፤ ከሰው ጋር መጋጨትን አልፈልግም፤ ሜዳ ውስጥ ስገባ ደግሞ በጣም እለኸኛ ነኝ፡፡

ሊግ፡- በየቱ የደቡብ ክልል ነው ተወልደህ ያደከው?

በላይ፡- በአርባምንጭ ከተማ ሲቀላ ከተማ ኮንሶ ሰፈር ውስጥ ነው ተወልጄ ያደግኩት፡፡

ሊግ፡-  በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ ሻምፒዮና በጣም ያስቆጨህ እና ያስደሰተ ግጥሚያ የቱ ነው?

በላይ፡- ያስቆጨኝ ከአዳማ ከተማ ጋር አቻ የተለያየንበት እና ሀድያ ሆሳህናን 4-1 መርተን 4-4 የተለያየንበት ግጥሚያ ነው፤ ሌላው ያስደሰተኝ ጨዋታ ደግሞ ከቡና ጋር ባደረግነው ጨዋታ ውጤት ርቆን ስለነበር እኔ ባገባሁት ጎል ስኬታማ ስለሆንን ልደሰት ችያለሁ፡፡

ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ አምስት እና ስድስት የሚደርሱ ተጨዋቾች የኮከብ ግብ አግቢነቱን ሽልማት ለማግኘት እየተፎካከሩ ይገኛል፤ በመጨረሻ ኮከብ ግብ አግቢው ማን የሚሆን ይመስልሃል?

በላይ፡- የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ነዋ! አድናቂውም ነኝ፤ እሱ አሸናፊ ቢሆንም ደስ ይለኛል፡፡

ሊግ፡- እናጠቃል?

በላይ፡- እንደ ግል አሁን ለደረስኩበት ደረጃ ከእኔ ጎን ሆነው ላገዙኝ ሁሉ ቅድሚያ ለፈጣሪ ልስጥና ምስጋናዬን አቀርባለሁ፤ ሌላው ዘንድሮ የማገኛቸውን የግብ አጋጣሚዎች ስለማልጠቀም እንጂ የኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር ውስጥም እገባ ነበር፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P